ያኔ ቀደም ባሉት አመታት ..እንደ አሁኑ በዘርና በጎሳ ሳንከፋፈል በፊት፤ አገራችን በእኛ እኛም በአገራችን ነበርን። እንደ አሁኑ በብሄርና በኃይማኖት ከመለያየታችን በፊት የአንድነት መገለጫችን መለያችን ነበር። አሁን ሁሉም ነገር ሌላ ነው..አንድነት ያቆነጀው ኢትዮጵያዊ መልካችን ዘርና ጎሳ፣ ብሄርና ኃይማኖት ገብቶበት ወይቧል።
ቀደም ባሉት ዘመናት ሩህሩህነት መገለጫችን ነበር፣ አይደለም እርስ በርስ ልንገዳደል ቀርቶ የተማረኩ የጠላት ምርኮኞችን አብልተንና አጠጥተን ተንከባክበን የምንሸኝ ነበርን። ዛሬ ሌላ ነን..የገዛ ወንድሙን በመግደል እና በማሰቃየት የሚኮፈስ ትውልድ አፍርተናል። በጋራ ብንኖርባት የምትበቃንን፣ በፍቅር ብንኖርባት የምትሰፋንን አንዷን ኢትዮጵያ ብዙ ቦታ ከፋፍለን እንዳትበቃን እየታገልን ነው። ተያይዞ መቆም እያለ፣ ተቃቅፎ መኖር እያለ ለመውደቅ እየተገፋፋን ነው።
ብሄሩን ትልቅ አድርጎ አገሩን ያሳነሰ፣ ዘሩን ኩሩ አድርጎ ሰውነቱን ያኮሰሰ ማህበረሰብ የኋላ ኋላ መውደቁ የማይቀር ነው። አለም ላይ ከአገራቸው ብሄራቸውን ያስቀደሙ፣ ከሰውነታቸው ዘራቸውን ያስቀደሙ ግለሰቦች ሆኑ ቡድኖች አወዳደቃቸው የከፋ እንደነበር መዛግብት ይመሰክራሉ። በታሪክ ውስጥ በነውረኝነት ተመዝግበዋል።
የእኛም በብሄር ስም የምናደርገው ያልተገባ መሯረሯጥ አንድም ለመውደቅ ከዛም በላይ ነውረኛ ታሪክ ከመጣፍ ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። ለሁላችን የምትበቃ አገር አለችን፣ በጋራ እሴት፣ በጋራ ባህል የተሳሰረ ማንነት አለን፤ በዚህ እውነት ውስጥ ጸንቶ መኖር እንጂ ለመውደቅ መገፋፋት ትርፍ የለውም።
ኢትዮጵያ አገራችን አንድ ናት..በአንድ ሀሳብ፣ በአንድ ህልም ያጸናናት የጋራ ቤታችን ናት። የአባቶቻችን አንድነት ምሰሶ ሆኖ፣ ዋልታና ማገር ሆኖ ያቆማት ናት። እኛ መዶሻ ሆነን በአንድነት ዋልታና ማገር የታነጸችውን አገራችንን ለማፍረስ መሽቀዳደም የለብንም። በብሄር ስም የምንለኩሰው እሳት መጀመሪያ የሚያቃጥለው እኛኑ ራሳችንን ነው። መርዝ መጀመሪያ ብልቃጡን እንደሚጎዳ ሁሉ ክፉ ሀሳብም መጀመሪያ ባለቤቱን ነው የሚጎዳው።
አሁን ከትናንት ተምረን ለማይጠቅመን ነገር መሮጥን ማቆም፤ በሚበጀን ነገር ላይ መትጋት ይጠበቅብናል። አሁን የሚጠቅመን በጋራ አገር ማሳደግ ነው። ከአለም ድሀ የሆነችውን አገራችንን ማልማት፣ ማሰልጠን ነው። አሁን የሚጠቅመን በቀን ሶስት ጊዜ መብላት ያልቻለ ማህበረሰባችንን መታደግ ነው። የፖለቲካ ቅራኔዎችን በእርቅ መፍታት ነው። በዘር ተኮር ፖለቲካ ያጣናቸውን በረከቶቻችንን መፈለግ ነው።
አሁን የሚጠቅመን ለወጣቱ የስራ እድል፣ ለዜጎች ደግሞ ምቹ አገር መፍጠር ነው። ህጻናት የሚያድጉባትን፣ አዛውንቶች የሚጦሩባትን አገር መገንባት ነው። አሁን የሚጠቅመን ትውልዱ የሚኮራበትን የጋራ እሴት መፍጠር ነው። ለዚህ ደግሞ ቀድመን በእርቅ ደም ማድረቅ ይጠበቅብናል። በመነጋገር ችግሮቻችንን መፍታት ያስፈልገናል። የዘር ፖለቲካ ያጠየመውን ኢትዮጵያዊነት ማደስ፤ የእኔነት አረም የበቀለበትን ሰውነታችንን ማከም ይኖርብናል።
እንዲህ ካልሆንን ንጋት አናይም። ኩርፊያና ጥላቻ ባጨለሙት ማምሻ ላይ ቆመን ንጋት መናፈቅ ሞኝነት ነው። መጀመሪያ ልቦቻችንን ለብርሀን እናዘጋጅ። መጀመሪያ አይኖቻችን ንጋት እንዲናፍቁ እናድርግ። በመጠላላት የመሹብን ንጋቶች፣ በዘር እሳቤ የዘገዩብን ተስፋዎች ከእርቅ በኋላ የሚነጉ ናቸው። እንዲነጋልን መታረቅ አለብን። መግባባት አለብን።
እስከመቼ በማይጠቅመን ነገር ላይ እየለፋን እንኖራለን? እስከመች አንድ ቦታ እየረገጥን እንደ ቀንድ አውጣ ስናዘግም እንኖራለን? የማይጠቅሙንን ስንከተል የሚጠቅሙን እያጣን እንደሆነ ለመረዳት ጊዜው አልረፈደብንም፤ ወደ ማስተዋላችን እንመለስ። አሁን ላይ ገባን ብለን የሄድንባቸው መንገዶች ያስከፈሉንን ዋጋ እናስላ። የገቡን ይሄን ያክል ካሰቃዩን በርግጥም የገቡን መሰለን እንጂ እንዳልገቡን ስለሚመሰክሩ ከዚህ መንገዳችን እንመለስ።
አሁን ከትናንት መንገዳችን ወጥተን ወደ አዲስ መንገድ እንግባ፤ ገብተውናል ያተርፉናል ባልናቸው እኔነት፣ ከፍ ያለ ራስ ወዳድነት፤ የብሄር ፖለቲካ ወዘተ .. ተሰቃይተናል። አሁንም እየተሰቃየን ነው። ገብቶናል ባልንው ዘረኝነት፣ ገብቶናል ባልንው ሀይማኖተኝነት የዘመናት እሴቶቻችንን አጥተናል። እስኪ ወደ ቀደሙት እሴቶቻችን /ወደ አልገቡን/ እንመለስ። እስኪ ወዳጣልናቸው/ወደ አልገቡን/እውነታዎች እንመ ልከት።
የጣልናቸው እሴቶቻችን የዘመናት ችግሮቻችን መፍትሄዎች፤ የህይወታችን አቅጣጫ ጠቋሚዎች ናቸው። ገብተውናል ባልናቸው ግን ደግሞ ባልገቡን ነውሮቻችን መሰቃየታችን ይብቃ። ያልገባን ፍቅር ነው..ያልገባን እኮ አንድነትና መቻቻል ነው። ያልተረዳነው እውነት ኢትዮጵያዊነት ነው።
እስኪ ወዳልገቡን የፍቅርና የአንድነት መንፈሶች ዞር ብለን ደግሞ እንሞክረው። እስኪ ወዳልገባን ኢትዮጵያዊነት ተመልሰን ሰላማችንን እንፈልገው፣ ሞታችንን፣ ጉስቁልናችንን እንታ ደገው። ወዳልተረዳንው ዞረን በፍቅር ሞታችንን እንግደለው።
ብሄርተኝነት ወልዶ ባሳደገው ምናምንቴ ጭንቅላት ስናስብ ተበልጠናል። የዘር ፖለቲካ ዘርቶ ባበቀለው ሰውነት ስንመጻደቅ ተበልጠናል። ጥላቻና ዘረኝነት ባስጎነበሰው ጎባጣ ጀርባና ትከሻ እየተራመድን ተበልጠናል። አሁን ሁሉም በልጠውናል። በሁሉም ተበልጠናል። ተለያይተን የተራመድንባቸው እነዛ የመጠላላትና የመገፋፋት ዘመኖች ዛሬ ላይ በብዙ ነገር ወደ ኋላ አስቀርተውን ለውጥ ናፋቂዎች አድርገውናል።
ከዘር ፖለቲካ ወጥተን በፍቅር የምንሞትባት ኢትዮጵያ ናፍቃኛለች። ሰው እኮ በፍቅር ይሞታል..ሰው እኮ ሌላውን በማፍቀር፣ ለሌላው በመኖር ይሞታል። ነፍስ እኮ ስለሌሎች ስቃይ ታልፋለች። በኢትዮጵያ ምድር የናፈቀኝ ይሄ ነው..በፍቅር መሞት። እስኪ በጥላቻ መሞት ቀርቶብን በፍቅር እንሙት። እስኪ በመዋደድ እንሙት፣ እስኪ በሌሎች መከራ፣ በሌሎች ስቃይ፣ በሌሎች ጉስቁልና እንሙት።
በጥላቻ መሞት ስንችል በፍቅር መሞት እንዴት አቃተን? እስካሁን ገለን የምንሞት ነን፣ ጠልተን የምንሞት ነን። የሚበጀን በፍቅር መሞት ነው። ከጥላቻ ወጥተን በፍቅር እንሙት። ህዝብ ለአገር ሲሞት አገር ለህዝብ ትሞታለች። አንዱ ለአንዱ ሲታመም ሰውነት ያኔ ዋጋ ያወጣል። ያኔ ነው አገርና ህዝብ፣ ትውልድና ታሪክ እርባና የሚኖራቸው።
ያኔ ነው እንደ አገር ወደ ፊት ለመሄድ ብርታት የምናገኘው። በፍቅር እንሙት..በሌሎች ስቃይ እንሰቃይ። የሌሎች ህመም ይመመን። የወገን ጉስቁልና ይሰማን..የፍቅር ሞት ይሄ ነው። እኔ በእናንተ ስታመም፣ እናንተ በእኔ ስትታመሙ ያኔ አገርና ህዝብ ትርጉም ያገኛል። የፍቅር ሞት ይሄንን ነው። በአንዱ ውስጥ የአንዱ መብቀል።
የፍቅር ሞት ህመም የለውም። የአንድነት ሞት ሞቶቻችንን ሁሉ የምንገልበት ጥበብ ነው። አሁን ላይ እየሞትን ያለነው በጥላቻ ሞት ነው። የጥላቻ ሞት ደግሞ ሌላ ሞት ይፈጥራል እንጂ ህይወት አይሰጥም። ሞቶቻችን የጥላቻዎቻችን ጽንሶች ናቸው። የጥላቻ ሞት ትንሳኤ የለውም። የጥላቻ ሞት ዳግም ህይወትን አይሰጥም። በፈጣሪ ፊት በክብር አያስቆምም።
ከፍቅር ርቀን ጠልተን ስንሞት በዚህኛውም አለም ሆነ በዚያኛውም አለም ትንሳኤ የለንም። ትንሳኤ ያላቸው ነፍሶች በፍቅር ኖረው በፍቅር ያለፉ ናቸው። ስለሌላው በመኖር፣ ስለሌላው በማሰብ፣ ስለሌላው በመጨነቅ በፍቅር እንሙት። ያኔ ሌላ እንሆናለን..አሁን ከሆንው ሌላ።
አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ጥበቦች መገኛ አገር ናት። ሌላው አገር ሰላም ሲያጣ፣ አንድነት ሲርቀው ወደ ኢትዮጵያ ነበር የሚመለከተው። ኢትዮጵያን የሰላም ቀንዲል፣ የአንድነት ዋርካ አድርገው ሀርና ህዝብ የመሰረቱ በርካቶች ናቸው። አገራችንን ተስፋ አድርገው፣ ህዝባችንን ተማምነው አገር የሆኑ እልፍ ናቸው። ዛሬ ይቺ ብዙዎችን ያስጠለለች ዋርካ አገራችን ዛፍ መሆን ባልቻሉ አገራትና ግለሰቦች ሰላሟን ስታጣ ማየት ጥያቄን ይፈጥራል።
ለሌሎች ተርፎና ተትረፍርፎ ለራስ መላ ማጣት ህመሙ በምን ቃል ይገለጻል። ሌሎችን አገርና መንግስት ያደረገች ቀዳማይት ምድር ዛሬ ዘመን ባለፈባቸው ነውረኛ ድርጊቶች ስትናጥ ማየት ከማስገረም ባለፈ ምን ሊባል ይችላል? አፍሪካን አንድ ያደረገች አገር ዛሬ ላይ በወንድማማቾች ደም ስትታጠብ ማየት ከማስቆጨትም በላይ ያማል።
አገሩን የሚወድ ሁሉ በእርቅ ደም ያድርቅ። በፍቅር ጥላቻን ይግደል። በዚች አገር ብዙ የተማጽኖ አደራዎች ተሰምተዋል። ብዙ የይቅር፣ ብዙ የእርቅ ድምጾች አስተጋብተዋል። አባቶች ተናግረዋል፣ የኃይማኖት መሪዎች አደራ ብለዋል ግን ካልገቡን ይልቅ የገቡን ልቀው ጆሮ ዳባ ብለን በራሳችን ላይ መከራ ፈጥረናል።
ካልተረዳናቸው መንፈሶች ይልቅ የተረዳናቸው የጥፋት እውነቶች ሚዛን ደፍተው ጸዳሎቻችንን ነጥቀውናል። በእርቅ ደም እንዲደርቅ፣ በፍቅር ሞት እንዲቀር ነፍሳችንን እናነቃቃ ። የሚበጀን ይሄ ነው..በእርቅ ደም አድርቀን፣ ይቅር ለእግዜር ተባብለን ወደ ፊት እንራመድ። አገር ፈርሳ መግቢያ ያለን ይመስል፣ ወገን ከድተን መጠጊያ ያለን ይመስል የጥፋት ሩጫችን አይጠቅመንም። የጥፋት ሩጫችን የሚያተርፈን የአለም መሳቂያና መሳለቂያ መሆንን ነው፤ ይህ ደግሞ የቀደመውን የአባቶቻችንን ታሪክ የሚያጎድፍ፤ ይህንንም ትውልድ ፈጽሞ የማይመጥነን ነው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17 /2014