
ና! ውረድ እንውረድ፣
ለእውነት እንፋረድ።
ተጠየቅ በሸንጎው!
ጠይቅ ችሎት በእኛው።
ተጠየቅ በእግዜሩ!
ጥበብ ነው አድባሩ።
ተጠየቅ! ልጠየቅ
እማኝ ለሀቅ ቢጸድቅ።
ጠይቅ በል ዘንገኛ
ቄሳር አይደል ዳኛ።
ብለን እንዲህ ስንኝ ብናወርድለት ማን በጥበብ ሊወራረደን ይነሳ ይሆን…ከወዲያ ማዶ ከነበረው ዘመን ግን የጠያቂ የሙግት አዝማች ከግጥም ከቅኔው ፍርድ ሸንጎው ላይ የሚንፈራገጥ፣ የሚወነጨፍ፣ የሚምዘገዘግ፣ እየተወረወረ የሚፈናከት ለያዥ ለገናዡም የቸገረ ጥበብ ይዞ ከሜዳው ላይ ይጠብቅ ነበር። በቅኔ ‘እሰጥ! እገባ!’ የሞጋቹን ሙግት ድባቅ ሊመታ፣ የዳኛውን ልብ ሊረታ እዚያች ዋርካው ስር ካለች ሜዳ ይፋጠጣል።
“ቆየት ባለው ዘመን በየችሎቱ ላይ የሚታይ አንድ ተውኔታዊ ጠባይ የነበረው ጉዳይ ነበር…” ይለናል፤ ደበበ ሰይፉ “የአማርኛ ሕዝባዊ ሥነ ግጥም ለአብነት ያህል” በሚል በአንድ ወቅት ባቀረበው ጥናታዊ ጽሑፉ። እና ይህ ቆየት ባለው ዘመን የነበረ ተውኔት መሳይ ነገር ምን ይመስለናል? እንኪያ ሰላምታ? እንቆቅልሽ፣ ተረት ተረት? ሙሾና ቀረርቶ? ሽለላና ፉከራ? ቅኔ ዘረፋ? ሌባሻይ? በላ ልበልሃ፣ ተጠየቅ?…ወይንስ ምን? ወደምላሹ ደጅ የሚያቀርበንን አንድ ነገር ከራሱ ከደበበ ገለጻ ውስጥ እንጨምርበትና ከእዚያ ግን መልሷን እናውጣት።
“…ይኸውም ዳኛው ችሎቱን ለማስቻል ዛፍ ስር ተቀምጦ፣ ሕዝብም ፍዝ ተመልካች ሳይሆን በተቺነት ንቁ ተሳታፊ ለመሆን አሰፍስፎ ባለበት ቦታ ከሳሽና ተከሳሽ ወይም ዘንገኞቻቸው(ጠበቆቻቸው) ከሚከራከሩበት ርዕሰ ጉዳይ ራቅ ባለ ጭብጥ ላይ ግጥም እያወረዱ እርስ በርሳቸው ይበሻሸቃሉ፤ አንደበተ ርዕቱነታቸውንም ይሞካከሩና ይመዛዘኑ ነበር” ይላል። ታዲያ አሁንስ ‘ከሳሽ’ እና ‘ተከሳሽ’ በሚሉት ሁለት ቃላት ብናሰምር መልሳችን ምን ይሆን? እዚህ ድረስ መጥተን አሁንም ምላሹ ከተሰወረብንማ ችሎት ልንቆም ልንሞገት ይገባናል። ሸንጎው ላይ፣ ዳኛው ፊት ቆመን ‘በላ! ልበልሃ!’ ልንባባል፣ ‘ተጠየቅ!’ ልንባል ‘ጠይቅ’ልንል ግድ ይላል። እንግዲህ መልሱም ይኸው የከሳሽና ተከሳሽ ተውኔታዊ የፍርድ ሸንጓችን የሆነው የተጠየቅ ሙግት ነው።
እኚህ ሁለት ሰዎች ከአንዲት የመንደር ዋርካ አሊያም ከፊላው ስር ፊት ለፊት ቆመውና ተፋጠው፣ በስንኝ ግጥም ሲያወርዱ፣ በቃላት ቅኔ ሲያዘንቡ፣ አንዳንዴም ዘንጉን ከትከሻ ሰቅለው ወዲያና ወዲህ ብለው ፎክረው ደግሞ ሸልለው ብንመለከት እየተወኑ እንዳይመስለን። ወይንም እንደ ሎሬት ጸጋዬ ያለው ፀሐፊ ተውኔት ያዘጋጀውን ስክሪፕት የሚጫወቱ የወጋየሁ ንጋቱ ቢጤዎች እንዳይመስሉን እንጂ ቢመስሉንስ አይገርምም። እኚህ ሰዎች ጥበብ ጠርታቸው ብሔራዊ አሊያም ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት የተገኙ ሳይሆኑ፤ ለፍትሕ ተጠርተው የመጡ እልም ያሉ ባላገሮች ናቸው። በቅኔ በግጥም የሚፋለሙት የትወና ብቃታቸውን ለማሳየት አሊያም ከፊታቸው የተሰበሰበውን ሕዝብ ለማዝናናት አይደለም፤ በሙግቶቻቸው ሽፋኑን እየፈለቀቁ ብቸኛዋን እውነትን ያገኘ አንዱ ብቻ በአሸናፊ ከፍ አድርጎ፣ ከፍ ለማለት ነው።
