በፈርቀዳጅነታቸው የማይደበዝዝ ታሪክ ካኖሩ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች መካከል አንዱ ሻምበል እሸቱ ቱራ ናቸው። እአአ በ1980 የሞስኮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ሁለት የወርቅና ሁለት የነሃስ በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን ባስመዘገበችበት በዚህ ውድድር እርሳቸው በ3ሺ ሜትር መሰናከል የነሃስ ሜዳሊያ ነበር ያስመዘገቡት። ይሁንና ይህ ታሪካዊ ድል በኦሊምፒክም ይሁን በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሳይደገም ዘመናትን ሊሻገር ግድ ብሎ ነበር።
ለንደን እአአ በ2012 ባሰናዳችው ኦሊምፒክ ደግሞ በሴቶች የመጀመሪያው በርቀቱ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሁለተኛው የብር ሜዳሊያ በአትሌት ሶፊያ አሰፋ ተመዘገበ። ከዓመት በኋላም በሞስኮ በተካሄደው የዓለም ቻምፒዮና አትሌቷ የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች። በርቀቱ በድጋሚ ሜዳሊያ ለማግኘት ዓመታት ከተቆጠሩ በኋላም በ2019 የዶሃ ዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ በአትሌት ለሜቻ ግርማ ተገኝቷል። ይህንኑ ድል በቶኪዮ ኦሊምፒክ የደገመው ለሜቻ ከሰሞኑ በተጠናቀቀው የኦሪጎን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሶስተኛውን የብር ሜዳሊያ ማሳካት ችሏል።
አስደሳች በሆነ መልኩም ኦሪጎን ላይ በሴቶች ተመሳሳይ ውድድር የብር እና የነሃስ ሜዳሊያ በአትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው እና መቅደስ አበበ ተመዝግቧል። ይህም በርቀቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ያስመዘገበው ትልቁ ውጤት ነው። ይህንንም ተከትሎ የ3ሺ ሜትር መሰናክል ተወዳዳሪ እና በርቀቱ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት ሻምበል እሸቱ ቱራ ለአዲስ ዘመን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በእሳቸው መሰረት ፈርቀዳጅ የሆኑበት የዚህ
ርቀት ውጤታማነት እምብዛም የሚባል ሆኖ ቢቆይም በጊዜ ሂደት ተስፋ እያሳየ በመምጣቱ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ። በዚሁ ስሜት ውስጥ ሆነውም በኦሪጎን ሲወዳደር የቆየውን ብሄራዊ ቡድን በአካል ተገኝተው አቀባበል አድርገውለታል።
በዓለም ቻምፒዮና መድረክ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ውጤት ማግኘቷ የሚያስደስት ሲሆን፤ አትሌቶችም በውድድሩ ላይ ያደርጉ የነበሩት እንቅስቃሴ፣ ህብረታቸው እንዲሁም መተጋገዛቸው እጅግ አስደሳች እንደሆነ ሻምበል እሸቱ ያስረዳሉ። ‹‹ይህ
የዓለም ቻምፒዮና ልዩ ነበር›› ሲሉም ይገልጹታል። ሁሉም ርቀቶች ላይ አትሌቶች ያሳዩ የነበረው ጥረት አስገራሚ ሲሆን፤ በተለይ የሴቶች 10ሺ ሜትር ውድድር አስጨናቂ ነበር። ሁለት ሜዳሊያ የተገኘበት የሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክልም ጠንካራ ከነበሩት ፉክክሮች መካከል አንዱ ነበር። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እየታየች ያለችው ወጣቷ አትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው በርትታ ከሰራች ስኬታማ እንደምትሆንና የብር ሜዳሊያውም ወደ ወርቅ እንደምትቀይረው አንጋፋው አትሌት ያላቸውን ተስፋ አጋርተዋል።
ቀደም ሲል ኬንያ እንደ ባህል ስፖርት ትቆጥረው በነበረው በዚህ ርቀት ኢትዮጵያ በጥቅሉ ሶስት ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች። በወንዶች በኩልም የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው አትሌት ለሜቻ ግርማ ካለው ተክለሰውነት እንዲሁም የአሯሯጥ ስልት ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንደሚችል አመላካች መሆኑን ሻምበል እሸቱ ተናግረዋል። ያሁኑን ጨምሮ በሁለት ዓለም ቻምፒዮናዎች እንዲሁም ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። በእርግጥ የውድድር ጫና ሲበዛ ስኬታማ መሆን አይቻልም፤ ይሁንና በቀጣዩ ኦሊምፒክ ወደ ወርቅ መቀየር አለበት። ለዚህም በቁጭት ተነሳስቶ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባው ምክራቸውን ለግሰዋል።
ይህም በርቀቱ ለወደፊት ያለውን ተስፋ ብቻም ሳይሆን፤ በበርካታ አትሌቶች በሚፈራው 3ሺ መሰናክል ላይ ከተሰራ አሸናፊ መሆን እንደሚቻል ያመለካከት ለውጥ ማምጣት የቻለ እንደሆነም አሰልጣኙ ያስገነዝባሉ። ስለዚህም ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ትታወቅበትና ስኬታማ እንደነበረችባቸው የረጅም ርቀት ሩጫዎች ሁሉ በዚህ ርቀትም ስሟ የሚጠራበትና ጠንካራ ተፎካካሪ አትሌቶች እንደሚኖራት የሚያመላክት እንደሚሆንም ያሰምሩበታል።
ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ካላት የወጣቶች ቁጥር እንዲሁም የታዳጊ ስፖርት ማሰልጠኛ ፕሮጀክቶች፣ አካዳሚዎችና ክለቦች አንጻር ውጤታማ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው። በመሆኑም እንደ አካዳሚ ባሉት ትልልቅ የማሰልጠኛ ተቋማት በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም ሻምበል እሸቱ ምክራቸውን አስቀምጠዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2014