ወርሃ ነሐሴ በርከት ያሉ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት የሚስተናገዱበት የደማቅ ክስተቶች ዕድለኛ ወር ነው። ዝናባማው የክረምቱ የአየር ጠባይ ስሜትን የማጨፍገግ ብርታቱ ጠንከር ያለ ቢሆንም አብዛኞቹ የወሩ ቀናት በባህላዊና በሃይማኖታዊ በዓላት የደመቁ ስለሆነ እንደ ተቀሩት የክረምት ወራት አውደ ዕለታቱ አኩርፈው ገብተው አኩርፈው የሚጠቡ አይደሉም። “ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት” የሚለው ነባር አባባል የወሩን ቀናት ተስፈኝነት ይበልጥ አመልካች ነው። በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ነሐሴ የሚጠራው የልጆችና የወጣቶች ደማቅ የበዓል ወር መባሉም ሌላው እውነታ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው። በነሐሴ ወር በቀዳሚነት የሚናፈቀውና የሚከወነው በጅራፍ ጩኸት የሚታጀበው የቡሄ በዓል የታዳጊ ልጆችና የወጣቶች ዋና ጉዳይ ስለሆነ ነው።
በሰሜናዊ የአገራችን ክፍል በድምቀትና ላቅ ባለ ፈንጠዝያ የሚከበሩት የሻደይ፣ የአሸንዳ/አሸንድዬ እና የሶለል ማራኪና ውብ የልጆገረዶች በዓላትም የዚሁ ወር የጸጋ ሰጦታዎች ናቸው። በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍ ባለ መንፈሳዊ ተመስጦ የሚከበረውና የወሩን እኩሌታ ያህል የሚሸፍነው ጾመ ፍልሰታም ሌላው የነሐሴ ወር በረከት ነው። ለጊዜው ያለንበትን ወር ነሐሴን በማሳያነት ጠቀስን እንጂ በእያንዳንዱ ወር የሚከበሩትን ማሕበራዊ፣ ሃይማኖታዊና መንግሥታዊ በዓላትን እየዘረዘርን ብንተርክ ብዙ ሊያጽፈን ይችላል።
የዚህ ጽሐፍ ዋነኛ ዓላማ አሉን የምንላቸውን የባህሎቻችንን ዓይነትና ብዛት፤ የየበዓላቱን የአከባበር ሥርዓትና ወግ ወይንም የታሪካዊ ዳራቸውንና የትፊታቸውን የት መጣ በመዘርዘር ለመተንተን ታስቦ ሳይሆን ባህሎቹና በዓላቱ ለማኅበራዊ አኗኗራችን ምን ፋይዳ እንዳላቸው ለማመልከትና ድባቡ የሚፈጥረውን በጎ የስሜት ተጽእኖ በወፍ በረር ቅኝት ለማስታወስ ነው። ከዚያ በፊት ግን ስለ ሁለቱ ባህልና በዓል ጽንሰ ሃሳቦች ጥቂት መንደርደሪያ ሃሳቦችን እንፈነጣጥቅ።
አገራችን እጅግ በርካታና ውብ መንፈሳዊና ቁሳዊ የባህል ሀብቶች የታደለች እናም “የተመረቀች” ምድር ነች። በቋንቋ የበለፀገች፣ በመልክአ ምድር ውበትና የከርሰ ምድር ሃብቶቿ የምታማልል፣ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው የገዘፉ የታሪክ ቅርሶች ባለቤት፤ እኛነት በእኔነት፣ እኔነት በእኛነት ውስጥ ተዋህደው ዓለም በምሳሌነቷ የሚያደንቃት መሆኑም አይካድም፤ አይታበልምም።
ክርስቲያኑ ከሙስሊሙ፣ ኢ-አማኒው ከአማኒው ጋር ተጎራብቶ ብቻ ሳይሆን፤ ባህሉና በዓላቱ ሳይገድቡት ተጋብቶም ሆነ ተዋልዶ፤ ወይንም ተቀላቅሎ የሚኖርባት መሆኗም እሙን ነው። ታሪክ፣ ሃይማኖታዊ መጻሕፍትና የእምነቱ ሊቃውንት አዘውትረው እንደሚተርኩልን በቀድሞ ስማቸው ከሚታወቁት ከቂሳርያ፣ ከቁስጥንጥንያ፣ ከታናሹ እስያ፣ ከኪልቂያ፣ ከቆስያና ከአንጾኪያ ተነስተው ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ታሪካዊ ገዳማት የገደሙት ተሰዓቱ ቅዱሳን (“ዘጠኙ መነኮሳት” በመባል የሚታወቁት) የተስተናገዱት የአንድ ባህርይ (ተዋህዶ) ባህላቸውንና በዓላቶቻቸው ተከብሮላቸው ነበር።
ነብዩ መሐመድም “አላህ መፍትሔ እስኪያመጣ ድረስ ወደ ሐበሻ ምድር ብትሄዱ መልካም ነው። በእርሷ ማንም የማይበደልባት ንጉሥ አለ። የእውነት አገር ናት።” በማለት እዝነት በተሞላበት ስሜት አሥር ወንዶችንና አራት (አምስት የሚሉም አሉ) ሴት ስደተኛ ሙስሊሞች እንዲጠለሉባትና መሸሻ እንድትሆን የመረጡት ኢትዮጵያን ነበር። “አል ሃምዱሊላሂ ታቦታችን ገባ” እያለ ወሎዬው ሙስሊም በየጥምቀተ ባህሩ ታቦት እየሸኘ የሚዘምረው፣ በመንዙማ ዜማው እየዘየረ የክርስቲያን ወገኑን ሃይማኖታዊ በዓላት የሚያደንቀውና የሚከባበረው ሌላው ሃይማኖት ያልከለለው ድንቅ ውበታችን ነው።
ቤተክርስቲያን ሲታነጽም የአካባቢው ሙስሊም ወገን ለእርዳታና ለትብብር አለሁ የሚለውን ያህል፤ መስጊድ ሲገነባም ክርስቲያኑ ወገን ለሙስሊም ወገኖቹ ድጋፉን በፍቅር ጭምር እየገለፀ “ወገኔ ሆይ እኔም ለአንተ ጉዳይ ፈጥኖ ደራሽ ነኝ” እየተባባለ እርስ በርስ የሚደጋገፍ ሕዝብ ነው።
ሙስሊም ወገኖቻችን በሚያከብሯቸው የመውሊ ድና የአረፋ በዓላት ላይ የገና፣ የጥምቀትና የትንሣኤ በዓላትን የሚያከብሩ ክርስቲያኖች የሚታደሙት ማሕበራዊ ቁርኝታችን እንዳይላላ ተደርጎ ስለተጣመረ ነው። በክርስቲያኖቹ በዓላት ላይም እንዲሁ ሙስሊም ወገኖቻችን “እንኳን አደረሳችሁ” በማለት ደስታቸውን የሚገልጹት የኢትዮጵያዊነት እሴቱ ስላስተሳሰረን ነው። ይህን መሠል መከባበርና መቀባበል እንደ ሸማ የተከናነበ የብዝኋን ሃይማኖት፣ ባህሎችና በዓላት ባለፀጋ አገርና ወገን ይፈለግ ከተባለ አለጥርጥር ቀድማ የምትጠራው የእኛዋ አገርና ሕዝብ ነው።
እንደ ሀረሬ ቆነጃጅት አልባሳትና ጌጣጌጦች ቀለመ ደማቅና ማራኪ የባህል ውበትና ክብረ በዓላት ያላት ወይንም እንደ ባህላዊ “የአገር ባህል የጥበብ ልብስና ሸማችን” እርስ በእርሳቸው የተንሰላሰሉ የባህል ሀብቶችና በዓላት ያላት ይህቺ አገራችን ራሷ ጥበብ ናት ብለን ብንጠቀልል ሳይሻል አይቀርም።
ባህል ምንድን ነው?
“ባህል” የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ በምልዓት ለማብራራት መሞከር እንኳን ከሙያው ለራቁት ለተርታው የማሕበረሰቡ አባላት ቀርቶ ለእውቀቱ ቤትኞችም ሳይቀር ምልዑ የሆነ ድንጋጌ ለመስጠት እጅግ አዳጋች እንደሚሆን በዘርፉ ጠበብት ታምኖበታል። ምክንያቱ ግልጽ ነው። ባህልን ለመደን ገግ ሥነ-ሰብን (Anthropology)፣ የማኅበረሰብ ሳይንስን (Sociology)፣ ታሪክን (History)፣ ሥነ-መለኮትን (Theology) ፎክሎርን (Falklore) ወዘተ. በመሳሰሉ የጥናት ዘርፎች ላይ መብሰልን ግድ ይሏል። እንደዚያም ቢሆን እንኳን አጥኚዎቹ በምርምር መስካቸው ዙሪያ ይህንኑ የባህልን ጉዳይ አስመልክተው የሚሰጧቸው ብያኔዎች፣ ትንተናዎችና መከራከሪያዎች እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ እስካሁን አልጠለሉም።
የባህል ድንጋጌው ብቻም ሳይሆን፤ “የሰው ልጅ ከባህሉ ጋር ያለው ቁርኝት እስከ ምን ድረስ የጠነከረ ነው?” በሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ዙሪያም ቢሆን እስከ ዛሬ ድረስ በጋራ መግባባት ላይ አልተደረሰም። ምክንያቱም መሠረታዊ ጽንሰ ሃሳቡ ከራሱ ከባለቤቱ የሰው ልጅ ረቂቅ ተፈጥሯዊ ሰብእና ጋር እጅግ ስለተወሳሰበ ውሉን በቀላሉ ለማግኘት ያዳግታል። በየትኛውም ደረጃና የሕይወት አቋም ላይ የሚገኝ ማንኛውም ሰው ራሱን ከባህሉ ነጥሎ ለማውጣት በፍጹም አይችልም። አንዳንዶች እንደሚገልጹት ባህል ከራሱ ከሰው ልጅ የነርቭ ንዝረት ጋር በፅኑ የተቆራኘ ነው። ሌላው ቀርቶ ለሕይወትና ለፍልስፍና እምነቱ ሳይቀር የንጽረተ ዓለሙ መነጽር የተቃኘው በባህሉ ዙሪያ ነው።
ስለዚህም፤ ማንም ሰብአዊ ፍጡር ለባህሉ ተገዥ የሚሆነው ወዶ ሳይሆን የባህሉ ብርታት የግድ ብሎ ስለሚያስገብረው ነው። አንድ ምሁር እንደገለጹት “በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ በሥጋና በነፍስ የተሸረበ ሰብአዊ ፍጡር ነው። ከዚሁ እውነታ ባልተናነሰም ያለ ባህሉ ውበትና ድምቀት ሰብአዊ ማንነቱ ትርጉመ ቢስ ነው። “የሰውን ልጅ ከሌሎች እንስሳት ልዩ ፍጥረት ያሰኘው የሥጋና የመንፈሱ ህልውና ጣጣ ብቻ ሳይሆን የባህሉ ብርታት ጭምር ነው” የሚባለውም ስለዚሁ ነው። ስለ ባህል ጽንሰ ሃሳብ ከዚህ በላይ ሰፋ አድርጎ መተንተኑ ከመነሻ ዓላማችን ስለሚያዛንፈን እዚሁ ላይ መግታቱ ይመረጣል።
በዓላትስ እንዴት ይደነገጋሉ?
አብዛኛውን ጊዜ በዓላት የሚቀዱት ከባህል ውቅያኖስ ውስጥ ነው። ከተለምዶ ሕይወታችን ተውስን ባህሎችንና በዓላትን በቀላልና ለንረዳው በምንችለው ተመሳስሎ እናነጻጽራቸው ከተባለም በተዋበ ኩታ ልንመስላቸው እንችላለን። በድርና በማግ የተሸመነው ዋነኛው መደረቢያ በባህል ቢመሰል፤ ኩታው የተዋበበትን ቀጭንና ዓይነ ግቡ ጥበብ ደግሞ ለበዓል ውክልና ልናውለው እንችላለን። ስለዚህም ነው የባህል የጥናት ዘርፍ ጎምቱዎች በዓላትን ከባህል ውበት መገለጫዎች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው ብለው የሚበይኑት። በዓላት በአንጸባራቂ የባህል ፈርጥነትም ሊመሰሉ ይችላሉ።
የበዓላት ማሕበራዊ ፋይዳ፤
ባህልም ሆነ በዓላት መንፈሳዊና ማሕበራዊ መስተጋብርን ለማሳለጥ ብቻም ሳይሆን ለግለ-ሕይወት ሁለንተናዊ ጤንነትም ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ጉዳዩን ከራሳችን ዐውዳዊ የአኗኗር ይትባሃል ጋር በማስተሳሰር ሰፋ አድርገን እንፈትሸው። አብዛኛው የአገራችን ዜጋ አእምሮው በበርካታ ወቅታዊና ዘርፈ ብዙ ውጥረቶች የፊጥኝ ታስሮ እንዳለ ምስክር አያሻውም። ኑሮውና ኢኮኖሚው በቀሊል ሸክም ሳይሆን የቋጥኝ ያህል ተጭኖብን እያንገዳገደን እንዳለ ለማስታወስ ካልሆነ በስተቀር ለክርክር የሚጋብዝ አይደለም።
