ሁሌም በዓለም ታላላቅ የስፖርት መድረኮች ኢትዮጵያን የሚያኮሯት ጀግኖች አትሌቶች ድል አድርገው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ሕዝብና መንግሥት ደማቅ አቀባበል ያደርግላቸዋል። የአቀባበሉ ድምቀት አትሌቶቹ እንዳስመዘገቡት የውጤት ደረጃና ክብደት ልዩነት ቢታይበትም አቀባበልና ሽልማት ቀርቶ አያውቅም። በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አራት ወርቅ፣አራት ብርና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያ በማስመዝገብ አሜሪካን ተከትሎ ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ ሆኖ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ከኦሪገን ሲመለስ ባለፉት ጥቂት ቀናት የተደረገለት አቀባበል በታሪክ እጅግ ደማቅ ተብሎ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከድላቸው ማግስት እንዲህ አይነት ደማቅ አቀባበል ሲደረግላቸው የዘንድሮው በግዝፈቱና በድምቀቱ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሊቀመጥ እንደሚችል ብዙዎች ይስማማሉ። ይህ የሰሞኑ ደማቅ አቀባበል በታሪክ ሁለተኛ ከሆነ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የትኛው ነው? ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድ ድምጽ ምላሹ የሲድኒ ኦሊምፒክ አቀባበል እንደሚሆን አያጠራጥርም። በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችንም ያንን ታላቅ የጀግኖች አትሌቶች አቀባበልና በወቅቱ የነበረውን አንዳንድ ኩነት በጥቂቱ እንመልከተው።
እለቱ አርብ ነው፡፡ ከሃያ ሁለት ዓመታት በፊት። አዲስ አበባ በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማዎች አሸብርቃለች፡፡ ሚሊዮኖች ወደ አደባባይ ወጥተዋል፡፡ መንግሥት ይህንን ቀን ሰራተኞች ወደ ስራ እንዳይሄዱ ፈቅዷል፡፡ ትምህርት ቤቶች እና ኮሌጆችም ተዘግተዋል፡፡ ሁሉም ላይ የአሸናፊነት፣ የትኛውንም ነገር መከወን ይቻላል የሚል ስሜት ይነበባል፡፡
በአውስትራሊያ ሲድኒ ኢትዮጵያን ወክለው የሄዱት 28 አትሌቶች፣ ሶስት ቦክሰኞች እና ሌሎች ልዑካንን የያዘው አውሮፕላን በልዩ ጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡
አራት ወርቅ፣ አንድ ብር እና ሶስት ነሀስ የምንጊዜም የኢትዮጵያ ትልቁ የኦሊምፒክ ድል ነው፡፡ በአፍሪካ ቀዳሚ ሆናለች፤ በአትሌቲክስ የሜዳሊያ ሰንጠረዡ ኢትዮጵያ አሜሪካንን ተከትላ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡ ብዙ ዋጋ ከፍለው፣ አንብተው፣ ቆስለው፣ ወድቀው እና ተነስተው ሰንደቅዓላማዋን በስስት ለብሰው የአሸናፊነትን እና የይቻላል መልዕክትን ለኢትዮጵያውያን ጽፈው አትሌቶቻችን ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡
ይሔንን ውለታ መመለስ የፈለጉ ኢትዮጵያውንም አዲስ አበባን ጠጠር መጣያ እስኪጠፋ ትንፋሽ አሳጥተዋታል፡፡ ባለድል አትሌቶችን የያዘው አውሮፕላን ወደ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እየተቃረበ ነው፡፡ ተዋጊ ጀቶች ለክብራቸው ከፍ ብለው በመብረር አውሮፕላኑን ያጅቡ ጀመር፡፡ ሁለት ሔልኮፕተሮችም የአየሩን ሰልፍ በክብር ከፊት እየመሩት ነው፡፡
አትሌቶቹ በሚወዷት ሀገራቸው ይሄን አይነት የክብር አቀባበል እንደሚጠበቅባቸው የጠረጠሩ አይመስልም፡፡ ከአውሮፕላን ከወረዱባት ደቂቃ ጀምሮ የማይደገም የሚመስል አቀባበል ነበር የጠበቃቸው፡፡ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር በአውሮፕላን ማረፊያ ከተገናኙ በኋላ፤ በፕሬዚዳንታዊ ሊሞዚኖች እና በክፍት አውቶብሶች ታጅበው ስሜቱን መግለጽ ወዳቃተው ሕዝብ ጉዞ ጀመሩ፡፡
ከዚያ በኋላ ያለውን እያንዳንዱን ትዕይንት መግለጽ እጅግ ከባድ ነው፡፡ “ይቻላል!” የሚለውን የማሸነፍ ስሜት የፈጠረውን፣ ሀገር መውደድን፣ ኢትዮጵያዊነት ያለውን ውድ ዋጋ ያንጸባረቀውን ያንን ድል እና የተመልካቹን ስሜት በምንም መንገድ መግለጽ አይቻልም፡፡
ባለድል ኮከቦችም የሚያዩትን ማመን አልተቻላቸውም፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠረው ሕዝብም አትሌቶችን የሚገልጽበት ድምጽም ትንፋሽም አጥሮታል፡፡ “ይሔንን ማመን ያቅታል፡፡ አቀባበል ጠብቄያለሁ፣ እንዲህ ይሆናል ብዬ ግን በፍጹም አልገመትኩም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ኢትዮጵያ ለእኔ ሁሉም ነገሬ ማለት ነው፡፡ እኛ ዕደለኞች ነን!” ሲል ከባለድሎቹ አንዱ የነበረው ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ታላቁን አቀባበል ያስታውሰዋል።
ሁሉም የሆነው ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊነት ክብር ነው፡፡ በኦሊምፒክ የቅብብሎሽ ታሪክ ሁሉ የማይቻለው የተቻለው፣ የማይፈጸመው የተፈጸመው… ሀገርን ለማንገስ በተደረገ ፍልሚያ ነው፡፡
ከህመም ጋር ታግለው ያሸነፉት፤ ሆዳቸውን ይዘው የሮጡት፤ ለመሮጥ ብቻ አይደለም፣ ለመቆም የሚከብድ የዕግር ህመም ችለው አንገት ለአንገት ተናንቀው የድል ክር የበጠሱት፡ ለኢትዮጵያዊነት ከፍ ማለት ነው፡፡ የአትሌቲክስን ረጅሙንም ፈታኙንም ውድድር በባዶ እግር ሮጠው ያሸነፉት ሀገራቸውን የአሸናፊነት ምልክት ለማድረግ ነው፡፡
ከአበበ ቢቂላ የአሸናፊነት ታሪክ የተነሳ፣ የአትሌቲክስ የማሸነፍ መንፈስ ሲድኒ ላይ እስካሁንም አቻ ወዳላገኘ ከፍታ ተንደረደረ፡፡ ሚሊዮኖች በሲድኒ ገድል ከጫፍ ጫፍ ከማንባታቸው ቀድሞ… ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር ካደረገችው ደም አፋሳሽ ጦርነት እና ባጋጠማት ረሀብ ከተፈጠረባት ድብታ በሲድኒ ኦሊምፒክ ድል ፈገግ ከማለቷ አስቀድሞ… የአሊምፒክ ልዑክ ቡድኑም ወደ አውስትራሊያ ከማቅናቱም አስቀድሞ… ብዙ ነገሮች ሆነዋል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም