የዛሬው ‹‹የፍረዱኝ አምድ ዝግጅታችን በአዲስ አበባ ከተማ፤ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ በተለምዶ አራት ኪሎ እየተባለ ወደ ሚጠራው አካባቢ ይወስደናል። አቤቱታ አቅራቢዎች በአራዳ ክፍለ ከተማ በወረዳ ዘጠኝ በሚገኘው የእፎይታ ሸማቾች ማህበር አባል የሆኑት አቶ ዘካሪያስ ሄራኖ የተባሉ ግለሰብ እና ሌሎች ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የእፎይታ ሸማቾች ማህበር አባላት እንዲሁም አንዳንድ የማህበሩ ሰራተኞች ናቸው።
ከዚህ ቀደም የእፎይታ ሸማቾች ማህበርን በቦርድ አመራርነት ሲያገለግሉ የቆዩ ሰዎች ማህበሩን ከመመሪያ እና አሰራር ውጭ እንደፈለጉ በመመዝበራቸው ምክንያት 649 ሺህ 645 ብር ጉድለት እንዳለ ከክፍለ በመጡ የኦዲት ባለሙያዎች ባወጡት ሪፖርት ተመላክቷል። የቦርድ አመራሮቹ ይህን ያህል ገንዘብ ማጉደላቸው በኦዲተሮች ተረጋግጦ ሳለ እነኝህ አመራሮች ለጎደለው ገንዘብ ተጠያቂ መሆን ሲገባቸው ከህግ እና ስርዓት ባፈነገጠ መልኩ አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ የማህበሩ የቦርድ አመራር ሆነው እንዲመረጡ ተደርጓል። «ይህ ውሳኔ ማህበሩን እና አባላቶቹን ለከፋ ለችግር እንዲጋለጡ እያደረገ ነው » ሲሉ አቶ ዘካሪያስ ሄራኖ እና ሌሎች የእፎይታ ሸማች ማህበሩ አባላት እንዲሁም ሰራተኞች ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቤቱታቸውን አቅርበዋል። የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ከሰዎች እና ከሰነዶች ያገኛቸውን መረጃዎች ዋቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ህዝብ ግራ እና ቀኙን በማየት መፍረድ ይችል ዘንድ የደረሰበትን ሙሉ የምርመራ ውጤቱን እነሆ ብሏል። መልካም ንባብ።
የቅሬታው መነሻ- ከአቶ ዘካሪያስ ሄራኖ አንደበት፡-
እንደ አቶ ዘካሪያስ ሄራኖ ገለጻ፤ በዚህ ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎች በመላው አገሪቱ እንደሚኖሩ ኢትዮጵያዊን ሁሉ የኑሮ ውድነትን በመከላከል ጤናማ ኑሮን ለመምራት በማሰብ በ2000 ዓ.ም የእፎይታ የሸማቾች ማኅበር የተባለ የህብረት ስራ ማህበር መሰረቱ። ማህበሩ ከ1ሺህ 800 በላይ አባላትን ይዞ የተመሰረተ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ማህበሩ ከ2ሺህ 500 በላይ አባላትን አቅፎ ይዟል። አቶ ዘካሪያስ ሄራኖ በዚህ ማህበር አባል ሲሆኑ የአክሲዎን ድርሻም አላቸው።
ማህበሩ ተጠሪነቱ ለአባላቱ ነው የሚሉት አቶ ዘካሪያስ፤ ችግር ሲፈጠር የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ችግሩን ተከታትለው መፍትሄ እንደሚያሰጡት ይናገራሉ። ማህበሩ ከዚህ ቀደም 2,000,000 ተንቀሳቃሽ ካፒታል እና 8 መቶ ሺህ ብር ለትርፍ ክፍፍል የተቀመጠ ካፒታል ነበረው። ማህበሩ ከተመሰረተበት ዓላማ አንጻር ለተወሰኑ ጊዜያት ትርፋማ የነበረ እና ለአባላቶቹም የትርፍ ክፍፍል እስከማድረግ ደርሶ ነበረ። ይሁን እንጂ አሁን ላይ የማህበሩ የቦርድ አመራሮች እና በማህበሩ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች በሚያደርጉት ‹‹አይን ያወጣ ዝርፊያ እና ሌብነት›› እንዲሁም የአየር ባየር ንግድ ሳቢያ ማህበሩ ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጉን ይናገራሉ።
በ2013 ዓ.ም አቶ ዘካሪያስን ጨምሮ በርካታ የማህበሩ አባላት እና ሰራተኞች በማህበሩ የሚስተዋሉ ያልተገቡ አሰራሮችን በማየታቸው ማህበሩ ኦዲት እንዲደረግላቸው ይጠይቃሉ። በዚህም መሰረት ከአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ጽ/ቤት ኦዲት ቡድን የመጡ የኦዲተሮች የማህበሩን ከሐምሌ 1 ቀን 2012 እስከ ሰኔ 30/2013 ዓ.ም የአንድ ዓመት አጠቃላይ ወጪ እና ገቢ የኦዲት ምርመራ ያደርጋሉ። በዚህ የኦዲት ምርመራ በማህበሩ 649 ሺህ 645 ብር ጉድለት መኖሩን ታወቀ።
ይህ በእንዲህ እያለ በጣም ጥቂት ቁጥር ያላቸው አባላት በተገኙበት ሰኔ 19/2014 ዓ.ም በወረዳ ዘጠኝ ስብሰባ ተካሄደ። በሸማች ማህበሩ ከፍተኛ የገንዘብ ብክነትን መኖሩን የተገነዘቡት የማህበሩ አባላት እና ሰራተኞች ይህ የኦዲት ጉድለት እንዲከሰት ያደረጉ የማህበሩ ሰራተኞች እና የቦርድ አመራሮች ይጠየቁ ሲሉ በስብሰባው ላይ ሃሳብ ቢያነሱም ለጥያቄአቸው ምላሽ የሚሰጥ ሰው ማግኘት ሳይችሉ መቅረታቸውን አቶ ዘካሪያስ ይናገራሉ።
የሸማች ማህበሩ ቅሬታ አቅርበው ኦዲተር ከክፍለ ከተማው ይመጣል ተብሎ በሰኔ 19/2014 ዓ.ም ቀጠሮ ያስያዙት ቅሬታ አቅራቢዎች ሆነው ሳለ በቀኑ በተካሄደው ስብሳባ ላይ ቅሬታ የሚያቀርቡ የማህበሩ አባላት እና ሰራተኞችን በማዳመጥ ተገቢውን መልስ ከመስጠት ይልቅ በስብሰባው ጉድለት የተገኘባቸው እና አቤቱታ የቀረበባቸው አመራሮች የስብሰባ አጀንዳውን ወደ ጎን በመተው የራሳቸውን አጀንዳ ለተሰብሳቢው በማቅረብ ራሳቸው ጠያቂ፤ ራሳቸው መላሽ ሆነው አረፉት ሲሉ አቶ ዘካሪያስ ያስረዳሉ።
