ትምህርት የሰው ልጅን ወደተሻለ ልዕቀትና ልዕልን የሚያሻግር መሣሪያ ነው። ሁሉም ሀገር ያደገውና የበለጸገው በትምህርት ነው። የትምህርት ባሕል/መሠረት የላቸውም የሚባሉ ሀገራት ቢያድጉ እንኳን ከተፈጥሮ ሀብታቸው ጋር ከሌላው ማኅበረሰብ የተማረውን ኃይል ይዘው ነው። በአንድ ሀገር የተሳካ ትምህርት ከሌለ ጥሩ ዜጋ ማፍራት፣ የሰለጠነ ሀገር መገንባትና የሀገርን የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም አይቻልም። የአንድ ሀገር የድኅነት መገለጫውም የትምህርት ውድቀት ነው። የተሳካ ትምህርት ባለበት ሀገር ዕድገትና ብልጽግና፣ ሥልጣኔና መራቀቅ፣ ሀብትና ባለጠግነት በሀገሩ ይኖራል።
የአስኳላው ትምህርት በኢትዮጵያ የተጀመረው በዳግማዊ አጼ ምንልክ ነው። ንጉሡ በጊዜው ሃይማኖታዊና ሀገር በቀል ትምህርት በሀገሩ ቢኖርም ለአውሮፓው ትምህርትም ልዩ ትኩረት ነበራቸው። ለዚህም እንዲህ ብለው ነበር ‹‹በጣም ወደኋላ የቀረን ሕዝቦች ነን፤ ገና ብዙ ስራ ስላለብን ወጣቶች መማር አለባቸው ›› በዚህ ብቻ አላበቁም ተተኪው ትውልድ ዘምኖ ለመኖር፣ በልቶ ለማደር፣ ሀገር ለማቅናት የሚችለው ሲማር ብቻ ስለሆነ እንዲህም ይመክሩ ነበር ‹‹እኔ ቤት እንጀራ የለም፤ እንጀራ ያለው ትምህርት ቤት ነው፤ ስለሆነም እሰራሁት ትምህርት ቤት ልጆቻችሁን እያስገባችሁ አስተምሩ ››
በዚህ አጭር የዘመናዊ ያልነው የትምህርት ታሪካችን ውስጥ በቅጡ የትምህርት ብርሃን በሀገሩ ሳይወጣ የትምህርት ፍቅርና ዓላማ እያደር አሽቆልቁሏል። የዛሬው አብዛኛው ተማሪ በኮሌጆችና በዩኒቨርሲቲዎች የምረቃ ከንፈር ላይ ሆኖ እንኳ በሙያው ከመስራት ይልቅ ‹ምን ሰርቼ፣ እንዴት ብዬ ገንዘብ ማግኘት እችላለሁ› የሚለውን ሐሳብ ከተገቢ የሙያዊ ክፍያ ጋር ያለውን ሁኔታ የሚመለከተው አካል ቆም ብሎ ማሰብ አለበት። አደጉ ያልናቸው ሀገራት ያደጉት በትምህርት ስለሆነ በሀገር ላይ በጎ ነገር ለማየት፣ የውስጥን ጥያቄ የሚያርስ መልስ ለማግኘት፣ በትውልድም ተስፋ ለማድረግ፣ ለአንድነታችን መልካም ነገር ለማሰብ፣ መጪው ጊዜ ብሩሕ ይሆናል ብሎ ለመመኘት፣ ጥሩ የታሪክ ገጽታም ከፊታችን እንዲገጥመን፣ ሕዝብ በፍቅርና በሐሴት ተሞልቶ እንዲኖር ትምህርት ቁልፍ መሣሪያ ነው። ለዚህም የትምህርት አመራሮች ድርሻችሁ ሰፊ ነው።
ትምህርት በአንድ ሀገር ላይ የሰለጠነ የሰው ሀብት ማፍሪያ፣ ምርታማ ስራ መከወኛ፣ በቴክኖሎጂ መበልጸጊያ፣ በክዕሎትና በዕውቀት መዳበሪያ፣ ለሚገጥሙን ሀገራዊ ተግዳሮቶች መፍትሔ አምጪና ጠቋሚ በመሆን በማኅበራዊ ኑሮና በፖለቲካው ባሕል ላይ ዓለምን የሚመጥን ሥልጡን ትውልድም ማፍሪያ ነው። ለዚህ ትሩፋት ደግሞ ትምህርቱን፣ የሙያው ባለቤት መምህሩንና መምህርነትን ማክበር ተገቢ ነው።
መምህርነት ሙያ ነው። ለዛውም ኅሩይና የተከበረ ሙያ። የሙያዎች ሁሉ ፈጣሪና አባት። ሀገር መሪው ሳይንቲስቱ፣ ፖለቲከኛው የኪነጥበብ ባለሙያው፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሊቁ፣ እንዲሁም የተለያዩ የክህሎትና የዕውቀት ባለቤቶች …ሁሉም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የመምህራን አሻራ ያረፈባቸው ናቸው።
ማንኛውም ሙያ ባለቤት አለው። አንድን ሙያ ደግሞ የምናከብረውን ያህል የሙያውን ባለቤት ልናከብረው ይገባል፤ ስናከብርውም ዕውቀቱን፣ ክዕሎቱን፣ አመለካከቱን፣ ልምዱንና የሙያውን ፍቅር ጭምር ልናከብረው ይገባል። በዋናነት የትምህርት ባለሙያዎችና ባለቤቶች ደግሞ መምህራን ናቸው። መምህራን እንደማንኛውም የተከበሩ ባለሙያዎች ሊታዩ ይገባል። ምክንያቱም የማስተማር ዓላማ የሰው ልጅ ሕይወቱና ስራው እንዲሻሻል፤ በሀገር ላይ ዕድገትና ሥልጣኔ እንዲመጣ፤ ዓለም እንዲቀና፤ የሰውልጅ የመልካም አመለካከት ባለቤት እንዲሆንና በጥበብ እንዲያብብ የሚያግዝ ነው።
በሌላው ሀገር ብዙኀኑ መምህራን የተስተካከለ ገቢ የሚያገኙ፣ መንግስትና ሕዝብ የሚንከባከባቸው፣ ከመሠረታዊ ፍላጎታቸው በላይ የሆኑ፣ ማኅበራዊ ከፍታና ከበሬታ ያላቸው፣ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነታቸው የማይነጥፍባቸው ናቸው። ለዚህም ሙያቸውን ወደውና አክብረው ይሰራሉ። እንደኛ ሀገር መምህራን በብዙ ዘመናት በተስፋ እየተሞሉ ጥቂት ተለግሷቸው በብዙ እየጎደላቸው ትኩረትና ክብር የተነፈጋቸው ይመስላሉ። በዚህ ሁሉ ከባድ ተግዳሮት እንኳን ለሙያው ትኩረት የሰጡና ራሳቸውን መስዋዕት ያደረጉት ለሙያው ካላቸው ፍቅር የተነሳ ነው።
አንድ ክፍለ ዘመን ያለፈው ይህ ግዙፍ ተቋም ሙያውን ሀ ብሎ ከጀመረበት እስከ ዛሬ እያደር በየመንግስታቱ ዘመናት የመምህራን ኑሮ፣ ክብር፣ ሞራል፣ ማኅበራዊ ተቀባይነትና የትምህርት ፍቅር እየወረደ ቢመጣም እንደዛሬ ዘመን የባሰበት ጊዜ ግን የለም ማለት ይቻላል። የዚህ ሁሉ ምክንያት ደግሞ እያደር ሙያውና ሙያተኛው ተገቢውን ክብር ስላላገኙ ነው። መምህርነት እንደሻማ ለሌላው እያበሩ ተቃጥሎ መሞት ሳይሆን፤ እንደ ፀሐይ ሰርክ አዲስ ብርሃን በመሆን የማይነጥቡበት ሕይወት ነው መሆን ያለበት።
ሁሉም ሙያ የራሱ ክብርና ልክ አለው
ሁሉም ሙያ በራሱ ልክ ተከባሪነት፣ ተደማጭነትና ታማኝነት አለው። ይብዛም ይነስም አንድ መሐንዲስ የሚገነባው ቤት ለዚህ ያህል ዓመት በምቾትና በጥራት ይቆያል ቢል ይታመናል። አንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሀገሪቷን የምጣኔ ዕድገት መንገድ ቢያመላክት ቅቡልነትን ያገኛል። አንድ የግብርና ባለሙያ የምርት ውጤት የሚለካው በዚህ መንገድ ነው ቢል ታምኖ ስራ ላይ ይውልለታል። አንድ የቤተ ሙከራ ባለሙያ የሰጠንን ውጤት እናምነውና እንጠቀምበታለን።
አንድ ሐኪም መርምሮ የነገረንን እንቀበላለን። የሰጠንን መድኀኒት አምነን እንወስዳለን። መምህራን ግን ለሥርዓተ ትምህርቱ፣ ለትምህርት ጥራት፣ ለተማሪው ለውጥ፣ ለትምህርት ውጤትና ለመማር ማስተማር ሂደት ሁሉ የሙያው ሐኪሞች ሆነው ሳለ ግን እንደሌሎቹ ባለሙያዎች አይታዩም። አንድ ታማሚ በሥነ-ባሕራዊም ሆነ በሳይንሳዊ መንገድ ፈውስ የሚያገኘው ሐኪሙ ላይ እምነት ሲጥል ብቻ ነው። እንዲሁም መምህራንም ለተማሪዎች የዕውቀት፣ የክዕሎት፣ የአመለካከት፣ የዕድገትና የልዕልና ሐኪሞች ናቸው።
በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ከታች ጀምሮ ያሉ መምህራን ሊደመጡ ይገባል ። ይህን ያህል የትምህርት ጊዜ፣ ይህ የትምህርት ይዘት፣ ይህ ትምህርት ሥርዓት፣ ይህ አይነት የማስተማሪያ መንገድ ይሻላል የሚሉት ነገር ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባዋ ልክ እንደ ሐኪሙ። ሐኪሙ ከታመነ ሐኪሙን የፈጠረው መምህርም ሊታመን ይገባዋል።
በተለይ ከቅድመ መደበኛ እስከ መሰናዶ ድረስ ያሉ እንደ ሙያው ልክ በክብር ሊያዙና ሊከበሩ ይገባል። ትንሽ የተሻለ የሆነው በኮሌጆችና በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ላሉት ነው። እሱም ቢሆን የአካዳሚው ነጻነት የሚያጠያቅ ይመስላል።
የመምህራን ልዩነት የሚመስል ከየት መጣ?
ዛሬ ብዙኀኑ የትምህርት ጥራት መውረድ መምህሩን ተጠያቂ የሚያደርጉ እንደሚበዙ ይታወቃል። በዚህ የሙያ መስክ ውስጥ ግን ለሙያው በቁ የሆኑ ባለሙያዎች ሞልተዋል። በመንግስትም ሆነ በግል የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ መምህራን በመንግስት ወይም በግል ኮሌጆች ውስጥ የተማሩ ናቸው። የትምህርት ጥራት በመንግስት ትምህርት ቤት ውስጥ ብዙኀኑ ተጠያቂ መምህራንን ሲደርጉ ይደመጣል። ግን የምንግሥት ትምህርት ቤት በሀገሪቱ ያበረከተው አስተዋጽኦ ቀለላል አይደለም።
ለምሳሌ ያህል በመንግስትና በግል የትምህርት ተቋማት ውስጥ የትምህርት ውጤት ልዩነት የመጣው በትምህርት አሰጣጥ ነጻነት፣ መምህሩ በሚኖረው ጥቅማጥቅምና የተማሪዎች የኑሮ ዘይቤ ምክንያት እንጂ በሌላ አይደለም። ለአብነት ያህል የሀገራችን መሪዎችና ባለስልጣናት ከመንግስት ትምህርት ቤት ተምረው የወጡ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በከፈቱት ትምህርት ቤት ውስጥ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ተምረዋል። /ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ቋንቋ እንደተማሩ መስማቴ እንደመረጃ ወስጄዋለሁ/ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በከፈቱት ትምህርት ቤት ውስጥ ኮኔሬል መንግስቱ ኃይለማርያም፣ የቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስተሮች አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃለማርም ደሳለኝ ተምረዋል።
ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ባስፋፉት ትምህርት ተቋም ውስጥ ጠ/ሚ ዶ.ር ዐብይ አሕመድ ተምረዋል። ሌሎችም ባለስልጣናት ከዚህ የተለየ ዕድል አላገኙም። /ተጨማሪ ውጭ ትምህርት ዕድል እንዳለ ሆኖ እሱም በለሱ ለቀናው ነው። / ታዲያ የመንግስት መምህራን ይህን ዐይነት ፍሬ ያፈሩ ከሆነ የመንግስት ትምህርት ቤትን ውጤት አልባ ማድረግ ምን ያህል ያሳምናል? በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ታሪክ ውስጥ የትኛው ዶክተርና ፕሮፌሰር፣ ተመራማሪና ሊዕቃን በጥናትና ምርምሩ ዘርፍ በሀገርና በዓለም አቀፍ የሚታወቁ ምሁራን ወይም የሀገር መሪዎች ከግል ትምህርት ቤት ወጡ? ዛሬ ያለው መሪ፣ ምሁርና ሌሎችንም ያስገኘው የመንግስትን የትምህርት ተቋምና መምህር ለምን ይወቅሳል?።
ከመንግሥት አካላት እስከ ማኅበረሰቡ ልጆቹንስ ለማስተማር ለምን አይደፍርም? ዛሬ እንደፈለጋችሁት አልሆን ካላችሁ ለምን አትለውጡትም ? ለነገሩ ማኅበረሰባችን ውድ ነገር የመውደድ አባዜ አለበት። ነገሮች በነጻና በቅናሽ ሲሆንበት አይወድም ለምሳሌ ለነርሰሪና ለዩኒቨርሲቲ ተማሪ ልጆቹ እኩል ክፍያ ከፍሎ ያስተምራል። በግል ትምህርት ቤት ለአንድ ሕጻን ምግብ፣ አልባሱና የትራንስፖርቱን ዋጋ ትተን በሺዎች ከፍለን የምናስተምረው ሕጻን አድጎ በዲግሪ ተመርቆ ስራ ሲይዝ ወርሃዊ ደመውዙ አራት ሺህ ብር አካባቢ ነው/ በመንግስት የደመወዝ እስኬል/። ሁሌ ውድ የከፈልንባቸው ነገሮች ትርፍ አይደሉም፤ ነጻና ዝቅተኛ ክፍያ ያደረግንበት ደግሞ ኪሳራ አይደለም። ብልህነት ነባራዊ ሁኔታውን ማሰብ ነው።
ዛሬ ብዙኀን የመንግስት መምህራን ለሙያው ኅሩይ ሆነው የተፈጠሩለትን ያህል በብዙ ፈታኝ ነገሮች ውስጥ ሆነው እንኳን ሀገርን እያገለገሉ ይገኛሉ። ለሀገር፣ ለትውልድ፣ ለሙያው ሟች ሆነው ሁሌም አሸናፊና የሙሉዕነት፣ የመሪነት፣ የተመራማሪነት ስሜት ተሰምቷቸው የሚታገሉ ባለሙያዎች አሉበት። በሚገጥማቸው ተግዳሮት እየተፋለሙ ለሙያው ሲሉ በነፍሳቸው ሰይፍ እንደሚልፍ እያወቁ እንኳን ለመከራዎቹ እጅ አልሰጡም። ዓላማቸውም ልክ ታላቁ ደራሲ ጋሽ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር እንዳለው ነው።
“የመምህርነትን ሙያ አቤት ስወደው ለምን መሰለህ ሽኩቻህና ፍልሚያህ ከማወቅና ካለማወቅ ጋር ነው። እምትመቀኘው ሌላውን ሳይሆን ድንቁርናን ነው። የሚያስደስተውም ደግሞ የዘራኸው አድጎ ሲያፈራ በማየት ነው። ስለዚህ በጣም እወደዋለው”
የሙያ ባለቤቶች ይህ ነው የሚባል ሀብትና ንብረት ሳይኖራቸው ንጹህ እረኛ ሆነው በጎችን በድንቁርና ተኩላ እንዳይነጠቁ የሚታደጉ ናቸው። ታዲያ በዚህ መስክ ውስጥ ይህንን ሙያተኛ ሐሳቡን መስማት፣ ተገቢ ክፍያና ጥቅማ ጥቅም መስጠት፣ ማኅበራዊ ከፍታ እንዲገኝ ማድረግ ካልተቻለ በትምህርት የታለመለት ግብ ላይ እንዴት መድረስ ይቻላል? ዓለም የተለወጠው በትምህርትና በትምህርት ብቻ ነው።
ትምህርት ያለወጠው ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ሀገርና ዓለም የለም። በተለይ ዛሬ ዓለም ራሷን ለውድድር ያዘጋጀችው በትምህርት ነው። ትምህርት ለዕድገት፣ለብልጽግና ለሥልጣኔ መሠረት መሆኑ ከታመነ ሊታሰብበት ይገባል። ለዚህም ከዛሬ በላቀ ብቁ መምህራን፣ ጥሩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች፣ መሰናዶዎችና ሃይስኩሎች እንዲሁም አንደኛ ደረጃና ደረጃቸውን የጠበቁ የመንግስት መዋዕለ ሕጻናት ሊፈጠሩ ይገባል /በዚህም ማኅበረሰቡ ያላግባብ ከመበዝበዝ ይድናል/።
በአጠቃላይ የድህነት፣ የኋላ ቀርነት፣ የበታችነት ታሪክ የሚታደሰውና ዕድገትና ሥልጣኔ የሚመጣው በትምህርት ነው። ለትምህርት ዕድገት ደግሞ ባለሙያውን መምህሩን ልናከብረው ይገባል።
መኩሪያ አለማየሁ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 16/2014