ተተኪ አትሌቶችን ወደ ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንደ ድልድይ ሆነው ከሚያሸጋግሩ ውድድሮች መካከል አንዱ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና ነው።በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድው ይህ ውድድር ለ19ኛ ጊዜ በቀጣዩ ሳምንት መጀመሪያ በኮሎምቢያ መዲና ካሊ ይካሄዳል። በዚህ ቻምፒዮና ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም ከትናንት በስቲያ ምሽት አሸኛኘት ተደርጎለታል።
እአአ ከ1986 ጀምሮ የታዳጊ አትሌቶች ቻምፒዮና በሚል ሲካሄድ የቆየው ይህ ውድድር፤ ከቅርብ ጊዜ አንስቶ የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በሚል መጠሪያ ተተክቶ እየተከናወነ ይገኛል። የአለማችን ወጣት አትሌቶች የሚፎካከሩበት ይህ ውድድር ነገ በታላላቅ መድረኮች አገራቸውን የሚወክሉ በርካታ ወጣቶች የሚታጩበት ነው። ኢትዮጵያም 10 ሴቶችና 9 ወንዶች በጠቅላላው 19 ወጣት አትሌቶችን ታወዳድራለች።
በውድድሩ ተካፋይ የሚሆነው ልኡክ በተዘጋጀለት የሽኝት መርሃ ግብር ላይ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዳይሬክተር አቶ አምበሳው እንየው፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መገኘታቸውን ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት የሽኝት መርሃግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ‹‹በቻምፒዮናው ላይ ለመካፈል ዝግጅታችሁን አጠናቃችሁ ለዚህ ሰዓት በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ። በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንዳየነው ሀገራችን ይህን የመሰለ አመርቂ ውጤትና የመልካም ገጽታ ግንባታን ያገኘችው ጀግኖች አትሌቶቻችን በሜዳ ውስጥ ያሳዩት በነበረው የትብብር ስራ ነው። በመሆኑም እናንተም ከቡድን አጋሮቻችሁ፣ ከአሰልጣኞቻችሁ እና በጠቅላላ ከልዑካን ቡድኑ ጋር ተናቦ በመስራት የተሻለ ስራ ሰርታችሁ አስደሳች ውጤት አስመዝግባችሁ በድል አድራጊነት ተመልሳችሁ እንድንገናኝ ከአደራ ጭምር ማሳሰብ እወዳለሁ›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ በበኩሉ ‹‹ውጤት እንዴት ማስመዝገብ እንደሚቻል ከኦሪገኑ የአትሌቶቻችን መናበብ በላይ ማሳያ ያለ አይመስለኝም›› በማለት የዓለም ቻምፒዮናው ድል ተሞክሮ እንዲሆናቸው ለቡድኑ አባላት አመላክቷል።
የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የቡድኑ መሪ የሆነችው አትሌት መሰለች መልካሙ ስለ ቡድኑ ዝግጅትና የጉዞ መርሃግብር በተመለከተ፤ በዚህ ውድድር ላይ ከ800 ሜትር እስከ 5ሺ ሜትር ሀገራቸውን ወክለው እንዲሳተፉ የተመረጡት አትሌቶች በሀገር
ውስጥ እና በውጪ በተደረጉ ውድድሮች ሚኒማ ያሟሉ መሆናቸውን ጠቁማለች። ጉዞውን በተመለከተም ቡድኑ ለሁለት ተከፍሎ የሚጓዝ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ጉዞም ትናንት ማለዳ ተደርጓል። የሁለተኛው ቡድን ጉዞ ደግሞ ከነገ በስቲያ እንደሚሆን አመላክታለች። አያይዛም በዚህ ውድድር ዝግጅት ላይ ተሳታፊ የነበሩ ባለድርሻ አካላትን አመስግናለች።
በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ ወጣቶችን ስታካፍል የቆየች ሲሆን፤ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ላይም አሜሪካ፣ ኬንያን እና ሩሲያን ተከትላ በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ከዚህ ውድድር 117 ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ የቻለችው ኢትዮጵያ፣ 40የወርቅ፣ 46የብር እና 31 የነሃስ ሜዳሊያዎች መሰብሰብ ችላለች። በመድረኩ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ስኬታማ ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ፤ በወንድና በሴት በጥቅሉ አምስት የሚሆኑ ክብረወሰኖችን ከእጃቸው ማስገባት ችለዋል።
በአንድ ውድድር ላይ በተለያዩ ርቀቶች ሁለት ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብም ከጥቂቶች ተርታ መሰለፍ ችለዋል። እነዚህም፤ በወንዶች በኩል አንጋፋው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ እአአ 1992 በደቡብ ኮሪያዋ ሴኡል በተዘጋጀው ቻምፒዮና በ5ሺ እና 10ሺ ሜትሮች ሁለት ድሎችን ሲያስመዘግብ፤ በተመሳሳይ ርቀት አትሌት አሰፋ መዝገቡም እአአ በ1996 አውስትራሊያ ሲድኒ ላይ በተካሄደው ቻምፒዮና የሁለት ሜዳሊያዎች ባለቤት መሆን ችሏል። በሴቶች ደግሞ አትሌት መሰረት ደፋር 3ሺ እና 5ሺ ሜትር ርቀቶች እአአ በ2002 በጃማይካዋ ኪንግስተን በተካሄደው ቻምፒዮና ሁለት ሜዳሊያዎችን ማግኘት የቻለች ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ናት።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2014