አገራችን አሁን ያለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንድትገኝ በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ ተፅዕኖ የማሳደር አቅም ያላቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል ብንል ማጋነን አይሆንም። የፖለቲካ ቡድኖች እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ተፅዕኖ የማሳደር አቅም ያላቸው ግለሰቦች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተስፋ ሰጪ ሀሳቦችን ሲሰነዝሩ እየተስተዋለ ነው።
የአገራችን ችግሮች መፍትሄ ኃይል እና አመጽ እንደሆነ ሲናገሩ የነበሩ አካላት ከተሳሳተው መንገዳቸው በመመለስ ውይይትና ድርድር የችግሮች መፍትሄ እንደሆነ ሲናገሩ እያዳመጥን ነው። የፖለቲካ ግብ በወታደራዊ እርምጃ እና በትጥቅ ትግል ብቻ ለማሳካት ጥረት መደረግ እንደሌለበትም እየተናገሩ ነው። የትጥቅ ትግሎችን እና ወታደራዊ መፍትሄዎችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሲተቹ እና ሲያወግዙ እየታዩ ነው። መግለጫዎችንም ሲያወጡ እያየን ነው።
ጽንፍ የረገጠ ፖለቲካ ሲያራምዱ የነበሩ ግለሰቦች ከዚህ በፊት ከሚታወቁበት ጽንፍ ከረገጠ አመለካከታቸው መለስ ብለው ወደ መሃል ፖለቲካ የመምጣት አዝማሚያዎችን እያሳዩ ነው። የራሳቸውን ብሄር ጉዳይ ብቻ አንግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት ከራሳቸው ብሄር ባሻገር ስለሌሎች ብሄሮች የመብት ጥያቄዎችም ሲናገሩ እየተደመጡ ነው። የብሄራቸው የመብት ጥያቄዎች ብቻውን ምላሽ ሊያገኝ እንደማይችል እና የአንዱ ብሄር ጥያቄ ተቀብሮ የሌላው ምላሽ ሊያገኝ እንደማይችል እያነሱ ነው። ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሄሮች እጣ ፈንታ በእጅጉ የተሳሰረ መሆኑን መገንዘባቸውን የሚያሳይ ነው።
ይህ ይበል የሚያሰኝ ነው። ይህ ሁሉ ውድመት እና መፈናቀል ሳይከሰት መሰል ሀሳቦች የበላይነት አግኝተው ቢሆን እጅግ ተመራጭ ነበር። የበርካቶችን ሞት፣ ስቃይ፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት ማስቀረት ይቻል ነበር። አገሪቱንም አሁን የገባችበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ቅርቃር ውስጥ እንዳትገባ ማድረግ ይቻል ነበር። አገሪቱ የጀመረችውን የልማት፣ የሰላም እና የብልጽግና ጉዟን እንድታፋጥን ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችል ነበር። የሆነው ሆኖ ለሰላም መቼም አይረፍድምና በየአቅጣጫው ይሰሙ የነበሩ የጦርነት እና የመብት ጥያቄዎችን በኃይል ስለማስፈጸም ሲነገሩ የነበሩ ንግግሮች ጋብ ብለው ስለ ድርድር፣ ስለ ውይይት መወራት መጀመሩ በራሱ የሚያስደስት ነው።
መንግስትም ለአገር ዘላቂ ሰላም ሲባል ትጥቅ ካነገቡ ኃይሎች ጋር ጭምር ድርድር ለማካሄድ ፍላጎት እንዳለው እየገለጸ ነው። በሶስተኛ ወገን አማካኝነት ሲካሄዱ የነበሩ ውይይቶችን በቀጥታ ለማካሄድ ፍላጎት እንዳለው ፍንጭ እያሳየ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በርካታ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ለአገር ሰላም ሲባል ትጥቅ ካነገበው ኃይል ጋር ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን እየገለፁ ነው። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ተደራዳሪ ቡድንም ይፋ አድርጓል። ይህ ከአንድ ኃላፊነት ከሚሰማው መንግስት የሚጠበቅ ትልቅ እርምጃ ነው። ጦርነት የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት መፍትሄ ሆኖ አያውቅምና።
ስለሰላም፣ ስለ እርቅ፣ ስለድርድር እና ስለ ውይይት እየተሰጡ ያሉ መግለጫዎች እና ቃለ ምልልሶች የአገሪቱን የፖለቲካ ትርክት ጭምር እየቀየሩ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው የሰላም ተስፋ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም እያደረገ ነው። ለሁለት ዓመት ገደማ በኢትዮጵያ ላይ ሲያሳርፉት የነበረውን ጫና የመቀነስ አዝማሚያዎችንም እያሳዩ ነው።
ሰላም በመፈለግ ብቻ እውን የሚሆን ነገር አይደለም። በቃለ ምልልሶች እና በመግለጫዎች ስለ ሰላም፣ ስለ ድርድር፣ ስለ እርቅ እና ስለ ውይይት እየተሰበኩ ያሉ ስብከቶች ወደ መሬት መውረድ አለባቸው። እነዚህ አካላት በመግለጫ ደረጃ ስለ ሰላም፣ ስለ ድርድር፣ ስለ ውይይት እና ስለ እርቅ ከማውራት ባሻገር፤ ሰላም ድርድር እና እርቅ የሚበጁ እውነተኛ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመር አለባቸው። የተለያዩ አካላት ለድርድር እና ለውይይት ቅድመ ሁኔታዎችን ከማቅረብ በመቆጠብ ምክክሩ ፍሬ እንዲያፈራ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው።
የፌዴራል መንግስት ለድርድር ዝግጁ መሆኑን እና ተደራዳሪ ቡድንን እንዳሳወቀው ሁሉ በሌላ ወገን ያለው ኃይልም ተደራዳሪ ቡድኖችን በማሳወቅ የድርድር ሂደቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጀምሮ አለመግባባቶች እልባት እንዲያገኙ እና አገሪቱ ወደ ሰላም፣ ልማት እና ብልጽግና ፊቷን እንድታዞር የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው። በአንድ በኩል ስለ ድርድር እና ስለ ውይይት እየተነገረ በሌላ በኩል የጦርነት ነጋሪቶችን የሚጎስሙ አካላት ከተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል። የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙትን ህዝብና መንግስት አደባ ሊያስገዛቸው ይገባል። በተለይም ህዝቡ ጦርነት ናፋቂዎችን ባለመስማት የተጀመረው የድርድር፣ ውይይት እና የምክክር ጥረቶች ውጤት ማፍራት እንዲችል የበኩሉን ሊወጣ ይገባል።
በተጨማሪም መንግስት ያቋቋመው አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዲችል ሁሉም አካል አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ አለባቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ መሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግና ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠር ሂደት እንዲመራና እንዲያስተባብር የተቋቋመው የምክክር ኮሚሽን የተለያዩ አላማዎችን አንግበው በፖለቲካው መድረኩ ላይ ያሉ ኃይሎችና ልሂቃን እንዲሁም ሕዝቡ ውስጥ ያሉ ጥያቄዎችና ሐሳቦችን መሰረት በማድረግ እንዲቀራረቡ በማድረግ ለአገራዊ አንድነት ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች እገዛ ወሳኝ ነው።
አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለብዙ አስርት ዓመታት ምላሽ ሳያገኙ እና መግባባት ሳይደረስባቸው የቆዩ ዋና ዋና ጉዳዮችን በማንሳት አሳታፊ እና ተከታታይ አገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ መግባባት ላይ መድረስ አንዲቻል ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎችን ባሳተፈ መንገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ መግባት ይጠበቅበታል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2014