በሁሉም አቅጣጫ ያሉትን የኢትዮጵያ ህዝቦች እንዳይበታተኑ ያስተሳሰሩ፤ እንዳይለያዩ ያጣመሩ፣ ጠንካራ ገመዶች በአገራችን ሁሉም ጫፎች ይገኛሉ። እኛነታችን የሚገለፅባቸው የተለያዩ በዓላት ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ሕብር ተጠብቆ እንዲቀጥል ከሚያደርጉ ገመዶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በዚህ ረገድ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምስራቅ ወይም ምዕራብ ላይ ሳይወሰን፤ አንዱ የሌላውን የሚያደንቅበት፣ አንዱ በሌላው ድንቅ ባህል የሚደመምበት፣ ይበልጥም አንዱ የሌላውን የሚያከብርበት፣ አንዳንዴም የአንዱ ከሌላኛው ጋር ተዋርሶና ተስማምቶ የሚገለጽባቸው በርካታ ህዝባዊ በዓላት አሉን።
ኢትዮጵያዊያን ከሰማኒያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ብቻ ሳትሆን፤ በየቋንቋ ባህል ቀለማቸው ተዋደውና ተዋህደው የኖሩ፣ ያሉና የሚኖሩ ስለመሆናቸው በርካታ የታሪክ፣ የባህል፣ የእምነት እና የቋንቋ ማስረጃዎች ማቅረብ የሚቻልባት ምድር ናት፡፡ ምክንያቱም አብሮ በመ ኖር ሂደት ውስጥ ተዋድዶና ተዋልዶ የተሰናሰለው ህዝብ፣ በአንድም በሌላም ባህሉን ማንነቱን ሲወራረስና ሲቀባበል ከመመልከት የላቀ እውነት አይገኝም፡፡ ከዚህም በላይ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት አገራት ጋር ጭምር የሚወራረሷቸውና የሚጋሯቸው ባህል፣ ቋንቋና ሌሎች ማህበራዊ እሴቶች አሏቸው፡፡
ሰሞኑን ከሚከበር አገራዊ በዓል ጋር አያይዤ አንድ ማሳያ ላንሳ፡፡ ለምሳሌ፣ ሰሜን ኢትዮጵያን ብንመለከት፤ ሰሜኑን የአገራችን ክፍል ከኤርትራዊያንን ጋር በአንድ የሚያስተሳስር ቋንቋ አላቸው፤ ከዚህም ባለፈ የጋራ የሆነ የባህል እሴት አጎልብተው ኖረዋል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያን ህዝቦች ከሚያስተሳስሯቸው እሴት ባህሎች ውስጥ ደግሞ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች የሚኖሩ የትግራይ፣ የአማራ፣ የአገው፣ የኩናማ እና የኢሮብ ህዝቦች መመሳሰልና መተሳሳርን የሚያሳየው የአሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል በዓላት ለዚህ ትስስር መገለጫ ብቻ ሳይሆኑ፤ የእውነት የተስፋ ማብሰሪያ በውብ ህብረ ቀለም የተቃኙ ናቸው፡፡
የዚህን በዓል አከባበር የተመለከተ የሩቅ አገር ሰው ሰሜኑ በሙሉ በአንድ ቋንቋ የሚናገር በአንድ አፍ የሚዘምር ነው የሚመስለው፡፡ በዚህም ከትግራይ አንስቶ እሰከ ሰቆጣ የልጃገረዶች ውበትና ድምቀት ጎልቶ የሚታየው ዜማቸው ድምፅ ከዚህኛው ተራራ እስከ ወዲያኛው ያስተጋባል።
በሰሜኑ ያሉት የኢትዮጵያ ልጆች ልክ እንደ ደቡቦቹ፤ ብሎም እንደ ምስራቅ፣ ምዕራቦቹ ልጆች ከሚያለያዩዋቸው ይልቅ አንድ የሚያደረጓቸው ጉዳዮች እንደሚበዙ ከአሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ እና ሶለል የላቀ ምስክር ከወዴት ይገኛል?።
በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል ያለው ይህ ውብ ባህል የፈጠረው የትስስር እሴት ከውስጣችን ሳይበተን ከዘለቅን ኤርትራ ያደርሰናል፡፡ እናም ባህል ከአገር አገር የሚናኝ እንጂ ይህ የኔ ነው ይህ የኔ ብቻ እንደማይባል ሙሉ የሰሜን ልጃገረዶች የነፃነት በዓል የላቀ ምን ሊኖር?። ሴት ልጅ የማጀት ብቻ በምትባልበት በዛ ዘመን እንኳን አደባባይ መወጣት ነውር ከማይሆንበት ወቅቶች አንዱ የአሸንዳ/ሻደይ የበዓል ወቅት ነው።
የጭፈራውን የበዓሉን አከባበር ለተመለከተ እውነት እነዚህ ልጃገረዶች ከተለያየ ብሄረሰብ የወጡ ናቸው? ለማለት አያስደፍርም። ምናልባትም የንግግር ቋንቋቸውን ለተመለከተ የዜማቸው ምትና ቅላፄ መለያየትን ያጤነ የንግግር ቋንቋቸውና ብሔራቸው ናቸው እንዴ ሊል ካልደፈረ በፍፁም በዚህ የባህል ሰንሰለት የተሳሰሩትን የሰሜን ኢትዮጵያን ህዝቦች አንድ ከማለት በቀር በሁለት እንዳይጠራ የማድረግ ኃይል ያለው ነው፡፡
የማህበረሰቡ ትስስር፣ በማንም ጫና ወይም አስገዳጅነት ሳይሆን ከሰው የጋራ ማንነትና የጋራ ታሪክ የሚነሳ የትላንት ታሪካቸውም ሆነ የዛሬ እውነታቸው ነው፡፡ ማንም ቀመር(ፎርሙላ) ሳያዘጋጅለት ይህ በዚህ ያ በዛ ያልተባለለት በራሱ መስመር የሚፈስ ንፁህ ኩልል ያለ ውሃ ሰሜን ሙሉ የሚዞር የሚያስተሳስር እውነት፤ የፍቅርና ሰላም አውድ ነው፡፡
የሰሜኑን የአገራችንን ህዝቦች ታሪከ ስንመረምር የአሸንዳ/ሻደይ በዓላት ከላይ እስከታች እንደየአመቱ ሁኔታ፤ እንደ ምርቱ መጠን ደመቅ ፈዘዝ ይበል እንጂ፣ ለዘመናት ሥርዓቱን እንደጠበቀ ተከብሯል። አሸንዳን የመሳሰሉት የጋራ እሴቶቻችን ከቀደምት አባቶቻችን ጋር በመንፈስ የሚያስተሳስሩን ፣ ወደፊትም አብረን እንድንጓዝ የሚያደረጉን መንገድ፤ ከመንገድም አልፎ አካሄጆቻችን ጭምር ናቸው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች የሚጾሙትን የጾመ ፍልሰታ ለማርያምን መፈታት ተከትሎ ከነሐሴ አስራ ስድስት ጀምሮ ባሉ ቀናት በተለያየ እድሜ ደረጃ ያሉ ሴቶች በዋናነት ግን በወጣቶችና ልጃገረዶች የሚከበረው የአሽንዳ/ሻደይ በዓል የተስፋ ማብሰሪያ የአዲስ ዓመት መቀበያ መልካም ምኞት ማስተላለፊያ ነው።
ይህ በዓል የሴት ልጆች በተለይም ወጣት ሴቶች አንገታቸውን አቀርቅረው በሚሄዱበትና በአደባባይ ወጥተው ፍላጎታቸውን በማይገልጹበት ወቅት ሁሉ፤ በሙሉ ነጻነት ይልቁንም በጋራና በአደባባይ የወደዱትን የሚያሞጉሱበት፣ የጠሉትን ሃሳብና ተግባር በነጻነት የሚያወግዙበት ድንቅ በዓል ነው። ይህ በዓል ጦር ከማመዘዝ ይልቅ በሀሳብ ልዕልና ማመንን የሚያስተምር ነው፡፡ የአሸንዳ/የሻደይ በዓል ልክ አንገታቸውን የደፉት ልጃገረዶች ቀና እንዳሉበት ሁሉ፤ የአገራችን ህዝቦች በሀዘን ካቀረቀሩበት ቀና እንዲሉ የሚሆንበት፤ ጥልና ክርክር ቀርቶ ከሰሜን እስከ ደቡብ በፍቅር ገመድ የሚተሳሰርበት የሰው ሁሉ እንባ ታብሶ ደስታ ብቻ የሚነገስበት ዘመን ይሆንልን ዘንድ ምኞቴ ነው።
አንድ አገር ህዝቦችን ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት ጋር የሚያቆራኘውን፣ ከአገራችን ኢትዮጵያ አልፎ ደቡባዊት ኤርትራ ውስጥ ጭምር የሚከበረው ይህ የአሸንዳ/ሻደይ በዓል ውበትና ልምላሜ የሚታይበት የአሸንዳ/ሻደይን በዓል እንደ በጎ ተምሳሌት ወስደን የኛ ልብ ውስጥ በጥላቻ የደረቀውን ተክል የምንነቅልበት፣ የፍቅር ልምላሜን የምናነግስበት ጊዜን ወደ ሕይወታችን እንድንጠራ ይሁን። ፈጣሪ ለእገሌና ለእገሌ ዝናብ፤ ለአገሌ ደሞ ድርቅ ሳይል በሙሉ እጁ ዘግኖ የሰጠንን የክረምትን በረከት እኛም የመከፋፈል የመለያየት መንፈሱን ከውስጣችን አውጥተን በፍቅር የምንለምልምበት ይሁን።
ያለምንም የሂሳብ ስሌት በመኖር ሂደት ውስጥ በባህል አንድ ሆኖ ከተሰፋው የአብሮነት ሙዳይ ውስጥ አንዲቷን የአሸንዳ/ሻደይ ሰበዝ እንምዘዝ እንጂ፤ እንመልከተው በደንብ እናስተውል ካልን ከሚያጣላን ነገር ይልቅ የሚያፋቅረን፣ ከምንናደድበት ይልቅ የሚያስደስተን ይበዛልና ቂም የጋረደውን አይናችንን በክረምት በሞሉት ወንዞቻችን ታጥበን በንፁህ መንፈስ ለእርቅ እንድንተጋ ይሁን።
እንደ አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል ውብ የባህል ህብር አገራችንም በአንድ እንድትደመር ይሁን። ተፈጥሮ አንድ ያደረገንን ፈጣሪ በአንድ ያዋደደንን ተመልክተን፣ ከእኔነት ወጥቶ እኛነት የሚለው ሀሳብ ውስጥ መግባት ተገቢ ነው። እናም ውዶቹ የአገሬ ልጆች እንደ ባህሎቻችን ሁሉ ፍቅራችን ወሰን አይኑረው፤ ድንበር አይበጅለት፤ ያለገደብ እንቀባበለው እንጂ አንግፋው፡፡ ለዛሬው አበቃሁ፤ ሰላም! ቸር ይግጠመን፤ ቸሩንም ያሰማን!
ብስለት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17 /2014