አለም በመጠየቅ ፍልስፍና ውስጥ ናት:: እውነት የት ነው ብሎ መጠየቅ የአንድ ማህበረሰብ ህዳሴ መሰረት ነው:: ሀገር በጥያቄ ስትገነባና በአሉባልታ ስትገነባ ሁለት አይነት ናት:: በጥያቄ የተገነባ ሀገር በአሉባልታ አይፈርስም:: በአሉባልታ የተገነባ ሀገር ግን በምንም ለመፍረስ ቅርብ ነው:: የድሮዋ ኢትዮጵያ እውነትና ፍቅር አንድነትም ያቆሟት የመጠየቅ ውጤት ነበረች:: የአሁኗ ኢትዮጵያ ግን የአሉባልታ ውጤት የመሆን አደጋ ውስጥ ነች:: በተለይ ባለፉት ሀምሳ አመታት ውስጥ ያልሰማንው የውሸት አሉባልታ የለም:: ዛሬ ላይ እያገፋፉን ያሉት እነዛ አሉባልታዎች ናቸው:: ዛሬ ላይ እያቀያየሙን ያሉት ያልጠየቅናቸው ጠይቀንም መልስ ያላገኘንባቸው ችግሮቻችን ናቸው::
የህዝቡን ስነ ልቦና የተረዱ አንዳንድ ራስ ወዳድ ግለሰቦች መልስ የሌለው ጥያቄ እየፈጠሩ ሀገራችንን ሲያስጨንቁ ኖረዋል:: ያልሆነና ያልተደረገ ነገር እንደሆነና እንደተደረገ በማስመሰል ህዝብ የሚያባሉ ጥቂቶች አይደሉም:: ህዝብ ካልጠየቀና ለጥያቄዎቹ መልስ ካላገኘ ትውልዱ ተጠራጣሪ መሆኑ የማይቀር ነው:: ተጠራጣሪ ትውልድ ደግሞ ለነገ የሚሆን ቀርቶ ለዛሬ የሚሆን ታሪክ ለመስራት የሚሆን ቁመና የለውም፤ አይኖረውምም:: ሳንጠይቅ ያለውንና የሰማውን ዝም ብሎ ተቀብሎ የሚሄድ ትውልድ የጥቂት ፖለቲከኞችና፣ ራስ ወዳድ ቡድኖች መጫወቻ መሆኑ የማይቀር ነው ::
ሀገርን በጥያቄ ውስጥ መፈለግ ችግሮችን በዘላቂነት ለማፈላለግ ወሳኝ አቅም ነው:: እኛም በችግሮቻችን ዙሪያ የመጠየቅ ባህል አዳብረን ቢሆን ኖሮ ችግሮቻችን በዚህ ልክ ስር ሰደው ግራ ባላጋቡን ነበር:: አንድ ነገር ሲፈጠር እውነት ነው ብለን ከመቀበላችንና ለውሳኔ ከመነሳታችን በፊት ስለችግሩ ማወቅና በቂ መረጃ ማግኘት ያሻናል:: ስሜታዊነት ሀገር አይገነባም:: የሀገር ልዕልና ያለው በሰከነ አእምሮና ልብ ውስጥ ነው:: የእስከዛሬ ችግሮቻችንን ዛሬ ላይ ያን ያክል ጥፋትና ውድመት ባላስከተሉ ነበር::
እኛ ከማድመጥ ይልቅ ለመናገር፣ ከመጠየቅ ይልቅ በለው፣ አሳደው የሚቀናን ነን:: ችግሮቻችን ከጎዱንና ብዙ ነገር ካሳጡን በኋላ የምንነቃ ነን:: የሰው ልጅ ከትላንቱ ካልተማረ ለራሱም ሆነ በዙሪያው ላሉ የሚጠቅመው አንዳች የለም:: እኛ ደግሞ የሚያስተምሩን ብቻ ሳይሆኑ ደም እንባ ያስለቀሱን ትላንትናዎች ያሉን ህዝቦች ነን:: ትላንትን ገሎ መቅበር ያቃተን የትላንት ባሪያዎች ነን:: ሰው እንዴት በትላንት ጥፋት ደጋግሞ ይሞታል? ሰው እንዴት አምናን እያስታወሰ ደጋግሞ ይሰቃያል:: ለዛውም ውሸታሞች በፈጠሩት የማስመሰል ድራማ፣ ለዛውም መሰረት በሌለው የፖለቲካ ጨዋታ:: እንጠይቅ..ወደ ከፍታ የሚወስደን፣ ወደ አንድነት የሚያደርሰን የእድገት ጎዳና የቱ እንደሆነ እንመርምር:: እንጠይቅ…አለም የተለወጠበት የስልጣኔ መርህ የቱ እንደሆነ እንድረስበት::
በዘመን ሀዲድ ላይ እስኪበቃን ተራምደናል:: ፊተኞች ተብለን፣ የነጻነት ምድር ተብለን አለም አውቆናል:: ግን ዛሬም ድረስ በጥንቱ ታሪክ የምንጠራ ነን:: ዛሬም ድረስ በአባቶቻችን ትውፊትና ስልጣኔ ላይ የቆምን ነን:: የራሳችንን ኢትዮጵያ መገንባት አልቻልንም:: የራሳችንን ታሪክ፣ የራሳችንን እውነት መጻፍ አልቻልንም:: ኋለኞች ፊተኞች ሆነው በእኛ ላይ ሀይልና ክንዳቸውን ሲያሳዩን እያየን ነው:: በአባቶቻችን የተፈጠሩ፣ በእኛ ስልጣኔ ቀን የወጡ ሀገራትና መንግስታት ዛሬ ላይ በእኛ ላይ የበላይ ሆነው ካልዳኘናችሁ እያሉን ነው:: ይሄ አያሳፍርም ትላላችሁ? ።
ኢትዮጵያ ጸንሳ የወለደቻቸው የአፍሪካ ሀገራት፣ በአባቶቻችን የደመቁ የአለም ሀገራት ዛሬ እኛን ከኋላ አስከትለው በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በስልጣኔ እናውቅላችኋለን ሲሉን ከዚህ በላይ ምን ውርደት አለ? እንጠይቅ..ጠይቀንም መልስ እናግኝ:: ኢትዮጵያችን በፍቅር ማጣት እየተጎሳቆለች ነው:: ኢትዮጵያችን በወንድማማቾች መካከል በሚፈጠር ጦርነት፣ በሚፈጠር የፖለቲካ ቁርሾ እየተንገዳገደች ነው:: በተባበረ ክንድ ታሪክ መስራት ተስኖናል:: ይሄን የመለያየት ካባ ማን እንዳለበሰን፣ ፍቅር በሌለው የመለያየት ቤት ውስጥ እንድንቆም ማን እንደፈረደብን እንጠይቅ:: በጠዋት ተነስተን ለፍቅር የሚረፍድብን፣ በጎህ ነቅተን ለይቅርታ የሚመሽብን ምን ስለሆንን ነው ስንል እንጠይቅ::
ለጥያቄዎቻችንም በጋራ መልስ እንፈልግ:: ሀገር ምክክር ላይ ናት:: ሀገር በእርቅና በተግባቦት ከፍ ለማለት ከህዝቦቿ ጋር እየሰራች ነው:: ሁላችንም የተሳተፍንበት፣ ሁላችንንም የሚያግባባ፣ ወደ ፍቅር የሚወስደን በመጠየቅ የተገኘ የላቀ እውነት ያስፈልገናል:: ከዚህ በኋላ ባለመጠየቅ ሲያሰቃዩን የነበሩ ችግሮቻችንን ነጠላ በማዘቅዘቅ አልቅሰን ቀብረን ዳግም ታሪኮቻችን የማይበላሹበትን፣ ኢትዮጵያችን የማታዝንበትን፣ ትውልዱ የማይመ ረዝበትን የጋራ ፖለቲካ መፍጠር አለብን:: ባለመነጋገር ለዘመናት ሲያባሉን የነበሩ ፖለቲካዊም ሆኑ ማህበራዊ ችግሮቻችንን ሳይንሳዊ በሆነ በተጠና አካሄድ አሸንፈን ቀና የምንልበትን የእፎይታ ጊዜ መፍጠር አለብን::
በዚህ የጋራ እውነት ውስጥ ካላለፍን “ውሀ ቢወቅጡት እንቦጭ “እንደተባለው መልሰን መላልሰን ያው ከመሆን ውጪ የምናመጣው ለውጥ አይኖርም:: መጀመሪያ በመጠየቅ ጥበብ የችግሮቻችንን መነሻ ምክንያት ፈልገን እናግኝ:: ከዛ በኋላ እዳው ገብስ ነው፤ መነሻው የታወቀ ነገር ሁሉ መድረሻ አለው:: እኛም ያን በመጠየቅ ያገኘነውን የችግራችንን መነሻ ይዘን በምክክርና በሀገራዊ እርቅ ወደፍጻሜው እንሄዳለን:: ችግር የሆነብን ሳንጠይቅና ማህበረሰቡን ሳናወያይ መነሻ ምንጩንም ሳናውቅ ለመፍትሄ መቀመጣችን ነው:: ምንጩ ያልታወቀ ችግር መፍትሄ የለውም:: ሁሉም ነገር በምክንያትና ውጤት ውስጥ የሚያልፍ ነው:: ውጤት ካለ ምክንያት አለ:: ምክንያት ካለ ውጤት ግድ ነው:: እኛም የችግሮቻችንን ማብቂያ ለማወቅ መነሻ ምክንያታቸውን ማወቅ ግድ ይለናል::
ሀገር መፍጠር ጀግና መፍጠር ነው:: ሀገር መፍጠር ታሪክ መፍጠር ነው:: እኛም በመጠየቅና ጠይቆ መልስ በማግኘት መጪው ትውልድ የሚኮራበትን ሀገርና ታሪክ መፍጠር ይጠበቅብናል:: በዜጎች በጥያቄ የተፈጠረች ሀገር እጣ ፈንታዋ ስልጣኔና ፊተኝነት ነው:: በዜጎች ጥያቄና መልስ የተፈጠረ ማህበረሰብ ፍቅርንና አንድነትን መርህ አድርጎ ከመኖር ባለፈ አማራጭ አይኖረውም:: ከዚህ እውነት በመነሳት የእኛ ሀገር ምን እንደነበረች መረዳት እንችላለን:: የእኛ ሀገር ዜጎች ጥያቄ አይጠይቁም፣ እንዲጠይቁም እድል አይሰጣቸውም::
በጣም የሚያስደንቀው ደግሞ አብዛኛው የአለም ስልጡን ሀገራት መንግስት ለዜጎች በፈጠረው የመጠየቅ መብት የተፈቱ መሆናቸው ነው:: ጥሩ ጥያቄ ጥሩ ሀገር ይፈጥራል፤ ጥሩ መልስ ግን በጥሩ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ጥሩ ህዝቦችንና ጥሩ ትውልዶችን ይፈጥራል :: ዛሬ ላይ ጥሩ ሀገር መፍጠር ያልቻልነው ጥሩ ጥያቄ ስለሌለን ነው:: ጥሩ ህዝብና ጥሩ ትውልድ መፍጠር የተሳነን ደግሞ በጥያቄ የተፈጠረች ሀገር ስለሌለችን ነው:: ጥሩ ጥያቄዎች ሁሌም ጥሩ መልስ አላቸው:: ጥሩ ጥያቄዎች ጥሩ ሀገርና ጥሩ ትውልድ ለመፍጠር መሰረት ናቸው::
ጥሩ ሀገር ለመፍጠር በጥያቄዎቻችንም ሆነ በመልሶቻችን ላይ እኩል ተሳታፊ መሆን ይኖርብናል:: የተወሰኑ ሰዎች እየጠየቁ የተወሰኑ ሰዎች የሚመልሱላት ሀገር የጋራ ታሪክ አይኖራትም:: የጋራ ሀገር፣ የጋራ ታሪክ፣ የጋራ እሴት እንዲኖረን በጋራ ጠይቀን በጋራ መልስ መፈለግ ይኖርብናል:: የሀገራዊ ምክክሩ ዋና አላማ ደግሞ ይሄ ነው:: በጋራ መክሮ፣ በጋራ መፍትሄ ማምጣት:: በጋራ ጠይቆ በጋራ መልስ መፈለግ:: በጋራ መክሮ፣ በጋራ ውሳኔ መወሰን ነው:: ሀገራችን የጋራችን እንደመሆኗ መጠን በጋራ መልፋት፣ በጋራ መድከም ይጠበቅብናል::
አንዱ እየለፋ፣ አንዱ ጉዳዬ አይደለም በሚል የምንአገባኝነት ስሜት የምትቆም ሀገር የለችንም:: ሀገራችን በጋራ አምጠን፣ በጋራ የምንወልዳት የጋራ ሀሳባችን ጽንስ ናት:: ጥሩ ሀገር ለመውለድ ጥሩ ሀሳብ ማማጥ ይኖርብናል:: ጥሩ ትውልድ ወልዶ ለማሳደግ ጥሩ ዘር መዝራት ይጠበቅብናል:: ዘራችን ሀሳባችን ነው:: ዘራችን ፍቅር ነው:: ዘራችን ተነጋግሮ መስማማት ነው:: ክፍት በሆነ የምክክር መድረክ ችግሮቻችንን በጥያቄ እናሸንፍ:: ድህነታችንን በመፍትሄ እንርታ::
ካለጥያቄ፣ ካለመፍትሄ ዜጋ መሆን ብቻውን ትርጉም የለውም:: ዜግነት በሀገር ጉዳይ ላይ ከመጠየቅና ጠይቆም መልስ ከመስጠት የሚጀምር ነው:: ዜግነት በሀገር ጉዳይ ላይ ከመንግስት ጋርም ሆነ ከየትኛውም የማህበረሰብ ክፍል ጋር የሚወያይና የሚነጋገር ነው:: የልጅነት እውቀታችን የሚነግረን እኮ ህዝብ ማለት መንግስት፣ መንግስት ማለት ህዝብ ነው ሲል ነው:: ዜግነት ብዙ ቁጥር ሲሆን ህዝባዊነት፣ መንግስታዊነት ነው::
የእኛ ሀገር ዜግነት ግን አስቂኝ ነው..ምን አገባኝ፣ አይመለከተኝም በሚል አፍራሽ አመለካከት ተኮትኩቶ ያደገ ነው:: ዜግነታችንን ለሀገር በመልፋት፣ ለሀገር በማሰብ፣ ለሀገር በመቆርቆር መጀመር አለብን:: በሀገር ጉዳይ ላይ በመነጋገርና በመመካከር ዜግነታችንን ጥቅም ላይ ካላዋልነው እኛ ሞኞች ነን:: ምክንያቱም የምንፈልገው ሰላም፣ የምንፈልገው እድገት፣ የምንፈልገው ስልጣኔ ሁሉ በእኛ ጥያቄና መልስ ውስጥ የተደበቀ በመሆኑ ነው:: ካለፈው ይልቅ የሚመጣው ይበልጣልና ለድህነትና ለሰላም ማጣት የዳረጉንን ችግሮቻችንን በማሸነፍ አዲስ የመጠየቅና የመመካከር ልምድን የእኛ እናድርግ ::
ራሳችንን ለይቅርታና ለትዕግስት ሳናስገዛ ለውጥ የለም:: ራሳችንን ለጠንካራ የምክክር ልምድ ሳናበቃ ለውጥ የለም:: ራሳችንን በእውቀት ሳናጎለምስ ለውጥ የማይታሰብ ነው:: ጊዜው የእኛን ታማኝነት የሚጠይቅ ነው:: ኮሮና አለ፣ የኑሮ ውድነት አለ፣ የሰላም ማጣት አለ፣ የውጪ ጫናዎች አሉ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሀገርን በታማኝነት ማገልገል የእውነተኛ ዜጋ መገለጫ ነው:: አንድን ሌባ ግለሰብ፣ ወይም አንድን ሙሰኛ ሰው፣ ወይም ደግሞ አንድን ነውጥ ፈጣሪ ወንበዴ ቤታችን ደብቀን ሌባ በዛ፣ አድሎ ተስፋፋ፣ መንግስት ህግ ማስከበር አልቻለም ብንል ልክ አይሆንም::
ልክ የሚሆነው ልክ የሆነ ነገር ብቻ ነው:: ልክ የሆነ ነገር ደግሞ ልክ በሆነ ስፍራ ላይ ነው የሚገኘው:: ሀገር በዜጎቿ ነው የምትጠበቀው:: የህግ የበላይነት ዋጋ የሚኖረው በዜጎች የያገባኛል መንፈስ ሲቃኝ ነው:: ህዝብ ወንጀልንና ወንጀለኛን ሲያጋልጥ፣ መንግስት ተገቢውን ቅጣት ሲሰጥ ያኔ ሁሉም ነገር ልክ መሆን ይጀምራል:: መጀመሪያ በቤታችን፣ በአካባቢያችን ያሉ ችግሮችን እንመልከት:: ጥያቄዎቻችን ሰላም ከሆነ መጀመሪያ እኛ ሰላም ወዳድና ሰላም ፈጣሪዎች እንሁን::
ጥያቄዎቻችን ልማት ከሆኑ ደግሞ መጀመሪያ በልማት የተጉ፣ በምክንያት የዳበሩ አእምሮን የእኛ ማድረግ ይጠበቅብናል:: ጥያቄአችን እድገት፣ ብልጽግና ከሆነ ደግሞ መጀመሪያ እጆቻችንን ለስራ መዘርጋት ግድ ይለናል:: ካለእኛ ተሳትፎ፣ ካለእኛ ሀላፊነት፣ ካለእኛ ትጋት መንግስት ብቻውን ምንም ማድረግ አይችልም:: መንግስት እንዲሰራም ሆነ እንዲቦዝን የሚያደርገው የዜጎች ጥያቄና የያገባኛል መንፈስ ነው::
ልክ የሆነ ነገር ያለው በመጠየቅ ውስጥ ነው:: ሳንጠይቅና ሳንመካከር ሀገራችንን ልክ ባልሆነ ስፍራ ላይ ያለክብሯ አስቀምጠናት ኖረናል:: አሁን ግን እንጠይቅ..ጠይቀንም መልስ እናግኝ:: ሰላሞቻችንን በመጠየቅ እንመልስ፣ አንድነታችንን በውይይት እናምጣ:: እስከዛሬ ያልሄድንባቸውን የልዕልና ጎዳናዎች በፍቅር እንሂድባቸው:: እነዛን ሳናውቅ ሲያገፋፉን የነበሩትን ፖለቲካ ወለድ አሉባልታዎች በይቅርታ እንሻገራቸው:: ከማይገባን ወጥተን ወደሚገባን ስፍራ ከፍ እንበል:: እንጠይቅ..ጠይቀንም መልስ እንፈልግ::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ነሃሴ 13/2014