በህይወታቸው ርክት ያሉ ሰዎች ራሳቸውን በምስጋና ውስጥ የደበቁ እንደሆኑ ታውቃላችሁ? በህይወት ሁሉን አጥተው ከስረው የሚኖሩ ራሳቸውን ከምስጋና ያራቁ እንደሆኑስ? ምስጋና የነፍሶች ህብስት ነው። የትም መቼም በእያንዳንዳችን ህይወት ውስጥ ሊኖር የሚገባው ትልቅ እውነት ነው ። በዚህ ራስ ወዳድ በሆነ አለም ላይ ራሳችንንም ሌሎችንም እንባርክበት ዘንድ የተሰጠን ጸጋችንም ነው። አብዛኞቻችን መኖር ምን እንደሆነ አናውቀውም ዝም ብለን ነው የምንኖረው ለዚህም ከስረንና እርባና ቢስ ሆነን እንኖራለን። ከምስጋና የራቀ ህይወት ማር እንደሌለው ቀፎ ባዶ ነው።
የመኖር ዋጋው ጥልቅ ነው..ብዙዎች በጥላቻና በመገፋፋት በሚኖሩበት በዚህ ሰዓት የምስጋናን ጥቅም ተረድተው በልዕልና የሚኖሩ እንዳሉም አውቃለሁ። እነሱ ምን ያክል እድለኛ እንደሆኑ ሳስብ እቀናባቸዋለሁ። ምስጋና ህይወትን ውብ የምናደርግበት አምላካዊ ጥበባችን ነው። አድናቆት የሌሎችን አለም፣ የሌሎችን ህይወት የምናደምቅበት፣ በርቱ ከዚህም በላይ ስሩ ብለን እውቅና የምንሰጥበት ሰውኛ ግብራችን ነው። የሰዎችን ልብ በነጻ የምንባርክበት፣ በነጻ የምንቀድስበት መላችን ነው ፡፡
ከሁሉ በፊት የሌሎችን ህይወት የምንባርክበት መልካም አስተሳሰብ ያስፈልገናል። ሁሉም መንገዶች ለቅን ልቦች ክፍት ናቸው። እስካሁን ድረስ የተዘጉ መንገዶቻችን ካለፍቅር በጥላቻ የተጓዝንባቸው ስለሆኑ ነው። በእርግማንና በወቀሳ ስለተራመድንባቸው ነው። እንደ ሀገር በመኖር ውስጥ ትልቅ ዋጋን ሊያስገኙልን የሚችሉ በረከቶች የቱ ጋ እንዳሉ ገና አላወቅንም። መልካም ህይወት በቁስና በገንዘብ የሚገኝ የሚመስለን ብዙዎች ነን። በህይወት ውስጥ በገንዘብ የማይመለሱ ነፍሳዊ ጥያቄዎች እንዳሉ አናውቅም፡፡
የሁሉም ጥያቄዎች መልስ አንድ ቦታ ነው ያለው እርሱም ቅን ልብ ውስጥ ነው። ቅን ልብ ደግሞ በምስጋና በፍቅር በይቅርታ የተሞላ ነው። ቅንነትና መልካምነት አብሮን እስከሌለ ድረስ እንቅፋቶቻችን ሁሉ የሚጥሉን ነው የሚሆኑት። የነካነው የሚገማ፣ የረገጥነው የሚከረፋ ነው የሚሆነው። ቅን ልቦች መራቂዎች ናቸው፣ ቅን ልቦች በራሳቸው ላይ እንዲሆን የማይፈልጉትን በሌሎች ላይ አያደርጉም። ቅን ልቦች ለሌሎች የሚሆን ብዙ ፍቅር ብዙ እውነት አላቸው..ቅን ልቦች በሀሳባቸው በግብራቸው ፈርሀ እግዚአብሄር አለ።
በህይወታችን እንዲሁም በኑሯችን ምርጥ መሆን ከፈለግን ራሳችንን እያመሰገንንና እየተመሰገንን ልናገኘው ይገባል። በህይወታችን ድንቅና ስኬታማዎች መባል ከፈለግን ሞት የሌለበትን ህይወት ፍቅርን ልንለብስ ይገባናል። ያኔ ከራሳችን አልፈን በዙሪያችን ለቆሙ ሁሉ አስፈላጊዎች እንሆናለን። ያኔ የሌሎች ቁስል ያመናል፣ የሌሎች መከራ ይሰማናል። ምክንያቱም ፍቅርን እናውቃለንና። ያኔ ሌሎች ለእኛ እኛም ለሌሎች ምን
ያክል አስፈላጊዎች እንደሆንን እንደርስበታለን። ያኔ የእውነት ሰው እንሆናለን። ጥላቻን ገድለን፣ ዘረኝነትን አውድመን በፍቅርና በምስጋና ሀይል አንድነትን በውስጣችን እናጸናለን፡፡
የዚህ አለም ታላቁ ጥያቄ እኔ ማነኝ? ለምንድነው ሰው የሆንኩት የሚለው ነው። ይሄን ጥያቄ ሳንመልስ፣ በዚህ ጥያቄ ላይ ሳንረማመድ ዘመናዊነት አይጎበኘንም። ተመኝተን የሚሳካልን አንዳች አይኖርም። ይሄን ጥያቄ ሳንመልስ የሚኖረን እውቀትና ማስተዋል አይጠቅመንም። ታላቁ ፈላስፋ ሶቅራጠስ “ያልተመረመረ ህይወት ዋጋ የለውም ይላል”። እውነት ነው ያልተመረመረ..ያልተጠየቀ ህይወት ትርጉም የለውም። መኖራችን ዋጋ የሚያገኘው ለምን ሰው እንደሆንን ስናውቅ ብቻ ነው፡፡
ራሳችንን በፍቅር ጠበል እንጥመቅ። በምስጋና ባህር እናርስ፣ በይቅርታና በውዳሴ ኩሬ ውስጥ እንንከር። እንረስርስ..ምስጋና በዝቶልን፣ ውዳሴ ተትረፍርፎልን እትት እንበል። ያኔ መኖር እንጀምራለን። በልዕልና እንኖር ዘንድ ለምን እንደተፈጠርን፣ በመኖር ውስጥም ስላሉ ለህይወት እጅግ አስፈላጊ ስለሆኑ ቁም ነገሮች ማወቅ አለብን። ዝም ብለን እንድንኖር አልተፈጠርንም። መልካም የሆነውን እንድንፈልግና እንድንከተል ነው ሰው የሆንነው። መልካም የሆነው ደግሞ ምስጋና ነው። ከሌሎች ጋር በፍቅር በመቻቻል መኖር ነው፡፡
ምስጋና የስልጡን ማህበረሰብ መገለጫ ነው። ማመስገን ከሌሎች ልዩ መሆን ነው። ለሌሎች የሚሆን በረከት እስከሌለን ድረስ ራሳችንን ልዩና ምርጥ ሆነን አናገኘውም። በአስተሳሰባቸው የላቁ ሰዎች በልባቸው ውስጥ ብዙ ምስጋና አለ። በህይወታቸው ስኬታማ የሆኑ ግለሰቦች የስኬት ምንጫቸው ምስጋና ነው ። እነዚህ ግለሰቦች ደስተኛና ጤነኛም ናቸው። ወንዝ ዳር እንደበቀለ አበባ ለምለምና ብሩህ ናቸው። በተቃራኒው ምስጋናን የማያውቁ ሰዎች በህይወታቸው ውስጥ ብዙ ባዶነት ያለባቸው ናቸው። በርሀ ላይ እንደበቀለ አበባ ጥመኛ። እስካሁን ድረስ የደረሱብን የህይወት ውጣ ውረዶች ሁሉ ካለበጎነት የሆኑ ናቸው። ሁሌም ጉድለታችን የፍቅር አለመኖር ነው…የደግነት የርህራሄ ማጣት ነው። ሌሎችን እስካላመሰገንንና በመልካም ስራችን እስካልተመሰገንን ድረስ መኖራችን ትርገም አይኖረውም፡፡
እርግማንን ወቀሳን እንጸየፍ። አሁን ላይ የብዙዎቻችን ችግር ይሄ ነው። ከሚጠቅመን ይልቅ ለማይጠቅመን የበረታን ነን። አዲስ ልብና አዲስ መንፈስን እስካልተላበስን ድረስ ላመል ደስታ አይኖረንም። ደስታ የተግባር ውጤት ነው። ደስታ ከውስጥ የሚመነጭ የራስ የአስተሳሰብ ውጤት ነው። ደስታን ፍለጋ ሩቅ የሚሄዱ ሁሉ ውስጣቸው ፍቅር የሌለ፣ ምስጋናን ይቅርታን የማያውቁ ናቸው። የሰላም ሁሉ ስፍራው ልብ ነው። ሰው ልቡን ካነጻ መሳቂያ አያጣም። ማረፊያ ስፍራ አይቸግረውም። ችግር የሆነብን ልባችንን አለማጽዳታችንና ለፍቅርና ለምስጋና ቦታ ማጣታችን ነው።
የሚጠላ ልብ እግዚአብሄርን አያውቅም። መሞት የምንጀምረው መጥላት ስንጀምር ነው። በህይወታችን የመጣና እንዲመጣ የምንፈልገው ልክነት ሁሉ በአፈቀርን ሰሞን፣ አመሰግናለሁ ባልን ሰሞን፣ አሜንና ተመስጌን ባልን ቅጽበት የሆነና የሚሆን ነው። የእስካሁኑ ህይወታችን በጥላቻና በእርግማን፣ በትችትና በወቀሳ ያለፈ ነው። ከእንግዲህ አትርፈን እንጂ ከስረን መኖር አይኖርብንም። በእያንዳንዱ ማለዳ የምናገኛቸውን ሰዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደምናገኛቸው ሆነን ልንወዳቸውና ፍቅር ልንሰጣቸው ይገባል። ባለንና በሌለን ነገር ላይ ማመስገንን እንልመድ። በህይወታችን ለሆነውና እየሆነ ላለው ሁሉ አሜን እንበል።
የተለያዩ ሰዎች ስለምስጋና ብዙ ብለዋል። አሜሪካዊቷ ጥቁር ቢሊየነር ኦፕራ ዊንፍሬይ ስለ ምስጋና ስትናገር እንደህ ነበር ያለችው ‹ካለ ምስጋና ያለፈ ህይወት የለኝም። ሁልጊዜም ባለኝና በሌለኝ ነገር አመሰግናለሁ እላለሁ። የአሁኑ የስኬቴ ምስጢርም ማመስገኔ ነው እላለሁ። ምስጋና ያለኝን የማቆይበት የሌለኝን ደግሞ የምስብበት ሀይሌ ሆኖ ሁሌም አብሮኝ አለ›። ብላለች፡፡
እኛ በብዙ ጭቆና በብዙ አፋኝ ስርዐት ውስጥ የኖርን ህዝቦች ነበርን። እውነት ናፍቃን አጎንብሰን ነበርን። አንድ የሀገር መሪ ከበታቹ ያሉትን ዝቅ ብሎ ሲያመሰግን እንደማየት ታላቅነት አለ ብዬ አላስብም። መሪዎች ሲያመሰግኑ አይተንም ሰምተንም አናውቅም። መሪ ሲቆጣና ሲቀጣ እንጂ ሲምርና ይቅርታ ሲያደርግ አናውቅም። ብርቃችን ነበር። ምክንያቱም ንጉስ ሲቆጣ ነዋ የምናውቀው።
ለውጥ ከማመስገን ይቅር ከማለት የሚጀምር ነው። በየትኛውም የእውቀት መስክ መርምሩት ምስጋና የምርጥ ሰዎች፣ የምርጥ መሪዎች መገለጫ ነው። ምርጥ ሰዎች ይቅር ይላሉ፣ ይቅር እንዲሉም ነው የተፈጠሩት። ምርጥ ያልሆኑ ደግሞ እንዲበቀሉ ወደዚህ አለም መጥተዋል። በምስጋናችን ማጣታችንን እናባረው ። በይቅርታ አርነት እንውጣ፡፡
ጥላቻ የሞት መንደር፣ የክፋት ዋሻ ነው ምንም አይጠቅመንም። ከለመድነው እውነት መውጣት ይኖርብናል። እስካሁን በወቀሳ በትችት በእርግማን ኖረናል። በውሸት በአሉባልታ በማስመሰል ኖረናል። በመጥላት፣ በማንቋሸሽ፣ በመሳደብ በመናቅ ኖረናል ከመክሰር ባለፈ ያተረፍነው አንዳች ነገር ግን የለም፡፡
ለማይጠቅመን ነገር ለምን እንለፋለን? ወደሚጠቅመን ለምን አንሄድም? ነጋችንን ብሩህ ይሆን ዘንድ ፍቅር ያስፈልገናል። ፍቅር ሞት የሌለበት አለም ነው። ሀገር አመስጋኝ ትውልድ ትሻለች። ፍቅር ህልማችን የሚሰምርበት፣ ተስፋችን የተሰወረበት ቅዱስ ስፍራ ነው። ምስጋና ክብራችን የተቀመጠበት ቦታ ነው። ስለዚህም ከፍቅርና ከምስጋና በቀር ራሳችንንና ህልማችንን የትም ልንፈልገው አይገባም። በቻልነው ባልቻልነውም አቅማችን አመስጋኝ እንሁን፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 /2014