
በጅማ እየተካሄደ የሚገኘው 6ኛው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ባለፉት ሰባት ቀናት በተለያዩ ስፖርቶች ጠንካራ ፉክክር እያስተናገደ ዛሬ በመቋጫው ዋዜማ ላይ ይገኛል። የባህል ስፖርቶችን ጨምሮ በ26 የውድድር ዓይነቶች የሚካሄዱ ፉክክሮች ከቀናት በፊት ፍፃሜ እያገኙ የመጡ ሲሆን ባለፉት ሁለት ቀናትም ተሳታፊዎች በርካታ ሜዳሊያዎችን የሚያፍሱባቸው ፉክክሮች ተጠናቀዋል። በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ቀዳሚ ሆኖ ለማጠናቀቅ የሚደረገው ፉክክርም በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መካከል ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በርካታ ሜዳሊያዎች በሚመዘገቡበት በአትሌቲክስ ውድድሮች ኦሮሚያ ክልል በሁለቱም ፆታ አጠቃላይ አሸናፊ የሆነበትን ውጤት ይዞ አጠናቋል። በዚህም 21ወርቅ፣ 14 ብር፣ 12 ነሐስ በድምሩ 47 ሜዳሊያ ወስዷል። ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው አዲስ አበባ 8 የወርቅ፣ 9 የብር፣ 3 የነሐስ በአጠቃላይ 20 ሜዳሊያ ማስመዝገብ ችሏል። 3 የወርቅ፣4 የብር፣ 5 የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያ ማሸነፍ የቻለው ትግራይ ክልል ሦስተኛ ሆኖ ፈጽሟል። አማራ ክልል 2 ወርቅ፣ 5 ብርና 2 ነሐስ በማስመዝገብ ቀጣዩን ደረጃ ሲይዝ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ ጋምቤላና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ፉክክር የሜዳሊያ ሰንጠረዡ ውስጥ መግባት ችለዋል።
ሌላኛው በርካታ ሜዳሊያ የሚመዘገብበትና ብርቱ ፉክክር በታየበት የውሀ ዋና ስፖርት አማራ ክልል በበላይነት ማጠናቀቅ ችሏል። ውድድሩ ከትናንት በስቲያ ሲጠናቀቅ ዘጠኝ ውድድሮች ፍጻሜ አግኝተዋል። በዚህም የአማራ ክልል 5 ወርቅ 2 ብር እና 2 ነሐስ ተጨማሪ ሜዳልያ መሰብሰብ ችሏል። አማራ ክልል በቡድን በተደረጉ ውድድሮች ከአዲስ አበባ እና ከኦሮሚያ ክልል ጋር የነበረውን ጠንካራ ፉክክር በተለይም በወንዶች እና በድብልቅ ውድድር በማሸነፍ ውጤቶችን አስመዝግቧል። እንደ አጠቃላይ በውሀ ዋና 22 ወርቅ 10 ብር እና 12 ነሐስ በድምር 44 ሜዳሊያ በመሰብሰብም አሸናፊ ሆኗል። አዲስ አበባ 15 ወርቅ እንዲሁም ኦሮሚያ 8 ወርቅ በማምጣት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቅቀዋል።
በበርካታ ስፖርቶች ብርቱ ተፎካካሪ በመሆን በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ቀዳሚ ሆኖ ለማጠናቀቅ ዕድል ያለው አዲስ አበባ ከተማ በቅርጫት ኳስ ስፖርት በሁለቱም ፆታ አሸናፊ ሆኖ ያጠናቀቀበትን ውጤት አስመዝግቧል። አዲስ አበባ በወንዶች የቅርጫት ኳስ የኦሮሚያ አቻውን በጨዋታ ብልጫ በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። ሁሉንም ዙሮች በጥሩ ብቃት ማሸነፍ የቻለው የሴቶች ቅርጫት ኳስ ቡድንም የበላይነቱን በማስጠበቅ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆን ችሏል።
በስፔሻል ኦሊምፒክ ውድድሮች ከሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከሠላሳ በላይ አትሌቶች በአምስት የውድድር ዓይነቶች ተሳትፈዋል። በዚህም አዲስ አበባ 8ወርቅ፣ 10 ብር፣ 7 ነሐስ በመሰብሰብ ቀዳሚ ሆኖ አጠናቋል። ኦሮሚያ በ8 ወርቅ፣ 4 ብርና 2 ነሐስ ሁለተኛ ሲሆን፣ ሲዳማ ክልል 2 ወርቅ፣ 1 ብርና 2 ነሐስ በማሸነፍ ሦስተኛ ሆኗል። ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 5 ብርና 4 ነሐስ በመውሰድ ቀጣዩን ደረጃ ይዞ ፈፅሟል።
በቴኳንዶ ውድድር ኦሮሚያ ክልል 7 የወርቅ፣ 4 የብርና 5 የነሐስ ሜዳሊያ በማስመዝገብ አሸናፊ ሲሆን፣ አማራ ክልል 5 ወርቅ፣ 3 ብርና 1 ነሐስ በመሰብሰብ ሁለተኛ ነው። አዲስ አበባ ደግሞ 4 ወርቅ፣ 4 ብርና 3 ነሐስ በማግኘት ቀጣዩን ደረጃ ይዟል። ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላና አፋር ክልሎች በቴኳንዶ ውድድር የሜዳሊያ ሰንጠረዡ ውስጥ መግባት ችለዋል።
ፍፃሜ ባገኘው የእጅ ኳስ ውድድር ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወርቅ ሜዳሊያው አሸናፊ ሆኗል። አዲስ አበባ የብር ሜዳሊያውን ሲወስድ ኦሮሚያ የነሐስ ሜዳሊያው ባለቤት ነው።
በሴቶች እግር ኳስ ትናንት በተደረገው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ኦሮሚያ ክልል አማራ ክልልን 3-2 በመርታት ለፍፃሜ ደርሷል። በተመሳሳይ ደቡብ ኢትዮጵያ ትግራይ ክልልን 1-0 አሸንፎ የዋንጫ ተፋላሚ ሆኗል። በዚህም መሠረት ኦሮሚያ ክልል ከደቡብ ኢትዮጵያ ለወርቅ ሜዳሊያ ሲፋለሙ፣ አማራ ክልል ከትግራይ ክልል ለደረጃ የሚጫወቱ ይሆናል።
ለዘጠኝ ዓመታት ተቋርጦ ዘንድሮ በተጀመረው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች የአንድ ሳምንት ቆይታ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ሀገርን የሚወክሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ትልቅ ተስፋ ሰጪ ተወዳዳሪዎች ታይተዋል። በርካታ ውድድሮችም አዳዲስ ክልሎች ተፎካካሪ ሆነው መውጣት ችለዋል።
በቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም