ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መወዳደር የጀመረችው ከመነሻው መሆኑን ሰነዶች ያሳያሉ። የፊንላንዷ ሄልሲንኪ እአአ 1983 ባዘጋጀችው የመጀመሪያው ቻምፒዮና ላይም ከአምስቱ ውድድሮች በማራቶን አትሌት ከበደ ባልቻ ባስመዘገበው ብቸኛው የብር ሜዳሊያ ኢትዮጵያ ከዓለም 15ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀችው። ከሩጫ ውድድሮች ሁሉ ረጅሙና ከፍተኛ ጥንካሬን በሚጠይቀው በዚህ ርቀት በድጋሚ ድል ለማስመዝገብም ሰባት ቻምፒዮናዎችን መታገስ ነበረባት።
እአአ በ2001 ኤድመንተን ላይ የምርጥ ማራቶን አትሌቶች መፍለቂያ የሆነችው ኢትዮጵያ አትሌት ገዛኸኝ አበራ ባጠለቀው የወርቅ ሜዳሊያ በርቀቱ ሁለተኛው ሆኖ ተመዘገበ። እስካሁን በተካሄዱት 18 ቻምፒዮናዎችም በአጠቃላይ ኢትዮጵያ 15 ሜዳሊያዎች (5 የወርቅ፣ 6 የብር እና 4 የነሃስ) ሲኖሯት፤ ከእነዚህ መካከል 12 የሚሆኑትን በማስመዝገብ ወንድ አትሌቶች የበላይነቱን ይይዛሉ።
የበዛ ጽናትን በሚፈልገውና እልህ አስጨራሽ በሆነው የማራቶን ውድድር፤ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተጠናቀቀው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናም 3 ሜዳሊያዎችን በሁለቱም ጾታ በማስመዝገብ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ደረጃ ልትይዝ ችላለች። በወንዶች በኩል አትሌት ታምራት ቶላ እና ሞስነት ገረመው ተከታትለው በመግባት የወርቅና ብር ሜዳሊያዎቹን ሲያጠልቁ፤ በሴቶች ደግሞ ብቸኛዋ እንቁ አትሌት ጎተይቶም ገብረስላሴ ወርቁን በእጇ በማስገባት ቻምፒዮን ሆናለች።
በዚህ ርቀት በተለይ በወንዶቹ በኩል ተከታታይ ድል ሲገኝ (በዶሃ እና ኦሪጎን ቻምፒዮናዎች የወርቅና ብር ሜዳሊያዎች)፤ የኦሪጎኑን ጨምሮ በአምስት ተከታታይ ቻምፒዮናዎች ላይ ደግሞ አምስት የብር ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ የሚፎካከራት የለም። ይህም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በመድረኩ ባስቆጠረቻቸው ሜዳሊያዎች ብዛት ኬንያን ተከትላ በሁለተኛነት ትቀመጣለች። በዚህ ስኬት ውስጥ ከፍተኛ ስኬት ያላቸው አትሌቶች ደግሞ ታምራት ቶላ እና ሞስነት ገረመው ናቸው። ሞስነት ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን ሲወስድ፤ ታምራት ደግሞ የወርቅና የብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት የጀግንነት ገድሉን ከሌላኛው አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ ጋር ይጋራል።
የዚህ ክብር ባለቤት እንዲሁም ኦሪጎን ላይ ከአሸናፊነት ባለፈ የቻምፒዮናውን ክብረወሰን ያሻሻለው አትሌት ታምራት ቶላ፤ ለኦሪጎኑ አጠቃላይ ድል አስቀድሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክቱን ይገልጻል። በማስከተልም ‹‹ሰው በሚሰራበት ነገር ላይ ስኬታማ ለመሆን ጥረት ያደርጋል፤ እኛም ወደ ኦሪጎን የሄድነው ለዚሁ ሲሆን ስኬታማም ሆነናል። በዚህ የዓለም ቻምፒዮና ክብረወሰን መስበር ብቻም ሳይሆን ማሸነፍ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። ከቡድኑ አባላት ጋር በጋራ በሰራነው ስራ ይህ ውጤት ሊመዘገብ ችሏል። ለዚህም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽናችንን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉን፣ አሰልጣኞቻችንን እንዲሁም ከእኛ ጋር የነበሩትን ሁሉ ላመሰግን እወዳለሁ›› ብሏል።
የሪዮ ኦሊምፒክ የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤቱ ታምራት የስኬቱ ምስጢር ከአምስት ዓመት በፊት እአአ በ2017 በተካሄደው የለንደን ዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ማስመዝገቡን ተከትሎ በቀጣይ ወርቅ ማምጣት እንዳለበት በማመን ጠንክሮ በመስራቱ እንዲሁም በወቅቱ የሰራቸውን ስህተቶች በማረሙ እንደሆነም ይናገራል። እንዳሰበውም ተሳክቶለት የወርቅ ሜዳሊያውን ማጥለቅ በመቻሉ ደስተኛ ሆኗል። ቀጣይ ዕቅዱም ከሁለት ዓመት በኋላ በሚካሄደው የፓሪሱ ኦሊምፒክ ለአገሩ ተመሳሳይ ስኬት ማስመዝገብ መሆኑንም አመላክቷል።
የኦሪገኑ የማራቶን ውድድር ፈታኝ እንደነበር የሚገልጸው የብር ሜዳሊያ ባለቤትና ሌላኛው የኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ የሆነው አትሌት ሞስነት ገረመው፣ በዓለም ላይ ፈጣን እና ምርጥ ከሆኑ የማራቶን ሯጮች መካከል በቀዳሚነት ይቀመጣል። በኦሪጎን ከጓደኞቹ ጋር በመሆን አገሩን ቀዳሚ ለማድረግ አቅዶ በተጓዘው መሰረት ውጤታማ መሆን ችሏል።
ፈታኝ የነበረውን ውድድርም በድል በማጠናቀቅ ቡድኑ ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ሆኖ በማጠናቀቁ ደስተኛ መሆኑን ጠቅሶ ለኢትዮጵያ ህዝብም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል። በሁለቱም ጾታ በዚህ ርቀት ውጤት እንዲገኝ ምክንያት የሆነው በቡድን ተሳስቦ መስራትና በቡድኑ ውስጥ በነበረው ፍቅር መሆኑንም ይገልጻል። የማራቶን ቡድኑ ወደ ኦሪጎን ከመጓዙ አስቀድሞ በርቀቱ ውጤት መምጣት እንዳለበት በተነጋገረው መሰረት ስኬታማ መሆን እንደቻሉም አትሌቱ አስረድቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 ቀን 2014 ዓ.ም