የፖለቲካ ትንተና አላዋጣህ ስላለኝ የፍቅር ትንተና ልገባ ነው (ፍቅር ገራገሩ ማንም እንደፈለገው የሚተነት ነው!) ‹‹ግን የፖለቲካ ተንታኝ ነበርክ እንዴ?›› የሚል ካለ፤ አዎ የፖለቲካ ተንታኝ ነበርኩ! ‹‹ደግሞ አንተ ምኑን አውቀኸው!›› ብሎ ጥያቄ የሚያስከትል ካለ፤ ወዳጄ ፌስቡክ ላይ ፖለቲካ ለመተንተን ምንም እውቀት አይጠይቅም ነው መልሴ!
ለማንኛውም አሁን አውቄም ይሁን ሳላውቅ ፖለቲካ አልተነትንም! በቃ ከዚህ በኋላ ጅንጀና ነው የምተነትን። በነገራችሁ ላይ ጅንጅና እና ፍቅር ይለያያል (ክፋቴ ግን ልዩነቱን አላብራራም) ትንታኔው ተጀምሯል።
በነገራችሁ ላይ እልም ያልኩ ውሸታም ነኝ። ያቺንም ስጀነጅን ሚስት የለኝም፣ ያቺንም ስጀንጅን ሴት አናግሬ አላውቅም፣ ያቺንም አንቺ ነሽ የመጀመሪያዬ ነው የምላቸው (አቤት ቢተዋወቁ እንዴት ጉዴ ይፈላ ነበር)። ችግሩ ሥራ ለሰሪው ሆነና ከሁሎችም ጋር አልፀናልኝም (ድሮስ አጭበርባሪ ሊፀናለት ነበር!)
ለነገሩ ይሄ በእኔ ብቻ ያለ ችግር አይደለም። ራሳቸው በምጀነጅናቸው ሴቶችም ያየሁት ችግር ነው። እንዲያውም አንዱን ገራሚ አጋጣሚ ልንገራችሁ።
ውይ! ለካ አሁንም የኔው አጭበርባሪነት ይቀድማል። በመጀመሪያ ለማጭበርበሪያ ብየ በስሜ ያልሆነ ሀሰተኛ የፌስቡክ አካውንት ከፈትኩ። ለነገሩ ይሄንንም ያደረኩት ወድጄ አይደለም። በትክክለኛው ስሜና በራሴው ፎቶ እምቢ ስላሉኝ ነው (የደረስኩበት ነገር እነርሱም ውሸታምና አጭበርባሪ እንደሚወዱ ነው) በትክክለኛው አካውንቴ ሳወራ አይመልሱልኝም፤ አንዴ ቢመልሱልኝም አይደግሙትም።
በማጭበርበሪያው አካውንቴ የሚከተለውን ምርጥ የስለላ ሥራ ሠርቸበታለሁ።
አንዲት ቆንጂዬ ልጅ በትክክለኛው አካውንቴ መጀንጀን ጀመርኩ። ባል አለኝ ብላ እምቢ አለችኝ። ሌላኛዋ ደግሞ ፎቶዬን ካየች በኋላ ‹‹ሂድ ወደዚያ ምን ይመስላል! ቆረቆንዳ!›› ብላ ሰደበችኝ። በተለይ በዚችኛዋ የከፋ ቂም ያዝኩባት!
ሁለቱንም በማጭበርበሪያው አካውንት መጀንጀን ጀመርኩ። ስሳደብ ይስቁልኛል፣ ነውር የሆነ ነገር ሳወራም ይስቁልኛል። አሁንስ ብሎክ አደረጉኝ ብየ በጣም ነውር የሆነ ነገር ስልክላቸው በጣም ይስቁልኛል። ይሄ ነገር እንዴት ነው? በጨዋነትና በቁም ነገር ሳወራ ዝም ይሉኛል፤ እንዲያውም ይባስ ብሎ ‹‹እስኪ አትጭቅጭቀኝ!›› ብለው ኩም ያደርጉኛል። ከዚያ ነገሩን ስገምት ለካ የሚያውቁትን ሰው ስለሚያፍሩ እንጂ እንዲህ አይነት ነውር ነገር ያስቃቸውዋል ማለት ነው አልኩ። ለነገሩ ስለማያውቁኝ ምን ይጃጃላል እያሉ እየሳቁብኝም ይሆናል። እስኪ ነገሩን በቁም ነገር ልሞክረው ብየ ደግሞ ሞከርኩት
በዚህ ውስጥ ያጠናሁት የአገራችንን ፖለቲካም ጭምር ነው። ከትክክለኛ ነገር ይልቅ የማስመሰል ነገር የበለጠ ተከታይና ተወዳጅነት አለው። ከተረጋገጠ ወሬ ይልቅ አሉቧልታ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው። ማነው፣ ምንድነው፣ እንዴት ነው… ብሎ የመጠየቅ ባህል የለንም።
ውይ! የተውኩትን ፖለቲካ ገባሁበት አይደል? እናላችሁ ከአንደኛዋ ጋር እልም ያለ ፍቅር ውስጥ ገባን። ይቺ በማጭበርበሪያው አካውንቴ እልም ያለ ፍቅር ውስጥ የገባችዋ ልጅ በትክክለኛው ስሜና
ፎቶዬ ‹‹ባል አለኝ›› ያለችኝ ናት። በማጭበርበሪያው አካውንቴ እንዳወራነው ገና አላገባችም፣ ኧረ እንዲያውም ‹‹ወንድ ሚባል ነገር አላውቅም›› ነው ያለችኝ። ቆይ ይቺን እዚህ ላይ ያዝ አርጓትና ሌላ ገጠመኝ ላስገባ (ይቅርታ ድንገት ትዝ ስላለኝ ነው)
በትክክለኛው አካውንቴ ጓደኛ አለኝ ያለችኝ ሌላኛዋ ደግሞ በሀሰተኛው እያወራን ምንም ጓደኛ የለኝም፤ ወንድ የሚባል አላውቅም አለችኝ፤ ‹‹እና ታዲያ ድንግል ነሽ ማለት ነው›› እላታለሁ ‹‹ሰገጤ ፋራ!›› ብላኝ ብሎክ አደረገችኝ። በዚችኛዋ ስለተቀጣሁ ድጋሜ እንዲህ አይነት ጥያቄ ጠይቄ አላውቅም።
ያቺን ነገር ይዛችሁ ቆያችሁኝ? እናላችሁ ባለትዳር ነኝ ካለችኝ ልጅ ጋር ምን አይነት ወንድ ትወጃለሽ? ምን አይነት ሴት ትወዳለህ ስንባባል ቆየን። እልም ያለ ፍቅር ውስጥ ገባን። ስለትዳር ማውራት ተጀመረ። ሁለታችንም የማጭበርበር ልምዱ ስላለን የምናወራው በጥንቃቄ ነው። እንዲህ እንዲህ እያልን ቤቴ ነይ፣ ቤትህ ልምጣ የመባባል ደረጃ ላይ ደረስን። እዚህ ላይ ግን አንድ ምክር መለገስ አማረኝ (የምር ይቺኛዋን ምክር ግን በቁም ነገር ያዙልኝ)
ብዙ ፍቅረኛሞች ከተዋወቁ በኋላ ወደ እሱ ቤት ወይም ወደ እሷ ቤት መሄድን አይፈልጉም። ከሴቶች እንደምሰማው ወንዶች ቤታቸውን ማሳየት አይፈልጉም ነው የሚባል፤ ከወንዶች እንደምሰማው ደግሞ ሴቶች ለመግደርደር ሲሉ ቤት መሄድ አይፈልጉም ነው። ቤቴ መጣች ይለኛል ብሎ ከመፍራት ይመስላል።
እዚህ ላይ ግልጽ መሆን አለባቸው። ግደለሽም ሳትፈሪ ‹‹ቤትህ እንሂድ›› በይው። አይ ቤቴማ አንሄድም ካለሽ ይሄ ሰው ቤቱ ሚስት አለው ማለት ነው፤ ወይም ሌሎች ሴቶች ስለሚያመላልስ ጎረቤትና አከራይ ምን ይለኛል ብሎ ይፈራል ማለት ነው። አንች ብቻ ብትሆኝ ኖሮ ግን እንዲህ አይጨነቅም! እርግጥ ነው ቤት መሄድ የመተማመን መጨረሻ አይደለም!
ኧረ የራሳችሁ ጉዳይ ወደራሴ ገጠመኝ!
በትክክለኛው አካውንቴ እምቢ ብላ በማጭበርበሪያው እሺ ካለችኝ ልጅ ጋር ተጃለስን (አራዳነኛ ለምን ይቅርብኝ) እላችኋለሁ። ፍቅራችን ተጧጧፈ፤ እንዲያውም በኋላማ ስንበላ ስንተኛ ሁሉ መፃፃፍ ሆነ።
‹‹የኔ ማር ቤት ገባክ?››
አዎ ገብቻለሁ
‹‹የኔ ማር ራት በላክ?››
አዎ በላሁ
‹‹የኔ ማር ተኛክ?››….. የተጠየቅኩትን ሁሉ አዎ ነው። ፍቅራችን እንዲህ ተጧጡፎ ልንገናኝ ተቀጣጠርን፤ ትዝ ቢለኝ ለካ በትክክለኛው አካውንቴ ታውቀኛለች።
ጎበዝ ይሄን ነገር በቁም ነገር መቋጨት ይሻላል።
በዚህ ዘመን ፍቅር የለም ለምትሉ ፍቅርን ያጠፋው ፌስቡክ ነው። መተማመን ጠፍቷል፤ ሁሉም እንደራሱ እየመሰለው ሌላውንም አያምንም። በዘጠኝ አካውንት የሚያጭበርብር ሰው ሌላውን ሊያምን አይችልም። በትዳሩ ላይ የሚወሰልት ወንድ ሚስቱን ሊያምን አይችልም፤ በትዳሯ ላይ የምትወሰልት ሴት ባሏ ጸሎት ቤት ቆይቶ ቢመጣ ራሱ ከመጠጥ ቤት ነው የመጣህ ብላ ድርቅ ልትል ትችላለች። ራሱ ታማኝ ያልሆነ ሰው ሌላውን አያምንም!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011
በዋለልኝ አየለ