እነተሰማ መንግስቴ የሚሰበሰቡበት መጠጥ ቤት እንደተለመደው በሰዎች ሁካታ ደምቋል። አስተናጋጆች ይሯሯጣሉ። ሰው ያለ እህል ምን ያህል? ሳይሆን ሰው በዕህል ምን እንደሚያሕል የሚታይበት ቦታ ነው። ‹‹ሰው ያለ እህል ምን ያህል?›› የሚለው አባባል በችግር እና በርሃብ ሲሰቃይ የነበረውን ብቻ ሳይሆን አሁንም ድረስ በችጋር ውስጥ ያለውን ኢትዮጵያዊ በእውነት በምግብ እጦት እንዴት እንደሚጎሳቆልና ምን እንደሚያህል በማየት ማረጋገጥ ይቻላል። በእርግጥ የእነተሰማ መንግስቴ መወፈርና ጥጋብ ሌላውን ኢትዮጵያዊ አይወክልም።
በመጠጥ ቤቱ የተሰበሰቡት ግን ገሚሱ የሚበላውን አዝዞ ሲበላ፤ ሌላው እጁን ታጥቦ ሲጠባበቅ አንዳንዶቹ አጠናቅቀው እንደተለመደው መጠጣቸውን ይዘው እየተሳሳቁ ያውካካሉ። ሁሉም ጉንጩ እና ሆዱ የተንጠለጠለ ነው። እነተሰማ መንግስቴ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ ያሉ አይመስሉም። ጠግበዋል፤ ተመችቷቸዋል። እነርሱ ሰፈር የዘመኑ ችግር የለም። እንኳን ኢትዮጵያን አለምን ረስተዋል።
ዘውዴ መታፈሪያ ጎራ ያለው ዘግይቶ ነበር። ሰውነቱም አጭር እና ቅጭጭ ያለ ሲሆን፣ ጎስቋላ እና ማዲያታም ነው። ያው ወግ አይቀር ከእነተሰማ ጋር እርሱም ተሰብስቧል። የሚበላውን አላዘዘም፤ ቀጥታ የገባው ወደ መጠጡ ነው። እንደሌሎቹ ምግብ ልብላ ካለ ገንዘቡ አይበቃውም። አብሮ ለመጠጣትም ቢሆን ነገ እዛ ቦታ ላይ መገኘት አይችልም። መጠጡንም ቢሆን አንዳንድ ቀን እነተሰማ እየጋበዙት እንጂ ባያግዙት በየቀኑ ከእነርሱ ጋር መቀላቀል ይሳነው ነበር።
መብላት መፈለግ ብቻ ሳይሆን ሰውነቱ ተገቢውን ምግብ ባለማግኘቱ እያላበው ቢልፈሰፈስም ገንዘብ ስለሌለው የምግብ ዝርዝር አይጠይቅም። ምንም እንኳ እነተሰማ ቢከፍሉለትም እንኳን ምግብ አዞ ሊበላ ‹‹ሰው ያለቤቱ ያንሳል ጉልበቱ›› እንዲሉ መጠጡንም ቢሆን ተዝናንቶ እስኪበቃው አይጠጣም። ተሳቅቆ ለሱሱ ያህል ትንሽ ይጎነጫል፤ ራሱን ለመርሳት እና ወጪውን ለመቀነስ ደግሞ እንደነተሰማ ውስኪ ከመጠጣት ይልቅ በቢራው ላይ አረቄ ይደርብበታል። ከዛ ሞቅ ሲለው መደንፋት ይጀምራል። በጠገበ ሆዱ ሳይሆን በተራበ አንጀቱ መጠጥ የሞላውን ጭንቅላቱን አንገቱ መሸከም እያቃተው ጎንበስ ቀና እያለ ያለበትን ደረጃ ይረሳል። እነተሰማ መንግስቴን ይሳደባል። አንዳንዴ በስካር ሌላ ጊዜ ደግሞ የሰከረ አስመስሎ ልቡ ውስጥ ያለውን በሙሉ ዘርዝሮ ይዘከዝካል።
አንዳንዴ እነተሰማ ጓደኛቸው ዘውዴ ሞቅ ብሎትም ቢሆን የሚናገረው እውነት እንደሆነ በማመን በልዩነታቸው ይሳቀቃሉ። በተለይ ፖለቲካ ነክ ጉዳይ ላይ መነጋገር ከተጀመረ፤ ዘውዴ ልቡ ጮቤ ይረግጣል። እንደፈለገ ይዘረጥጣቸዋል። እነተሰማ ለመከላከል ይሞክራሉ፤ ነገር ግን ለእርሱ ምላሽ መስጠት ቀላል አይሆንላቸውም። ‹‹እናንተ ኢትዮጵያዊ አይደላችሁም። ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያ የሚሞት እንጂ ለሆዱ የሚሞት ከርሳም በልቶ አደር አይደለም። ›› ይላቸዋል። በተለይ የአንድአንድ ቀን ንግግሩ ለመስማት ከባድ ይሆናል።
