በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ከተሰጣቸው ጥቂት የጎዳና ላይ ሩጫዎች መካከል አንዱ የሆነው የቺካጎ ማራቶን በመጪው ወር መጀመሪያ ይካሄዳል:: ታሪካዊ በሆነው በዚህ ውድድር ላይም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በርካታ ዝነኛ አትሌቶች እንዲሁም የውድድሩ የአምና አሸናፊዎችም ተሳታፊ እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል:: ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያዊያን የረጅም ርቀት አትሌቶችም በዚህ ውድድር እንደተለመደው አሸናፊ ይሆናሉ በሚል ቅድመ ግምት አግኝተዋል::
በወንዶች በኩል ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከጥቂት ተፎካካሪዎቻቸው ባለፈ እርስ በእርሳቸው ለአሸናፊነት የሚያደርጉት ፍልሚያም ተጠባቂ ሆኗል:: ይህም የሆነበት ምክንያት ተሳትፏቸውን ካረጋገጡት እውቅ አትሌቶች መካከል ባላቸው ፈጣን ሰዓት በቀዳሚነት የተቀመጡት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በመሆናቸው ነው:: በግል ፈጣን ሰዓቱ ከአትሌቶች ዝርዝር ሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አትሌት ሰይፉ ቱራ ደግሞ አሸናፊ ይሆናል በሚል በተለይ ግምት ያገኘ አትሌት ነው:: ይኸውም አትሌቱ ያለፈው ዓመት የቺካጎ ማራቶን አሸናፊ በመሆኑ ነው::
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጆች የጤና ስጋት በሆነው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ከሁለት ዓመታት መቋረጥ በኋላ በተካሄደው 43ኛው የቺካጎ ማራቶን፤ የወንዶች ውድድር የተጠናቀቀው በኢትዮጵያዊው አትሌት አሸናፊነት ነበር:: በዚህ ውድድር 2:06:12 በሆነ ሰዓት ርቀቱን በማጠናቀቅ ቀዳሚ የሆነው አትሌት ደግሞ ሰይፉ ቱራ ነው::
ይህ የአትሌቱ በውድድሩ ላይ ድጋሚ መሳተፍም ለሁለተኛ ጊዜ አሸናፊ የውድድር ዓመት በተካፈለበት የሚላኖ ማራቶን አራተኛ ደረጃን የያዘ ቢሆንም፤ በወቅቱ ያስመዘገበው 2:04:29 የሆነ ሰዓት ግን አትሌቱ ማራቶንን መሮጥ ከጀመረበት እአአ ከ2017 ጀምሮ ፈጣን በሚል ተመዝግቦለታል:: በመሆኑም አትሌቱ ያለውን የርቀቱን እንዲሁም የቦታውን ልምድ ተጠቅሞ አሸናፊ የመሆን እድሉ የሰፋ እንደሚሆንም በስፖርት ቤተሰቡ እምነት አግኝቷል::
በውድድሩ ከሚካፈሉት መካከል 2:03:40 የሆነ ሰዓት ያለው አትሌት ሂርጳሳ ነጋሳ ፈጣኑ ሲሆን፤ ይህንንም ሰዓት እአአ በ2019 የዱባይ ማራቶን ያስመዘገበው ነው:: ሌላኛው የውድድሩ አሸናፊ እና ጠንካራ ተፎካሪ እንደሚሆን የተገመተው አትሌት ደግሞ ዳዊት ወልዴ ነው:: አትሌቱ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የሮተርዳም ማራቶን 2:04:27 የሆነ ሰዓት ሲኖረው፤ ይኸውም የርቀቱ ምርጥ በሚል ተይዞለታል:: 2:04:43 የሆነ ሰዓት ያለው አስራር አብድራህማንም ለአሸናፊነት ከሚፎካከሩት መካከል ይገኝበታል::
የኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ተፎካካሪና ፈተና እንደሚሆኑ ከሚጠበቁት መካከል አንዱ ዩጋንዳዊው አትሌት ስቴፈን ኪሳ ነው:: በቶኪዮ ኦሊምፒክ 10ሺ ሜትር ሃገሩን የወከለው አትሌቱ በማራቶንም ተሳታፊ ሲሆን፤ የግሉ ፈጣን ሰዓት ደግሞ 2:04:48 ነው:: አትሌቱ በሃምቡርግ፣ ለንደን እና ቶሮንቶ ማራቶኖች ልምድ ያለው ሲሆን፤ ለአሸናፊነት በሚደረገው ፉክር የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ዋነኛ ፈተና እንደሚሆንም ነው የሚጠበቀው::
በሴቶች በኩል በሚካሄደው ውድድርም በተመሳሳይ የአምናው የውድድሩ አሸናፊ የሆነችው ኬንዊቷ አትሌት ሩት ቼፕንጌቲች በድጋሚ ተካፋይ እንደምትሆን አወዳዳሪዎቹ አሳውቀዋል:: የርቀቱ የ2019 የዓለም ቻምፒዮናዋ አትሌት በዚያው ዓመት በተካፈለችበት የዱባይ ማራቶን አሸናፊ የሆነችበት 2:17:08 የሆነ ሰዓት የግሏ ፈጣን በሚል ተይዞላታል:: ባለፈው ዓመት በተካሄደው የቺካጎ ማራቶን ቀዳሚ ሆና የገባችበት ሰዓት 2:22:31 ነው::
ይሁንና አትሌቷ ኢትዮጵያ ቻምፒዮን በሆነችበትና ያለፈው ወር በተካሄደው የኦሪጎን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ውድድሩን ለማቋረጥ ተገዳ ነበር:: ይኸውም አትሌቷ በድጋሚ የውድድሩ አሸናፊ ትሆናለች በሚል የተሰጣትን ግምት አጠራጣሪ አድርጎታል:: በኬንያ በኩል ሴልስቲን ቼፕቺርቺር እንዲሁም ቪቪያን ኪፕላጋት የውድድሩ ተካፋዮች እና የሃገራቸው ልጅ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ነው የሚጠበቀው::
በኢትዮጵያ በኩል በብቸኝነት ተካፋይ እንደምትሆን የታወቀችው አትሌት ሄቨን ሃይሉ ናት:: ወጣቷ አትሌት እአአ በ2012 የአምስተርዳም ማራቶን ሶስተኛ ሆና የገባችበት 2:20:19 የሆነ ሰዓት የግሏ ፈጣን ነው:: የዚህ ዓመት የሮተርዳም ማራቶን አሸናፊ የሆነችው አትሌት ሄቨን ከኬንያዊያኑ አትሌቶች ጋር ያላት ተቀራራቢ ሰዓት ሲሆን፤ በዓመቱ ካለችበት መልካም አቋም አንጻር የውድድሩ አሸናፊ ልትሆን እንደምትችል ትጠበቃለች::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 16/2014