መጀመሪያውኑ ስብሰባ መካሄድ ያለበት ምዕላተ ጉባኤ ሲሟላ ነው የሚሉት አቶ ዘካሪያስ፤ ከ2 ሺህ በላይ ማህበሩ አባላት ያሉት ቢሆንም በስብሰባው የተገኘው አጠቃላይ የሰው ብዛት ከ70 አይበልጡም፤ ከእነኝህ መካከልም አብዛኛዎቹ የራሳቸው የቅጥር ሰራተኞች መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ይህን ተከትሎ ምዕላተ ጉባኤው ሳይሟላ ስብሰባው መደረግ የለበትም! ውሳኔ ማስተላፍም ተገቢ እና ህጋዊ አይደለም! ነገር ግን አመታዊ የማህበሩን ሪፖርት እወቁ የምትሉ ከሆነ አውቀን እንሄዳለን። ይሁን እንጂ ምዕላተ ጉባኤው ሳይሟላ የሚጸድቅ፣ የሚሻር እና የሚሻሻል ነገር መኖር የለበትም የሚል ቅሬታ ለስብሰባው አዘጋጆች ቢያቀርቡም የስብሰባ አዘጋጆች ከማዳመጥ ይልቅ የመብት ጥያቄ ባነሱ የማህበሩ አባላት ላይ ማስፈራሪያ እና ዛቻ እንደደረሰባቸው አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ።
በዚህም አቶ ዘካሪያስ እና ሌሎች ያቀረቡት ቅሬታ ተቀባይነት ያጣል። የማህበሩ አባላት እና ሰራተኞችን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ስብሰባውን ያዘጋጁት ሰዎች «እኛ የመጣነው በሌሎች ወረዳዎች በሚገኙ ማህበራት ላይ እንዳደረግነው ሁሉ በዚህም ወረዳ በሚገኘው የሸማች ማህበር ሪፎርም ለማድረግ ነው።» ይሏቸዋል። ይህን ተከትሎ ሪፎርሙ ምን እንደሆነ እንስማው፤ ነገር ግን ሌላ ውሳኔ ግን ምዕላተ ጉባኤው ሳይሟላ መወሰን አትችሉም ሲሉ በድጋሚ ለሰብሳቢዎች ሊያመላክቱ መሞከራቸውን ነገር ግን ለችግራቸው ጆሮ ሊሰጥ የሚችል ማግኘት አለመቻላቸውን ይገልጻሉ።
ይህን ተከትሎ የማህበሩ አባላት ቢያንስ ቢያንስ 649 ሺህ 645 ብር ጉድለት እንዲፈጠር ያደረጉ አካላት ይጠየቁልን? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። ስብሰባውን የሚመራው አካል ጉድለት እንዲፈጠር ያደረገን አካል ከመጠየቅ ይልቅ የተፈጠረው ጉድለት በሪፎርሙ ይስተካከላል በማለት አድበስብሶ ማለፉን እና ዛሬ የምንወስነውን ውሳኔ በጭብጨባ ማጽደቅ አለባችሁ ብሎ እንዲያጨበጭቡ መገደዳቸውን ያስታውሳሉ።
እንደ አቶ ዘካሪያስ ገለጻ፤ ለስብሰባ የተጠሩት አርባ የማህበሩ አባላት ብቻ ናቸው። ምክንቱም ሌሎች የማህበሩ አባላት ቢገኙ ችግር ይፈጥራሉ፤ ይቃወሙናል በሚል ነው። ይሁን እንጂ የተገኙት እነኝህ አርባዎቹም በራሳቸው በፈቃደኝነት ሪፖርቱን ተቀብለው ሪፎርሙን ተቀብለው የኮሚቴዎችን ምርጫ አላጻደቁም።
ሰብሳቢዎችም የማህበሩን አባላት ፍላጎት ወደጎን በመተው ሪፖርቱን በጭብጨባ ካጸደቁ በኋላ ኮሚቴ ምርጫ ይካሂድ ተባለ። ይህን ተከትሎ ጠቅላላ ጉባኤ ባልተገኘበት ምርጫ ማካሄድ አይቻልም ምክንቱም እዚህ የሚገኘው የማህበሩ አባል ከ2 ሺህ ስምንት መቶ መካከል ስብሰባው ላይ የተገኘው አርባ አይሞላም። ይህ በሆነበት የኮሚቴ ምርጫ መካሄድ የለበትም የሚል ተቃውሞ ማንሳታቸውን ይናጋራሉ። ሪፖርቱን ሰምተናል፤ በዚህም ጉድለቱን ሰምተናል። ይህን ጉድለት ያደረሱ ሰዎች ሳይጠየቁ በፊት ሌላ ኮሚቴ መመረጥ የለበትም ቢባሉም ጥያቄ አናስተናግድም በማለት የኮሚቴ ምርጫ አንዲካሄድ ተደርጓል።