የወዲህኛው ግንድ፣ የወዲያኛውም ስሩ፣ ከሀገሬው የሸንጎ አድባር በላይ የተንጣለሉት የዋርካው ቅርንጫፎች ጥላቸው ያረፈው ከተጠየቅ ሙግት በላይ ነው። ለዘመናት ባሕልና ወጉ ባደረገው የፍትህ ሥርዓት ውስጥ ሕግን ከጥበብ ጋር አጋምዶና አዋዶ ለማመን በሚከብድ ዕውቀት ውስጥ ሀገራችን አልፋለች። ፊቷ ያልበለዘ፣ አካለ ውበቷ ያልተሸነቆረ፣ ድምጽዋ ያልሰለለ፣ በሰውነት ያልከሳች፣ በመልኳ ያልጠቆረች፣ ፈገግታዋ እንደ ጠዋት ጮራ የሚፈነጣጠቅ ሥርዓተ ሕግ፣ ሕገ-ጥበብ ከማኅበረሰባችን ውስጥ ነበረች። ከሳሽና ተከሳሽ፣ እውነትና ሀሰት ችሎት ቆመው የሚሞግቱበት የተጠየቅ(በላ ልበልሃ) የፍትሕ ሥርዓት፣ በቅርብ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ በርዝራዥም ቢሆን የምንመለከተው ነበር። ከብዙ የሀገራችን ክፍሎች እየተነነ እንዲሄድ ምክንያት የነበረውም የ1923ቱ ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ መዋሉ ነበር። ምናልባትም ተጠየቅ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው መንዜዎቹ መንደር ሊሆን ይችላል። የቅርብ በነበሩ ጊዜያት ሁሉ በመንዝ ማኅበረሰብ ውስጥ ይከወን እንደነበር ይነገራል።
በአብዛኛው የሀገራችን ክፍሎች ሲከወን የኖረና ማኅበረሰባችን ፍትሕን ያገኝባቸው ከነበሩ መንገዶች መካከልም ‘አውራው መንገድ’ ልንለው የምንችለው ነበር። ያኔ የፍትሐብሔርም ሆነ የወንጀል ሕግ አልነበረምና ሕገ መንግሥቱ ባሕል፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ተጠየቅ፣ አንቀጽ ንኡስ አንቀጹ ቅኔ፣ ግጥም፣ ተረትና ምሳሌ…ፍርድ ቤቱ የጥበብ፣ ዳኛውም ዕውቀት ነበር። ሙግት ዘንገኛ(ጠበቃ)፣ አቃቤውም አመክንዮ ነበር።
ግነት ሳይሆን ማኅበረሰባችንስ የእውነትም ከልቡ ሊቅና ጠቢብ ነበር። ነገርን ከስር መሠረቱ አንጓሎ ለማየት የምትከብደውን የአልማዝ ፈርጥ ማውጣትን ይችልበታል። እንዲያውም ብላታ ጌታ ማኅተመ ሥላሴ በ1961ዓ.