በኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ለሥራ ዕድል ፈጠራ ብሎም ሀብት መፍጠሪያ ከመጠቀም አኳያ መልካም እና አበረታች ጅምሮች መታየት ጀምረዋል። የሥራ ዕድል ፈጠራውን ውጤታማ ለማድረግም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እገዛ እያደረጉ ሲሆን፣ የፈጠራ ስራ ሃሳብ የሚያቀርቡ ተወዳዳሪዎች ተሸላሚ የሚሆኑበት አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራም ነው።
ሰሞኑንም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሁለተኛውን ብሔራዊ የሥራ ጉባዔ «ዘላቂ ሥራ ለብሩህ ነገ» በሚል መሪ ሀሳብ ሁለተኛውን የስራ ጉባኤ ባካሄደበት ወቅት ከተከናወኑ ተግባሮች የፈጠራ ሥራቸውን ባቀረቡ መካከል ውድድር ተካሂዷል። የፈጠራ ስራቸውን ካቀረቡ ዘጠኝ ተወዳዳሪዎች መካከልም አሸናፊ የሆኑ ሶስት ተወዳዳሪዎች ተሸላሚ ሆነዋል።
በውድድሩ አንደኛ የወጣው የ23 ዓመቱ ወጣት ናትናኤል ታከለ ይባላል። ናትናኤል፤ በአራዳ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ አጠቃላይ ብረታ ብረትና የፋብሪካ ውጤቶች ሥራን መሰረት ካደረገ የትምህርት ክፍል የተመረቀ ሲሆን፤ ለውድድር ይዞ የቀረበውም አካል ጉዳተኞች የሚጠቀሙበት ዊልቸር ነው።
ወጣት ናትናኤል የሠራው ዊልቸር የአካል ጉዳተኞችን ድካምና እንግልት ማቃለል የሚችል፣ በሶላር የሚሠራ፣ የራሱ የሆነ ቻርጄብል ባትሪ፣ የፊት ለፊት መብራት ያለውና የብሉቱዝ ቴክኖሎጂ የተተከለለትም ነው።
ዊልቸሩ የራሱ የሆነ አፕሊኬሽን እንዲኖረውም ተደርጓል፤ ተገልጋዮች አፕሊኬሽኑን በእጅ ስልካቸው ላይ በመጫን ዊልቸሩን እስከ ሰባት ሜትር ድረስ በቀላሉ ማዘዝና መቆጣጠር የሚያስችላቸው እንደሆነ ያስረዳው ናትናኤል፤ ይህ ደግሞ የአካል ጉዳተኞችን ሕይወት ቀለል በማድረግ የተሻለ ሕይወት መምራት ያስችላቸዋል ብሏል።
ገና ልጅ እያለ ጀምሮ የፈጠራ ሥራ ይሞካክር እንደነበር የሚገልጸው ወጣት ናትናኤል፤ ተሸላሚ ያደረገውን ዊልቸር ለመስራት ያነሳሳው የ10ኛ ክፍል ተማሪ እያለ በዊልቸር የሚሄድ አካል ጉዳተኛ ከድካሙ የተነሳ ዳገት መውጣት አቅቶት መሀል መንገድ ላይ ቆሞ በመመልከቱ ነው። በወቅቱ አካል ጉዳተኛው የሚገጥመውን ችግር በዝርዝር ጠይቆ መረዳት በመቻሉና ለችግሩ መፍትሔ ያለውን ሁሉ ሲሠራ ቆይቶ በዚህ ጉባኤ ተወዳዳሪና ተሸላሚ ያደረገውን በማንዋል የሚሠራ ዊልቸር በፈጠራ ሥራ ማሳየት ችሏል።
ብዙዎች የሚጠቀሙበት ዊልቸር በሁለት እጅ የሚገፋና እጅግ አድካሚ ከመሆኑ የተነሳ አካል ጉዳተኞቹ ለተለያዩ የጤና ችግሮች የሚጋለጡ ስለመሆናቸው በመንገዱ ላይ ካገኘው አካል ጉዳተኛ የተረዳው ወጣት ናትናኤል፤ ችግሮቻቸውን ሁሉ መቅረፍ የሚያስችል የፈጠራ ሃሳብ ይዞ መቅረብ እንዳለበት በማሰብ የተለያዩ ዲዛይኖችንና ጥናቶችን በማድረግ በፈጠራ ሥራው ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆነ ዊልቸር መሥራት ችሏል።
ዊልቸሩ በሞተር የሚሠራ ሲሆን፣ ልክ እንደ መኪና ፍጥነት መጨመሪያና መቀነሻ ያለው፤ 360 ዲግሪ ባሉበት ቦታ ሆነው መቆጣጠር የሚያስችል ነው። ሀዛርድና ለምሽት የሚያገለግል የግንባር መብራት እንዲሁም የራሱ የሆነ የጸሐይ መከለያም ያለውና ከፊት 10 ኪሎ ግራም፤ ከኋላ ደግሞ እስከ 70 ኪሎ ግራም የሚደርስ በድምሩ 80 ኪሎ ግራም ዕቃ ይዞ መንቀሳቀስ የሚያስችል ዊልቸር እንደሆነም ወጣት ናትናኤል አስረድቷል።
በተቻለኝ አቅም የአካል ጉዳተኞችን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ሥራ ነው የሠራሁት የሚለው ወጣት ናትናኤል፤ በቀጣይም ከውጭ ሲገባ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀውን ዊልቸር በአገር ውስጥ በስፋት በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማዳን፤ ለአካል ጉዳተኞቹም ዊልቸሩን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ አቅዷል። ለአንድ ዊልቸርም እስከ 85 ሺ ብር ይጠይቃል። በአሁኑ ወቅትም ፈረንሳይ ጉራራ አካባቢ የማምረቻ ቦታ ከመንግሥት ማግኘት የቻለው ወጣት ናትናኤል፤ ለሥራ ማስጀመሪያ የሚሆን ፋይናንስ ሲያገኝ ወደ ምርት እንደሚገባ ነው የተናገረው።
ሌላኛው በፈጠራ ሥራው ተወዳድሮ ተሸላሚ የሆነው የኮምቦልቻው ፉአድ መሀመድ ነው። ፉአድ፤ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ምሩቅ ነው። በአካባቢውም ከልጅነቱ ጀምሮ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ይሞካክር እንደነበር ገልጾ፤ የተወዳዳረበት የፈጠራ ሥራም ሊዝ ማሽን የተባለ ግዙፍ ማሽን እንደሆነ ያስረዳል። ማሽኑ አንድ ነገር ብቻ የሚሠራ ሳይሆን፣ በየትኛውም ቦታ ማንኛውንም ነገር መሥራት የሚያስችል ነው ይላል።
ሊዝ ማሽን ከስሙ ጀምሮ የማሽኖች አባት በመባል የሚታወቅ እንደሆነ ያስረዳው ፉአድ፤ ይህን ማሽን መሥራት ከተቻለ ሌሎች ማንኛቸውንም አይነት ቅርጽ ያላቸውን ማሽኖች በቀላሉ መሥራት የሚያስችል ነው ብሏል። የተለያዩ ማሽኖችን ለአብነትም ከብሎን ጀምሮ መሥራት የሚጠቅምና የተፈለገውን ቅርጽ ማስያዝም የሚያስችል እንደሆነ አስረድቷል።
ማንኛውንም መሥራት የተፈለገን አንድ ነገር በተለያየ ዲዛይን በሶፍትዌር በመሥራት በማሽኑ ማምረት ይቻላል የሚለው ፉአድ፤ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ እያለ ሂሊኮፕተር ለመሥራት አንዳንድ አካላትን ለማሠራት በሄደባቸው የተለያዩ ቦታዎች ለትንሹ ሥራ ይጠየቅ የነበረው ዋጋ የሚቀመስ እንዳልነበረም ያስታውሳል። ይሄኔ ታዲያ ለምን ማሽኑን አልሠራም በማለት እንደተነሳሳ ይገልጻል።
በመሆኑም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚጠይቀውን ግዙፍ ማሽን ለመሥራት ባደረገው ጥረት በፌዴራል ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አማካኝነት ተወዳድሮ ሁለተኛ ደረጃን ማግኘት የቻለው ፉአድ፤ ማሽኑን ለመሥራት ከራሱ ከ60 እስከ 70 ሺ ብር ማውጣቱንም ይናገራል። አብዛኛው ወጪ በስፖንሰር መሸፈኑን ይገልጻል፤ አጠቃላይ ማሽኑ እስከ 200 ሺ ብር ወጪ መጠየቁን ተናግሯል።
‹‹በግል ፈጠራ የሠራሁት ማሽን በየትኛውም ኩባንያዎች ይፈለጋል›› የሚለው ፉአድ፤ በቀጣይም ይህንኑ ማሽን በማምረት ለተለያዩ ኩባንያዎች የማስረከብ ዕቅድ አለው። ማሽኑን ለማምረትም የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ በመግለጽ አሁን ለሠራው ግዙፍ ማሽን እገዛ ሲያደርጉለት ለነበሩ ለኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅና ለአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ምስጋና በማቅረብ በቀጣይም እገዛቸው እንደማይለየው ያለውን ተስፋ ገልጿል።
በውድድሩ ቀርበው ተሸላሚ የሆኑት ሶስት የፈጠራ ሥራ ባለቤቶች እያንዳንዳቸው የአምስት ሺ ዶላር ወይም የ260 ሺ ብር ተሸላሚ ሆነዋል፤ ሶስቱም ያቀረቧቸው የፈጠራ ሥራዎች ወደ አገልግሎት ሊለወጡ የሚችሉ መሆናቸው ልዩ የሚያደርጋቸው እንደሆነ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በሁለተኛው ብሔራዊ የሥራ ጉባኤ መድረክ ላይ ከተካሄዱ ሁነቶች መካከል የፈጠራ ሥራ ውድድር አንዱ እንደነበር የገለጹት በሥራና ክሂሎት ሚኒስቴር የሥራ ዕድል ፈጠራ ሃሳቦች ማበልጸጊያ ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ አለምጸሐይ ደርሶልኝ፤ ውድድሩ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች የሚያበረታታ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም የፈጠራ ሃሳብ ላላቸው ወጣቶች ጥሪ ተደርጎ ነበር። ውድድሩ ግንቦት ወር ሊደረግ ታስቦ በተለያዩ ምክንያቶች ተገፍቶ ነሐሴ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ተካሂዷል። ለውድድሩ 251 ወጣቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከቀረቡት የፈጠራ ሃሳቦች መካከልም የትኞቹ ችግር ፈቺዎች ናቸው? ለውጥ ማምጣትስ የሚችሉት ምን ያህሎቹ ናቸው? ምቹና የተለየ ነገር ይዘው የመጡትስ እነማን ናቸው? በሚል ተመልምለዋል። ዕድሜያቸው እስከ 29 ዓመት የሆኑ ወጣቶች የተጋበዙ ሲሆን፣ ለውድድሩ የቀረቡ መስፈርቶችን ማሟላት የቻሉ ወጣቶች እንዲወዳደሩ ተደርጓል።
በቀረበው መስፈርት መሰረት በተለያዩ ባለሙያዎች ሲመረጥ አብዛኛዎቹ ለውድድር የቀረቡ ወጣቶች መስፈርቱን ሊያሟሉ አልቻሉም ያሉት ኃላፊዋ፣ 10 ልጆች ብቻ ለውድድሩ ተመርጠው ከአስሩ ዘጠኙ የፈጠራ ሥራቸውን አቅርበው ሶስቱ ተሸላሚ ሆነዋል ብለዋል። አሸናፊዎቹም እያንዳንዳቸው የአምስት ሺ ዶላር ወይም 260 ሺ ብር ማግኘት እንደቻሉ ኃላፊዋ ጠቅሰው፤ ገንዘቡም ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን መገኘቱን ወይዘሮ አለምጸሐይ ገልጸዋል።
ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን አጠቃላይ የሥራ ዕድል ፈጠራውን በተለያየ መንገድ የሚደግፍ የውጭ ድርጅት እንደሆነ የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶችና ወደ ንግድ መግባት የሚችሉ ሰዎችን ለመደገፍ ድርጅቱ በመደበው በጀት ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ፈጠራ ከሌለ፣ አዳዲስ ሀሳቦች ካልመጡና ኢንተርፕራይዞች ካልተመሰረቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሊኖር እንደማይችል ያመለከቱት ወይዘሮ አለምጸሐይ፤ ለዚህም የተለያዩ ድጋፎች እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት። በተለይም አዳዲስ ሃሳብ ይዘው የሚመጡ ልጆች ሃሳባቸው ተደግፎ ኢንተርፕራይዝ እንዲሆኑና ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲችሉ የተለያዩ ድጋፎች እንደሚደረጉ ጠቁመው፣ ይህም የአዳዲስ ሃሳብ ባለቤቶቹ ይበልጥ እንዲነሳሱና ሌሎችም እንዲበረታቱ ያደርጋል ብለዋል።
እንደ ወይዘሮ አለምጸሐይ ገለጻ፤ አዳዲስና ችግር ፈቺ ናቸው የተባሉ የፈጠራ ሃሳቦችን ወደ ተግባር ለመቀየርና በሥራ ላይ አውሎ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንዲቻል በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮዎች ትልቅ ድርሻ አላቸው። በመሆኑም የፌዴራል ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች በክልል፣ በወረዳና በቀበሌ ካሉ ቢሮዎች ጋር በማገናኘት የተለያዩና አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን በማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን እንዲፈጥሩላቸው ያደርጋል።
ከዚህ ቀደምም ‹‹ብሩህ የፈጠራ ሃሳብ›› በሚል በሁለት ዙር ውድድር ተካሂዶ 55 ልጆች ተሸላሚ ሆነዋል። በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ ወጣቶችን በየጊዜው በመከታል መዳረሻቸውን ለማወቅ ጥረት ይደረጋል። በመሆኑም በርካታ ቁጥር ያላቸው ልጆች ሥራቸውን ቀጥለው ጥሩ ቦታ መድረስ የቻሉ ሲሆን፤ ከፊሎቹ ደግሞ በቦታ እጥረትና በሌሎች ምክንያቶች ሥራውን ማስቀጠል እንዳልቻሉ ይገልጻሉ። ለዚህም በአካባቢው የሚገኘው የሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ተናግረዋል።
የተለያዩ የልማት አጋሮችን በማስተባበር የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች የማበረታታት ሥራ በቀጣይም የሚሠራና አሁን የተጀመረውም ቀጣይነት እንዲኖረው እንፈልጋለን የሚሉት ኃላፊዋ፤ ለአብነትም የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጠቅሰዋል፤ ድርጅቱ የአምስት ዓመት ፕሮግራም እንዳለውና ሁለት ዓመት ማስቆጠሩንና በቀሪዎቹ ዓመታትም ውጤታማ ሥራ እንደሚሰራም አስታውቀዋል። ይህ ሲባል ታዲያ ድጋፍ የተደረገላቸው ወጣቶች የት እንደ ደረሱ ተከታትሎ ማሳየትና መደገፍ ያስፈልጋል ይላሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም የገጠር ወረዳና ቀበሌዎች የሚገኙ ወጣቶች የፈጠራ ሃሳብ እያላቸው ዕድሉን የማያገኙ አሉ። እነዚህ ወጣቶች ጋር ተደራሽ ለመሆን ከቀበሌዎች ጀምሮ ወደ ወረዳ ብሎም ወደ ዞን እያሉ መምጣት እንዲችሉ የማድረግ ሥራ ይሠራል፤ ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በቅርቡ ባካሄደው ሁለተኛው ብሐራዊ የስራ ጉባኤ መዝጊያ ላይ በ2014 በጀት አመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ኢንተርፕርይዞች፣ የዘርፉ አስፈጻሚ አካላት፣ ስራ ፈጣሪዎች እና የማእከል አገልግሎት ሰጪዎች እውቅና የመስጠት መርሀ ግብር አካሂዷል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በስራ ፈጠራ ፕሮግራም በክህሎት የበቃ የተፍታታና አምራች የሆነ ትውልድን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የላቀ አፈጻጸም ያሳዩ ኢንተርፕራይዞችና አስፈጻሚ አካላት፣ ስራ ፈጣሪዎችና የማእከል አገልግሎት ሰጪዎች የኢኮኖሚውን መሰረት ሲጥሉ መበረታታት እንደሚገባቸው አስታውቀዋል፡፡
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው መድረኩ በላቀ አፈጻጸም የተሸለሙትን በዘርፉ ከተሰማሩ አካላት ልቀው የተገኙትን ተሸላሚዎች ተምሳሌት እንዲሆኑ ለማስቻል ታልሞ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሽልማቱ በአነቃቂነቱ ትልቅ እሴት አካይ የሆነ ውጤት ይኖረዋል ብለን እንጠብቃለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፤ በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን በመግለጽ በዘርፉ የአውትሶርሲንግ፣ ፍሪላንሲንግ፣ እና ጊግ የተባሉ የሥራ ዘርፎች እየተለመዱ መምጣታቸውን ተናግረዋል። እነዚሁ ዘርፎችም ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉና የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎችም የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ጋር «እንቆጳ» የተሰኘ ዲጂታል ኢንተርፕሩነርሽፕን የማስተዋወቅና የማለማመድ ሥራ በመሥራት ላይ እንደሆነ አቶ ንጉሱ ገልፀው፤ እንቆጳ ውይይት በዲጂታል መንገድ ዓለም አቀፍ ተሳታፊዎችን በማሳተፍ ሰፊ ልምድ ከማስገኘቱም በላይ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሃብት በማሳየት ወደ አገሪቱ ማምጣት እና የሥራ ዕድል መፍጠር መጀመሩን አብራርተዋል።
ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም፣ መርሲኮርፕ፣ ጂ.አይ.ዜድ፣ ጀነሬሽን አንሊሚትድ፣ ዩኒሴፍና የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድል ፈጠራን እያገዙ መሆናቸውንም ጠቅሰው፤ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አቀናጅነት ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም፣ መርሲኮርፕ፣ ጂ.አይ.ዜድ፣ ጀነሬሽን አንሊሚትድ እና ዩኒሴፍ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች «ብሩህ» ተብሎ በተሰየመ የሥራ ዕድል ፈጠራ የገንዘብ እና የባለሙያ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17 /2014