ሰላም፣ ልማት እንዲሁም ዴሞክራሲ በአንድ አገር ውስጥ አስፈላጊ የመሆናቸው ጉዳይ የሚያጠያይቅ ባይሆንም፤ አንዳቸው በአንዳቸው ውስጥ የሚገለጡ፣ አንዳቸው ለሌላቸው መሰረት እንደሆኑም የሚናገሩ በርካቶች ናቸው። ያለ ሰላም ልማት፤ ያለ ልማትና ሰላም ደግሞ ዴሞክራሲ የማይታሰብ፤ ሊሆንም የማይችል ነው ሲሉም ይሞግታሉ። ምክንያቱም በአንድ አገር ውስጥ ሰላም በሌለበት ልማትና ብልጽግናን እውን ማድረግ አይቻልም፤ ልማትን እውን ማድረግ ቀርቶ የለማውን ኢኮኖሚ እንኳን ባለበት ማስቀጠል እጅጉን ፈታኝ ነው። ምክንያቱም ኹከት፣ ግርግርና ግጭት ባለበት አገር ውስጥ ሀብትን ለልማት ሳይሆን ለጦርነትና መልሶ ግንባታ ማዋል ላይ ትኩረት መደረጉ፤ በተቃራኒው የለሙ መሰረተ ልማቶች ለውድመት መጋለጣቸው ደግሞ እንደማሳያ ይጠቅሳሉ።
እንደ ልማት ሁሉ ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ ሰላም እጅጉን ወሳኝ መሆኑም ነው የሚነገረው። የሰላም መደፍረስ ባለበት፣ ጦርነትና አለመረጋጋት እንዲሁም የደህንነት ስጋት በሚስተዋልበት አገር ውስጥ ስለ ዴሞክራሲ ማሰብ የቅንጦት ያህል መሆኑን የዘርፉ ሰዎች ያስረዳሉ። ሰላምን ለማስፈን እንዲሁም የአገር እና የሕዝብን ህልውና ለማስጠበቅ ሲባል የሚጣሉ ገደቦች፤ የሚወሰዱ እርምጃዎች በዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ የሚፈጥሩት ጫና መኖሩን እንደ አብነት ይጠቅሳሉ። እንደ ሰላም ሁሉ በልቶ የማደር ሕልውናውን ባላረጋገጠ አገር ውስጥ ስለ ዴሞክራሲ ማሰቡ ባዶ ተስፋ መሆኑ የታወቀ ነው። በመሆኑም በአንድ አገር ልማትን እውን ለማድረግ፣ ዴሞክራሲንም ለማረጋገጥ ሰላም ወሳኝና መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን አበክረው ይገልጻሉ።
ስለ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ቁርኝት ይሄን ያህል ካልኩ፤ እነዚህ ሶስት ነገሮች በአንድ አገር እንዲኖሩም ሆነ እንዳይኖሩ በማድረግ ሕዝብ ለምሬት አልያም እፎይ ብሎ በተረጋጋ መንፈስ እንዲጓዝ የሚያደርጉ ገፊ ምክንያቶች አሏቸው። እነዚህ ገፊ ምክንያቶችም ተወራራሽነት ያላቸው፤ አንዱ ምክንያት ለሌላው መነሻ የሚሆኑ ናቸው። ለምሳሌ፣ የኮንትሮ ባንድ ንግድና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር በአንድ በኩል በኢኮኖሚ ላይ የሚሰራ ሻጥር ሲሆን፤ በሌላው ጎኑ ደግሞ የሰላም መደፍረስ ሁነኛ መነሻ ነው። በተመሳሳይ ይሄን የሰላምና የኢኮኖሚ በሽታ ለማስወገድ በሚወሰድ እርምጃ በሰዎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ የሚጥለው ገደብ ይኖራል።
በዚህ መልኩ የሚገለጹ በርካታ ምክንያቶች ያሉ ቢሆንም፤ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ሕዝቡን ለምሬት የዳረጉና ጎልተው የሚታዩ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች አሉ። እነዚህም ሕዝቡ ወጥቶ የመግባት ስጋት ውስጥ እንዲገባ፤ በልቶ የማደር ሕልውናው እንዲፈተን፤ ማሕበራዊ ቁርኝቱ እንዲላላና እርስ በእርሱ እንዲገፋፋ እያደረጉት ያሉ ሲሆን፤ እነዚህን ችግሮች ላይቶ መፍትሄ መስጠት ደግሞ ለነገ የማይባል ይልቁንም ሕዝቡ ከችግሮቹ ባሻገር ያሉ የልማትና ብልጽግና መዳረሻዎቹን እንዲመለከት ማስቻል ነው። ከሰሞኑም ብሔራዊ የደሕንነት ምክር ቤት ባካሄደው ግምገማም ይሄንኑ የለየ ሲሆን፤ ሕዝቡን በሚያማርሩ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ የሙስና፣ የኮንትሮባንድ፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ወዘተ ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ሕዝቡ እፎይ እንዲል ማድረግ እጅጉን አስፈላጊ እና ለዚሁ ሁሉም የራሱን የቤት ስራ ሊወጣ እንደሚገባም ነው ያሳሰበው።
