መንግስት አገሪቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂው እንዲሁም በዲጂታል ኢኮኖሚው ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንድትችል፣ በእነዚህ ዘርፎች የሚከናወኑ ተግባሮችን በሚፈለገው ፍጥነትና የጥራት ደረጃ ለመስራት የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች በመንደፍ ስራ ላይ አውሏል። ከእነዚህ ስትራቴጂዎች አንዱ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ›› ነው።
የአገሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞ ለማሳለጥ እንዲሁም የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን በግንባር ቀደምትነት ለመምራት የሚችሉና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሊጠቀሙ የሚችሉ አራት ስትራቴጂያዊ ቅድሚያ የተሰጣቸው ዘርፎች መለየታቸውን በ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ተመልክቷል። ለዚህም ግንባር ቀደም ተብለው ከተለዩት ውስጥ ግብርና፣ የማምረቻ ዘርፍ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂና ቱሪዝም ዘርፎች መሆናቸው ተጠቁሟል።
ሁሉም ቁልፍ ዘርፎች ዘመኑ የሚጠይቀውን ሳይንሳዊና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንዲከተሉ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። አገሪቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ወደኋላ ከቀሩት የዓለም አገሮች ጋር የምትመደብ መሆኗ እሙን ነው። ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ግን ተስፋ ሰጪ ጥረቶች እየታዩ ናቸው። ለእዚህም በግብርናው ዘርፍ ላይ በጎ ውጤት ሊያስከትል የሚችለውን የሳተላይት ቴክኖሎጂን፣ የቴሌኮም አገልግሎቶችን፣ የክፍያ ስርአቶችን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል።
ከዚህ አኳያ በቴሌኮም አገልግሎቶች በኩል በኢትዮ ቴሌኮም እየተከናወነ ያለውን ተግባር ሰሞኑን የቴሌ ብር የፋይናንስ አገልግሎቶች በተመረቁበት ወቅት የወጡ ዋና ዋና መረጃዎችን በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችን ይዘን ቀርበናል።
ኢትዮ ቴሌኮም ዘመኑ የደረሰበትን የቴሌኮም አገልግሎቶችን ማቅረቡን ቀጥሏል። በአፍሪካ ቀደምትና ለ128 ዓመታት የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ተቋም የሆነው ኩባንያው፣ የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽነትን በከተማም በገጠርም ለማረጋገጥ ሲሰራ ቆይቷል። የኢትዮጵያውያንን ተጨማሪ እና ከፍተኛ አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ መድቦ የዘረጋውን መጠነ ሰፊ መሠረተ ልማት በመጠቀም “ቴሌብር” የተሰኘውን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ባለፈው አመት መጀመሩ ይታወሳል።
የኩባንያው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ቴሌብር ወደ ስራ የገባው ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም ነው። በዚህም የአገሪቱን የገንዘብ ዝውውር ስርዓት በማቀላጠፍና በማዘመን አስተማማኝና ምቹ የግብይት ስርዓት እንዲኖር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። አሰራሩ በርካታ ተቋማት ፈጣንና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ከደንበኞቻቸው ገንዘብ መሰብሰብ እንዲችሉና ደንበኞችም ካሉበት ሆነው ክፍያቸውን እንዲፈፅሙ አስችሏል።
አገልግሎቱ በጥሬ ገንዘብ ዝውውር ላይ ላሉ ውስንነቶች መፍትሄ ሆኖ ተገኝቷል። በቴሌ ብር አገልግሎት የግብር ክፍያ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ፣ የአየር ሰዓት ሽያጭ እና የመሳሰሉትን መፈጸም ተችሏል። በዚህም እንግልትና ጥሬ ገንዘብ ይዞ መንቀሳቀስ ቀርቷል። በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገውን የነዳጅ ድጎማ ክፍያም በቴሌ ብር እየተፈጸመ ይገኛል።
ቴሌ ብር ስራ ከጀመረ 14 ወራት ተቆጥረዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ብቻ 22 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የቴሌብር ደንበኞችን በቴሌ ብር ማፍራት ተችሏል። በዚህ ጊዜ የ34 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ግብይት/ዝውውር ተፈፅሟል፤ አንድ ነጥብ 02 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ከ37 አገራት ተልኮበታል፤ ይህ ውጤት ለሌሎች አገራትም በመልካም ተሞክሮነት የሚወሰድ እንደሆነም ተመስክሮለታል።
እስከ አሁን የአየር ሰአት ሲሞላበት፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የፋይናንስ ድጋፍና ሌሎች መሰል የዲጂታል ክፍያዎች ሲፈጸምበት፣ ህዝቡ ኑሮ እንዲቀል ሲደረግበት የቆየው ቴሌ ብር፣ እነሆ አሁን ደግሞ በቴሌ ብር ገና ብዙ እናያለን የሚያሰኙ አዳዲስ አገልግሎቶችን ይዞ ከተፍ ማለቱን ኢትዮ ቴሌኮም ሰሞኑን ይፋ አድርጓል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከዳሸን ባንክ ጋር ይዟቸው የመጣውን እነዚህን አዳዲስ አገልግሎቶች ቴሌ ብር እንደ ኪሴ ወይም ኦቨር ድራፍት፣ ቴሌ ብር መላ ወይንም ክሬዲት ሰርቪስ እንዲሁም ቴሌ ብር ሳንዱቅ ወይም ሴቪንግ የሚሰኙ ናቸው። እነዚህን አገልግሎቶች ማግኘት የሚቻለውም በቴሌ ብር መተግበሪያ ወይም በቴሌብር አጭር ቁጥር ኮከብ 127 መሰላል ላይ በመጠቀም ይሆናል።
አገልግሎቱ ሰሞኑን በተጀመረበት ወቅት የብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ ከቴሌብር በፊት የኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ከአፍሪካ አገራት አንጻር እጅግ የወረደ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን የቴሌብርና ሌሎች የዲጂታል ፋይናንስ ተጠቃሚዎች ቁጥር በኢትዮጵያ ከ43 ሚሊዮን በላይ መድረሱን አስታውቀዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከዳሸን ባንክ ጋር በመተባበር ቴሌብር እንደ ኪሴ፣ ቴሌብር መላ (ብድር) እና ቴሌ ብር ሳንዱቅ (ቁጠባ) የተሰኙ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ማስተዋወቁ ደግሞ የዲጂታል ኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት መጣሉን ያሳያል ብለዋል። ብሔራዊ ባንክ በቀጣይም ልክ እንደ ቴሌብር ሁሉ ከባንኮች ጋር በመተባበር የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት መስጠት ለሚፈልጉ ተቋማት ሁሉ አስፈላጊውን ፈቃድና አገዛ እንደሚያቀርብም አስታውቀዋል።
የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው አለሙ በበኩላቸው የአገልግሎቱን መጀመር የሐገራችን ልማት ዲጂታል እንቅስቃሴ አብነት ሲሉ ገልጸውታል። ዳሸን ባንክ የህልውና መሰረቱን ያጸናው የአገራችንን ጥቅምና የህብረተሰቡን እድገት ተቀዳሚ መርህ በማድረግ በተሰማራበት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሁሉም አቅጣጫ ምሳሌ የሚሆን ተግባር በማከናወን ጭምር ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ባንኩ የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪን የሰለጠነው አለም በደረሰበት ዘመናዊ አገልግሎት ደረጃ ለማድረስና በቴክኖሎጂ የታገዙ አዳዲስ አሰራሮችን በመጀመር የፋና ወጊነት ሚናውን እየተጫወተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ባንኩ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀ አብሮ የመስራት የመተጋገዝ ግንኙነት እንዳለው አቶ አስፋው ጠቅሰው፣ ይህም ግንኙነት አድጎ ዛሬ የተሟላ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ለሚገመቱ 60 በመቶ ያህል ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እለታዊ የፋይናንስ ፍላጎታቸውን በማሟላት በየተሰማሩበት የስራ መስክ ራሳቸውን ለማሻሻል የሚችሉበትን የዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎት በአጋርነት ለመዘርጋት ያስችላል ሲሉ አብራርተዋል።
‹‹በዚህ አለም ስንኖር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ማህበረሰቦችን ማገልገል፣ ችግራቸውን መፍታትን ያህል ምንም ነገር የለም›› ሲሉ የጠቀሱት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ ‹‹ሰፊውን የማህበረሰብ ከፍል የፋይናንስ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችለውን የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት መጀመር ስናበስር በታላቅ ደስታ ነው›› ብለዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ እንዳሉት፤ የቴሌብር ፋይናንስ አገልግሎት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አጋዥ ከሆኑ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው። አገልግሎቱ ሰፊውን የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደርጋል። በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል ችግር ለማቃለል ይረዳል።
የፋይናንስ አገልግሎት ሲባል መቆጠብ ብቻ አይደለም፤ ማበደርንም ይጨምራል። የቴሌ ብር ፋይናንስ ኅብረተሰቡ የእለት ከዕለት እንቅስቃሴውን ለመምራትና ኑሮውን ለማሻሻል የሚረዳው አገልግሎት ነው። የተረጋጋ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት እንዲኖር ሰፊውን የማኅበረሰብ ክፍል የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለዚህም ነው አስፈላጊ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተደርገው የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት እንዲሰጥ ፈቃድ የተሰጠው።
ኩባንያው የአገሪቱን የዲጂታል ኢትዮጵያ ህልም እውን ለማድረግ በርካታ ተግባሮችን እያከናወነ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ጠቅሰው፣ ተደራሽነት ብቻ ሳይሆን አቅምን ያገናዘበ አገልግሎት ለመስጠት በርካታ ማሻሻያዎችን ሲሰራ መቆየቱንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
ብድር ያለማስያዣ (Collateral) የሚሰጥበት የአሰራር ስርዓት አለመኖሩ ሰፊው የኅብረተሰብ ክፍል የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ይህን ችግር ለማቃለል ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌብር ፋይናንስ አገልግሎት ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ እንዳሉት፤ የቴሌ ብር የፋይናንስ አገልግሎት የእለት ተእለት ኑሮን በማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል፤ አሁን ደግሞ ገንዘብ ማስተላለፍ፣ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን መበደር ጭምር የሚያስችል አገልግሎት ኢትዮ ቴሌኮም ይዞ ቀርቧል።
ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን በቴሌብር አማካኝነት ሲያቀርብ ዳሸን ባንክ ደግሞ የፋይናንስ አቅርቦቱን ያመቻቻል። ማንኛውም ደንበኛ ተያዥና ማስያዣ ንብረት ሳይጠየቅ የብድር አገልግሎት ማግኘት ይችላል።
ለቴሌብር የብድርና ቁጠባ አገልግሎት በዓመት 19 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ተዘጋጅቷል። የቴሌ ብር እንደ ኪሴ ደንበኞች በቴሌብር አካውንታቸው ላይ በቂ ገንዘብ ባይኖራቸው እንኳ፣ እስከ ሁለት ሺህ ብር ድረስ ተበድረው አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ የሚያግዝ አገልግሎት ነው። በተጨማሪም ቴሌብር መላ ለደንበኞች ብድር የሚቀርብበት ሥርዓት ሲሆን፣ ቴሌብር ሳንዱቅ ደግሞ ቁጠባ አገልግሎት የሚሰጥበት ነው።