ም ገደማ ባሳተሙት “ባለን እንወቅበት” መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ይላሉ “ሕዝባችን ብልኅ ነው፤ ፈጥኖ የመረዳትና የማስረዳት ችሎታ አለው። የነገርን አካሄድ ይመረምራል፣ የአስተዳደር ምክር፣ ክርክር፣ ዳኝነትና ፖለቲካ የተፈጥሮ ገንዘቡ ናቸው…” ይላሉ፤ የጻፉት በአሁኑ ዘመን ያለነውን እየተመለከቱ ቢሆን ኖሮ ምን ብለው እንደሚጽፉልን እንጃ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የምንመለከተው የዘመናዊው የሕግ ሥርዓት መንገድና አካሄዱ የተመዘዘው ከሀገራችን ባሕላዊ የፍትሕና የሽምግልና ሥርዓት ውስጥ መሆኑን ለመገንዘብ ጥቂት ነገሮችን ብቻ ማወቁ በቂ ነው። አሁን ላይ ‘አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት…ከፍተኛ ፍርድ ቤት…ሰበር ችሎት’ የሚሉት ደረጃዎች እንኳን በተጠየቅ ሥርዓት ውስጥ የነበሩ ናቸው። ሁለቱ ወገኖች ለመስማማትና ሀቁን ለመተማመን ያልቻሉ እንደሆን የፍርድ ሂደቱን የሚጀምሩት ከታች ነው። በእድር፣ በገበያ፣ በሰንበቴ፣ በማህበር፣ በመንገድ…ድንገት በአንደኛው ሲገናኙ ላገኙት አዋቂ ሰው የሆነውን ተናግረው እንዲዳኛቸው ይጠይቁታል። በእዚህ የመጀመሪያ ደረጃ ‘የፍረደኝ’ ሂደት ሊፈታ ካልተቻለ በአካባቢው ወዳለ የሀገር ሽማግሌ ያመራሉ። በእርሱም ካልሆነ በሦስተኛ ደረጃ በመንግሥት ወደ ተሾመው የአካባቢው ‘መልከኛ’ ወይንም ‘ጭቃ ሹም’ በመሄድ የተጠየቅ የፍርድ ሥርዓት ያካሂዳሉ። ታዲያ እንደ ሌባ ሻይ ባሉት ሁሉ እስከ ሰበር ዙፋኑ የሚደርሱ ችሎቶችም አሉ።
ሕግና ጥበብ በአንድ ተለውሰው ከሚሠሩበት ከእዚህ የተጠየቅ ሸንጎ የሚከሰቱት ከሳሽና ተከሳሽ ብቻ ሳይሆኑ፣ ነገረፈጅ የሚያስንቁ ነበልባል እማኞችም በሁለት ወገን ወግነው ለእውነት ይፋተጋሉ። ‘ስሙልኝ እማኝ አንድ…እዩልኝ እማኝ ሁለት…’ የተባሉም ጭምር ለምስክርነት ይቀርባሉ። እንደ ታዳሚም የሚኮለኮለውም ብዙ ነው። ነገር አዋቂ ሹማምንት ሁሉ መንገዱን ለማቅናት በክብር ይቀመጣሉ። ግራ ቀኙን የሚሰሙት ብይን ሰጪ ዳኛውም ከነመዶሻቸው ይሰየማሉ።
እንግዲህ የተጠየቅ ሸንጎው ይለይልን ያሉ ከሳሽ ከተከሳሽ ‘ውረድ! እንውረድ!’ ተባብለው ከፍልሚያ ሜዳው ይደርሳሉ። ከሳሽ በቀኝ፣ ተከሳሽም በግራ ቦታቸውን ይዘው ይቆማሉ። ከሳሽ ረዥም ሽመሉን እየወዘወዘ ወደ ተከሳሽ ዞሮ “ተጠየቅ!…” ሲል ተከሳሹን ሊያንቀጠቅጠው ይጀምራል። ተከሳሹም “ልጠየቅ!…” ሲል በተራው ሊያርበደብድ ይገባል። በእዚህ ሙግታቸው ውስጥ አንዱ ሌላውን ለመርታት ሲል ፈሊጥ፣ ተረትና ምሳሌ፣ እንቆቅልሽ፣ ቅኔ ዘረፋ፣ የግጥም ናዳ…የማይጠቀማቸው ምንም ነገሮች አይኖሩም። አለባበስ፣ ተውኔት የሚያስንቅ የሰውነት እንቅስቃሴው…ሌላ ወቸው! የሚያስብል ትርዒት ነው። በእዚህ ሁሉ መካከል የተሟጋቾቹ ሥርዓት አክባሪነት ወሳኝ ነው። በተናጋሪው ንግግር መሃል ዘው ብሎ ነገር ላለማበላሸት ስሜቱን ተቆጣጥሮ ተራውን መጠብቅ ግድ ነው። ማኅበረሰቡም ሆነ ሹማምንቱ ይህን ትርዒት መመልከት አዝናኝም ጭምር ነው። ታዲያ ሁለቱ ወገኖች ማለዳ ከፀሐይዋ እኩል ወጥተው በጠዋቱ የያዙት ፍጥጫ የምሽት ጀንበር እስክታዘቀዝቅ ድረስ ሊውሉበትም ይችላሉ።
በተጠየቅ ውስጥ ትልቅ ቦታና ነጥብ ያለው አንድ ፍልስፍና አመክንዮ ነው። የተሟጋችን ንግግር፣ የሚወርደው ግጥም፣ የሚዘንበው ቅኔ ብልትና ስልቱን ጠብቆ ከአመክንዮ ቀለበት ውስጥ አሸንፎ መውጣት የሚችል መሆን አለበት። የተሟጋች አዕምሮ በጥልቀት የነገሮችን አካሄድ መርምሮ፣ በፍጥነት የመረዳት ችሎታ ከሌለው ተቃራኒው ሰው በቀላሉ ሊጥለውም ሆነ ነጥብ ሊያስጥለው ይችላል። ለስንት ሰዓታት ቆሞ የደረደረውን ግዙፍ ጭብጡን በአንዲት ዐረፍተ ነገር ብቻ ጨብጦ፣ የሃሳብ ክምሩን ሊንድበት ሁሉ ይችላል። ግዙፉን ጎልያድን በዳዊት ጠጠር እንደመጣልም ነው። የእዚያ ሰው ጭብጥና ክርክርን ፉርሽ! አድርጎ በዳኛው ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው የሚያደርግ ድንገተኛ ቦምብ ነው። አመክንዮው አንዳንዴ የመስቀለኛ ጥያቄ ባሕሪና ሚናም ያለው ነው። በተጠየቅ ውስጥ የሚንጸባረቀው የሥነ አመክንዮ ጉዳይ ራሱን የቻለና ብዙ ልንመራመርበት፣ ልንሠራበት የሚገባ ግዙፍ ባሕረ ሃሳብ ቢሆንም በምሁራኑም ዘንድ እምብዛም አልተስተዋለም። ማጣቀሻ ብንፈልግ እንኳን ልንጠቅስም ሆነ ልናጣቅስ የምንችለው በ1953ዓ.ም “ተጠየቅ” ከሚል ርዕስ ስር ከተጻፈው የተክለ ማርያም ፋንታዬ መጽሐፍ ውስጥ ነው።
ሳናደንቅ የማናልፈው አንድ ነገር ደግሞ አለ፤ ከዋናው ጭብጥና ክርክር ወጣ ብለው የሚጫወቱት የሥነ ልቦና ጨዋታ ነው። ዛሬ ላይ በተለይ በሠለጠኑ ሀገራት ፍርድ ቤቶች ውስጥ የሚዘወተር ነው። ሙግቱ መሃል ድንገት እንደ ሻይ ቡና ዕረፍት ያለ የሁለቱ ሰዎች የሥነ ልቦና የበላይነትና የአዕምሮ ጥልቀት ማስመስከሪያም ነው። ከዋናው ክርክራቸው ጋር በምንም የማይገናኝ ጉዳይ ድንገት ከአንዳቸው ጣል ይደረጋል። ጥያቄ ወይንም ቀለል ያለ ክርክር ይሆናል፤ አሽሙር፣ ቀልድና ፌዝም ሊሆን ይችላል። የተሰበሰበውን ሕዝብና ዳኛውንም በሳቅ ሊያነፍር የሚችል ቢሆንም፤ መጨረሻው ግን ግብ የሚመቱበት አንድ ነገር ይኖራል። አንደኛው በሌላኛው ላይ የሥነ ልቦና የበላይነት ከማሳየቱ ባሻገር፣ ‘ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ’ ነውና ምንም ከማይገናኝ ነጥብ ተነስቶ ተቃራኒውን ጉድ መሥራትም አለ። ምንም ባልጠበቀበት አሳቻ መንገድ ብቅ ብሎ የማይሆንና ነጥብ የሚያስጥል ነገር ሊያናዝዘውም ይችላልና።
