በወንጀል የተገኘ ገንዘብ/ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀል ምንድነው?

ይህ የወንጀል ዓይነት በእንግሊዘኛው ቋንቋ አገላለፅ “መኒ ላውንደሪንግ” ወይም ወደ አማርኛ በቀጥታ ስንመልሰው “ገንዘብን ማጠብ” የሚል ስያሜ አለው። ታዲያ ይህ ስያሜ ገንዘብ እንዴት ይታጠባል ወይም ለምን ይታጠባል የሚል ሃሳብን ማስነሳቱ አይቀሬ ነው። በዘርፉ የዳበረው የወንጀል ሥነ-ሕግ እንደሚገልፀው ገንዘብ የሚታጠበው ሲቆሽሽ ነው፤ ገንዘብ ቆሸሸ የሚባለው ደግሞ የወንጀል ፍሬ ሆኖ ሲገኝ ነው። ይህንን የወንጀል ፍሬ የሆነን ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ የተገኘ ንፁህ ገንዘብ እንዲመስል ለማድረግ የሚፈፀሙ ማናቸውም ሂደቶች ገንዘብን የማጠብ ተግባር ተደርገው ይወሰዳሉ።

የዚህ የወንጀል ድርጊት መከላከያ ሕግ ዋነኛ ዓላማ ሰዎች ከወንጀል ድርጊታቸው እንዳያተርፉ ለማድረግ ነው። ይህ ማለት ለምሳሌ አንድ የመንግሥት ባለስልጣን 1 ቢሊዮን ብር ዘርፎ እና ገንዘቡን በተለያየ መንገድ ለሰዎች አስተላልፎ ቢገኝ፤ ከዛም በሙስና ወንጀል ብቻ ቢከሰስ እና ጥፋተኛ ተብሎ ቢቀጣ ቅጣቱን ጨርሶ ሲወጣ ያልተወረሰውን እና በሌሎች ሰዎች ስም ያስቀመጠውን ገንዘቡ በነፃነት መጠቀም ይችላል። ይህ ማለት ደግሞ ግለሰቡ ከወንጀል ድርጊቱ አተረፈ እንደማለት ይሆናል። ነገር ግን ይህ ግለሰብ ከሙስና ወንጀል በተጨማሪ በመኒ-ላውንደሪንግ ወንጀል የሚከሰስ ከሆነ በሌላ ሰው ስም ጭምር የተገኘው ገንዘብ እንዲመለስ/እንዲወረስ ስለሚደረግ ከወንጀል ድርጊቱ እንዳያተርፍ ለመከላከል ያግዛል። ይህንን ዓላማውን ለማሳካት ግን በእውቀት እና በጥንቃቄ የሚመራ፤ ከፖለቲካ አስተሳሰብ ነፃ የሆነ ሕግ አስከባሪ እንደሚያስፈልገው ልብ ማለት ይገባል።

በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ለዚህ “መኒ-ላውንደሪንግ” ተብሎ ለሚጠራው ወንጀል የተሰጠው ትርጉም ቀጥተኛ የሆነ ድርጊቱን የሚገልፅ ትርጉም ሲሆን ይኸውም በወንጀል የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀል ተብሎ ይጠቀሳል። ይህ የወንጀል ዓይነት በሀገራችን ኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ጨምሮ በብዙ የሕግ-ሥርዓቶች ውስጥ ረጅም ዕድሜ የሌለው የወንጀል አይነት በመሆኑ በተለምዶ ማኅበራዊ ወንጀሎች እንደሚባሉት እንደ ስድብ፣ ዛቻ፣ እጅ እልፊት፣ ስም ማጥፋት…ወዘተ ወይም ደረቅ ወንጀሎች እንደሚባሉት እንደ ስርቆት፣ ውንብድና፣ ግድያ….ወዘተ በማኅበረሰቡ ውስጥ በበቂ ደረጃ የታወቀ የወንጀል ዓይነት አይደለም። ከዚህም የተነሳ ይህንን የወንጀል ድርጊትን የሚያቋቁሙ ድርጊቶችን ካለማወቅ በመፈፀም ብዙ ሰዎች ተጠርጣሪ ሆነው ፍርድ-ቤት ሲቀርቡ ይስተዋላል።

በመሆኑም በወፍ በረር ዕይታ የተወሰኑ ግንዛቤዎችን ለመፍጠር በማሰብ በኢዲስ ዘመን ጋዜጣ ይታተም ዘንድ ይህንን አነስተኛ ፅሑፍ አቅርቤያለሁ።

ይህ የወንጀል ድርጊት መነሻው ለገንዘብ ተብሎ የሚፈፀም ሌላ ወንጀል ሲሆን ይህ የመጀመሪያው ወንጀል አመንጪ ወንጀል ተብሎ ይጠራል። ስሙ እንደሚያመላክተው አመንጪ ማለት የቆሸሸውን ገንዘብ ያመነጨው ወንጀል ማለት ነው። ከባድ ስርቆት፣ ውንብድና፣ ሙስና፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የጦር መሳሪያ ንግድ፣ የግብር ስወራ/ማጭበርበር ዋና ዋናዎቹ አመንጪ ወንጀሎች የሚባሉ ሲሆን እነዚህን አመንጪ ወንጀሎችን በመለየት ረገድ ሀገራት የተለያየ መስፈርቶችን ይጠቀማሉ። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ የምትከተለውን መስፈርት ከስር እንመለከታለን።

ታዲያ አንድ አመንጪ ወንጀልን በመፈፀም ገንዘብ ወይም ንብረት የያዘ ሰው ከዚህ አመንጪ ወንጀል የተገኘውን ገንዘብ የት ላስቀምጠው፣ እንዴት ልደብቀው፣ እንዴት አድርጌ ሕጋዊ አስመስዬ ላቅርበው፣ እንዴት አድርጌ ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ ላስገባው..ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎችን ለመመለስ ሲል የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ በዚህ ወንጀል ውስጥ ያርፋሉ። በሕጉ አነጋገር ይህንን የቆሸሸ ገንዘብ ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ውስጥ ለማስገባት የሚደረጉ ጥረቶች በሦስት ደረጃዎች የሚታወቁ ሲሆን በእንግሊዘኛው “Placement, layering and Integration” በጥሬው ሲተረጎም አቀማመጥ፣ ማጠጋጋት እና ማዋሃድ ይሰኛሉ። በእነዚህ ሦስት ደረጃዎች ውስጥ ያሉ ተግባሮች ሁሉ ወንጀሉን ያቋቁማሉ።

ለምሳሌ ያክል አንድ ሰው አንድ ሚሊዮን ብር ጉቦ ተቀብሎ ይህንን ገንዘብ ወደ ሶስት ሰዎች በመበታተን በባንክ ቢያሰራጨው ወይም በገንዘቡ ንብረት ቢገዛበት ወይም ሎተሪ ከደረሰው ሰው ሎተሪውን ገዝቶ ሎተሪ ደረሰኝ በማለት ለማሳሳት ቢሞክር …ወዘተ እና በወንጀል ምርመራ ቢደረስበት 1ኛ ክስ በሙስና ወንጀል 2ኛ ክስ በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ለማቅረብ መሞከር ወይም ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀሎች መጠየቁ አይቀሬ ነው። እንዲህ አይነቶቹ ድርጊቶች ሁሉ ወንጀሉን ያቋቁማሉ።

ታዲያ አንድ ወንጀለኛ ወንጀል የሚፈፅመው በገንዘቡ ሊጠቀምበት አይደለም ወይ? በወንጀል ፍሬው በመጠቀሙ ሁለተኛ ወንጀል ማቋቋም ለአንድ ዓላማ ለተፈፀመ ድርጊት በድጋሚ መቅጣት አይሆንም ወይ? የሚሉ እና ሌሎች የሥነ-ሕግ ጥያቄዎች በዚህ ወንጀል ዙሪያ የሚነሱ ሲሆን በሌሎች ክፍሎች የምናያቸው ይሆናል። አሁን በቀጥታ ይህንን ጉዳይ ስለሚመለከቱ ሕጎች እና በዚህ ወንጀል ተሳታፊ መሆን እስከምን ድረስ ነው የሚለውን እንመልከት።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህ ወንጀል ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና የተሰጠው እ.ኤ.አ በ1988 በተደረገው የቬይና ኮንቬንሽን ሲሆን ወንጀሉ የተጠቀሰውም ከአደገኛ እፅ ዝውውር ወንጀል ጋር ተያይዞ ከወንጀል ድርጊቱ ከፍተኛ ሀብት የሚያጋብሱትን ሰዎች ለመቆጣጠር በማሰብ ነበር። በዚሁ ስምምነት መሰረት ከአደገኛ እፅ ዝውውር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት መሆኑን እያወቁ ይህንን ንብረት የመያዝ፣ የመጠበቅ፣ የማስተላለፍ እና መሰል ድርጊቶች እንደ መኒ-ላውንደሪንግ ወንጀል ተቆጥረዋል። ከዚህ በመቀጠል የወጡት የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዓለም ዓቀፍ ስምምነት (እ.ኤ.አ 2003) እና ሙስናን ለመዋጋት የተደረጉ ዓለም ዓቀፍ ስምምነት (እ.ኤ.አ 2005) በተከታታይ የዚህን ወንጀል አመንጪ ወንጀሎችን በማስፋት ሕጉ እንዲያድግ እና ዛሬ የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ አድርገዋል።

ይህ ወንጀል በሀገራችን የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በግልፅ ወንጀል ነው ተብሎ የተደነገገው በ1996 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ ሲሆን የ1949 ወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ እንዲሻሻል ምክንያት ከነበሩት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነበር። ሆኖም ለጉዳዩ በተናጠል አዋጅ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል በሚል ጉዳዩን ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ከሚል ሌላ የሕግ ጉዳይ ጋር በማያያዝ ሁለቱን ጉዳዮች ብቻ በአንድ ላይ አጠቃሎ የያዘ አዋጅ ቁጥር 657/2002 እንዲወጣ ተደርጓል። በኋላም ይህንኑ አዋጅ ማሻሻል በማስፈለጉ ለረጅም ጊዜ በሥራ ላይ የነበረውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 በማውጣት አዋጅ ቁጥር 657/2002 እንዲሻር ተደርጓል። አሁን በቅርቡ ደግሞ ይህ አዋጅ ተሽሮ በተለይም ከወንጀል ምርመራ ጋር ተያይዞ ለመርማሪዎች በሰጠው ስልጣን ሲተች የነበረውና ይህ አንቀፅ እንዲሻር የተደረገበት አዲስ አዋጅ መውጣቱ የሚታወቅ ነው። ስለዚህ አዲስ አዋጅ ዝርዝር ይዘት በቀጥይ ፅሑፍ እንመጣበታለን።

ለዚህ ፅሑፍ መፃፍ ዋና ምክንያት ወደ ሆነው ጉዳይ ስንመለስ ዋናውን ወንጀል ሆን ብለው ከሚፈፅሙ ሰዎች ውጭ ያሉ ሌሎች ሰዎች በተባባሪነት እንዳይጠየቁ ሊያደርጓቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች ምን ምን ናቸው የሚለውን ጉዳይ ከብዙ በጥቂቱ መመልከት ጠቃሚ ነው።

1ኛ. የወንጀል ፍሬ የሆነን ገንዘብ ከዋናው ወንጀለኛ ጋር በመሆን መጠቀም ተጠያቂ ያደርጋል። አንድ ሰው መኪና ገዝቶ ቢሰጣችሁ ያንን ለማድረግ የሚያስችል መደበኛ ገቢ እንዳለው ማወቅ ይጠበቅባችኋል። ይህንን ሳታደርጉ ቀርታችሁ መኪናውን ገዝቶ የሰጣችሁ ሰው በዚህ ወንጀል የሚጠየቅ ከሆነ የተቀበለው ሰውም ተጠያቂ ይሆናል። ስጦታው የተሰጠው በትክክል ለተቀባዩ እስከመጨረሻው እንዲወስደው ወይም ስመ-ንብረቱ ብቻ በተቀባዩ ሆኖ ስጦታ ተቀባዩ እንዲጠቀምበት ቢሆንም በሁለቱም መንገድ አስቀጪ ነው። ይህ ለመኪና ብቻ ሳይሆን ለቤት ወይም ለሌሎች ተንቀሳቃሽ ንብረቶችም የሚሠራ ይሆናል። የዚህ ወንጀል ዋና ዓላማ አብሮ መብላት፣ ስጦታ መሰጣጣት፣ ወይም መረዳዳት መልካም ባሕላችን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ከወንጀል ፍሬ ከሆነ ገንዘብ እንዳይፈፅሙ ማድረግ ነው። በሕብረተሰብ መካከል ያልተገባ አለመተማመንን እንዳይፈጥር መመዘኛው ማወቅ ወይም ምክንያታዊ ጥርጣሬ አለማድረግ ነው።

2ኛ. ሌላው እና አሁን ላይ ብዙ ሰዎች እየተጠየቁ ያሉበት መንገድ የባንክ ሂሳብ አካውንትን ለገንዘብ ማስቀመጫ/ማስተላለፊያ መጠቀም ነው። ከወንጀል ፍሬ የሆነ ገንዘብ ወደ ሂሳብ አካውንታችሁ ከገባ “ገንዘብን መከተል” በሚባለው የወንጀል ምርመራ ዘዴ ስለሚደረስበት ተጠርጣችሁ መመርመራችሁ

አይቀሬ ነው። ታዲያ አካውንታችሁን ለሰዎች ገንዘብ እንዲያስቀምጡበት/እንዲያስተላልፉበት ስትፈቅዱ ይህንን የሚያደርጉትን ሰዎች እና የገንዘቡን ምንጭ በትክክል ማወቅ ይጠበቅባችኋል።

3ኛ. ነጋዴ ከሆናችሁ ደግሞ በመደበኛ ግብይት ጊዜ ገንዘቡን ላስገባላችሁ ሰው በስሙ ደረሰኝ መቁረጥ ሌላው የጥንቃቄ እርምጃ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደረሰኙ የተፃፈለት ሰው እና ገንዘቡን የሚያስገባው ሰው ይለያያል። ታዲያ ይህ የገባው ገንዘብ በአጋጣሚ የወንጀል ፍሬ-ሆኖ ቢገኝ እና ለጥያቄ ብትጠሩ ገንዘቡ በግብይት ያገኘሁት ገንዘብ ነው ስትሉ አስረጂ አድርጋችሁ የምታቀርቡት ደረሰኝ ነው። ደረሰኙ ላይ ያለው ስም እና ገንዘቡን ያስገባው ስም የተለያየ በሆነ ጊዜ የደረሰኙ የአስረጅነት ኃይል ጥርጣሬ ውስጥ መውደቅ አይቀሬ ነው። በእርግጥ ነጋዴዎች ይህንን ለማስታረቅ ፈታኝ እንደሚሆንባቸው እና ደረሰኙ የሚፃፍለትን ሰው ስም የሚመርጠው ገዥ መሆኑን ከተለያዩ ጉዳዮች ፀሐፊው ለመገንዘብ ሞክሯል። ይህንን ችግር ለማጥበብ ታዲያ በተቻለ አቅም አንድም ደረሰኝ መፃፍ የምትችሉት ገንዘቡን ባስገባው ሰው ስም እንደሆነ ለገዥው ብትገልፁ ይህ ካልተቻለ ደግሞ ገዥው ደረሰኙ በሌላው ሰው ስም እንዲቆረጥ መፈለጉን በተናጠል ወረቀት ብታስፈርሙት ተጨማሪ ማስረጃ ሆኖ የሚያግዛችሁ ይሆናል።

ይቀጥላል……..

ይግረማቸው ከፈለኝ ወግደረስ (LLB, LLM) (ጠበቃ፣ የሕግ አማካሪ እና በወንጀል ፍትህ አስተዳደር አሰልጣኝ)

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You