ይህ ግምገማና አቅጣጫ ዛሬ ላይ ሕብረተሰቡ ላለበት ችግር መፍትሄ ያገኝ ዘንድ አንድ እርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ምክንያቱም ሕዝቡ ዛሬ ላይ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት እጅጉን ምሬት ውስጥ የከተተው፤ ውሎ ካደረም የሰላም ስጋት ወደሚሆንበት ደረጃ የሚያመራው ስለመሆኑ ሕዝቡን ቀርቦ ማየትና ሕዝቡ ውስጥ መኖር ብቻ በቂ ነው። በተመሳሳይ ሰላምና ደህንነቱ በከተማውም ሆነ በገጠሩ ማሕበረሰብ ላይ የስጋት ጥላውን ከማጥላቱም በላይ፤ የችግሩ ገፈት ቀማሽ አድርጎታል። ከሞተው ንብረቱን በጠራራ ፀሐይ እየተቀማ፣ አካላዊ ደሕንነቱም ሆነ የሕይወት ደሕንነቱ በአንድ ዘራፊ ወንበዴ በድንገት የሚወሰንበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በገጠሩ አካባቢም ቢሆን ሕብረተሰቡ ለሕይወቱም፣ ለንብረቱም ከለላ የሚሆነው አጥብቆ የሚሻበት፤ በሽብርተኞች መዳፍ ውስጥ ሲወድቅም በደቂቃ ውስጥ ሕይወቱንም፣ ንብረቱንም የሚነጠቅበት፤ ለከፋ አካልና ሥነልቡና ጉዳት፣ መፈናቀልና ስደት የሚዳረግበት ወቅት ነው።
በተመሳሳይ፣ ሕወገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ የኮትሮባንድ ንግድ፣ የኢኮኖሚ አሻጥርና ሙስና ሌላው የማህበረሰቡ ትብታብ ሆነው አላላውስ ያሉት፤ ለሰላሙም ሆነ በልቶ ለማደሩ ስጋት ላይ እንዲወድቅ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ያሉ ክፉ ተግባሮች ናቸው። እነዚህ ከአገር በላይ ስለ ግል ጥቅምና ከፍታ ሲባል የሚፈጸሙ ፀረ ሕዝብና አገር ተግባራት፤ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን ለከፋ የሰላም እና የኢኮኖሚ ስብራት፤ ኢትዮጵያውያንንም ከፍ ላለ የሰላምና ደሕንነት እንዲሁም የኑሮ ውድነት ችግር ዳርገው ሕልውናቸውን እየተፈታተኑ ይገኛሉ። በእነዚህ ክፉ ተግባራት ምክንያት ሕዝቡም ስለ ነገ ልማትና ብልጽግናው ሳይሆን ስለ ዛሬ ሕልውናው ብቻ እንዲጨነቅ፤ እፎይታ አልባ የምሬት ኑሮን እንዲገፋ ሆኗል።
ይህ ምሬትና የሕልውና ስጋት ደግሞ ውሎ ሲያድር የራሱ የሆነ አደጋን መጋበዙ፤ የላቀ ስጋት መሆኑ አይቀሬ ነው። ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱም ችግሩን ገምግሞ አቅጣጫ ሲያስቀምጥ ይሄንኑ በመረዳት ነው። ከዚህ አኳያ ችግሩን ከማቃለል አኳያም የተጀማመሩ ተግባራት መኖራቸው እሙን ነው። ይሁን እንጂ፣ የችግሩን ስፋትና ግዝፈት የመጠነ ስልት ነድፎ መስራት፤ በሂደቱ የሚታዩ እንከኖችን ያለ አንዳች ማመንታት እየነቀሱ ማውጣትና እርምጃ መውሰድ፤ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ኃላፊነቱን የሚወጣበትንና ባይወጣ ሊደርስበት የሚችለውን የተጠያቂነት ልክ አስገንዝቦ በሙሉ ልብና አቅም መስራትን ይጠይቃሉ።
ትልቁ የቤት ስራም የሚሆነው ይሄው በሙሉ ልብና አቅም ችግሮችን እፈታለሁ፤ የሕዝቡን ምሬት በእፎይታ ለመተካት አስፈላጊውን መስዋዕትነት እከፍላለሁ ብሎ ወደ ተግባራዊ እርምጃ መግባቱ ነው። ምክንያቱም ስራው ከቃል ያለፈ ተግባርን፤ ከማስመሰል የተሻገረ ራስን አሳልፎ መስጠትን፤ ከመሸንገል የላቀ የሕዝብ ወገንተኝነትና ተቆርቋሪነትን፤… የተላበሰ አመራር፣ ባለሙያ፣ እንዲሁም ሕዝብ በእጅጉ ይፈልጋል። ይሄን ሆኖ መገኘት ደግሞ ከሁሉም የሚጠበቅ፤ ከራስ በላይ ስለ አገርና ሕዝብ አለኝታነትን የመግለጥ እውነት ነው። እናም ሕዝብ ከምሬትና የሕልውና ስጋት የሚላቀቅበት ጊዜ እንዳይርቅ ሁሉም በያለበት ቦታና መስክ ሁሉ በኃላፊነቱ ልክ የቤት ስራውን ወስዶ ሊወጣ ይገባል።
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 4 /2014