ስፖርታዊ ውድድሮች እንደየደረጃቸው የሚያስተናግዱት ፉክክርም ይለያያል:: ከወረዳ አንስቶ እስከ ዓለም ዋንጫ እና ኦሊምፒክ ባሉ ውድድሮች አሸናፊ ለመሆን የሚደረገው ፍልሚያ በስፖርቱ ክብርን ከመቀዳጀት ያለፈ ነው:: ሃገራት በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በሚወከሉባቸው ውድድሮች ላይ በሚያስቆጥሯቸው የሜዳሊያዎች ብዛት አሊያም በሚያነሱት ዋንጫ መመዘናቸው አሁን አሁን እርግጥ እየሆነ ነው:: ምክንያቱ ደግሞ ባለንበት በዚህ ወቅት ሃገራት ከኢኮኖሚያዊ አቅማቸው፣ የፈረጠመ ፖለቲካቸው አሊያም ማኅበራዊ ሁኔታቸው እኩል ስፖርትም የክብርና የመልካም ገጽታ ምንጭ በመሆኑ ነው::
በቅርቡ በተጠናቀቀው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የታየው ሁኔታ ለዚህ ማስረጃ ሊሆን ይችላል:: ኃያሊቷና የውድድሩ አዘጋጅ የሆነችው አሜሪካ በዚህ ውድድር እንደቀደመው ጊዜ የሜዳሊያ የበላይነቷን ስታስጠብቅ፤ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ኢትዮጵያ ደግሞ ሁለተኛውን ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው:: ታዲያ ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያውያንን ብቻም ሳይሆን መላውን አፍሪካዊ የሚያኮራና በዓለም አቀፍ ደረጃም በስኬት የሚጠቀስ ድል ሆኗል:: በሃገር ውስጥ የነበረው ሁኔታም ሕዝቡን ከማስደሰት ባለፈ በፖለቲካዊ ምክንያት ያደረበትን ቅሬታ ፍቆ በርካቶችን ያቀራረበ ሆኗል:: በርካታ ታዳጊና ወጣቶችም ስፖርተኝነትን ሕልማቸው አድርገው እንዲይዙትና ሃገርን ማስጠራት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው የሚማሩበትም ነው::
ከማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታው ባለፈም አሸናፊነት ኢኮኖሚዊ ጠቀሜታን ማስገኘታቸው እሙን ነው:: ለአብነት ያህል በኦሪጎኑ የዓለም ቻምፒዮና አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች 70ሺ ዶላር፣ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤቶች ደግሞ 35ሺ እና 22ሺ ዶላር ተሸላሚዎች ሆነዋል:: ይህ የገንዘብ ሽልማት እስከ ስምንተኛ ለሚወጡ አትሌቶች እንደየደረጃቸው የሚሰጥ ነው:: አንድ ሃገር በተለያዩ ርቀቶች ከ1-8 የወጡ አንድ አንድ አትሌቶች ቢኖሯት 172ሺ የአሜሪካ ዶላር ታገኛለች:: ይህ ቁጥር ከተገኘው የሜዳሊያ ብዛት አንጻር ሲሰላ ደግሞ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ወደ ሃገር ገብቷል ማለት ይቻላል::
የአሸናፊነት ጠቀሜታ ከዚህም ይሻገራል:: አልፎ አልፎ በትልልቅ የውድድር መድረኮች ላይ አሸናፊ ይሆናሉ አሊያም በሜዳሊያ ብዛት ቁንጮ ይሆናሉ በሚል ተጠባቂ የነበሩ ሃገራት ላይሳካላቸው ይችላል:: በአንጻሩ ያልተጠበቁ ሃገራት በአስደናቂ ሁኔታ ወደ አሸናፊነቱ ሽቅብ ሊምዘገዘጉ ይችላሉ:: ታዲያ ይህ ሁኔታ በስፖርቱ አዲስ ተፎካካሪ ተገኘ ከሚለው ባለፈ እንደ ሃገር ከፍተኛ ለውጥ የማምጣት አቅም ይኖረዋል:: ይኸውም በዚያ ስፖርት ላይ ሃገራቱ አተኩረው ሊሠሩ የሚችሉበትን ፖሊሲ እስከማርቀቅ የሚደርስ ነው:: በመሆኑም በውድድር አሸናፊ መሆን ያልተጠበቁ አቅጣጫዎችን በመቅደድም በኩል ሚና እንዳላቸው መረዳት አስፈላጊ ነው::
ታድያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ላለው ሃገራዊ የስፖርት የበላይነት ሃገራት ምን ያህል ይጓዛሉ? ጥረታቸውስ ምን ይመስላል? ለዚህ ጥያቄ ምላሾችን በዝርዝር ማቅረብ ቢቻልም ቀዳሚውና የበርካቶች ተግባር የሆነው አቅማቸው በፈቀደ ሁኔታ ብሄራዊ ቡድናቸውን ማዘጋጀት ነው:: አትሌቶቻቸውን በልዩ ሁኔታ እንዲዘጋጁና ለውድድር ብቁ እንዲሆኑላቸውም በሳይንሳዊ ዘዴ የታገዘ ስልጠና እንዲያገኙ ያደርጋሉ:: በዕቅድ ይዘው ለሚከውኑት ለዚህ ፕሮጀክትም እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ያደርጋሉ:: ለስፖርተኞቻቸውም አሸናፊ እንዲሆኑ የተለያዩ ማበረታቻዎችንና ማማለያዎችን ያቀርባሉ::
በተቃራኒው በአትሌቶቻቸው ብቃት ውጤት እንደማያገኙ ያረጋገጡ ሃገራት ረጅም ርቀት ተጉዘው ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ:: ይኸውም እንደ ሃገር ዕውቅና የተሰጠው የስፖርት ማጭበርበሪያ መንገዶችን በመጠቀም ሲሆን፤ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ለአትሌቶች መስጠትን ከዚህ ቀደም በስፖርት ታሪክ የተመዘገበ ቅሌት ነው:: ከዚህ ጋር በእጅጉ ስሟ የሚነሳው ሩሲያ ከውድድሮች እንድትገለል ለመደረጓ ዋነኛ ምክንያት ይኸው አሸናፊነትን ከምንም በላይ አብልጣ መሻቷ ነው:: በርግጥ ተያያዥ የሆኑ ለአሸናፊነት የሚያበቁ ቴክኒኮችን መጠቀም በአውሮፓውያን ሃገራት ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ እየተስተዋለ ነው::
ሌላው አሁን አሁን እየጨመረ የሚገኘውና በራሳቸው አሸናፊነት የማይተማመኑ ሃገራት ዜግነት ማስቀየርን ተያይዘውታል:: ከእነዚህ ሃገራት መካከል እስያውያኑ ዓረብ ሃገራት በተለይ እንደ ባህሬን እና ኳታር ያሉት ቀዳሚ ሲሆኑ፤ አሜሪካ እና አውሮፓውያን ሃገራትም በተመሳሳይ ይህንኑ ይተገብራሉ:: ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ መነሻቸውን ከምስራቅ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ እና ሞሮኮ ስኬታማ የአትሌቲክስ ሃገራት ያደረጉ ከ300 በላይ የመምና የጎዳና ላይ አትሌቶች ዜግነታቸውን ቀይረው ለሌሎች ሃገራት በመሮጥ ላይ እንደሚገኙ ጥናቶች ያመላክታሉ:: አትሌቶች በድህነት እንዲሁም በሃገራቸው ተገቢውን ዕድል በማጣታቸው ምክንያት ወደ ሌሎች ሃገራት ለማማተር ይገደዳሉ:: በአንጻሩ ሃገራት በርካታ ገንዘብ ባወጡባቸው አትሌቶች የኦሊምፒክና የተለያዩ ቻሻምፒዮና ሜዳሊያዎችን ለመግዛት ለምን ፈለጉ የሚለው ጥያቄ የሚያስነሳ ነው:: ለዚህ ምላሽ የሚሆነው ደግሞ ሃገራት በውድድር የሜዳሊያ ሰንጠረዦች አናት ላይ መገኘታቸው የሚያስገኝላቸው የተለየ ክብርና ጠቀሜታ በመኖሩ የሚል ነው::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም