ሰው የዕለት ጉርሱን አግኝቶ ለመኖር የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል። ከዕለት ጉርሱ አልፎ የነገ ኑሮውን ለማቃናት ደፋ ቀና የሚለውም በርካታ ነው። ተሳክቶለት የሥራ መሥመሩ የተቃናለት ያገኘው ላይ ለመጨመር የሚታትረው እንዳለ ሆኖ የሰው መሥራትና ማግኘት በቅናት የሚያንገበግበውን ቤቱ ይቁጠረው። አይኑ በቅናት ደም ከመልበስም አልፎ ለመንጠቅ ለመቀማት የሚያሰላስለው ብሎም ወደ ተግባር የሚቀይረው ብዙ ነው። ከሥራ ወዳዶቹ መካከል ለህዝብ የትራንሰፖርት አገለግሎት የሚሰጡት የባጃጅ ሹፌሮችና ባለቤቶች ተጠቃሽ ናቸው።
እነዚህ ሥራ ወዳድ የባጃጅ ሹፌሮችና ባለቤቶች ማልደው ከቤት በመውጣት ለሥራቸው መቃናት ደፋ ቀና ይላሉ። ለሥራቸው መቃናት በጠዋት የሚወጡት የባጃጅ ሹፌሮችና ባለቤቶች በአከባቢው በፍጥነት ውር ውር ሲሉ ይታያሉ። የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ብሎም ጥሪት ለማፍራት የእለት ሥራቸውን በጠዋት ከሚጀምሩት የባጃጅ ሹፌሮች መካከል ወጣት ማናየ እንየው አንዱ ነው።
ታታሪው የባጃጅ ባለቤት
ወጣቱ ማናየ እንደ ልማዱ በጠዋት ተነስቶ ባለቤቱ ያዘጋጀችለትን ቁርስ ቀማምሶ ወደ ሥራው ተሰማርቷል። በጠዋት ወደ ሥራው ለመድረስ የተጣደፈውን ተሳፋሪ ሲያመላልስ ውሎ ረፈድፈድ ሲል ሥራውም ጋብ አለለትና አረፍ ብሎ ከጓደኞቹ ጋር ሲጨዋወት ቆየ ። የሥራ መውጫ ሰዓት ሲደርስም ጠዋት የሸኘውን ሰው ወደየቤቱ ሲመልስ አመሸ።
የዕለቱን ሥራ አብቅቶ ወደ ቤቱ ለመግባት በሚዘጋጅበት ወቅት ተገልጋዮችን አገኘ።ከእነዚህ ተሳፋሪዎች ጋር በሰላሳ ብር ኮንትራት ይዘው ለመሄድ ይስማማሉ። ተሳፋሪዎቹ ወደ ማናየ ቤት አቅራቢያ ይሄዱ ስለነበር ሳያቅማማ የባጃጁን በር ከፍቶ አስገባቸው። ሀገር ሰላም ብሎ ሲሠራ የዋለው የባጃጅ ሹፌር ቀኑን ሙሉ ያጠራቀማትን ይዞ ወደ ቤቱ ሊገባ እግረ መንገዱን የያዛቸውን ተሳፋሪዎች ይዞ ተጓዘ።
ያልታሰበ ዱብዳ
ጥር ሀያ ሰባት ቀን ሁለት ሺ አስራ ሶስት አመተ ምህረት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ከሰላሳ አከባቢ ነበር። ሁሉም ሰው ቤቱ ተከቷል፤ የተወሰኑ ባጃጆች በአካባቢው ከመታየታቸው በቀር ዝር የሚል አንድም ፍጥረት አልነበረም። በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስራ ሁለት ክልል ልዩ ቦታው ቦሌ ቡልቡላ ሙሉ ወንጌል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ነው። የባጃጅ ባለቤት የሆነው ማናየ እንየውን በሰለሳ ብር ኮንትራት በማናገር ወደ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን እንዲወስዳቸው በመስማማት ወደ ባጃጁ ገቡ። ተሳፋሪዎች በፀጥታ ተጓዙ፤ አሳቻ ሥፍራ ከደረሱ በኋላ ቀድመው ያቀዱትን ተግባር መፈፀጸም ጀመሩ።
ወደ መንገድ ዳር ጠጋ ብሎ ከባጃጁ ሊያወርዳቸው ሲቆም አንደኛው ተሳፋሪ አስራት አበበ የባጃጁን ሹፌር ማናየ እንየውን በክርኑ አንቆ በመያዝ ትንፋሹን አሳጥሮ ህይወቱ እንዲያልፍ አደረገ። ዮሃንስ ማጠሉ እና አስራት አበበ የማናየን እግር በጋራ ይዘው በማውረድ መሞቱን ሲያረጋግጡ ከቤተ ክርስቲያኑ ፊት ለፊት ካለ የመንገድ ቱቦ (የውሃ መውረጃ) በመክተት መዝረፍ ይጀምራሉ። ማናየ ማለዳ ወጥቶ ላቡን አፍስሶ ያገኘውን አምሰት ሺ ብር የሚገመት ስልክ እና አንድ መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ብር የሚገመት ባጃጅና ገንዘብ ወሰዱ፡፡
እንደገና ጥፋት
በተመሳሳይ ምትኩ መለሰ የተባለ ሌላ የባጃጅ ሹፌር እሱም እንደሥራ ባልደረቦቹ በጠዋት ወደ ሥራው ወጥቶ የሚለፋ ወጣት ነበር። ከጠዋት እስከ ማታ ያለ እረፍት የሚሥራው ይህ ወጣት፤ ከባጃጅ ሥራ ሊያወጣው የሚችል ጥሪት ለማጠራቀም እረፍት ብሎ ነገር አያውቅም። አንዴ በተራው ሌላ ጊዜ በኮንትራት ሥራውን ሲያጧጡፍ እንደሚውል የሚያውቁት ይናገራሉ። ልረፍ ቢል እንኳን ምግብ ለመቀማመስ ካልሆነ ሥራና ሥራ ብቻን ዓለማው አድርጎ የሚንቀሳቀስ ወጣት ነበር።
ከሥራ ቤቱ፤ ከቤቱ ወደ ሥራ ብቻ መገላጫው የሆነው ይህ ወጣት ገንዘቡን ለማጠራቀም እቁብ ገብቶ በየቀኑ ለሚጥለው እቁብ ገንዘቡ እንዲሞላለት ሲጣጣር ይውላል። ከእቁብ ተርፎም ቤተሰቡን ለማስተዳደር የሚበቃው ገንዘብ ለማግኘት አንድም ቀን ሰለቸኝ ታከተኝ ሳይል ይሠራል። እቁብ ሲደርሰው በከንቱ ከማጥፋት ይልቅ ለአለማው መሳካት በባንክ ይቆጥባል። በላብ በጥረቱ የህልሙ ቦታ ለመድረስ ሥራን አማራጭ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ወጣት ነበር።
በተቃራኒው ደግሞ በሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን በጥበቃ ሥራ የሚተዳደሩት ነገር ግን ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ብቻ የሆነባቸው የራሳቸውን ስራ ፈጥረው ታሪካቸውን ከመቀየር ይልቅ ማልደው ከቤታቸው ወጥተው ለሥራ ውር ውር የሚሉት ባጃጆች ላይ አይናቸውን የሚጥሉት ነፍሰበላዎች እንደልማዳቸው ምትኩ ላይ አይናቸውን ጥለዋል። ከላብ አዳሪዎች መካከል ምትኩን ወይም ሌላውን አንዱን ገለው ዘርፈው በወንጀል ላይ ወንጀል ለመጨመር ዝግጅት ላይ ናቸው። በተለይ ምትኩ መለሰ ላይ አይናቸውን ጥለዋል።
ቀድመው ከዘረፉት ንብረት ላይ ያየዙትን ይዘው ከአከባቢው የተሰወሩት ወንጀለኞች ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም ሆኖባቸው የመጀመሪያውን ወንጀል ከፈጸሙ ከአምስት ቀናት በኋላ፤ የካቲት ሁለት ቀን ሁለት ሺ አስራ ሶሰት አመተ ምህረት ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ከሰለሳ አከባቢ ፤ አስራት አበበ ወጣት ምትኩ መለሰን የጀኔሬተር ባትሪ ሊሸጥለት መሆኑን በመግለፅ እና በማስማማት ምትኩን ደውሎ እንዲመጣ በማድረግ አስራት እና ተባባሪው ዮሃንስ ማጠሉ በጥበቃ ሠራተኝነት ከሚሰሩበት ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ጊቢ ውስጥ እንዲገባና እንዲደበቅ አደረጉ።በኋላም ዮሃንስ ማጠሉ “ሌባ ሌባ” በማለት ምትኩን በያዘው የጥበቃ ዱላ ጭንቅላቱን ሲመታው አስራት ተከትሎ ምትኩ በወደቀበት ተባብረው በመቀጥቀጥ ህይወቱ እንዲያልፍ አደረጉ።
ይህን እኩይ ተግባር በመተባበር ከፈፀሙ በኋላ ቀደም ሲል የገደሉትን የማናየ እንየውን አስክሬን በከተቱበት ውሃ መውረጃ ቱቦ ውስጥ በድጋሚ ያጠፉትን የምትኩ መለሰን አስክሬን በመደበቅ ለሌላ ጥፋት ይዘገጃጁ ጀመር። ተከሰሾቹ ቀጥቅጦው ከገደሉት ከወጣት ምትኩ መለሰ ባጃጁን አራት ሺ አምስት መቶ ብር የሚገመት ስልክ እና ይዞት የነበረውን ሶስት ሺህ ብር በመውሰድ ከአከባቢው ይሰወራሉ።
የፖሊስ ምርመራ
ዋል አደር ሲል በጠዋት ወጥተው ወደ ቤታቸው ያልተመለሱት የባጃጅ ሹፌሮች ጉዳይ ያሳሰባቸው ቤተሰቦቻቸው ጉዳዩን ይዘው ፖሊስ ጋር ቀረቡ። ሁለቱም እጅግ ሰለማዊ ብዙውን ጊዜያቸውን በሥራ ከማሳለፍ በስተቀር ከሰው ጋር ግጭት ያልነበራቸው ሰዎች እንደነበሩ ተገለፀ። የሟቾቹ ቤተሰቦች ባጃጃቸውን ይዘው ከወጡ በኋላ ወደ ቤት ሳይመለሱ ቀናቶች ያሳለፉት ወጣቶች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ፖሊስ መፍትሄ ይስጠን ሲሉ ጥያቄ አቀረቡ።
መጣላት የማይወዱ ከሆነ ከቤታቸው በሰላም ከወጡ ምን ገጠማቸው ? ሲል ፖሊስ አሰሳውን ጀመረ። በሌላ በኩል ደግሞ የአከባቢው ጠረን መቀየር ያሳሰባቸው እነዛ የሟች አስክሬኖች የተጣሉበት የውሃ መውረጃ ቱቦ አከባቢ ነዋሪዎች ጉዳዩ ምን እንደሆነ ለማጣራት አፍንጫቸውን ተከትለው ፍለጋ ጀመሩ። ያን ጊዜ የሁሉም ሰፈርተኞች እግር አንድ ቦታ ላይ ተገናኘ። ይህ ሰፈሩን የበከለው መጥፎ ሽታ ከሚመጣበት ትቦ ስር ጎንበስ ብለው ሲመለከቱ ባልጠበቁት ሁኔታ የሁለት ሰዎችን አስክሬን አዩ።
ያኔ ለፖለስ ጥቆማ ደረሰው።ፖሊስ በአከባቢው ሲደርስ ቀድሞ በደረሰው የሰው ጠፋብን ጥቆማ መሰረት ሟቾቹ የባጃጆቹ ሹፌሮች ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ጥርጣሬ አስክሬናቸውን ወደ ፎረንሲክ ምርመራ በመላክ ሟቾቹ እነሱ መሆናቸው እንዲረጋገጥ ተደረገ።
ለሥራ የወጡት ከነባጃጃቸው ለቀናት ወደ ቤታቸው ያልተመለሱት ሹፌሮችን ማን ሊገላቸው እንደሚችል ፖሊሰ መርመራውን ይጀምራል። ከበርካታ እልህ አስጨራሽ ጥረት በኋላ አንዱ ዘራፊ ባልተለመደ ሁኔታ ገንዘብ በብዛት ሲያወጣ የተመለከቱት የአከባቢው ነዋሪዎች ለፖሊስ ጥቆማ ያደርሳሉ። ያኔ ምርመራው ተጠናክሮ ሲቀጥል አንዱ አንዱ ላይ እየጠቆመ ተጠርጣሪዎች ተይዘው ሲጣራ፤ የውንብድና ወንጀል መፈፀማቸው እና የባጃጆቹን ሹፌሮች መግደላቸው ተረጋገጠ።
ተከሳሾች በፖሊስ ክትትል እና በህብረተሰቡ ድጋፍ ተይዘው፤ ፖሊስ ያገኘውን ማስረጃ በማጠናከር ለዐቃቤ ህግ አቀረበ። በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዲሪ የወንጀል ህግ በመተላለፍ በፈጸሙት የሰው መግደል እና ከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።
ውሳኔ
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያሳየው፤ ተከሳሾቹ በተለያየ ጊዜ በመገናኘት ባጃጅ ከግለሰቦች ላይ በሀይል ለመንጠቅ ሲመካከሩ እና ሲዘጋጁ ቆይተው ድርጊቱን በመፈፀማቸው ይህ ግምት ውስጥ ገብቶ በከባድ የውንብድና ወንጀል እንዲጠየቁ ለፍርድ ቤቱ ክሱ ቀረበ።
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው መግደል ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች ድርጊቱን አልፈፀምንም በሚል የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡ በመሆኑ፤ ዐቃቤ ህግ ያሰባሰባቸውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች በማቅረብ ተከራከረ። ተከሳሾችም መከላከያ ማስረጃ በማቅረብ ያሰሙ ቢሆንም፤ በዐቃቤ ህግ የቀረበውን ሰው እና የሰነድ ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹን በተከሰሱበት አንቀፅ ሥር ጥፋተኛ ናቸው በማለት ብይን ሰጠ፡፡
በመጨረሻም ሐምሌ ሀያ አምስት ቀን ሁለት ሺ አስራ አራት አመተ ምህረት በዋለው ችሎት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የፈፀሙት ተደራራቢ ወንጀል በመሆኑ፤ በሁለቱም ክሶች አንድ የቅጣት ማክበጃ በመያዝ እያንዳንዳቸው በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 /2014