በአገራቸው ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ(ቻን) ለመሳተፍ የመቶ ሰማንያ ደቂቃ ፍልሚያ ብቻ የሚቀረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ዛሬ በወዳጅነት ጨዋታ የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድንን ይገጥማሉ። ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የሚያደርጉት ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታ የሚካሄድበት ቀን በተደጋጋሚ ሲቀያየር የቆየ ቢሆንም ዛሬና የፊታችን እሁድ እንደሚካሄድ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ሁለቱም ግጥሚያዎች አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ላይ የሚደረጉም ይሆናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ለወዳጅነት ጨዋታ በተደጋጋሚ የሚገጥሙት የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ አሁንም ከዋልያዎቹ ጋር ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። በቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን ሚቾ የሚመራው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በቻን ውድድር የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታ ከታንዛንያ አቻው ጋር ጠንካራ ፍልሚያ ይጠብቀዋል።
በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የቻን ውድድር ለማለፍ የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ከሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር ነሐሴ 20 እና ነሐሴ 29 የሚያከናውኑት ዋልያዎቹ ዝግጅታቸውን ከቀናት በፊት በአዳማ ማድረግ እንደጀመሩ ይታወቃል።
ደቡብ ሱዳንን በድምር ውጤት 5-0 አሸንፎ የመጨረሻውን ዙር ማጣሪያ የተቀላቀለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሳምንት በፊት መሰባሰቡ የሚታወስ ሲሆን፣ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጥሪ ከቀረበላቸው ተጫዋቾች መካከል ሱራፌል ዳኛቸው በጉዳት ምክንያት በወንድማገኝ ኃይሉ ከመተካቱ በስተቀር የቡድኑ አባላት በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ።
የፊታችን ነሐሴ 20 እና 29 የደርሶ መልስ ጨዋታውን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልምምዱን በአዳማ በመቀጠል ነሐሴ 18 የሜዳ ጨዋታውን ወደሚያደርግበት ታንዛንያ እንደሚያመራ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያደርገው የማጣሪያ ጨዋታ የሚከናወንበት ቀናት እና ቦታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ይፋ መደረጉ ይታወቃል። በዚህም በመጀመሪያው ጨዋታ ዋልያዎቹ ባለሜዳ ሆነው ነሐሴ 20/2014 ታንዛንያ ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ላይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። የመልሱን ጨዋታ ደግሞ ነሐሴ 29/2014 ሩዋንዳ ላይ እንደሚደረግ የወጣው መርሐ ግብር ያሳያል።
በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታው ከደቡብ ሱዳን ጋር የተደለደለችው የኢትዮጵያ ስቴድየሞች የካፍን መመዘኛ መስፈርት አለማሟላታቸውን ተከትሎ በተጣለው ዕገዳ ልክ እንደ አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎቿ ሁሉ ይህንንም ጨዋታ ከሜዳዋ ውጪ ታንዛኒያ ላይ ለማድረግ ተገዳለች።
የመጨረሻውን የማጣሪያ ጨዋታም ኢትዮጵያ እና ተጋጣሚዋ ሩዋንዳ የካፍን መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም የሌላቸው መሆኑን ተከትሎ እገዳ ላይ ቢገኙም ሩዋንዳ ቀናት በፊት አንድ ስቴድየሟ ጨዋታ እንዲያስተናግድ ፍቃድ ማግኘቱ ታውቋል። ይህንን ተከትሎ ሩዋንዳ ነሐሴ 29 የሚደረገውን የመልስ ጨዋታ በሁዬ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደምታስተናግድ ይፋ ተደርጓል። ኢትዮጵያ ግን አሁንም ስቴድየሞቿ ፍቃድ ስላላገኙ ከሩዋንዳ ጋር ነሐሴ 20 የሚደረገውን የመጀመሪያ ጨዋታ በታንዛኒያ ዳሬሰላም ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም እንደምታደርግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬ ሽን ገልጿል።
በአፍሪካ ከዋናው አፍሪካ ዋንጫ ቀጥሎ ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ የሆነው የቻን ዋንጫ በአገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ብቻ ለማበረታታት በካፍ አማካኝነት እኤአ በ2007 የተዋወቀ ሲሆን 2009 ላይ በኮትዲቯር አዘጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ ተካሂዷል። ከጊዜ ወደ ጊዜ በውድድሩ የሚሳተፉ አገራት ቁጥርም እያደገ ሄዶ ትኩረት ከሚሰጣቸው የስፖርት መድረኮች አንዱ ሆኗል። የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ፊፋም እኤአ 2010 ላይ ለዚህ ውድድር እውቅና ሰጥቶታል።
ኢትዮጵያ ከሰላሳ አንድ ዓመታት በኋላ እኤአ 2013 ላይ በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፏን ተከትሎ በእግር ኳሱ የተፈጠረው ከፍተኛ መነቃቃት ይታወሳል። የዚያ ትውልድ ታሪካዊ ተጫዋቾችና የዋልያዎቹ አሰልጣኝ የነበሩት ሰውነት ቢሻው ከአፍሪካ ዋንጫው ማግስት በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተካሄደው የቻን ዋንጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፍ ችለዋል። ለዚህ ተሳትፎም የመጨረሻውን የማጣሪያ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር ከሜዳቸው ውጪ ተፋልመው ማለፋቸው አይዘነጋም።
ዋልያዎቹ በቀጣዩ የቻን ውድድርም በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እየተመሩ በጋቦን በተካሄደው ዋንጫ ላይ መሳተፍ ችለዋል። በሁለቱም ብቸኛ ተሳትፏቸው ግን ከምድባቸው ሳያልፉ ቀርተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 13/2014