የዓለም ጤና ድርጅት በኬፕ ቨርዴ እያካሄደ ባለው ሁለተኛው የአፍሪካ የጤና ፎረም ላይ ባወጣው ሪፖርት አፍሪካ በበሽታ ምክንያት በየዓመቱ 2 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር እንደምታጣ ገልጿል፡፡
የኦል አፍሪካን ዘገባ እንደሚያመለክተው እ.አ.አ. በ2015 በ 47 ቱ የአፍሪካ ሀገራት 630 ሚሊዮን ሰዎች በተለያዩ በሽታዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በሪፖርቱ መሰረት እንደ የልብ ህመም፣ ካንሰር፣ ስትሮክና ስኳር ያሉ በሽታዎች በዓለም ላይ ቀዳሚ ገዳዮች ሆነዋል፡፡ በበሽታ ምክንያት ከሚከሰቱ አስር ሞቶች ሰባቱ በእነዚህ በሽታዎች ምክንያት የሚከሰቱም ናቸው፡፡
በአፍሪካም ከፍተኛ ጫና በመፍጠር 37 በመቶ ድርሻ ያላቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽዎች ሲሆኑ ተላላፊ በሽታዎች ደግሞ 36 በመቶ ድርሻ በመያዝና ከፍተኛ ወጪ በማስወጣት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ የእናቶችና ሕፃናት በሽታዎች እንዲሁም ከአመጋገብ ጋር የተያያዙ የጤና እክሎች ደግሞ ቀሪውን ድርሻ ይይዛሉ ተብሏል።
በሪፖርቱ እ.አ.አ. በ 2030 የሚጠናቀቀው የዘላቂ ልማት ግብ እቅድ የሚሳካ ከሆነ አፍሪካ 47 በመቶ ወጪዋን በመቀነስ ኪሳራዋን ማስቀረት እንደምትችል ተገልጿል፡፡ ሆኖም በዘላቂ ልማት ግብ የተቀመጠው ዓለም አቀፍ የጤና ተደራሽነት የአራት ዓመት አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆኑን የጤና ድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶክተር ማትሺዲሶ ሞይቲ ገልጸዋል፡፡
በጤናው ዘርፍ በዘላቂ የልማት ግብ የተቀመጠውን ዓለም አቀፍ የጤና ተደራሸነትን ለማሳካት የአፍሪካ ሀገራት በየዓመቱ በትንሹ 271 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከሀገራቱ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ ሰባት ነጥብ አምስት በመቶ በጀት ለጤናው ዘርፍ መመደብ እንዳለበት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2011
የትናየት ፈሩ