የውስጥና የውጭ ነባራዊ ሁኔታዎችና ችግሮች ከእንቅልፍም ሆነ ከእፎይታ አርቀውን ቆዛሚ አድርገውናል። የብዙዎች ሕይወት ተመሰቃቅሏል። በጦርነት የተፈናቀሉብን በሺህ ምንተ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ሲሆኑ ድርቅና ችግር ለስደት የዳረጋቸውም የዚያኑ ያህል በሚሊዮን ቁጥር የሚገለጹ ናቸው። የውስጥ ፖለቲከኞቻችንና የማሕበራዊ ሚዲያ ሰልፈኞችም ችግሮቻችንን እያጦዙ ተስፋችን እንዲመናምንና ብሶተኛ እንድንሆን ጫና እየፈጠሩ ፋታ ነስተውናል። አገልግሎት ለማስፈጸም ወደ መንግሥታዊ ተቋማት ጎራ ሲባል ያለው ውጣ ውረድና የሙሰኞች ዓይን ያወጣ ድፍረት “ወይ አገር!” እያሰኘ ያስቆዝመናል፤ ሲበረታም የእምባ ግብር ያስከፍለናል።
በዚህ ሁሉ ቱማታ መካከል ሕዝባችን ተረጋ ግቶ፣ ከውጥንቅጥ ኑሮውና ግራ ከተጋባበት ሕይወቱ ፋታ በማግኘት ለጥቂት ቀናትም ቢሆን በእፎይታ የሚተነፍሰው በበዓላት ሰሞን ነው። የኑሮ ጉዳተኛም ይሁን ኑሮው የተሳካለት ዜጋ የበዓል ሰሞን የሚኖራቸው ተስፋና መረጋጋት እጅግም ልዩነቱ የሰፋ እስከማይመስል ድረስ ሽር ጉዱ፣ በየቤተ እምነቱ እየተገኙ የሃይማኖታዊ ሥርዓቶችንና የአምልኮተ ፈጣሪ ልምምዳቸውን የሚፈጽሙት በተስፋ ስሜት ውስጥ ሆነውና በፈጣሪያቸው ኤልሻዳይነት እየተጽናኑ ነው።
ማጀቱ የተሟጠጠባቸውም ሆነ ማዕዳቸው የተትረፈረፈላቸው ዜጎች በእኩል ተመሳሳይ ስሜትና በጠንካራ እምነት በዓላትን ማክበራቸው ምናልባትም ልዩ መገለጫችን ይሆን ብለን ብንጠይቅ በራስ ውበት አፍቃሬነት ሊተረጎምብን አይገባም። በማጠናከሪያ የምናቀርበው ማስረጃ ሳይቀር እንኳን እኛ ባለጉዳዮቹ ቀርተን ባእዳን እንግዶችና ቱሪስቶች ሳይቀሩ በበዓላቶቻችን እጅግ እንደሚመሰጡ ምስክርነታቸውን ደጋግመን አድምጠናል። ይሄም ቢሆን ግን “በዓሉን በምን ጥሪቴ አድምቄ እንደ ሰው ተደስቼ ልዋል?” የሚሉ በጭንቀት የታፈኑ ድምጾች በፍጹም አይኖሩም ብሎ ለመከራከር አይቃጣንም። በሚገባ ይኖራሉና።
ይህንን መሰሉን ውስንነታችንን የሚቀርፍልን ትልቁ እሴታችን በበዓላት ሰሞንና ቀናት እየተጠራራን ቤት ያፈራውን መቋደሳችን ሁነኛ ማሳያ ነው። ስለዚህም በዓላት ለእኛ ማኅበረሰብ የዓውዳመት ፌሽታ መገለጫ ብቻ ሳይሆኑ ለተወሱኑ ቀናት ያህል ከስሜት ህመም የሚፈውሱንና ተስፋችንን የሚያለመልሙ መድኃኒቶች ጭምር መሆናቸውን አስረግጠን እናሰምርበታለን።
እስካሁን አድምቀን ለማሞካሸት የሞከርነው የበዓላትን ስሜት ፈዋሽነትና ተስፋ አለምላሚነት ነው። ይህ ማለት ግን “በዓልን አራክሶ የከበረ፤ ጦም ገድፎ ያተረፈ የለም” በሚለው ብሂል ሥር ተጠልለን ሃይማኖታዊዎቹም ሆኑ ማሕበራዊ በዓላቶቻችን ከሥራ ሊያዘናጉን፣ ከእርሻ ሊያስተጓጉሉንና ከጥረታ ችን ሊያሳንፉን አይገባም። በሳምንት ሰባት ቀናት፣ በቀን ሃያ አራት ሰዓታት፣ ከወር ወርና ከዓመት ዓመት በዓላትን ካላከበርን ብለን እስረኛ እንዳንሆን ልንጠነቀቅ ይገባል። ሁሉን በአግባቡ መያዙና ማስተናገዱ ተገቢ ስለሆነ። ሃሳባችንን የምንቋጨው በሚከተለው ማሳረጊያ ነው። ባህሎቻችንና በዓላ ቶቻችን ለስሜት ፈውስ፣ ለመረጋጋት እድል የሚፈ ጥሩልን ማረፊያዎቻችን መሆናቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ እነርሱን እያሳበብን በብክነትና በክስረት ውስጥ እንዳንወድቅና የበዓላቶቻችን ተጠቂዎች በመሆን የከፋ ችግር ላይ እንዳንወድቅ ኑሯችንን በጥበብና በማስተዋል ልንመራ ይገባል። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 /2014