ሩስያ ኤስ-400 (S-400) የተባሉ ሚሳይሎችን ክሪሚያ ላይ ለማስቀመጥ እቅድ እንዳላት መግልጿ ጎረቤቷን ዩክሬንን አስቆጥቷል፡፡ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሩስያን እቅድ አውግዟል፡፡ ረቡዕ ዕለት አንድ የሩስያ ጦር ባልደረባ አገራቸው ኤስ-400 (S-400) ከመሬት ወደ አየር ተወንጫፊ ሚሳይሎችን በቀጣይ ሳምንታት በክሪሚያ እንደምታስቀምጥ ገልጸዋል፡፡
በዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ ዳይሬክተር የሆኑት ኦሊክሲይ ማኬዬቭ የሩስያ እቅድ ለዩክሬን ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ባሕር ቀጣና ጭምር አደገኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የሚሳይሎቹ ዒላማን የመምታት አቅም የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (North Atlantic Treaty Organization – NATO) አባል የሆኑ የጥቁር ባሕር ቀጣና አገራትን ጭምር እንደሚያሰጋም ገልጸዋል፡፡
ሞስኮ ክሪሚያን ከ2014 ጀምሮ የጦር መሳሪያዎች ማከማቻ እንዳደረገቻትና ሩስያ በግዛቲቱ ውስጥ ካከማቻቸው መሳሪያዎች መካከል ኑክሌር ተሸካሚ የጦር አውሮፕላኖች እንደሚገኙበት ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይህ ዕርምጃ የሩስያ የጦር መሳሪያዎች ተጨማሪ ርቀት ተጉዘው ዒላማ መምታት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ጥቁር ባሕርን አልፎ እስከ ሜዲትራኒያን ባሕር ድረስ የዘለቀ ርቀት ሊጓዙ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከጥቁር ባሕር አልፎ የደቡብ አውሮፓን፣ የመካከለኛው ምሥራቅንና የሰሜን አፍሪካን ሰላም አደጋ ላይ ይጥላል›› ብለዋል፡፡
የሩስያና የዩክሬን የሰሞኑ ፍጥጫቸው መነሻው ሩስያ ከጥቁር ባሕር ወደ አዞቭ ባሕር ሲጓዙ የነበሩ ሦስት የዩክሬን የጦር መርከቦችን ኬርች የባሕር ሰርጥ ላይ ማገቷ ነው፡፡ ይህ የሩስያ ድርጊት ዓለም አቀፍ ተቃውሞን አስነስቶባታል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩስያን ድርጊት አውግዘው ከሩስያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ሊያደርጉት የነበረውን ውይይት ሊሰርዙት እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ፣ ሩስያ መርከቦቹን ያገተችው ዩክሬን በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የባሕር ሕግ በመተላለፋቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ የአሜሪካ ድርጊት ክፉኛ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም አሜሪካ ዩክሬን በሩስያ ላይ ጦርነት እንድትከፍት ከማበረታታት ይልቅ ዩክሬንንና እ.አ.አ ከ2014 ጀምረው የዶኔትስክንና ሉሃንስክ ክልሎችን ተቆጣጥረው የሚገኙትን አማፂ ኃይሎችን እንዲያደራድሩ ጠይቀዋል፡፡
የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ዩሪ ዩሻኮቭ በበኩላቸው፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሚያደርጉት ውይይት ለሁለቱም አገራት ብሎም ለመላው ዓለም ሰላም ጠቃሚ እንደሆነ ጠቁመው፣ ‹‹ውይይቱን እሰርዘዋለሁ ብሎ ማስፈራረቱ ተቀባይነት የለውም›› ብለዋል፡፡
ኦሊክሲይ ማኬዬቭ፣ ‹‹ማንኛውም ዩክሬናዊ የሩስያን ውሸት መስማት አይፈልግም፡፡ መሬታችንን መጠበቅ የሚያስችል በቂ አቅም አለን፡፡ የአሜሪካና የአወሮፓ ኅብረት ድጋፍም አለን›› በማለት ለሩስያ ባለስልጣናት ክስ ማስጠንቀቂያ አዘል ማስተባበያ ሰጥተዋል፡፡
ዩክሬን ድንበሬን ከሩስያ ወረራ ለመከላከል በሚል ምክንያት ከ27ቱ የአገሪቱ ክልልች ውስጥ በ10 ክልሎች ላይ ተግባራዊ የሚሆንና ለ30 ቀናት ያህል የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ክሪሚያ ውስጥ የሚገኝ አንድ የሩስያ ፍርድ ቤት በታገቱት መርከቦች ላይ የነበሩት 24 ዩክሬናውያን በእስር እንዲቆዩ ወስኗል፡፡
የዩክሬን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች በ2014ቱ የዩክሬን አብዮት ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ ሩስያና ዩክሬን የለየለት ፖለቲካዊ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ሩስያ የዩክሬን ግዛት አካል የነበረችውን ክሪሚያን በጦር ኃይልና በሕዝበ ውሳኔ ወደ ግዛቷ ከቀላቀለች ወዲህ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል፡፡ የሰሞኑ ፍጥጫም ከሁለቱ አገራት በተጨማሪ ለወትሮውም ከሩስያ ጋር ሆድና ጀርባ የሆኑትን አሜሪካንና የአውሮፓ ኅብረትን ከዩክሬን ጎን አሰልፎ ወደ ወታደራዊ ግጭት እንዳያመሩ ተሰግቷል፡፡
አንተነህ ቸሬ