በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ አገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ዋንጫ ለመሳተፍ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ ጋር ለሚጠብቀው የደርሶ መልስ ጨዋታ ዝግጅቱን ከቀናት በፊት ጀምሯል።
ደቡብ ሱዳንን በድምር ውጤት 5-0 አሸንፎ የመጨረሻውን ዙር ማጣሪያ የተቀላቀለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፈው ሐሙስ ተሰባስቧል። በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጥሪ ከቀረበላቸው ተጫዋቾች መካከል ሱራፌል ዳኛቸው በጉዳት ምክንያት በወንድማገኝ ኃይሉ የተተካ ሲሆን ሙሉ ቡድኑ ሐሙስ እለት በጁፒተር ሆቴል ተሰባስቦ የጂምናዚየም ስራዎችን ከከወነ በኋላ አርብ እለት ወደ አዳማ ተጉዞ በአዳማ ኤክስኪዩቲቭ ሆቴል ማረፊያውን በማድረግ በእለቱ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከ10:30 ጀምሮ የመጀመሪያ ልምምድ አከናውኗል።
የፊታችን ነሐሴ 20 እና 29 የደርሶ መልስ ጨዋታውን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልምምዱን በአዳማ በመቀጠል ነሐሴ 18 የሜዳ ጨዋታውን ወደሚያደርግበት ታንዛንያ እንደሚያመራ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያደርገው የማጣሪያ ጨዋታ የሚከናወንበት ቀናት እና ቦታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ይፋ መደረጉ ይታወቃል። በዚህም በመጀመሪያው ጨዋታ ዋልያዎቹ ባለሜዳ ሆነው ነሐሴ 20/2014 ታንዛንያ ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ላይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። የመልሱን ጨዋታ ደግሞ ነሐሴ 29/2014 ሩዋንዳ ላይ እንደሚደረግ የወጣው መርሐ ግብር ያሳያል።
በአገር ውስጥ ሊጎች በሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ በካፍ አዘጋጅነት በየሁለት አመቱ የሚደረገው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የማጣሪያ ጨዋታዎች ከነሀሴ ወር መጀመሪያ አንስቶ እየተከናወኑ ይገኛሉ። በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታው ከደቡብ ሱዳን ጋር የተደለደለችው የኢትዮጵያ ስቴድየሞች የካፍን መመዘኛ መስፈርት አለማሟላታቸውን ተከትሎ በተጣለው ዕገዳ ልክ እንደ አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎቿ ሁሉ ይህንንም ጨዋታ ከሜዳዋ ውጪ ታንዛኒያ ላይ ለማድረግ ተገዳለች።
የመጨረሻውን የማጣሪያ ጨዋታም ኢትዮጵያ እና ተጋጣሚዋ ሩዋንዳ የካፍን መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም የሌላቸው መሆኑን ተከትሎ እገዳ ላይ ቢገኙም ሩዋንዳ ቀናት በፊት አንድ ስቴድየሟ ጨዋታ እንዲያስተናግድ ፍቃድ ማግኘቱ ታውቋል። ይህንን ተከትሎ ሩዋንዳ ነሐሴ 29 የሚደረገውን የመልስ ጨዋታ በሁዬ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደምታስተናግድ ይፋ ተደርጓል። ኢትዮጵያ ግን አሁንም ስቴድየሞቿ ፍቃድ ስላላገኙ ከሩዋንዳ ጋር ነሐሴ 20 የሚደረገውን የመጀመሪያ ጨዋታ በታንዛኒያ ዳሬሰላም ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም እንደምታደርግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል።
በአፍሪካ ከዋናው አፍሪካ ዋንጫ ቀጥሎ ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ የሆነው የቻን ዋንጫ በአገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ብቻ ለማበረታታት በካፍ አማካኝነት እኤአ በ2007 የተዋወቀ ሲሆን 2009 ላይ በኮትዲቯር አዘጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ ተካሂዷል። ከጊዜ ወደ ጊዜ በውድድሩ የሚሳተፉ አገራት ቁጥርም እያደገ ሄዶ ትኩረት ከሚሰጣቸው የስፖርት መድረኮች አንዱ ሆኗል። የአለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ፊፋም እኤአ 2010 ላይ ለዚህ ውድድር እውቅና ሰጥቶታል።
ኢትዮጵያ ከሰላሳ አንድ አመታት በኋላ እኤአ 2013 ላይ በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፏን ተከትሎ በእግር ኳሱ የተፈጠረው ከፍተኛ መነቃቃት ይታወሳል። የዚያ ትውልድ ታሪካዊ ተጫዋቾችና የዋልያዎቹ አሰልጣኝ የነበሩት ሰውነት ቢሻው ከአፍሪካ ዋንጫው ማግስት በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተካሄደው የቻን ዋንጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፍ ችለዋል። ለዚህ ተሳትፎም የመጨረሻውን የማጣሪያ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር ከሜዳቸው ውጪ ተፋልመው ማለፋቸው አይዘነጋም።
በተለይም በዚያ የመጨረሻ የማጣሪያ ፍልሚያ የዋልያዎቹ ቋሚ ግብ ጠባቂ የነበረው ጀማል ጣሰው ጨዋታው በመለያ ምት እንደሚጠናቀቅ ከአሰልጣኙ ጋር ቀደም ብለው በመግባባት የመለያ ምት የማዳን የተሻለ ብቃት ያለው ግብ ጠባቂ ሲሳይ ባንጫ ተቀይሮ እንዲገባ ማድረጋቸው አይዘነጋም። ሲሳይ ባንጫም ተቀይሮ ገብቶ ሁለት የመለያ ምቶችን በማዳን ዋልያዎቹን ለቻን ዋንጫ ያበቃበት ክስተት የሚታወስ ነው።
ዋልያዎቹ በቀጣዩ የቻን ውድድርም በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እየተመሩ በጋቦን በተካሄደው ዋንጫ ላይ መሳተፍ ችለዋል። በሁለቱም ብቸኛ ተሳትፏቸው ግን ከምድባቸው ሳያልፉ ቀርተዋል። ዘንድሮም በመጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታ በአሰልጣኝ ውበቱ እየተመሩ ለሶስተኛ ጊዜ ለመሳተፍ የሩዋንዳን ፈተና ለማለፍ ተዘጋጅተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 9/2014