የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ትናንት የኢትዮጵያዊያን የሃገር ፍቅር ስሜት በግልጽ የተንፀባረቀባቸው ነበሩ። ደምን በሚያሞቀው የጀግኖች አትሌቶች አቀባበል መርሃግብር ላይ ህዝቡ ማልዶ አደባባይ በመውጣት ደስታውን ሲገልጽ ታይቷል። ህጻናት፣ ወጣቶችና አረጋዊያን ሳይቀሩ ጀግኖች አትሌቶች በሚያልፉባቸው ጎዳናዎች ግራና ቀኝ በመቆም በባንዲራ አሸብርቀው፣ በድል ዜማዎች ታጅበው በደስታ እንባ ጭምር ለእንቁዎቹ አትሌቶች ፍቅር የተሞላበት የጀግና አቀባበል አድርገዋል።
ለመላው አፍሪካዊያን የነጻነት ምልክትና ተምሳሌት የሆነው የኢትዮጵያ ባንዲራ በዓለም አደባባይ ደግሞ በአትሌቶቿ ድል በየዘመናቱ እየተውለበለበ ዘመናትን ተሻግሯል። ስለ ሰንደቅ አላማ ፍቅር እንዲሁም ስለ ሃገር ክብር ሲሉ በፈጣን እግሮቻቸው እየተምዘገዘጉ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያደመቁ ጀግኖች ዛሬም እንደ በፊቱ የሞቀና የደመቀ አቀባበል ከሕዝብ አግኝተዋል። አንድነት፣ መተባበርና በቡድን መስራት መለያቸው የሆነው እነዚህ ጀግና አትሌቶች አሁንም በድላቸው ህዝባቸውን ማኩራት ሃገራቸውንም ከማስጠራት ወደኋላ አላሉም። አንዳቸው ለሌላኛው ቅድሚያ እየሰጡ ዛሬም እንደ ትናንቱ መደማመጥን፣ መከባበርን እንዲሁም ነገሮችን በምክክር መከወንን በኦሪገን አስ ተምረዋል።
አሜሪካ አዘጋጅ በሆነችበትና በኦሪጎን ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ስሟ በተደጋጋሚ በክብር ሊጠራ ችሏል። 179 ሃገራት በተሳተፉበት የአትሌቲክስ ስፖርት ትልቁ ውድድር የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና 29 ሃገራት ብቻ የወርቅ ሜዳሊያውን ማጥለቅ ችለዋል። ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያ አራት ወርቅ በጀግኖች አትሌቶቿ በማሳካት ባንዲራዋን ከፍ አድርጋለች። ለአሸናፊነት ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉ ሌሎች አራት አትሌቶች ደግሞ ለጥቂት ተቀድመው የብር ሜዳሊያዎችን ሲያስመዘግቡ፤ ሁለቱ ደግሞ የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤቶች ሆነዋል። ከእነዚህ 10 ሜዳሊያዎች መካከል 7ቱ የተገኙት ደግሞ በሴት አትሌቶች ነው።
በሜዳልያ ሰንጠረዥ ባልገቡ ነገር ግን ከ4-87ኛ ባለው ደረጃ በወጡ አትሌቶች ደግሞ 11 የሚሆኑ ዲፕሎማዎች ተገኝተዋል። ይህም ኢትዮጵያን ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ በሆነ ታሪካዊ ድል ውድድሩን እንድታጠናቅቅ አድርጓታል። ይኸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መቀዛቀዝ እያሳየ በቆየው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤት እንዲሁም የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክን ጨምሮ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ይታይ በነበረው የግለኝነት ስሜትና አለመግባባት ምክንያት አዝኖ የቆየውን ስሜት ዳግም ወደነበረበት የመለሰ ሆኗል።
እአአ 1983 ሄልሲንኪ ላይ በተጀመረው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሳታፊ የነበረችው ኢትዮጵያ በአትሌት ከበደ ባልቻ የማራቶን ብቸኛ የብር ሜዳሊያ ነበር ያጠናቀቀችው። ይህ የሜዳሊያ ቁጥር በየጊዜው እያደገ በመምጣት እአአ 2013 ሞስኮ ላይ 10 ሜዳሊያዎችን በማስቆጠር ከፍተኛው ቁጥር ተመዝግቦ ነበር። ይሁንና ኦሪጎን ኢትዮጵያ ያገኘችው ሜዳሊያ በወርቅና ብር ሜዳሊያዎች ቁጥር ብልጫ በመያዙ ከ18ቱ የመድረኩ ተሳትፎዎች ቀዳሚው ሆኖ በታሪክ ሊመዘገብ ችሏል። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ እምብዛም በማትታወቅበት ርቀትም በሁለቱም ጾታ በጥቅሉ ሶስት ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብም አዲስ አቅጣጫ ያሳየ ውድድር ነው።
ይህንን ድል ያስመዘገበው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም ከትናንት በስቲያ ምሽት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ አባላት በመገኘት አቀባበል አድርገውላቸዋል። አትሌቶቹ ማረፊያቸውን በስካይላይት ሆቴል ካደረጉ በኋላም ትናንት ከማለዳ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ በክፍት መኪና በመሆን በህዝብ የጀግና አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በመቀጠልም በብሄራዊ ቤተመንግስት በተዘጋጀው መርሃ ግብር መሰረት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በዚህም ውድድራቸውን በቀዳሚነት አጠናቀው የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆኑት አትሌቶች የ1ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ሽልማት ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እጅ ወስደዋል። ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ ያገኙ አትሌቶች እያንዳንዳቸው 1ሚሊየን ብር ሲበረከትላቸው፤ የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤቶች ደግሞ የ700ሺ ብር ተሸላሚ ሆነዋል። የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናውን ክብረወሰን ያሻሻሉ አትሌቶች ተጨማሪ 250ሺ ብር ሲያገኙ፤ ለተገኙት ሜዳሊያዎች በቡድን በመስራት ምክንያት የሆኑ አትሌቶች ደግሞ 500 ሺ ብር ተበርክቶላቸዋል። የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ባይካተቱም ዲፕሎማ ያገኙ እንዲሁም በተለያየ የስራ ኃላፊነት ከቡድኑ ጋር ለተጓዙም እንደየደረጃቸው የገንዘብ ተሸላሚዎች ሆነዋል። በአጠቃላይ ልኡኩ ከ1ነጥብ 5 ሚሊየን እስከ 50ሺ ብር ድረስ ተሸላሚ ሊሆን ችሏል።
በሽልማት መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ‹‹በሃምሌ ክረምት ጭጋግ ለሃገራችን ደማቅ ጸሃይ እንዲያበራልን አድርገውልናል›› ሲሉ የጀግኖቹን ጣፋጭ ውጤት ገልፀውታል። ‹‹የሃገርን ስም በበጎ በማስነሳት ኢትዮጵያዊያን በያሉበት አንገታቸውን ቀና እንዲያደርጉ አድርገዋል። ይህ ድል ከሜዳሊያም ያለፈ ነው፤ ይህ ድል የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓለማ ከሌሎች ሃገራት በላይ እንዲውለበለብ ከማድረግ ያለፈ ነው። የሃገር መዝሙር በውጪ ሃገር እንዲዘመር ከማድረግ ያለፈ ነው። ለተጨነቀው፣ ላዘነው ለተከዘው፣ ኑሮ ለከበደው፣ እንደሃገር የት ነን ለሚለው ፈገግታን ያስገኘ ነው።›› ብለዋል።
ፕሬዚዳንቷ አክለውም ‹‹እኔ ላሸንፍ ብቻም ሳይሆን በመተባበርና በቡድን በመስራት ሌሎች ለሌሎች በር ሲከፍቱም አይተናል። ይህም ትልቅ ትምህርት ነው። ጀግኖች አትሌቶቻችን በኦሪጎን የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ላይ በአፍሪካ አንደኛ በዓለም ሁለተኛ በመውጣት ለሃገራችን ላስገኙት ድል አትሌቶች እንዲሁም መላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ። ዛሬ እናንተ ያሳያችሁት የአሸናፊዋን ኢትዮጵያ ገጽታ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ በንግግራቸው፤ በጋራ መስራት ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑ የተረጋገጠበት ውድድር መሆኑን ጠቁመዋል። ‹‹አንድ ሆነን እንስራ ኢትዮጵያ ታሸንፍ›› የሚለው መሪ ሃሳብ የሆነበት ምክንያትም ለአንድ ዓላማ በቡድን በመስራት ስኬታማ በመሆናቸው ነው። ከድል አድራጊ አትሌቶች የህብረት ስራ ኢትዮጵያዊያን ብቻም ሳይሆኑ የዓለም ህዝብም ተጨማሪ ልምድ እንደቀሰመም ገልጸዋል።
ድል አድራጊ አትሌቶች ሽኝት ሲደረግላቸው የተባሉትን በመፈጸም እጅግ ስኬታማ በሆነ ሁኔታ የሃገርና የህዝባቸውን ስም፣ ክብርና ዝና በአለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲሰማና እንዲታወቅ በማድረጋቸው ህዝቡ በእጅጉ ተደስቷል ኮርቷልም። ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ከፍተኛውን የሜዳሊያ ቁጥርና ዓይነት ማግኘቷ፣ በማራቶን በሁለቱም ጾታ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆኗ እንዲሁም የአትሌቶች የቡድን ስራ ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ የታየበት ውድድሩን ከሌላ ጊዜ የተለየ እንደሚያደርገውም ጠቁመዋል። ኦሪጎን ላይ የተሰራው ታሪክ በሃገሪቷ የሚታዩትን የከፋፋይ ድርጊት ጉም የበተነ ሲሆን፤ ሁሉም እንደ ሃገር ቢያስብ የማንሻገረው ፈተና እንደሌለ የሚያስተምር መሆኑንም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ፤ ስለተደረገው አቀባበልና ድጋፍ ምስጋናዋን አቅርባለች። አክላም የኢትዮጵያ ህዝብ 10 ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ሜዳሊያ እንደሚፈልግ ጠቁማለች። በመሆኑም የአትሌቲክስ ስፖርት ባለድርሻ አካላት የሆኑ ሁሉ በቀጣዩ ውድድር ከዚህ በላይ ሜዳሊያ ለማምጣት ጥረት ማድረግ አለብን ብላለች። በቶኪዮ ኦሊምፒክ ውጤት አምጥተው በዚህ ቻምፒዮና ያልተሳካላቸው አትሌቶችም በቀጣይ ዓመት ሕዝብ እንደሚክሱ ያላትን ተስፋ ገልፃለች።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንን እየመሩ ወደ ኦሪጎን የተጓዙት አቶ ተፈራ ሞላ፤ ቡድኑን ወክለው መልዕክት አስተላልፈዋል። በዚህም ‹‹ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትታይ እንደ ሃገር መሪ ጠንካራ አመራር ሰጥታችሁ፣ እንደ አትሌቲክሱ ባለቤትነታችሁም እንቅልፍ አጥታችሁ፤ ከሚሮጡት ጋር እየሮጣችሁ ድጋፍ ለሰጣችሁን ሁሉ ይህ ውጤት የእናንተ በመሆኑ በልኡኩ ስም ምስጋና አቀርባለሁ›› ብለዋል። ከአትሌቶቹ ጥንካሬ ባሻገር የቡድኑ አባላት ስራዎችን በመከፋፈልና በቅንጅት ተናቦ በመስራት እንዲሁም ከውድድር በኋላ ጉድለትና ጥንካሬን ለይቶ አቅጣጫ በማስቀመጥ ይህ ውጤት መምጣቱን ጠቁመዋል።
አያይዘውም የኢትዮጵያ መገለጫ በሆኑት የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች በወንዶች በኩል የታዩትን ክፍተቶች በማረም በቀጣዩ የዓለም ቻምፒዮና እንዲሁም በፓሪሱ ኦሊምፒክ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከወዲሁ የቤትስራ አድርገው መውሰዳቸውም ቡድን መሪው ጠቁመዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2022