በርካታ አስደሳች እና ታሪካዊ ትዕይንቶች የተስተዋሉበት የኦሪጎን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተጠናቆ ለሌላኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ቦታውን ለቋል። ትናንት የተጀመረው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ደግሞ ተረኛው የአትሌቲክስ ቤተሰቡ የትኩረት ማዕከል ሆኖ ለጥቂት ቀናት ይቆያል። ቀጣይ የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮና ጀግኖች የሚታዩበትና ወጣት አትሌቶች ከዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ወዳጆች ጋር የሚተዋወቁበት ይህ ውድድር በኮሎሚቢያዋ ከተማ ካሊ አስተናጋጅነትም ይካሄዳል።
በዚህ ቻምፒዮና ላይም ከ145 ሃገራት የተወጣጡ 1ሺ500 ወጣት አትሌቶች ተካፋይ እንደሚሆኑ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያሳያል። ኢትዮጵያም በዚህ ውድድር ተካፋ ከሚሆኑ ሃገራት መካከል አንዷ ስትሆን፤ በመድረኩ 117 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በታሪክ ከዓለም አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። የበርካታ ወጣት አትሌቶች ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በኬንያ አስተናጋጅነት በተደረገው በዚህ ውድድር ላይ 12 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሁለተኛ ብትሆንም በወርቅ ሜዳሊያዎች ተበልጣ በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷ የሚታወስ ነው።
ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን በያዘው በዚህ ውድድር ደግሞ 10 ሴቶችና 9 ወንዶች በጠቅላላው 19 አትሌቶችን ከ800 ሜትር እስከ 5ሺ ሜትር ባሉት ርቀቶች ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ። ኢትዮጵያን የሚወክለው ልኡክ በሁለት ዙር ተከፋፍሎ ወደ ስፍራው ማቅናቱ ይታወሳል። ትናንት ምሽት የወንዶች 1ሺ500 ሜትር፣ ሴቶች 800 እና 3ሺሜትር ማጣሪያ ውድድር የተደረገ ሲሆን፤ ሌሊት ላይ ደግሞ የሴቶች 3ሺ ሜትር እንዲሁም የወንዶች 5ሺ ሜትር ፍጻሜ ውድድሮች ተካሂደዋል።
ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡት ከእነዚህ ወጣት አትሌቶች አብዛኛዎቹ በዚህ ውድድር ተካፋይ የሚሆኑት ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ ሊሆን ይችላል። በአንጻሩ 15 የሚሆኑት አትሌቶች በማይጠበቅ መልኩ በኦሪጎኑ የዓለም ቻምፒዮና ሃገራቸውን ለመወከል የቻሉ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያዊት አትሌት ትገኝበታለች። በቻምፒዮናው የሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ሃገራቸውን ከወከሉት አትሌቶች መካከል ወጣቷ ሲምቦ አለማየሁ ከሳምንት በኋላ ካሊ ተገኝታለች።
የ17 ዓመቷ ሲምቦ በተያዘው ዓመት ጠንካራ ችሎታዋን ያሳየች ሲሆን፤ በፓሪሱ ዳመንድ ሊግ 9:09.19 የሆነ ሰዓት ማስመዝገቧ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ከ18 ዓመት በታች ቻምፒዮና ላይ ተመሳሳይ ብቃቷን ያስመሰከረችው አትሌቷ በኦሪጎኑ ቻምፒዮና የማጣሪያ ውድድሩን አምስተኛ ሆና ብታጠናቅቅም ለፍጻሜው መብቃት አልቻለችም። ይሁንና አትሌቷ ካላት ልምድ በመነሳት በዚህ ቻምፒዮና ውጤታማ ልትሆን እንደምትችል ይጠበቃል።
ከሲምቦ ባሻገር በውድድሩ ላይ የሚካፈሉ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር ከማድረግም ባለፈ እንደለመዱት በርካታ ሜዳሊያዎችን ጠራርገው ይወስዳሉ በሚል ይጠበቃል። ይህም ግምት በየርቀቱ ተሳታፊ የሚሆኑ አትሌቶች ካላቸው ምርጥ ሰዓት በመነሳት ነው። ለአብነት ያህል በ800 ሜትር ወንዶች ኤርሚያስ ግርማ የግሉ ፈጣን ሰዓት 1:44.36 ሲሆን፤ ይህም በርቀቱ ቀዳሚው አትሌት ያደርገዋል። አትሌቱ በ1ሺ500 ሜትርም በተመሳሳይ ፈጣን አትሌት ሲሆን ምርጥ ሰዓቱ 3:36.28 ነው። ይህም አትሌቱ በሁለቱም ርቀት ውጤታማ የመሆን እድሉ የሰፋ እንደሚሆን በግልጽ የሚያመላክት ነው።
የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ውድድሩን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም ‹‹ይህ ቻምፒዮና አዲስ ብቃት የሚታይበት ነው፤ በመሆኑም ለሁላችንም ትልቅ ውድድር ነው። እአአ በ2002 ጃማይካዊው ዩሴን ቦልት ከዚያ ቀደም ያልታየ ችሎታው ገሃድ የወጣበት ነበር። እአአ 2015 ደግሞ እንደ ሲድኒ ማክላገሊን እና ሞንዶ ዱፕላንቲስ የተባሉትን ወጣት አትሌቶች ችሎታ አሳይቶናል። እነዚሁ አትሌቶች በኦሪጎን ዓለም ቻምፒዮና የክብረወሰን ባለቤት በመሆን ስኬታማ ሆነዋል›› ማለታቸውን ድረገጹ አስነብቧል።
ፕሬዚዳንቱ አስከትለውም የዚህ ውድድር አስፈላጊነት አብዛኛዎቹ አትሌቶች ከወጣትነት ወደ አዋቂነት የሚሸጋገሩበት ዕድል አናሳ በመሆኑ እንደ ድልድይ ለመሆን እንደሆነም ገልጸዋል። በስፖርቱ ብቃት ያላቸውን ወጣት አትሌቶች ከመለየት ባለፈ ማበራታታትም የውድድሩ አንዱ አላማ ነው። የስፖርት ባለሙያዎች በስፖርቱ በሶስትና አራት ዓመት ውስጥ እየታየ ያለውን ለውጥ የሚመለከቱበት መድረክ መሆኑን እንዲሁም በዚህ ውድድር ላይ የሚታዩ ወጣት አትሌቶች በ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ የሚደምቁበት መድረክ እንደሚሆን አመላካች መሆኑን ገልፀዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም