አስደናቂ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን አሰናድታ ከሳምንት በፊት ድግሷን ያጠናቀቀችው ኦሪገን ከ179 አገራት 1700 አትሌቶችን በእንግድነት ተቀብላ ሸኝታለች። በታላቁና ደማቁ ዝግጅቷም 29 አገራት የወርቅ ሜዳሊያ ይዘው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። 40 አገራት ባዶ እጃቸውን አልተመለሱም።
አንድና ከዚያም በላይ ሜዳሊያዎች ወስደዋል፡፡ 3 የዓለም ክብረወሰኖች እንዲሁም 13 የዓለም ቻምፒዮና ክብረወሰኖችም ተሰብረዋል። 150ሺ የስታድዬም ተመልካቾች፤ ከ400ሺ በላይ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮች፤ ከ41 ሚሊዮን በላይ የቪዲዮ ተመልካቾች የኦሪገንን ድግስ አድምቀው ከትናንት በስቲያ ሌሊት ጀምሮ ፊታቸውን ከሰሜን አሜሪካ ወደ ደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ኮሎምቢያ አዙረዋል። ካሊ ከሰኞ ሌሊት ጀምሮ ለቀጣይ ጥቂት ቀናት የአትሌቲክስ ቤተሰቡ አይን የሚያርፍባት ከተማ ነች።
የዓለም ከ20 አመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በካሊ መካሄድ ሲጀምር ኢትዮጵያውያን ወጣት አትሌቶች የበላዮቻቸው ባለፉት ሳምንታት በኦሪገን እንደደመቁት ሁሉ ከውድድሩ የመጀመሪያ ቀን አንስቶ በካሊ ማንጸባረቅ ጀምረዋል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በኦሪገኑ የዓለም ቻምፒዮና በወንዶች 5ሺ ሜትር የገጠማቸው አስደንጋጭ ውጤት ካሊ ላይ አልተደገመም። የነገ የርቀቱ ተተኪ የሆኑ ወጣቶቹ ኮከቦች በርቀቱ በአዋቂዎች ኢትዮጵያ ያጣችውን የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ የቻምፒዮናውን ጉዞ በድል ጀምረዋል። እጅግ አስደናቂ ፉክክር በታየበት በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያን ወጣት አትሌቶች ከዓለም የርቀቱ ከዋክብት ወጣቶች ጋር እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ አድርገው ለድል በቅተዋል። በርካታ አገራት በርቀቱ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ብቅ ባሉበት ውድድር ኢትዮጵያውያኑ ወጣት አትሌቶች አዲሱ ይሁኔና ገበየሁ በላይ በድንቅ የቡድን ሥራ እንዲሁም በራስ መተማመን ያሳዩት ጀግንነት አስደናቂ ነበር።
ሁለቱም አትሌቶች ከኬንያ፣ ዩጋንዳና ኤርትራ አትሌቶች ብርቱ ፉክክር የገጠማቸው ቢሆንም ውድድሩን በራሳቸው መንገድ ተቆጣጥረው አገራቸውን ለድል አብቅተዋል። ሁለቱም ወጣት አትሌቶች ተከታትለው ለመግባት ያደረጉት ጥረት ባይሰምርም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ፍጹም በራስ መተማመን ይነበብበት የነበረው አትሌት አዲሱ ይሁኔ በ14:03.05 ወርቁን ማጥለቅ ችሏል። ወርቅ ለማጥለቅ ድንቅ ፉክክር ያደረጉት ኤርትራውያኑ አትሌቶች የኢትዮጵያውያን ድንቅ አትሌት የአጨራረስ ብቃት መመከት ባይችሉም የብርና የነሐስ ሜዳሊያውን ከኬንያና ዩጋንዳ አትሌቶች መንጠቅ ችለዋል።
በዚህም መርሃዊ መብርሃቱ በ14:03.33 ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ሃብቶም ሳሙኤል በ14:03.67 ሰዓት ሦስተኛ ሆኖ ውድድሩን ፈጽሟል። ሜዳሊያ ውስጥ ለመግባት ትልቅ ጥረት ያደረገው ኢትዮጵያዊው አትሌት ገበየሁ በላይ በ14:04.55 ሰዓት አራተኛ በመሆን የዲፕሎማ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። ባለፈው አመት በናይሮቢ በተካሄደው ተመሳሳይ የዓለም ከ20 አመት በታች ቻምፒዮና አዲሱ ይሁኔ አራተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ኤርትራውያኑ አትሌቶች አምስተኛና ስድስተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወቃል።
በተመሳሳይ ዕለት በሴቶች መካከል በተካሄደው የ3ሺ ሜትር የፍጻሜ ውድድርም ኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ያገኘችበትን ውጤት አስመዝግባለች። ከውድድሩ አጋማሽ ጀምሮ ኬንያውያን አትሌቶች ሌሎቹን ተፎካካሪዎች ከውድድር ውጪ ለማድረግ ያሳዩትን ጥረትና እቅድ ለማክሸፍ የታገለችው ጺዮን አበበ ያደረገችው ትልቅ ትንቅንቅ በመጨረሻም የብር ሜዳሊያ ለማጥለቅ አብቅቷታል።
ኬንያዊቷ ቤቲ ቼላንጋት አስደናቂ የአጨራረስ ብቃቷን ባሳየችበት ፉክክር 9:01.03 በሆነ ሰዓት ወርቅ ከማጥለቅ ያገዳት አልነበረም። ይህች ጠንካራ ኬንያዊት የአገሯን ልጅ ናንሲ ቺሮፕን አስከትላ ለመግባት ያደረገችውን ጥረት ፉርሽ ያደረገችው ጺዮን አበበ የብር ሜዳሊያውን በ9:03.85 ሰዓት ወስዳለች። በ9:05.98 የነሐስ ሜዳሊያውን ናንሲ ቺሮፕ ስታጠልቅ እሷን ተከትላ ኢትዮጵያዊቷ ብርቱካን ወልዴ በ9:18.20 ሰዓት አራተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በወጣት አትሌቶች መካከል በካሊ የሚደረገው ፉክክር ዛሬ ሌሊት ሲቀጥልም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ1500 ሜትር ወንዶች እንዲሁም በስምንት መቶ ሜትር ሴቶች በሚያደርጉት የፍጻሜ ፍልሚያ ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን ያስመዘግባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም