ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ሙሌት በስኬት መጠናቀቅን ተከትሎ ትናንት ያስተላለፉት መልዕክት
የዛሬው ቀን ለሁላችንም ልዩ ቀን ነው:: ለዚህ ልዩ ቀን ለመድረስ አስተዋፅዖ ያደረግን ሁሉ ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ በዓለም አደባባይ በሁሉም ዘርፍ በዲፕሎማሲ፣ በቴክኒክ ስራ፣ በጥናት፣ በሙያው ድርሻ እዚህ ለመድረስ ያበቃችሁን በሙሉ፤ የሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት አባላት ሁላችሁም እንኳን ለዚህ ታሪካዊ ቀን አደረሳችሁ፤ አደረሰን ለማለት እወዳለሁ::
ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ብዙ ፈተናዎችን እየተሻገሩ ጠንካራ አገር ታላቅ ህዝብ ሆነን እዚህ ደርሰናል:: ይህ የዛሬው ልዩ ቀን ለተከታታይ ዓመታት ባደረግነው ርብርብና ስራ በአንድ ድምጽ፣ በአንድ ልብ፣ በአንድ የተባበረ ክንድ ብዙ ፈተናዎችን ተሻግረን ለዚህ ስኬትና ለዚህ ቀን በቅተናል:: ይህ ኢትዮጵያውያን ተባብረን አምጠን የወለድነው ታሪካዊ ስኬት እና ድል ነው:: በዚህ ልንኮራ፣ በዚህ ለላቀ ድልና ለላቀ ስኬት ልንሰለፍ ይገባናል/ይበቃናል::
ይህ የተፈጥሮ ፀጋ ከኢትዮጵያ ማህፀን እየፈሰሰ ለሺህ ዓመታት ተጉዟል:: አሁን ያለ አዲስ ነገር ቢሆን ኢትዮጵያውያን ተባብረን ፀጋውን ለብልጽግና፣ ፀጋውን ድህነትን ለማሸነፍና ለመለወጥ እንዲሁም የኢኮኖሚ አቅም ለማድረግ አንድ ርምጃ ተጉዘናል:: ዓባይ ብዙ ተብሎለት ለሺህ ዓመታት ተጉዞ አሁን ዛሬ ለኢትዮጵያውያን አንድ ወሳኝ የልማት አቅም ሆኖ ኃይል አመንጭቶ ወደታችናው ተፋሰስ ጉዞውን ቀጥሏል:: ይህ የዛሬው ስኬት እውነት
ስለሆነ፣ መብት ስለሆነ፣ ሳይንሳዊም ስለሆነ፣ ፍትሃዊም ስለሆነ ለዚህ በቅተናል::
በተለያየ መልክ ልዩ ልዩ ትርጉም እየተሰጠው፣ ጥርጣሬ እየተዘራበት ብዙ ፈተናዎችና ውጣ ውረዶች አጋጥመውናል:: ነገር ግን ይሄ የተፈጥሮ ፀጋ ለሁላችንም ይበቃል፤ ዋናው ነገር ለሁላችንም የሚበቃ ፀጋ እስከሆነ ድረስ ተከባብረንና ተማምነን የየድርሻችንን ማበልጸግ መጠቀም ስንችል ነው:: 21ኛው ክፍለ ዘመን የሚጠይቀውም እንዲህ አይነት አሰላለፍንና ተጠቃሚነትን ነው:: አንዱን ያገለለ ለሌላው ብቻ የሆነ ፀጋ አይኖርም::
ኢትዮጵያ በእውነትና በፍትህ በዓለም አደባባይ አቋሟን እያሳወቀች፤ ብዙ ብዥታዎችና ጫናዎች ሲደርሱ የእውነት መንገድን እየጠበቀች እዚህ ደርሳለች:: ዛሬ ያሳካችውም ድል (የዓባይ ኃይል ማመንጨት) የዓባይ የሺህ ዓመታት ጉዞ እንደሚቀጥል ያረጋግጣል:: በአንደኛው ሙሌት የታየው ተግባር ይሄው ነው:: በሁለተኛው ሙሌት የተገኘው ውጤትም ይሄው ተግባር ነው:: ሦስተኛው ሙሌት ዛሬም ስንመለከተው ያንኑ የሚያረጋግጥ ነው::
ከዚህ ባለፈ ለተለያዩ ፍላጎቶች የኢትዮጵያን የፍትህ መንገድ ለመጫን፣ ለማዛባት፣ ወደነበረው ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ከእውነት ያፈነገጡ፤ የኢትዮጵያውያንንም መብት የሚጋፋ ስለሆነ ተቀባይነትም፣ ቦታም አይኖረውም:: ነገር ግን ይሄ የተፈጥሮ ፀጋ በተፈጥሮ ሁላችንንም ያስተሳሰረ እንደመሆኑ መጠን ተባብረን፣ ተደማምጠን የበለጠ ሁላችንም እንጠቀምበታለን:: ለዚህ እውነት፣ ለዚህ ሳይንሳዊ መንገድ፣ ለዚህ ፍትህ መሰለፍ፤ ቀሪውን ስራም በተሟላ ስኬት ማረጋገጥ ይጠብቀናል::
እንደ ሕዳሴው ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የምክር ቤት አባላት፣ የጽህፈት ቤት አመራሮች፣ ሁላችሁም ባለድርሻ አካላት፣ በውጭ የምትኖሩ የዳያስፖራ አባላት፣ በአገራችን በልዩ ልዩ ሙያ እየተሳተፋችሁ ጊዜያችሁን እውቀታችሁን ለፍትህ ለኢትዮጵያውያን ለዚህ ዘመን ታሪካዊ ስራ የሰራችሁ ሁሉ እጅግ እንኮራባችኋለን፤ እጅግ እናመሰግናችኋለን:: ኢትዮጵያውያን ስንተባበር እንዴት እንደሚያምርብን፤ በልዩ ልዩ ትንንሽ አጀንዳዎች ስንጎዳዳ እንዴት አንገት እንደሚያስደፋ በተግባር እያሳየን ነው::
አሁንም ቢሆን ለበለጠ ጠንካራ አገር ግንባታ በየዘመኑ የተፈተነ፣ ለጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነትና ጉልበት ወደኋላ የማያየው ሰፊው ሕዝባችን፤ እንዲህ አይነት ድሎችን የበለጠ በማጠንከር ለላቀ ጉዞና ከፍታ ተጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል:: የዛሬዋ ቀን ልዩ ናት ስንል የመጨረሻው ነው ማለታችን አይደለም:: ተጨማሪ ስራዎች አሉን፤ ተጨማሪ ንቅናቄ ያስፈልጋል፤ ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል:: በመጪው ጊዜ በበለጠ ድል ታጅበን ለመጪው ዘመን የምናወርሰው በእኛ ታሪክ የምንኮራበት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል:: መልካም ጊዜና ዘመን ይሁንልን፤ እጅግ አመሰግናለሁ::
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7 /2014