‹‹እናንተ እኮ ለኢትዮጵያ ልጆቿ ሳትሆኑ የሩቅ ባዳዎች ናችሁ። እንዲያውም ባዳ ያው ባዳ ነው። ቢያንስ ሰው ላይ ላይደርስ ይችላል። እናንተ ግን ባዳ መሆን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ እሳት እየጫራችሁ እስከ ማፋጀት የምትደርሱ የአንጀት ስር በሽታዎች ናችሁ። ሆዳችሁን መሙያ ካገኛችሁ ምንም ለማድረግ ወደ ኋላ አትሉም። እኛ እውነተኛ ልጆቿ የምንልሰው የምንቀምሰው ያጣን ምስኪን ድሃዎች ነን። ሃብታችንን መጠቀም የተከለከልን በዛም ምክንያት በረሃብ እየተቆላን ያለን ምስኪን ድሃዎች፤ በገዛ ሃብታችን ሌላው እየበላ ሲጠግብ እኛ ግን የሚበሉትን እያየን ልክ እኔ ዛሬ እንደሆንኩት እንራባለን። እኛ ርቦናል፤ ረሃባችንን እናስታግስበት ብንላቸውም እንደናንተ አይነት የውጪ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሊገባቸው አልቻለም። ሳይርበው የሚበላ ርሃብን አያውቀውም እንደሚባለው እነርሱ ተርበው አያውቁም፤ ስለዚህ የእኛ ርሃብና ችግር አይገባቸውም።
ሰው ያስገድላል አባይ፤ ውሃ ያስጮሃል ድንጋይ እንዲሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች በውሸት ይኖራሉ። በውሸት ሰው ያስገድላሉ። የኢትዮጵያ አድባር የኢትዮጵያ ሲሳይ የሆነውን አባይ መነሻው ኢትዮጵያ እንደሆነ አያምኑም። ውሸት ያወራሉ፤ ሰው ያሳስታሉ። አንድ ሰውን ብቻ ሳይሆን ትውልድን በተሳሳተ መንገድ ይነዳሉ። እንኳን መራብ ጥጋባቸው እንዲቀንስ አይፈልጉም። እናንተም ተመሳሳይ ናችሁ። እነርሱ ጠግበው ለአገራቸው ይቆማሉ። እናንተ በተቃራኒው የውስጥ የኢትዮጵያ ጠላቶች የገዛ አገራችሁን አጥንቷን ግጣችሁ ሆዳችሁን በመሙላት ፈጥናችሁ እየተራመዳችሁ የተሰጣችሁን ሃላፊነት ከመወጣት እና አገር ከመጥቀም ይልቅ ቦርጫችሁን በመከራ ትጎትታላችሁ። ሰው እና እንጨት ተሰባሪ መሆኑን አትረዱም። ከዚህ አሁን ስትወጡ ተሰብራችሁ ልትቀሩ ትችላላችሁ፤ ይህንን ማሰብም ሆነ መስማት ስለማትፈልጉ ምንም ማድረግ አይቻልም። ነገር ግን ማወቅ ያለባችሁ የነገ የታሪክ ተወቃሾች ናችሁ። ›› አለ።
አላቋረጠም ቀጠለ፤ ‹‹አሁን ኢትዮጵያን እየበደላት ያለው የውጪው ብቻ ሳይሆን ውስጧ ያለው ጨካኝ ልጇ ነው። ማንኛውም ሰው አላፊ በመሆኑ የማይሞት ሥራ በመሥራት እንደገና እንዲወለድ መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፈቀደበት ወቅት ቢሆንም፤ አንዳንዶች ግን በአላፊ ንዋይ ተመስጠው እና በዛም ተታልለው አገራቸውን እየጎዱ ነው። ግብፅ ‹ናይል የፈጣሪ ገፀ-በረከቴ ነው› ብላ በውሸት ለመጠቀም ስትሞክር፤ እኛ ደግሞ አባይ ከገዛ ምድራችን የሚመነጭ መነሻውን በተራራው ላይ ያደረገ የግብፅ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የተሰጠ የፈጣሪ ስጦታ ቢሆንም ግብፅም ሆነች ሱዳን እንዲሁም ሌሎቹም የተፋሰሱ አገሮች ሊጠቀሙበት መብት አላቸው ብለን የራሳችንን ርሃብ ለማስታገስ ስንዳክር ነገር ግን እንደናንተ አይነት ከርስ ወዳድ መብላትም ሆነ ረሃባችንን ማስታገስ እንዳንችል እንቅፋት ሆኖብናል። ባንጠግብ እንኳ እንዳንራብ ብትፈቅዱልን ምን አለ?›› ሲል ሁሉንም በጥያቄ አፋጠጣቸው። መልስ የሰጠው አልነበረም።
ወረቱን የተቀማ ነጋዴ ዋግ የመታው ስንዴ እንዲሉ እነተሰማ ሁሉም ጥጋባቸው ጠፋ፤ ድንጋጤ ተሰማቸው። አንደኛው ጓደኛቸው አዳነ ግን ለዘውዴ መልስ መስጠት ፈለገ። ‹‹በምን መስፈርት እኛ እና ግብፅ አንድ እንሆናለን? ይሔ መቼም ለምን ወፈሩ? በሚል ቅናት እንጂ ለምንበላበትም ሆነ ለምንጠጣበት ግብፅ ገንዘብ ለእኛ የምትሰጥበት ምንም አይነት መንገድ የለም። ሊኖርም አይችልም ይህንን ጠንቅቀህ ታውቃለህ። ›› አለው።
‹‹በማያገባቸው የሚገቡ ያለሃሳብ የሰው በቅሎ የሚስቡ ጣልቃ ገቦች እየሰጡን አይደለም ብለሕ ሞግተኝ። ›› በማለት ዘውዴ አዳነ ላይ አፈጠጠ። አዳነ አልገባውም ግራ ገባው ‹‹እነርሱ ደግሞ እነማን ናቸው? ›› ሲል ጠየቀ። ዘውዴ በበኩሉ ‹‹ያው ተዘዋዋሪ የኢትዮጵያ ጠላቶች ናቸው። ›› አለና መለስ ብሎ ለነገሩ እናንተ አይገባችሁም። ገንዘቡ ኪሳችሁ ውስጥ መግባቱ እንጂ የመጣው ከየት እና እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ አያሳስባችሁም፤ ጭራሽ አይገባችሁም። ለእናንተ ማስረዳት ድንጋይ ላይ ውሃ እንደማፍሰስ ነው። ›› ሲል አዳነ በስጨት አለ። ወዲያው ራሱን ተቆጣጠረ፤ ቀጫጫው ዘውዴ ላይ እጁን መሰንዘር አልፈለገም።
አዳነ ዘውዴን የውሃ ላይ ኩበት እንደሆነ በከንቱ የሚንሳፈፍ ከመፍረስ ውጪ ተስፋ የሌለው ነው ብሎ በመገመት ‹‹ አንተን እኔ ሳልመታህ ሕይወት ራሷ መትታ ከምድር ታጠፋሃለች። ›› አለው። ዘውዴ መረር ብሎ ተናገረ፤ ‹‹እውነት ትቀጥናለች እንጂ አትበጠስም ሲባል አልሰማህም? እኔ ሁልጊዜም የምናገረው እውነት ነው። መቀበል ያለባችሁን ተቀበሉ። እንደግብፃውያን ስለአገራችሁ ቁሙ። በምልጃ እና በውንብድና ሰርታችሁ ከማግኘት ይልቅ በሃቅ ላይ ተመስርታችሁ ፍትሃዊ አገልግሎት ስጡ። ሁሉንም እኩል ካገለገላችሁ እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች ትሆናላችሁ። ምንም እንኳ እስከ ዛሬ ኢትዮጵያን ብታስቸግሩም፤ ብዙ ጥፋት ብታጠፉም ይቅር ትባላላችሁ። ጠግበው እያደሩ ኢትዮጵያን ከሚያስርቡ ወይም ኢትዮጵያውያን በልተው እንዳያድሩ ከሚተጉ የውጪ ጠላቶች ተለይታችሁ ትታያላችሁ። የዘመድ ጥል የሥጋ ትል እንዲሉ ብንጣላም አንለያይም ። የዘመዳም ጠብ ቂም ስለሌለው አያራርቅምና ተለያይተን አንለያይም።
ይቅር እንላችኋለን። ነገር ግን እንደግብፅ ወይም በማያገባቸው እየገቡ አሸማጋይ ለመምሰል የሚሞክሩ እና ኢትዮጵያውያንን እንዳያድጉ እንደሚተጉ ክፉ የውጪ ሰዎች አትሁኑ። እንደግብፃውያን ሁሉ ስለሃገራችሁ ትጉ፤ ለአገራችሁ ታሪክ በመስራት ዳግም ተወለዱ። የአባይ ግድብ ተጠናቆ ኢትዮጵያ ከፍ እንድትል ሃላፊነታችንን እንወጣ፤ የግብፅ ስግብግብነት በልክ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን በየሰበቡ በኢትዮጵያውያን መካከል የሚፈጠር ክፍተትን እንድትጠቀምበት አንፍቀድላት።
የአህያ ስጋ ከአልጋ ሲሉት ከአመድ እንዲሉ ያለበለዚያ ክብር የሌለው ሰው በገዛ እጁ እንደሚዋረደው ሁሉ እኛም እንዋረዳለን። የኢትዮጵያ ዕድገት የሁላችንም ዕድገት ነው። የኢትዮጵያ ጉስቁልና እና ጉዳት የሁላችንም ጉስቁልና እና ጉዳት በመሆኑ እንደራሳችን እንየው፤ እየጠገቡ የተራበን መርሳት አያዋጣም። አሁን በዚህ ዘመን ለዓባይ ግድብ የሠራ ሁሉ ዳግም እንደተወለደ ነው። ከውጪው በላይ ውስጥ አዋቂ የበለጠ የሚጎዳ በመሆኑ ከውስጥ ሆናችሁ አገራችሁን ኢትዮጵያን እንዳትጎዷት›› ሲል አጠቃለለ።
ተሰማ ግን የዘውዴ ማጠቃለያ ትንሽ ቆርቁሮታል፤ ‹‹ ውስጥ አዋቂ በመሆኑ የበለጠ የሚጎዳው ማን ነው? ለምን አንተ ሁል ጊዜ ራስህን ነፃ፣ ምንም ያላደረገ ፣ አገሩን ብቻ ሲጠቅም የኖረ ሰው ታስመስላለህ? ይህ ትክክል አይደለም። ኢትዮጵያን ጎድታችኋል ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ጎድተናታል በል። ›› አለው።
ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹እኔ ኢትዮጵያን አልጎዳሁም የሚል ሃሳብ አልሰነዘርኩም። ›› ሲል ተሰማ ደግሞ ‹‹እናንተ ኢትዮጵያን ጎድታችኋታል፤ ማለት እኔን አያካትትም እያልክ ነው። አንተም የእኛው አካል ስለሆንክ ኢትዮጵያን ጎድተናታል በል›› አለው።
ዘውዴ ቆም ብሎ ሁለት እጆቹን ደረቱ ላይ አድርጎ ‹‹እናንተ ብቻ አይደላችሁም፤ እኔም ኢትዮጵያን ጎድቻታለሁ። ቢያንስ ሌሎች ሲጎዷት እያየሁ ዝም ብዬ አልፌያለሁ። ስለዚህ ተጠያቂ ነኝ። እኔም ሃላፊነት አለብኝ። ነገር ግን ከአሁን በኋላ ቢያንስ የአገር ልጅ የማር እጅ እንዲሉ ወገን አገርን የሚረዳ እና በችግር ጊዜ የሚደርስ ነውና ለጎስቋላዎቹ ኢትዮጵያውያን እንድረስላቸው እላለሁ። በሉ ለዛሬ ለእኔም ድረሱልኝ የጠጣሁበትን ክፈሉልኝ›› ብሎ ሲወጣ ሁሉም አውካኩ። ዘውዴ መንገድ ሲጀምር ስካሩ ለቅቆት ነበር። ዛሬ የተበሳጨው በድህነቱ ሳይሆን በግብፅ ስግብግብነት ነው። ያንንም ለነተሰማ ስለገለፀ ደስ እያለው መንገዱን ቀጠለ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12 /2014