የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የቻን ማጣሪያ ውድድር ደቡብ ሱዳንን በደርሶ መልስ ጨዋታ 5ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል። ይህንን አስመልክቶም የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከትናንት በስቲያ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫው ላይ ከደቡብ ሱዳኑ ጨዋታ በተጨማሪ አሰልጣኙ በተጠናቀቀው ኮንትራታቸው ዙሪያ አስተያየት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ ኮንትራታቸውን በተመለከተ ከፌዴሬሽኑ ጋር የተጀመሩ ነገሮች ቢኖሩም ጠንከር ያለ ንግግር እንዳላደረጉ ገልጸዋል። አሰልጣኙ በእሳቸው በኩል መሆን ያለባቸውን ነገሮች እንዳቀረቡ የጠቆሙ ሲሆን ከዚህ በኋላ ለእሳቸውም ሆነ ለብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ሰዓት ስለሆነ ብዙ የሚያሳስብ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል። “እኔ ይሄ ብዙ አያሳስበኝም። ውሉ አልቋል። የምትስማማ ከሆነ ትቀጥላለህ ፤ ካልሆነ ሌሎች አማራጮችን ታያለህ። በእኔ በኩል ከክለብ የመጡ የተጨበጡ ጥያቄዎችን ከብሔራዊ ቡድኑ መልስ ሳላገኝ አልመልስም ብዬ የዘለልኳቸው ሁለት ሦስት ጥያቄዎች አሉ።
በእግር ኳስ ቅጥርም ስንብትም ቅርብ ስለሆነ ከጨዋታው በላይ አያሳስበኝም። የሩዋንዳ ጨዋታ ከፊት አለ። ማሰብም መዘጋጀትም የምፈልገው ለዛ ነው። በግሌ ራሴ ነፃ እንደሆንኩ ነው የሚሰማኝ። ምክንያቱም ቀድመው መተው የነበሩትን ነገሮች ፌዴሬሽኑን ሳላናግር ውሳኔ ውስጥ ላለመግባት አሳልፌያቸዋለው። ይሄንን ደግሞ ፌዴሬሽኑም ያውቃል። ከዚህ በኋላ ሁለተኛ ጥበቃ በእኔ በኩል መኖር አለበት ብዬ አላስብም። ለጊዜው ግን ከሌላ ቦታ የመጣ ነገር ስለሌለ ውሌን ከመጨረስ ውጪ ብዙ የሚያሳስብ ነገር የለም” ሲሉም አሰልጣኝ ውበቱ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ በኮንትራታቸው ዙሪያ ተሰብስበው አንድ ውሳኔላይ ደርሰዋል የሚል እምነት እንደሌላቸው የጠቆሙት አሰልጣኝ ውበቱ፣ ይህም አሁን በኮንትራታቸው ዙሪያ የተጨበጠ ነገር እንደሌለ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል። “በግልፅ የገባኝ ነገር ፍላጎቱ አላቸው ግን ከወቅቱ አንፃር ቁጭ ብለው ዝርዝር ነገሮችን አይተውታል ብዬ አላስብም። ስለዚህ ይህ ከሆነ እነሱም ከእኔ የተሻለ አማራጫቸውን ሊያዩ ይችላሉ ፤ እኔም ሀገሬን ማገልገል ብፈልግም እስካሁን ያጣሁት ነገር ቢኖርም ከዚህ በኋላ እነርሱን እየጠበኩ መቀመጥ አለብኝ ብዬ አላስብም” ሲሉም አክለዋል።
የኮንትራቱ ጉዳይ ከመጪው የሩዋንዳ የቻን ማጣሪያ ጨዋታ ጋር ግንኙነት እንደሌለው ያስረዱት አሰልጣኙ ውላቸው እስካለ ድረስ ስራዎችን በትኩረት መስራት እንደሚፈልጉ አብራርተዋል። ዋልያዎቹ ከሩዋንዳ ጋር ስለሚጠብቃቸው ፍልሚያም የደቡብ ሱዳኑ ጨዋታ ከተጠናቀቀ ጀምሮ እያሰቡበት እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ከደቡብ ሱዳን ጋር የነበረውን የደርሶመልስ ጨዋታ በተመለከተ አሰልጣኝ ውበቱ በሰጡት ማብራሪያ፣ ዋልያዎቹ 0ለ0 ከተጠናቀቀው የመጀመሪያው ጨዋታ ከቀናት በኋላ የነበሩ ክፍተቶች ታርመው በሰፊ ብልጫ 5ለ0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ እንደተቻለ አብራርተዋል። የዋልያዎቹ እንቅስቃሴ ከመጀመሪያው ጨዋታ አንፃር በሁለተኛው ጨዋታ በሁሉም የጨዋታ ክፍሎች ላይ መሻሻል መሆኑንም አክለዋል።
በቀጣይ ከሩዋንዳ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ትኩረት በመስጠት ዋልያዎቹ ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩም ተናግረዋል። በቻን ውድድር ላይ ወጣት ተጫዋቾች መጠቀምን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ አሰልጣኙ መልስ ሲሰጡም “እኛ ራሳችንን የምስራቅ አፍሪካ የተለየ ቡድን አድርገን ነው የምናስበው። ግን አይደለንም። ይሄ እንዳልሆነ ደግሞ በተግባር ያየነው ነው። በዋናውም ሆነ በዚህ ውድድር ያለን ታሪክ ያን ያህል የሚያኩራራ አይደለም። ስለዚህ በሁለተኛ ቡድናችን እንጫወት የሚያስብል ደረጃ የሚያስደርስ አይደለም።
ይሄንን ስል በሌሎች ባልተመረጡ ተጫዋቾችና አሁን በቡድኑ ውስጥ ባሉ ተጫዋቾች መካከል ሰፊ ልዩነት አለ ማለቴ አይደለም። የትኛውም ተጫዋች በማንኛውም ጊዜ በሌላ ተጫዋች ሊተካ እንደሚችል አምናለው። ግን እነዚህን ለአፍሪካ ዋንጫ ፤ እነዚህን ደግሞ ለቻን ብለን የምናስብበት ብሔራዊ ቡድን አለን ብዬ አላስብም። ሀገራችን በአፍሪካ ደረጃ ያላት ደረጃ እዛ ላይ ነው ብሎ መናገር የሚያስደፍር አይመስለኝም። ከ7 ጊዜ ሁለቴ ተካፍለናል ግን ሁለቱንም ከምድባችን ማለፍ አልቻልንም። አንደኛውን እንደውም ያለምንም ጎል ነው የመጣነው። እንደውም እዚ ውድድር ላይ ከተካፈልን ቆይተናል።
ከቻልን ሩዋንዳን አሸንፈን ወደ ቻን ለመግባት መዘጋጀት እና ውድድሩ ላይ ደግሞ አሁን ያሉትን ተጫዋቾች ሀገራቸውን እንዲያስተዋውቁ ማድረግ ነው። እኛም እየሰራን ያለነው ለዚህ ነው። ይሄንን ስል ግን ላልተመረጡ ተጫዋቾች ያነሰ ግምት ኖሮኝ አይደለም። ማንኛውም ተጫዋች ቦታውን እስከመጠነ ድረስ ወደዚህ መጥቶ መጫወት እንደሚችል አምናለው። ለራሳችን የምንሰጠው ግምት ግን ትንሽ የተጋነነ ይመስለኛል”ብለዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/ 2014