በየአራት አመቱ ውዝግብ የማይጠፋው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ የፊታችን ነሐሴ 21 እና 22 ጎንደር ላይ ይካሄዳል።
ባለፈው ግንቦት 7 /2014 ፌዴሬሽኑ ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ባጸደቀው መመሪያ ደንብ መሠረት የተመረጠው ምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስራውን ቀደም ብሎ የጀመረ ሲሆን ከትናንት በስቲያ አመሻሽም እጩዎችን ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት ለፕሬዘዳንታዊ ምርጫው ሶስት እጩዎች የሚወዳደሩ ሲሆን ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ሃያ ስድስት እጩዎች ተወዳዳሪ ሆነው ቀርበዋል።
በፕሬዘዳንታዊ ምርጫው አሁን ፌዴሬሽኑን እየመሩ የሚገኙት አቶ ኢሳያስ ጅራ ለተጨማሪ አራት አመታት ለማገልገል ከኦሮሚያ ክልል ተወክለው የሚወዳደሩ እጩ ሆነዋል። ሁለተኛው እጩ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የቀድሞ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ ቻይ ከአማራ ክልል እጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን፣ የድሬዳዋው ተወካይ አቶ ቶኩቻ አለማየሁ ከተማ ሶስተኛው እጩ ሆነው ቀርበዋል።
ምርጫውን ሰላማዊና ህጋዊ የማድረግ ስልጣኑ በጠቅላላ ጉባኤ የተሰጣቸው የአስመራጭ ኮሚቴው ባለፈው ወር ምርጫውን በተመለከተ መግለጫ መስጠቱ ይታወቃል። የህግ ጠበቃውና የምርጫ አስፈጻሚው ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሀይሉ ሞላ ሲሆኑ፣ በኮሚቴው የአዲስ አበባ ከተማን እግር ኳስ በምክትል አመራርነት ለበርካታ አመታት ያገለገሉት አቶ በለጠ ዘውዴ፣ የመድን እግርኳስ ክለብ ከፍተኛ አመራርና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መንግስቱ መሃሩ፣ የኢትዮ ኤሌክትሪክ የስፖርት ክለብን ለአመታት የመሩና በሙያቸው የተቋሙ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ኢሳያስ ደንድርና ከድሬዳዋ ወዘሪት ራህማን ያካተተ ነው።
በዚህ የምርጫ ስነስርዓት ህግ መሠረት ይግባኝ ሰሚ ሆነው የተመረጡት በአዲስ አበባ ከተማ እግርኳሰ ፌዴሬሽን የማይረሳ ስራ የሰሩትና በአቶ ሳህሉ ገ/ወልድ የአመራርነት ዘመን ፌዴሬሽኑን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት አቶ ብርሀኑ ከበደና በቅርብ አመታት ውሰጥ የወጣቶችና ስፖርት ድኤታ ሆነው ያገለገሉትና በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን በዳይሬክተርነት እየመሩ የሚገኙት አቶ አንበሳው እንየው መሆናቸው ታውቋል።
“ታሪካችንና ስማችንን ጠብቀን ምርጫው ሀቀኛ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ እንሰራለን” በማለት ባለፈው መግለጫ ላይ የተናገሩት የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሃይሉ ሞላ ናቸው። በኮሚቴው የስነምግባር መመሪያም መሰረት “እንቀድሞው ምርጫ ማንም እየተነሳ መግለጫ መስጠት አይችልም” ሲሉ አስረድተዋል።
ኮሚቴው የምርጫ ተወዳዳሪዎቹን ይፋ ካደረገ በኋላ ቅሬታ ያለው ወገን ከሐምሌ 26- ነሐሴ 2/2014 ድረስ ይግባኝ የመጠየቅ መብቱ እንደሚከበርም በመግለጫው ተጠቁሞ ነበር።
ኮሚቴው እንዳስረዳው፣ ለፕሬዝዳንትም ይሁን ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የሚወዳደር አንድ ዕጩ የአንድ ክልል ፌዴሬሽንና የአምስት ክለቦችን ድጋፍ ማግኘት አለበት። የክለቦቹንና የክልል ፌዴሬሽን ማህተም የታተመባቸው ስድስት ደብዳቤዎችም ያስፈልጋል። አንድ ክልል ዕጩ ሲልክ ሁለት ወንድና አንድ ሴት የግድ መሆኑን ቁጥሩን መጨመር እንጂ መቀነስ አይቻልም። አለበለዚያ ግን የቀረበው እጩ ከውድድር ውጪ ይደረጋል።
በዚህም መሰረት አስመራጭ ኮሚቴው እጩዎችን ይፋ ሲያደርግ በአቶ ሳህሉ ገ/ወልድ፣ በአቶ ጁነዲን ባሻና በአቶ ኢሳያስ ጅራ የፕሬዝዳንትነት ዘመን ባለፉት 12 አመታት በስራ አስፈጻሚነት የሰሩት የአፋሩ ተወካይ አቶ አሊሚራህ መሀመድ ከምርጫ ውጪ ሆነዋል። ኮሚቴው በተከታታይ ሶስት አመት ይሁን በተለያየ ጊዜ ያገለገለ እጩ በዚህ ምርጫ አይካተትም በሚለው መመሪያ መሰረት አቶ አሊሚራህን ከውድድሩ ውጪ ማድረጉ ታውቋል።
በተጨማሪም ኮሚቴው በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ቡና ስራ አስኪያጅ ሆነው እየሰሩ የሚገኙት አቶ ገዛኸኝ ወልዴ የሀረሪ ክልል የሰጣቸውን ውክልና ማንሳቱን ተቀብሎ ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ውጪ እንዳደረጋቸው ታውቋል። አቶ ገዛኸኝ “ክልሉ ውክልናዬን ማንሳት አይችልም” ቢሉም ኮሚቴው በተቀመጠው ህግ ክልሉ ውሳኔውን የመሻር መብት አለው ብሎ ውክልናውን ውድቅ አድርጎታል።
ሁለቱም ዕጩዎች ከትናንት ጀምሮ በአቶ አንበሳው እንየውና በአቶ ብርሀኑ ከበደ ለሚመራው ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ይግባኝ የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ጠቁሟል።
አቶ ገዛኸኝ የሀረሪ ክልል የሰጣቸውን ውክልና ማንሳቱ ተቀባይነት የሌለውና ህጉን ያልተከተለ በመሆኑ በምርጫው ላይ እንደምሳተፍ ርግጠኛ ነኝ” ሲሉ ከቀናት በፊት ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። እንደ አቶ ገዛኸኝ ገለጻ፣ የምርጫው ቀን የተጨመረው እጩዎችን መላክ ላልቻሉ ክልሎች ዕድል ለመስጠት እንጂ ለሌላ አይደለም፣ “ሐምሌ 7 ውክልና ሰጥተው አጥጋቢ ባልሆነ ምክንያት ሐምሌ 19 ውክልና አንስቻለሁ ማለት አይችሉም፣ ከምርጫ አስፈጻሚው ተገቢ የሆነ ምላሽን እፈልጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ገዛኸኝ እንዳስረዱት “የዛሬ አራት አመት ትግራይ ክልል አቶ ተስፋዬ ካህሳይን ወክሎ ባለቀ ሰአት ውክልናዬን አንስቻለሁ ሲል በወቅቱ የነበረው አስመራጭ ኮሚቴ አልተቀበለውም አሁን ካለው የምርጫ አስፈጻሚም ተመሳሳይ ምላሽ እጠብቃለሁ” ሲሉም ገልጸዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም