ቴክኖሎጂ እያንዳንዱን የዓለም እንቅስቃሴ እየተቆጣጠረ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገትን ከቴክኖሎጂው ዘርፍ እድገት ውጭ ማሰብ የሚቻል አይሆንም። ዛሬ በምጣኔ ሀብታቸው የዓለማችን ቁንጮ የሆኑት ልዕለ ኃያላን ሀገራት የቴክኖሎጂ ዘርፋቸው እጅግ የተራቀቀ ነው። እነዚህ ሀገራት አሁን ያሉበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ የደረሱት ዘርፉ በየጊዜው እድገትንና መሻሻሎችን እንዲስመዘግብ ባከናወኗቸው ተግባራት ነው።
ጀማሪ ለነበሩት የቴክኖሎጂ ተቋሞቻቸው ያደረጓቸው ልዩ ልዩ የሕግና የፋይናንስ ድጋፎችና ማበረታቻዎች ተቋማቱ አሁን ያሉበት ደረጃ እንዲደርሱ አግዟቸዋል። ሀገራቱ በቴክኖሎጂ ተቋሞቻቸው መካከል የልምድ ልውውጥ እንዲኖርና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር በማድረግ ጀማሪዎቹ ከትልልቆቹ እንዲማሩና አቅማቸውን አጎልብተው በሀገራቱ እድገት ላይ ትልቅ አሻራ እንዲኖራቸውና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አድርገዋል።
ትልልቅ የቴክኖሎጂ ኤክስፖዎች በቴክኖሎጂ ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት በማዳበር ለጀማሬ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥና የገበያ ትስስር አቅም ማደግ ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው። መሰል የቴክኖሎጂ ኹነቶች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከማስተዋወቅ ጀምሮ የዘርፉን ተዋንያን በገበያና በፈጠራ በማስተሳሰር የተሻሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እውን እንዲሆኑም ያግዛሉ።
ይህንኑ ዓላማ ያነገበው የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ (African Tech Expo 2022)፣ ከጳጉሜ ሁለት ቀን 2014 ዓ.ም አንስቶ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ስካይትላይት ሆቴል ይካሄዳል። ኤክስፖው በኢትዮጵያ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፤ ከመላው ዓለም የሚመጡ ከ250 በላይ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።
የዘንድሮው የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ በጆርካ ኤቨንትስ (Jorka Event Organizers PLC) እና በኤ.ቲ.ኤክስ (ATX) ትብብር የሚዘጋጅ ሲሆን በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የዘርፉ ተዋንያን ይሳተፉበታል። የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችንና ፖሊሲ አውጭዎችን ጨምሮ ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በሚሳተፉበት በዚህ ኤክስፖ ላይ፤ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ፣ የዲጂታል የክፍያ ስርዓት፣ የቴሌኮሙኒኬሽን እና የፋይናንስ ቴክኖሎጂዎች ዐቢይ ትኩረት የሚደረግባቸው ዘርፎች ይሆናሉ።
በኤክስፖው የሚሳተፉ አካላት የተሰማሩባቸው የምርትና አገልግሎት ዘርፎች በርካታ ሲሆኑ ዋና ዋናዎቹም ፡-
* የሮቦቲክስ
* የብሎክቼይን
* የሳይበር ደህንነት
* የባዮቴክኖሎጂ
* የደህንነትና ስለላ
* የባንክ
* የፀሐይ ኃይል
* የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች
* የማኅበራዊ ሚዲያ
* የኮምፒዩተር እቃዎች
* የቤት ውስጥ መገልገያዎች
* ሞባይልና ኤሌክትሮኒክስ
* የኢንተርኔት
* የመድኃኒት
* የግብርና ማሽኖች
* የግንባታ እቃዎች
* የተሸከርካሪዎች
* የፕላስቲክ
* የሆቴል እቃዎች
* የኢንዱስትሪ ቁሳቁስ … ቴክኖሎጂዎች ናቸው።
የአፍሪካ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ትልልቅ ኩባንያዎችም ይሳተፉበታል። ከእነዚህ ትልልቅ ኩባንያዎች መካከል ‹‹ማይክሮሶፍት›› (Microsoft)፣ ‹‹ሜታ›› (Meta)፣ ‹‹አማዞን››፣ (Amazon)፣ ‹‹ጁሚያ›› (Jumia)፣ ‹‹ኦራክል›› (Oracle)፣ ‹‹ቻይና ዩኒኮም›› (China Unicom)፣ ‹‹አክሰስ›› (Access) እና ሌሎችም ስመ ጥር ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት ይጠቀሳሉ።
የእነዚህ ተቋማት ተሳትፎ በራሱ ብዙ ፋይዳዎች አሉት። ተቋማቱ በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸው በመሆኑ ተሳትፏቸው ሌሎች አካላት፣ በተለይም ጀማሪ የቴክኖሎጂ ተቋማት፣ ልምድ እንዲቀስሙ የማድረግ እድል ይፈጥራል። የሥራ ትስስር በመፍጠርም ጀማሪዎቹ ከትልልቆቹ ልዩ ልዩ ድጋፎችን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
የቴክኖሎጂ ኤክስፖው አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማስተዋወቅም እድል ይፈጥራል። ይህም የኤክስፖው ተሳታፊዎች በሚያተኩሩባቸው ዘርፎች (ኤሌክትሮኒክስ፣ ሮቦቲክስ፣ ፋይናንስ፣ ኢንተርኔት፣ ኮምፒዩተር …) ያሉና ዘመኑ የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማወቅና በቴክኖሎጂዎቹ ላይ ተመስርቶ ስራን ለማቀድ ያግዛል።
ኤክስፖው ለቴክኖሎጂ ተቋማቱ፣ ለተጠቃሚው፣ ለፖሊሲ አውጪዎች እና ለሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ ይጠበቃል። የቴክኖሎጂ ተቋማት ምርቶቻቸውና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ እንዲሁም ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር የሥራ ትስስርና የልምድ ልውውጥ ለመፍጠርም ያግዛቸዋል። ተጠቃሚዎች በበኩላቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማወቅና የምርቶቹ ተጠቃሚ ለመሆን ያስችላቸዋል፤ከዚህ በተጨማሪም ከተቋማቱ ጋር ግንኙነት ለመመስረት ይረዳቸዋል። ፖሊሲ አውጪዎች ደግሞ የዘርፉን አጠቃላይ ቁመና ለመገንዘብ፣ ክፍተቶችን ለመለየትና ዘርፉን በብቃት ለመምራት የሚያስችሉ ሕጎችን ለመቅረፅ ግብዓቶችን ለመሰብሰብ ይጠቀሙበታል።
የጆርካ ኤቨንትስ ማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽንስ ኃላፊ አቶ ሳምሶን ኃይለኢየሱስ ኤክስፖው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ተናግረዋል። እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ከኤክስፖው ዓላማዎች መካከል አንዱ የአፍሪካን የቴክኖሎጂ ገበያ ለኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችና አምራቾች ማስተዋወቅና መክፈት ነው። ኤክስፖው የሚፈጥረው የስራ ግንኙነትና ትውውቅ የገበያ ትስስር እንዲጎለብት ያደርጋል። ይህ የገበያ ትስስር ደግሞ ለአገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገትና ለዘርፉ ማደግ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለመገንባትም ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራል። ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ትልልቅ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በኤክስፖው ስለሚሳተፉ የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ ለማሳየት እድል ይፈጥራል። ይህም ጎብኚዎችም ሆኑ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በማበረታታት ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ጥቅሞችን ያስገኛል።
ኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን ለማድረግም ኤክስፖው ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። የኢንቨስትመንት ተግባራት በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው የቴክኖሎጂው ዘርፍ እድገት በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ አለው። ኤክስፖው የቴክኖሎጂው ዘርፍ የሚተዋወቅበት በመሆኑ የኢንቨስትመንት ስራዎችን በቴክኖሎጂ ውጤቶች በመደገፍ የኢንቨስትመንት ውጤታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
የቴክኖሎጂ ኤክስፖው በዘርፉ ልምድ ያላቸው ትልልቅ ኩባንያዎች ለጀማሪዎቹ ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት በመሆኑ ጀማሪ ባለሙያዎችም አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ እድል ይፈጥርላቸዋል። ስለሆነም ጀማሪ የቴክኖሎጂ ተቋማት (Startup Businesses) በኤክስፖው ተሳታፊ እንዲሆኑ እንደሚደረግ አቶ ሳምሶን ተናግረዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የቴክኖሎጂ እድገትና ሽግግር ለዘላቂ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት እጅግ አስፈላጊ ግብዓት መሆኑን ጠቁመው፤ ኤክስፖው ለቴክኖሎጂ ሽግግርና ለልምድ ልውውጥ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስታውቀዋል።
እንደአምባሳደር ዲና ማብራሪያ፣ የኢንቨስትመንት ተግባራት ቴክኖሎጂን መሰረት በማድረግ የሚከናወኑ በመሆናቸው ኤክስፖው በዘርፉ ከሚያስገኘው የኢንቨስትመንት ፍሰት በተጨማሪ ሌሎች የኢንቨስትመንት ተግባራትም ውጤታማና ቀልጣፋ እንዲሆኑ እገዛ ይኖረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ኤክስፖው ለሀገር ገጽታ ግንባታም አወንታዊ ሚና ይኖረዋል።
በኤክስፖው ላይ የፖሊሲ አውጪዎችም ተሳታፊ ስለሚሆኑ ለቴክኖሎጂው ዘርፍ እድገት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ሕጋዊ አሰራሮችን ለመዘርጋት ለሚደረገው ጥረት ግብዓት ለመሰብሰብ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል። የቴክኖሎጂው ዘርፍ የዘርፉን ተለዋዋጭነት ከግምት ውስጥ ባስገቡ ግልጽ ሕጋዊ ማዕቀፎች ካልታገዘ እድገቱን መምራትና ማስተዳደር ስለማይቻል የፖሊሲ አውጪዎች በኤክስፖው ላይ መሳተፋቸው የዘርፉን አስተዳደር በሰለጠነ ሕጋዊ አሰራር ለመምራት ለሚደረገው ጥረት ቀላል የማይባል ሚና ይኖረዋል።
በኹነቱ የሚስተናገዱ ሲምፖዚየሞችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ያሉበትን ደረጃ ለመገምገምና በአፍሪካ አህጉር በዘርፉ ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለመቃኘት እንደሚያስችሉ ተነግሯል። ከዚህ በተጨማሪም ሲምፖዚየሞቹ ስለቴክኖሎጂ ፖሊሲ ጉዳዮች ሰፋ ያለ ግንዛቤ የሚፈጠርባቸው መድረኮች እንደሚሆኑም አዘጋጆቹ ገልፀዋል። የመንግሥትንና የግሉን ዘርፍ ትብብር ማሳደግና የቴክኖሎጂውን ዘርፍ በፋይናንስ መደገፍ ስለሚቻልበት ሁኔታ እንዲሁም በየአካባቢው ያሉ መልካም ተሞክሮዎችን በአፍሪካ ብሎም በመላው ዓለም በማስፋት በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተረጋጋ የስራ ሁኔታ (Better Business Certainty) እና አዳዲስ እድሎችን ለመፍጠር ምክክር ይደረጋል።
በኤክስፖው ጀማሪ ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ከትልልቆቹ የቴክኖሎጂ ተቋማት ልምድ እንደሚቀስሙ ይጠበቃል። የቴክኖሎጂውን ዘርፍ በማሳደግ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገት ለማስመዝገብ እነዚህን ጀማሪ ባለሙያዎች መደገፍ ያስፈልጋል።
አዲሱ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲም ጀማሪ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች አቅማቸውን እንዲገነቡ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ማዕቀፍ ሆኖ ተዘጋጅቷል። ጀማሪ ተቋማት እና የኢኖቬሽን ሥርዓተ-ምህዳር ገንቢዎች (STI Incubation Centers) የፋይናንስ፣ የቴክኒክ፣ የመስሪያ ቦታ እና መሰል ድጋፎችን የሚያገኙበት፤ ለጀማሪ ተቋማት (Technology Startups) የገበያ ዋጋ ትመና እና የኢንቨስትመንት እድል የሚፈጠርበት፤ ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት ባላቸው የቴክኖሎጂ መስኮች የግልና የመንግስት አጋርነት የሚኖርበት፤ በጥናት ላይ የተመሠረተ የእሴት ሰንሰለት እና የኢኖቬሽን ክላስተሪንግ ስርዓት የሚስፋፋበት እንዲሁም ውጤታማነታቸው የተረጋገጠና ወደ ምርትና አገልግሎት የተቀየሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚያበረታታ የግዥ ሥርዓት የሚዘረጋበት የአሰራር ስርዓት እንዲኖር እንደሚደረግ በፖሊሲው ላይ ተጠቅሷል።
የቴክኖሎጂ አቅም ክምችትንና የዕውቀት ሽግግሩን ለማሳለጥ ሀገርን ምርታማና ተወዳዳሪ ለሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ እንዲሁም የሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀምና ለማሳደግ የሚያስችል ስርዓት እንደሚዘረጋ በፖሊሲው ላይ ተመላክቷል። የኢኖቬሽን ሥነ-ምህዳር በመፍጠርና የሃገሪቱን የኢኖቬሽን አቅም በማዳበር ኢኖቬሽንን በሰፊው ለልማትና ሰፊ የሥራ ዕድሎችንና ሀብቶችን ሊፈጥር በሚችል መልኩ፣ በሀገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ በርካታ ኢንተርፕራይዞችን ለመፍጠር እንደሚሰራም ተገልጿል።
ታዲያ የጀማሪ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ ያስችላሉ ተብለው በፖሊሲው ላይ የተጠቀሱትን ግብዓቶች በተግባር ለመተርጎም እንዲህ ዓይነት መድረኮች የሚያስገኟቸውን መልካም አጋጣሚዎችን በሚገባ መጠቀም ይገባል።
ከአስር ዓመቱ ሀገራዊ የልማት እቅድ ስትራቴጂካዊ ምሰሶዎች (Strategic Pillars) መካከል አንዱ የቴክኖሎጂ አቅም እና ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት ነው። ይህን ለማሳካት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ውጤታማነት ማሳደግ ወሳኝ ግብዓት እንደሆነ ይታወቃል። የዘርፉን ውጤታማነት ለማጎልበት ከሚተገበሩ አቅጣጫዎች መካከል ጀማሪ የስራ ፈጣሪዎችንና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ሃሳባቸውን ወደ ቢዝነስ ተግባራት የሚያሸጋግሩባቸውን እድሎችን መፍጠር ተጠቃሽ ተግባር ነው። የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ለዚህ ተግባር ስኬት ቀላል የማይባል አስተዋኦ ይኖረዋል። ስለሆነም ኤክስፖው የሀገር መልካም ገጽታን በመገንባት፣ የልምድ ልውውጥና የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስተዋወቅ ረገድ ያስገኛቸዋል ተብለው የሚጠበቁትን እድሎች ሁሉ መጠቀም ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 10 /2014