ምርጫውን የሚያካሂዱ ሰዎች ደግሞ ከክፍለ ከተማ የመጡ ሰዎች ናቸው። ምርጫውን ያካሄዱት ሰዎች ምንም ስለማህበሩ የማይመለከታቸው ሰዎች ናቸው። የማህበራት ማደራጃዋ አንድ ቆጣሪ በመሆን ምርጫው እንዲካሄድ ተደረገ፡፤ ምርጫው ሲካሄድ 649 ሺህ 645 ብር ጉድለት ተጠየቂ መሆን የሚገባቸው ሰዎች እንደገና ተመረጡ። ከዚህ በፊት የነበሩ እና በስራ ዘመናቸው 649 ሺህ 645 ብር ጉድለት ያጎደሉ ሰዎች በምርጫው እንኳን መካተት የለባቸውም የሚለውን ለመናገር እድሉን ሳናገኝ ቀረን ። በዚህም መሰረት ራሳቸው መራጭ፣ አስመራጭ እና ራሳቸው አጽዳቂ፣ ራሳቸው ቆጣሪ በመሆን ከክፍለ ከተማ ሪፎርም ተብሎ የመጡ ሰዎች ይህን አይነት ውሳኔ አስተላልፈው ሂደዋል።
ቅሬታ አቅራቢው አቶ ዘካርያስ እንደተናገሩት፤ 649 ሺህ 645 ብር ጉድለት እየታየ እና በርካታ በማህበሩ ውስጥ ያልተጣሩ እና የተዝረከረኩ እንዲሁም የባከኑ ሃብቶች እያሉ ተጠያቂ መሆን የሚገባቸውን ሰዎች መልሶ የቦርድ አባል አድርጎ መመረጥ የለባቸውም። ለጉድለቱ ተጠያቂው ሳይታወቅ ማንን ተጠያቂ በማድረግ ነው ምርጫ የሚደረገው? አይደለም 649 ሺህ 645 ብር ያህል ብር ይቅርና የህዝብ ንብረት እስከሆነ ድረስ አንድ ብር ጉድለት ካለ ያጎደለው ሰው ሊጠየቅ ይገባ ነበር። ሪፎርሙስ የጎደለውን ራሱ ያስተካክክለዋል የሚባለው ሪፎርሙ ከየት አምጥቶ ነው ጉድለቱን የሚያስተካክለው? ሲሉ ይጠይቃሉ።
ሌላው አቤቱታ አቅራቢ ስማቸው እንዲጠቀስ አልፈለጉም። እኝህ አቤቱታ አቅራቢ በማህበሩ ሰራተኛ እና የማህበሩ ባለአክሲዎን አባል ናቸው። እንደ አቤቱታ አቅራቢው በየጊዜው የሚበላሹ የማህበሩ ሸቀጦች አሉ። ለእነዚህ ሸቀጦች መበላሸት ዋና ምክንያት አመራሮች ናቸው። ምክንያቱም ለመስረቅ ይመቻቸው ዘንድ ሆነ ብለው የሚያደርጉት መሆኑን ይናገራሉ። መጋዘን ውስጥ ቢገባም በርካታ የተባላሹ እቃዎች እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ሌላው አመራሮች የተጠቀሙት የመዝረፊያ ስልት ደግሞ ለመከላከያ፣ ለአባይ ግድብ እና መሰል አገራዊ ለሆኑ ግዳጆች በሚል ሰበብ መሆኑን አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ። በዚህም ያለ ማህበሩ አባላት እውቅና ከመቶ ሺህዎች እስከ ሚሊዮን የሚደርሱ ገንዘቦችን በእርዳታ ስም እየተዘረፉ እንዲወጡ ተደርጓል ይላሉ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 /2014