ሁለቱ የፕላኔታችን ትልልቅ ክፍለ ዓለማት እስያና አፍሪካ በቆዳ ስፋታቸው ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ብዛታቸውም ስድሳ በመቶ የሚጠጋው የዓለማችን ሕዝብ የሚኖርባቸው ግዙፍ አህጉራት ናቸው፡፡ እስያ ብቻ 41 ነጥብ 84 በመቶ የሚሆነውን የዓለማችን ሕዝብ የሚያዋጣ ሲሆን፤ አፍሪካ ደግሞ 17 ነጥብ 20 የሚሆነውን ድርሻ በመያዝ የሁለተኝነቱን ደረጃ ትይዛለች፡፡ ይህም ማለት በቀሪዎቹ አምስት አህጉራት ያለው የሕዝብ ቁጥር አንድ ላይ ተደምሮ በእስያና በአፍሪካ ብቻ ከሚገኘው የሕዝብ ቁጥር በሃያ በመቶ ያነሰ ነው እንደማለት ነው፡፡
የወጣቶችን ቁጥር በተመለከተም እንደዚሁ በድምሩ ከዓለማችን ወጣት የሕዝብ ቁጥር 80 ነጥብ 7 የሚሆነውን ድርሻ በመያዝ ሁለቱ ግዙፍ አህጉራት እስያና አፍሪካ በተመሳሳይ ከፊት ይቀመጣሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 58 በመቶው የእስያ ሲሆን 22 ነጥብ 7 በመቶው ደግሞ ስድሳ በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ ከሃያ አምስት ዓመት በታች፣ ከሲሶ በላይ የሚሆነው ሕዝቧ በ15 እና በ34 ዓመት ዕድሜ መካከል የሚገኝባትና እስከ ሰባ በመቶ የሚሆነው የሕዝብ ቁጥሯ በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝባትና “ወጣቷ አህጉር” በመባል የምትታወቀው የእኛዋ አፍሪካ ናት፡፡
ይህም ሁለቱ ግዙፍ አህጉራት በአግባቡ ከተጠቀሙበት ከራሳቸው አልፈው ዓለሙን ሙሉ ሊለውጡበት የሚችሉበት ወጣትነትን የሚያክል የዓለማችንን ግዙፍ ኃይል ጠቅልለው መያዛቸውን ያመላክታል፡፡ ሆኖም “የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው” እንዲሉ አበው እንደአለመታደል ሆኖ ይህ ሁሉ የዕድገትና የለውጥ ኃይል ባለበት እስያና አፍሪካ አብዛኛው ሕዝባቸው ዛሬም ከድህነት አረንቋ ያልተላቀቀባቸው የሃብታም ድሃ አህጉራት ናቸው፡፡ ያም ሆኖ በእምቁ የአህጉራቱ ሃብትና በግዙፉ የዕድገትና የለውጥ ኃይል፤ በወጣትነት ላይ በአግባቡ ከተሠራና ኢንቨስት ከተደረገ ዛሬም የማደግና የመበልጸግ ዕድሉ አለ፡፡
ለዚህም ግማሽ ክፍለ ዘመን ባልሞላ ጊዜያት ውስጥ የዓለምን ኢኮኖሚና ፖለቲካ እንደ አዲስ አፍርሶ እየሠራ የሚገኝ አስደማሚ ዕድገትና ልዕለ ኃያል የኃይል ሚዛን መፍጠር የቻሉት እንደቻይና ዓይነቶቹ አገራት ማሳያዎች ናቸው፡፡ ሌላዋ እስያዊት የግዙፍ የሰው ሃብት ባለቤት ሕንድም ወደዚህ ጎዳና እመጣች ነው፡፡ ከአፍሪካም አገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ እንደ ናይጀሪያ የመሳሰሉ በርካታ አገራት ይህ ዕድል አላቸው፡፡ ይህንኑ ለማድረግ ግን ትልቅ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትና አያሌ ኢንቨስትመንትን ይጠይቃል፡፡
ለዚህ ደግሞ ከአህጉራቱ መሪዎችና ከራሱ ከወጣቱ በርካታ ሥራ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ረገድ ዋና ዓላማውን ያላቸውን ግዙፍ የወጣት ኃይል በመጠቀም በሁለቱ ትልልቅ አህጉራት መካከል ትብብርንና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ላይ አድርጎ በባለ ራዕይ ወጣት አፍሪካውያንና እስያውያን ወጣት መሪዎች አማካኝነት በአውሮፓውያኑ 2018 የተመሠረተው የአፍሪካ ኢስያ ወጣቶች ፎረም እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ አርዓያነት ያለው መልካም ጅምር ነው፡፡
ፎረሙ ዋና መቀመጫውን አፍሪካ ውስጥ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ፤ በእስያ ደግሞ በታይላንድ ባንክኮክ አድርጎ ባለፉት አራት ዓመታት መደበኛ ባልሆነ መንገድ የወጣቶችን አቅም የሚገነቡና ወደመሪነት የሚያመጡ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን ከሰሞኑ ደግሞ “በአፍሪካና እስያ መካከል ቀጣይነት ያለው ዘላቂ ትብብርን ለማረጋገጥ የወጣቶች ሚና” በሚል መሪ ሃሳብ በመዲናችን አዲስ አበባ የመጀመሪያ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡ ሰላም ግንባታ፣ ሥራ ፈጠራ፣ የወጣቶች መሪነትና ግብርና ላይም ዋነኛ አጀንዳዎቹ አድርጎ ተወያይቷል፡፡
በመድረኩ ላይ ከሦስት መቶ የሚበልጡ የሁለቱ ሃገራት ወጣቶች ተገናኝተው በተቀሱት አጀንዳዎች ላይ ተወያይተዋል፣ በተለያዩ ዘርፎች ላይም የልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡ ወጣቶቹ ብቻ ሳይሆን ከሁለቱ አህጉራት የተውጣጡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትና ፖሊሲ አውጭዎች፣ ታዋቂ የሥራ ፈጠራና የፋይናንስ ዘርፉ አንቀሳቃሾች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ከሌሎች አህጉራት የተጋበዙ ወጣቶችና የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ መሪዎች ተገኝተው አፍሪካውያንና ኢስያውያን ወጣቶችን አዳምጠዋል፡፡ ወጣቶቹ ለአህጉሮቻቸውና ለመላው ዓለም ዘላቂ ልማት የልማትና የዕድገት አቅም መሆን የሚችሉበትን መንገድ በጋራ መክረዋል፡፡
በመድረኩ በስኬታማ መሪዎች ስብእናዎች፣ ፈጠራ የታከለበት አመራር፣ የወጣቶች በጎ ፈቃደኝነት፣ ራስን ማሳደግ በሚሉ ጉዳዮች ላይም ትኩረት አድርጎ የወጣቶችን ውሳኔ ሰጭነት ሚና ማሳደግ በሚቻልበትና የአገር ተረካቢ የሆኑትን ወጣቶች ለአመራር ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያግዙ የዕውቀትና የክህሎት ትጥቆችን ማስጨበጥ ላይ ያለመ ውይይም ተካሂዷል፡፡ በአንድ ወቅት የጀኔራል ኤሌክትሪክ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበረው ታዋቂው አሜሪካዊ መሃንዲስ፣ ደራሲና የቢዝነስ ባለሙያ ጃክ ዌልች ነው እንዳለው መሪ ከመሆን በፊት ስኬት ማለት ራስን ለማሳደግ የምናከናውነው ማንኛውም ተግባር ነው፤ መሪ ከሆንን በኋላ ደግሞ ስኬት የሚባለው ሌሎችን ለማሳደግ የምንሠራው ማንኛውም ሥራ ነው፡፡
ስለሆነም የተፈጠረውን ዕድል በመጠቀም ወጣቶች ራሳቸውን በዕውቀትና በቴክኖሎጂ በማብቃት ብሎም በመልካም ሥነ ምግባር በማነጽ መሪነትን ከራሳቸው መጀመር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚያም አገራቸውንና አህጉራቸውን ለማልማትና ለመምራት ይቻላቸዋል፡ ፡ ከዚህ አኳያ እንዲህ ዓይነቱ የወጣቶች የትብብር መድረክ ብቁ አገር ተረካቢ ተተኪ አመራሮችን ለማፍራት ትልቅ ዕድል የሚፈጥርና ግዙፎቹ አህጉራት ያላቸውን ግዙፍ የዕድገትና የለውጥ የወጣትነት ኃይል በአግባቡ ለመጠቀምና ከቆዳ ስፋታቸውና ከሕዝብ ቁጥራቸው ጋር አብሮ የሚሄድ ግዙፍ አቅምና ኃይል ለመገንባት የሚያስችል ነውና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እንላለን፡፡
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3/2014 ዓ.ም