ለግለሰቦች እስከ 10 ሺህ ለአነስተኛ ተቋማት ደግሞ እስከ 100 ሺህ ብር የብድር አቅርቦት ተመቻችቷል፤ ይህም ለሥራ ዕድል ፈጠራና አብዛኛውን ኅብረተሰብ የፋይናንስ ተደራሽ ለማሳደግ የሚረዳ ቴክኖሎጂ ነው ።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አገልግሎቶቹን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ የመጀመሪያው ‹‹መላ›› የተሰኘ ሲሆን ግለሰብ ደንበኞች፣ ነጋዴዎች እንዲሁም ወኪሎች በቴሌብር ሂሳባቸው አማካኝነት አነስተኛ የብድር አገልግሎት (Micro Credit) የሚያገኙበት መንገድ ነው። ይህ አገልግሎት ሲቀርብ ብድር ያለማስያዣ ማግኘት ያስችላል፤ የደንበኞች መረጃዎች ምስጢራዊነትም ይጠበቃል። ሰዎች ራሳቸው ለራሳቸው ዋስ የሚሆኑበትን አሰራር የሚፈጥርና መተማመንን የሚያጎለብት ዘዴ ነው። ብድር በሚቀርብበት ጊዜ ደንበኛው በቴሌብር ላይ ያለው ተሳትፎ ይታያል።
ይህ የብድር አሰራር የፋይናንስ ውስንነት ያለባቸውን አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት በንግድ ስራ ላይ እንዲሰማሩና ስራውን ለማስፋት እንዲችሉ ያግዛቸዋል። ልዩ ልዩ ተሰጥኦዎች ያሏቸው ወጣቶች በገንዘብ እጥረት ምክንያት ህልማቸው እንዳይጨናገፍ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙም ያስችላቸዋል። ቴሌብር መላ ለግለሰቦችና ለንግድ ተቋማት የቀን፣ የሳምንትና የወር አገልግሎቶች አሉት።
ሁለተኛው አገልግሎት ‹‹እንደ ኪሴ›› የተሰኘ ሲሆን የቴሌብር ደንበኞች በአካውንታቸው ላይ ያላቸው ቀሪ የሂሳብ መጠን በቂ ባልሆነበት ጊዜ የሚጠቀሙበት የብድር አገልግሎት (Micro Overdraft) ነው። ይህ አገልግሎት የጎደለውን የሚሞላ አጋር ነው። ቴሌብር ‹‹እንደ ኪሴ›› በቴሌ ብር ክፍያ የሚፈጸምባቸውን ሁሉንም አገልግሎቶችን የሚመለከት የቴሌብር ፋይናንስ ዘዴ ነው።
ሌላው የቴሌብር ፋይናንስ አገልግሎት ደንበኞች እንደየፍላጎታቸው ከወለድ ነፃ ወይም በየቀኑ የሚሰላ የወለድ መጠን የሚታሰብላቸው የቁጠባ አይነቶችን የሚጠቀሙበት ‹‹ሳንዱቅ›› የተሰኘው የቴሌብር አገልግሎት (Micro Saving) ሲሆን፤ አገልግሎቱ ትንንሽ ገንዘቦችን ለመቆጠብና ወደ ኢኮኖሚው ለማስገባት ያስችላል።
ይህ የቴሌብር ፋይናንስ አገልግሎት የክፍያ ስርዓቱን በማዘመን ሰፊው የኅብረተሰብ ክፍል የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ያግዛል። አገልግሎቱ አዳዲስ የሥራ እድሎችን በመፍጠር በአጠቃላይ አገራዊ ኢኮኖሚ እድገት ላይ የራሱ ሚና ይኖረዋል።
በዚህ አገልግሎት የመጀመሪያው ዓመት ላይ 108 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውሮችን ለማከናወን ታቅዷል። በዓመቱ ለ12 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ደንበኞች (Unique Users) ተደራሽ በመሆን በቴሌ ብር ‹‹መላ›› ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ብድር ለመስጠት፣ በ‹‹እንደ ኪሴ›› ስድስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ለማበደር እንዲሁም በ‹‹ሳንዱቅ›› ደግሞ ሦስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ለመቆጠብ በአጠቃላይ የ19 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ብድርና ቁጠባ ለማከናወን ታቅዷል።
የፋይናንስ አገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት ብዙ ተሰርቷል፤ የቴሌ ብር የፋይናንስ ስርአትን ከስማርት ፎን በተጨማሪ በሌሎች የሞባይል ስልኮችም ይሰጣል። ለዚህም ተደራሽነት ሲባል ኮከብ 127 መሰላል መተገበሪያ ተዘጋጅቷል።
የፋይናንስ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ አማራጮች መዘርጋታቸውም ተጠቁሟል። ኢትዮ ቴሌኮም ከ13 ባንኮች ጋር ትስስር ያለው በመሆኑ ደንበኞች ከአካውንቶቻቸው ገንዘብ ማንቀሳቀስ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ኩባንያው በየአካባቢው ከ79 ሺ በላይ ኤጀንቶች አዘጋጅቷል፤ በእነዚህ ኤጀንቶች በኩልም ገንዘብ ማስገባት ማውጣት የሚቻልበት ሁኔታ ተዘጋጅቷል። በተጨማሪም የኩባንያውን ምርቶች /ፕሮዳክትስ/ ለደንበኞች የሚያደርሱ ከ360 ሺ በላይ አጋሮች ያሉት በመሆኑም ለቴሌብር የፋይናንስ አገልግሎት ሌሎች አማራጮች ተደርገው ያገለግላሉ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3/2014 ዓ.ም