የተከበሩ አቶ አገኘው ተሻገር፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፤
ክቡራን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች፣ ክቡራን እንግዶች፣ እንኳን ለዚህ ዛሬ እያየን ላለነው ድል አበቃን፤ እንኳን ደስ ያላችሁ፤ እንኳን ደስ ያለን ማለት እፈልጋለሁ፡፡
በያዝነው በ2014 ዓ.ም በለስ ቀንቶናል፤ ታግለን ሰርተን ውጤት አግኝተናል፡፡ በተለይ በስፖርቱ ቀደም ሲል ከነበረ ችግር ወጥቶ፣ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወደዚህ በስፖርቱ አካባቢ የመዳከም ሁኔታዎች ሲታዩ የነበረበትና ህዝቡ ትንሽ ያዘነበት፤ በተለይ በቶኪዮ 2020 ያዘነበትን እናስታውሳለን፡፡ ከዛ አንሰራርቶ ዛሬ አንጸባራቂ የሆኑ ድሎች እየተገኙ እንደሆነ ሁላችንም እየተከታተልን ነው፡፡
በዚህ ዓመት እ.አ.አ ከማርች 18 እስከ 20 በነበረው የሰርቢያ ቤልግሬድ የቤት ውስጥ ውድድር ብዙ ያልተነገረለት፤ ግን ከዓለም አንደኛ የሆንንበት፣ አትሌቶቻችን “ታላቋ” የምትባለውን አሜሪካን አሸንፈው በአንደኝነት የገቡበት ድል ነበር፡፡ በዛ ውድድር ዘጠኝ ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል፡፡ በመቀጠል እአአ ከጁላይ 15 እስከ 24 በነበረው በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ድል ስንከታተለውና ስናከብረው የከረምነው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡ ፡ እናም ኢትዮጵያ ገጽታዋ ከፍ ያለበት፤ የኢትዮጵያ ህዝብም የኮራባቸውን ትልቅ ድል አትሌቶቻችን አስገኝተውልናል፡፡
አሁን ደግሞ በመቀጠል በእናንተ በአፍላ ወጣቶች፣ በጥሩ እድሜ ላይ ያሉና ገና ሮጠው ባልጠገቡ አትሌቶቻችን በኮሎምቢያው ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 12 ሜዳልያዎችን በማስገኘት ከዓለም ሶስተኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ አንደኛ ሆነው እንደዚህ በድል ሲገቡ ቀደምት አትሌቶች አንጋፋዎቻቸውን ፈለግ ተከትለው ድሉን በማስቀጠላቸው እንኳን ደስ ያለን፤ እንኳን ደስ ያላችሁ፤ እነዚህን ልጆች በደማቅ ጭብጨባ አመስግኑልኝ፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫ መስኮች አንዱ ብቁና ንቁ ዜጋ፣ አሸናፊ ዜጋን ማፍራት ነው፡፡ እናንተም እንኳን አሸነፋችሁ፡፡ ዓላማውም ብቁ እንድትሆኑ፣ ብቁ እንድንሆን ነበርና፤ እንኳን ለዚህ በቃችሁ፤ እንኳን ለዚህ አበቃችሁን፡፡ እንኳንም ለድል በቃን፤ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡
ሌላው የባህልና ስፖርት ግብ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ነው፡፡ እነዚህ ዛሬ በድል የገቡት ልጆች ተተኪ አትሌቶች ናቸው፡፡ ተተኪ አትሌቶችን መፍጠር ነው ስራችን፤ እናንተም እንኳን ተተኪ ሆናችሁ ተፈጠራችሁ፡፡ ለወደፊቱም በቀጣይ ላሉት አህጉራዊና ዓለማቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያን ወክላችሁ፤ በተለይም ከሁለት ዓመት በኋላ ዛሬ አፍላ ወጣቶች ያልኳቸው ነገ ደግሞ ከሌሎች ወጣቶችም ጋር በእድሜና በደረጃቸው ፈረንሳይ ፓሪስ በሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ እንደምትሳተፉ ከወዲሁ እተማመንባችኋለሁ፤ እንተማመንባችኋለንም፡፡ ስለዚህ የዛሬ ድላችሁ የነገ ስንቃችሁ ነውና ጥረታችሁን ቀጥሉ ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ለምንድን ነው ይሄንን ሁሉ ድል ማግኘት የቻልነው ብለን ካልን፤ የአመራር፣ የአሰራር፣ በተለይ ደግሞ በስፖርቱ አካባቢ ሰላም ማስፈን በመቻሉ ነው፡፡ ስፖርቱን የሚያውኩ አየሮች አሉ፤ ስፖርቱን የሚረብሹ አካሄዶችን ቀስ ብለን እያስወገድን በመስራታችንና በስፖርቱ ጎራ በተለይ በአትሌቲክሱ ጎራ የተረጋጋ ስራ በመሰራቱ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄንን ስፖርት ለመደገፍ፣ ለማጠናከር በገንዘብም፣ በሞራልም በሃሳብም የሚደግፉትን በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ከሩቅም ከቅርብም ሆነው ደግሞ መረበሽ የሚፈልጉትን ተሰብሰቡ፤ ተቆጠቡ በማለት መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡
በመጨረሻም፣ እንኳን ደስ ያለን፤ እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት፤ በዚህ አጋጣሚ ደግሞ ልክ እንደነዚህ ወጣቶች በየጦር ግንባር በተለይም ደግሞ በጉባ በረሃ ላይ የህዳሴን ግድብ በመገንባት የሁለተኛው ተርባይን ኃይል እንዲያመነጭ እና የሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እንዲከናወን ላበረከቱ ወጣቶች፤ እንዲሁም ለሌሎች መሐንዲሶቻችን፣ ሰራተኞቻችን ምስጋና ይገባችኋል ማለት እፈልጋለሁ፡፡ እንኳን ደስ አለን፤ አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን ነሃሴ 9/2014