ስለ ሕዝባችን የክርክር ጸባይ ብዙ ሊሂቃን እንደገለጹት፤ ሁሉ ዋናው ሙግትም ሆነ በጎን የሚደረጉ ሥነ ልቦናዊ ጨዋታዎች አዋቂነቱ የሚላክበትም ጭምር ነው። በክርክር የረታ ሰው በማኅበረሰቡም ሆነ በሹማምንቱ ዘንድ ያለው ከበሬት ልዩ ነው። ምክንያቱም ክርክር በሀገሬው ዘንድ ትልቅነትን ማሳያ፣ አዋቂ ጠቢብነትን ማስመስከሪያም ጭምር ነበር። ጥበብ በተሞላበት በእዚህ የዕውቀት ፍልሚያ ይፈተኑና ይፈታተኑ ስለነበር ኢትዮጵያውያን ከዓለም በተለይ ከአፍሪካ ሕዝቦች የተለዩ የጥበብና የዕውቀት አደባባይ ተደርገው እንዲታዩ አድርጓቸዋል። መታየት ብቻም ሳይሆን ፊደል ሳይቆጥሩ በዕውቀትና ጥበብ የሚራቀቁ ሊሂቃንና ጠቢባን እንዲፈጠሩም ያደረገ ነው።
በተጠየቅ የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ያለውን ሂደት ግራ ቀኙን ስንመለከት አንዲት ጥያቄ ማንሳት ያለብን ይመስለኛል፤ ችሎቱ ለተሟጋቾቹ የክርክር ሂደት ትልቅ ትኩረት ከመስጠቱ አንጻር እውነት የምትመዘነው በተሟጋቹ ኃይል አይሆንም ወይ? በእርግጥ ተጠየቅ ‘ፍጹም’ ወይንም ‘ሙሉ ለሙሉ የተዋጣለት ነው’ ለማለት አይቻልም። በክርክር ሂደት ውስጥ እውነታውን የያዘው ተሟጋች በደንብ ለማስረዳት ሳይችል ቀርቶ፣ በተቃራኒው ደግሞ ጥፋተኛው የእዚያን ሰው ደካማ ጎን ተጠቅሞ ፍርዱን የተገላቢጦሽ ሊያደርገው ይችላል። ነገር ግን፤ ይህ ዓይነቱ ነገር በዘመናዊው የፍርድ ሂደት ውስጥም ያለ ነው። በሁለቱም ላይ ‘ማስረጃ’ እና ‘መረጃ’ የሚባሉ ሁለት መሠረታዊ ነገሮች አሉ። በግጥሙም፣ በቅኔውም፣ በንግግሩም እነኚህን ሁለት ነገሮች በጥንቃቄና በብልሃት መከወን ለቻለ እውነት የቅርቡ ትሆናለች፤ የእርሱ ናት ማለት ግን አይደለም። እንደ ዳኛው ሁኔታ ከክርክሩ ወጣ ብሎ የራሱን ምርመራ የሚያደርግበት አጋጣሚ ይኖራል። በእዚያ ላይ ደግሞ ማኅበረሰቡ ለእውነትና ለምስክርነት ሲቆም ከባሕልና ሃይማኖት አንጻር የነበረው አመለካከት ጥብቅ ስለነበረ ያንን ክፍተት ያጠበዋል።
ሌላው ደግሞ በሙግት ሂደቱ ውስጥ በተለይ ተበዳይ ጥንቃቄ ሊያደርግበት የሚገባው አንድ ወሳኝ ነገር አለ፤ ክርክሩ በግጥም፣ በዘይቤ፣ በቅኔ …ነውና ስሜታዊነት የሚበዛበት እንደሆን ለመገመት አያዳግትም። ጥበብ አንድ ጊዜ ከውስጥ የተለኮሰች እንደሆን ሁሉን አስረስታ በእሳት የምታቀጣጠል ናት። በቅኔ ሲሆን ደግሞ የባሰ ነገረ ዓለምን የሚያስጥል ነው። የዳበሩ የቅኔ ተማሪዎች ወይንም የቅኔ መምህራን ቅኔ ሲዘርፉ ተመልክተን እንደሆን ፍጹም በሆነ እንግዳ ስሜት ውስጥ ገብተው እየተቀጣጠሉ ያሉበትን ቦታና ሁኔታ ሁሉ ሊረሱት ይችላሉ። እናም በአንድ የተጠየቅ መድረክ ላይ በጭብጥ ብቻ የሚገደብ ባለመሆኑ ሙግቱ በጥበብ ኃይል እየተገፋ ከርዕሰ ጉዳያቸው በተቃራኒ ርቀው ሊሄዱ ይችላሉ። ተከሳሹ ይህን ስልት በመጠቀም በብልሃት ከሳሹን ከዋናው የትግል ሜዳ ውጪ አድርጎ ጊዜ፣ ጭብጥና እውነትን ሊያመክንበት ይችላል። ከሳሽ ከማይሆን ገብቶ እሽክርክሪት እንደሚጫወት ሕጻን ልጅ ሰማይ ምድሩ እየዞረበት፣ የራሱ እውነት አዙሮ መሬት ሊዘርረውና ሊሸነፍም ይችላል።
ልናነሳበት የምንችለው ክፍተት እንዳለ ሆኖ፤ በዘመናዊው የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ከተጋረጡ ከአብዛኛዎቹ ህጸጾች ግን የራቀ ነው። ለአብነት በተጠየቅ ውስጥ ገንዘብ ኃይል አነበረውም። በዝምድና ወይንም በውለታ የሚታሠር አይደለም። ክርክሩ በአደባባይና በብዙ አዋቂዎች ፊት የሚደረግ እንደ መሆኑ ዳኛው ብቻውን ፈላጭ ቆራጭ አይሆንም። ሁሉም ነገር ከመጀመሩ በፊት ደግሞ አንድ ወሳኝ ነገር አለ፤ የተጠየቅ ቃለ መሃላ ነው። ይህን ቃለ መሃላ የሚፈጽሙትም ዳኛው እና እማኞቹ(ምስክሮቹ) ናቸው። ከላይ ባነሳነው የማኅተመ ሥላሴ “ባለን እንወቅበት” መጽሐፍ ውስጥም ቃለ መሐላውን እንደሚከተለው አስፍረውታል።
“ይፍረድብኝ! ይፍረድብኝ! ባደላም ያድላብኝ። በጌታዬ ጠላት ሰይፍ ሞት ይፍረድበት። የራቀውን በመድፍ የቀረበውን በሰይፍ አርዶ ፈርዶ ይጣለው” ከሚል መሐላ ጋር ለእውነት ለመቆም፣ ሀሰትን ለመፋረድ ቃል ይገባባሉ።
“በላ ልበልሃ የዐጤ ሥርዓቱን፣
የመሠረቱን፣
አልናገረም ሐሰቱን፣
ሁልጊዜ እውነት እውነቱን…” በማለትም እስቲ እግዜር ያሳይዎ…› ሲል የክስ ጅምሩን በውርድ አነዛዝ አካሄድ፤ አመልካች እየጠቀሰ በግጥም፣ በቅኔ፣ በምሳሌ…በቻለው ሁሉ ይወራረዳል።
ተጠየቅን የመሳሰሉ በሰፊው ማኅበረሰብ የሚከወኑና በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ የሚዘወተሩ ባሕላዊ የፍትሕ ሥርዓቶቻችን እጅግ ብዙ ናቸው። ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያለውን የዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓታችንን ለማሻሻል እነኚህን ከያሉበት አስሶ አንድ አዲስ ፍኖት ለመቅረጽ ይቻላል። ሕግ አርቃቂያኑ(ላው ሜከርስ) እንዲያስቡበት ብቻ ሳይሆን እንዲሠሩበትም ያስፈልጋል።
እንግዲህ እኚህ ስለተጠየቅ ያነሳሳናቸው እንደ መግቢያ የሚሆኑ ሃሳቦቹን እንጂ ጥበብ፣ ፍልስፍና ዕውቀት የያዘውን ተጠየቅን ገና አላየንበትም። በግጥም፣ በቅኔ፣ በተረትና ምሳሌ፣ በፈሊጥና አሽሙር፣ በዘይቤና እንቆቅልሽ…የሚደረገውን ተውኔት መሳይ መድረክ ላይ ያለውን ሂደት ለማሳየት ራሱን የቻለ ሌላ ቀጠሮ ግድ የሚለን ነው። ሁሌም ግን ያለንን አውቀን ባለን እንጠቀም።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም