በኦሪገን፣ አሜሪካ አስተናጋጅነት በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያስመዘገቧቸው አስደናቂ ድሎች አገራቸውን ያኮሩ፤ ዓለምንም ያስገረሙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ አማካኝነት ባስመዘገበቻቸው 10 ሜዳሊያዎች (አራት የወርቅ፣ አራት የብር እና ሁለት የነሐስ) በአስተናጋጇ አሜሪካ ብቻ ተበልጣ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡
ውጤቱ ኢትዮጵያውያንን በእጅጉ ያስደሰተ እንደሆነ ታዝበናል፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በውድድሩ ላይ ያስመዘገቡት ውጤት በበርካታ ችግሮች ውስጥ ለምትገኘው ኢትዮጵያና ለዜጎቿ ከስፖርታዊ ድል የተሻገረ ትርጉም አለው። ከበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚሰሙ አሳዛኝ የንፁሃን ግድያዎች፣ መፈናቀሎች፣ የሰላም እጦት፣ የኑሮ ውድነት ችግሮች … ኢትዮጵያውያንን አሳዝነዋል፤ አስጨንቀዋል፡፡
በዚህ መከራ መሐል የታዩት የጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንፀባራቂ ድሎች ኢትዮጵያውያንን ያነቃቁና ከተባበሩና ከሁሉም ነገር በፊት አገራቸውን አስቀድመው ከተነሱ በችግሮቻቸው ላይ ድል እንደሚቀዳጁ ያስገነዘቡ ሆነዋል፡፡
ባለፉት ወራት ስለኢትዮጵያ በርካታ የውሸት ዜናዎችን ሲያሰራጩ የከረሙት የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ድልና የአትሌቶቹን ብቃት አወድሰዋል፡፡ ድሎቹ ኢትዮጵያውያን በርካታ መከራዎች ቢገጥሟቸውም እንደሚያንሰራሩና በመጨረሻም የድል ባለቤት እንደሚሆኑ ማሳያዎች እንደሆኑ እነዚህ ስለኢትዮጵያ ክፉ ክፉውን ብቻ ሲናገሩ የከረሙት መገናኛ ብዙኃን ዐይተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚፈፀሙ አሳዛኝ የንፁሃን ግድያዎች፣ መፈናቀሎች፣ የሰላም እጦት፣ የኑሮ ውድነት ችግሮች … ቢያዝኑና ቢጨነቁም፤ ጀግኖች አትሌቶች በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባስመዘገቡት ድል እንደተደሰቱ ሁሉ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የፈጠሩትን አሳዛኝ ገፅታንም መለወጥ እንደሚቻል ድሉ ትምህርት ሰጥቶ አልፏል፡፡ አትሌቶቹ ድሉን ያስመዘገቡት ከራሳቸው ይልቅ አገራቸውን አስቀድመው፣ በወኔ፣ በትብብር፣ በቁርጠኝነትና በጽናት ባደረጉት ስፖርታዊ ተጋድሎ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የገጠሟትን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ድል ለማድረግ ከግል ጥቅም ይልቅ ኢትዮጵያን ማስቀደም ይገባል፡፡ ከግላዊ ዓላማና ስንቅ ይልቅ አገራዊ ዓላማ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ለአገር ጥቅምና ኩራት የሚከፈል ዋጋ መራራ ቢሆንም ውጤቱ ግን ጣፋጭና የሚያኮራ ነው፡፡ የአትሌቶቹ የድል ምስጢር አገርንና ሕዝብን መውደድ እንደሆነ ሁሉ ኢትዮጵያን ከህመሟ ለመፈወስ በቅድሚያ አገርንና ሕዝብን መውደድና ማክበር ይገባል፡፡
የአገርና የሕዝብ ፍቅር ያለው ግለሰብና ቡድን ሁልጊዜም ቢሆን ኃላፊነት ይሰማዋል፡፡ ኃላፊነቱን ለመወጣት ደግሞ ከሌሎች ጋር ስለመተባበር፣ በጥንቃቄና በፅናት ስለመራመድ ብሎም ስለማሸነፍ ያስባል፤ ይተጋል፡፡
አገር ከችግር የምትላቀቀው በሁሉም ዜጎች ትብብር እንጂ በተናጠል እርምጃ አይደለም፡፡ አትሌቶቹ በትብብር የቡድን ስራ ሰርተው ድል እንዳስመዘገቡ ሁሉ ኢትዮጵያውያንም በችግሮቻቸው ላይ ድል ለመቀዳጀት በትብብር መስራታቸው አስገዳጅ ይሆናል፡፡ በትብብር ያልተሰራ ስራ ዘላቂና አስተማማኝ ውጤት የማስገኘት እድሉ አነስተኛ ነው፡፡ ስለሆነም አቅምን አሰባስቦና ደምሮ በቅንጅት ለመሰለፍ ቁርጠኝነትና ዝግጁነት ሊኖር ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ችግሮች ለመፍታት የሚያስፈልገው ሌላው ግብዓት ጽናት ነው፡፡ በኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ድል ያስመዘገቡ ጀግኖች አትሌቶች እንዴት እስከመጨረሻው ድረስ በጽናት እንደተፋለሙ ተመልክተናል፡፡ አትሌቶቹ ተስፋ ሳይቆርጡ እስከመጨረሻው ድረስ ተፋልመው ያስመዘገቧቸው አስደናቂ ድሎች ኢትዮጵያውያንን ቁጭ ብድግ ያደረጉና በደስታ ያስለቀሱ ነበሩ፡፡
የኢትዮጵያ ችግሮችም እልህ አስጨራሽ ትግል፣ ጽናትንና ተስፋ አለመቁረጥን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ አንዱ ችግር ሲፈታ ሌላ የችግር ምንጭ እንደሚፈልቅ ዐይተናል፡፡ እነዚህን ችግሮች ጠራርጎ ለማስወገድ ደግሞ ተስፋ አለመቁረጥ ያስፈልጋል፡፡ የሁሉንም ችግሮች ምንጭ ለማድረቅ የሚያስችል የጽናት ኃይል መታጠቅ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን አንዱን ችግር ከፈቱ በኋላ፣ ሌላ ችግር ሲፈጠር ተስፋ የሚቆርጡ ከሆነ ሁለ ገብ ድል አይገኝም፡፡ የዘላቂና አስተማማኝ ድል ባለቤት ለመሆን ችግሮች በየጊዜውና በየቦታው ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ቀድሞ መጠበቅና መዘጋጀት እንዲሁም ሁሉንም ችግሮች ለመጋፈጥ በጽናት መቆም ይገባል!
ጀግኖቹ አትሌቶች እዚህ ደረጃ ደርሰው ይህን የመሰለ አኩሪ ገድል ያስመዘገቡት ብዙ ውጣ ውረዶችንና መሰናክሎችን አልፈው ነው፡፡ ኢትዮጵያም ያጋጠሟት ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ብዙ ውጣ ውረዶችንና መሰናክሎችን በጽናት ማለፍ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያ በየዘመናቱ፣ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆና በትውልዶች ውስጥ የነበሩ ጀግኖች አትሌቶች አገራቸው ከመከራዋ ቀና እንድትል በርካታ አስደናቂ ትንቅንቆችን አድርገው ኢትዮጵያን አኩርተዋል፡፡ በኦሊምፒክ ውድድር አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ የወሰደ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ መሆን የቻለው የማራቶኑ ፈርጥ ጀግናው ሻምበል አበበ ቢቂላ ‹‹ሮምን በባዶ እግሩ የወረረው ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ወታደር›› ተብሎ በኢጣሊያ ጋዜጦች ሲሰየም የአበበ ድል ብዙ ትርጉም ነበረው፡፡
የአበበ የሮም፣ ኢጣሊያ፣ ድል ኢትዮጵያን በግፍ በመውረር በኢትዮጵያና ዜጎቿ ላይ ተነገሮ የማይታመን፣ ተቆጥሮ የማያልቅ አሰቃቂ በደልና ግፍ የፈፀመውን የፋሺስቱ የቤኒቶ ሙሶሊኒ መንግሥትን እንድናስታውስ ስለሚያደርገን ድሉ ከስፖርታዊ ድልነት የዘለለ ትርጉም እንዳለው አንዘነጋውም፡፡
በውድድሩ ማግሥትም የኢጣሊያ ጋዜጦች ‹‹ኢትዮጵያን ለመውረር የኢጣሊያ አገር ወታደር ሁሉ አስፈልጎ ነበር፤ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ግዙፍ ጦር አዝምቶም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ግን አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮምን ወረረችው …›› የሚል ጽሑፍ ይዘው የመውጣታቸው አንድምታም ለኢትዮጵያውንም ሆነ ለቀሪው ዓለም ብዙ ትርጉም ነበረው፤ አለውም፡፡
የሻምበል አበበ ድል የኢትዮጵያና የእርሱ ስምና ዝና በመላው ዓለም እንዲናኝ ከማድረጉም ባሻገር ብዙ ጥቁር አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ በር ከፍቷል። የአሁኑ የአትሌቶቻችን ድልም ሌሎች ተተኪ ኢትዮጵያውያን ወደ መስኩ እንዲመጡና የአገራቸውን ስም በበጎ እንዲያስጠሩ እንደሚያነሳሳ አያጠራጥርም፡፡
ሻምበል አበበ ቢቂላ በሮም ኦሊምፒክ ያስመዘገበውን ድል ለየት የሚያደርገው በባዶ እግሩ ሮጦ ያስመዘገበው ድል መሆኑ ነው፡፡ አበበ ቢቂላ የማራቶንን ርቀት ሮጦ ያሸነፈውና ሪከርድ ያስመዘገበው በባዶ እግሩ መሆኑ ደግሞ የመላ ዓለም ስፖርት አፍቃሪዎችን በእጅጉ ያስደነቀ …የአበበ በቂላን ስምና የኢትዮጵያን ዝና በመላው ዓለም ተቀርፆ እንዲቀር ያደረገ ነበር፡፡
ጋዜጠኞች አበበ ለምን ያለ ጫማ በባዶ እግሩ እንደሮጠ ጠይቀውት ‹‹ … እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሌም የምናሸንፈው በጀግንነትና በወኔ እንደሆነ ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ በመፈለጌ ነው…›› ብሏል፡፡ እንግዲህ ሻምበል አበበ ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ላይ በግፍ ወረራ ፈፅማ በነበረችው አገር ዋና ከተማ ላይ በባዶ እግሩ ሮጦ፣ የተወዳደረበትን ሩጫ ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር ማሸነፉ እንዲሁም በባዶ እግሩ የሮጠበት ምክንያት ለዛሬው ትውልድም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መነቃቂያና መነቃነቂያ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት ወኔ ያስፈልጋል፡፡ ሻምበል አበበ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሌም የምናሸንፈው በጀግንነትና በወኔ እንደሆነ ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ በመፈለጌ ነው…›› እንዳለው ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች አሸናፊ እንድትሆን የአሸናፊነት ወኔ ሊኖር ይገባል፡፡ ልብ ከደከመና ተነሳሽነት ከሌለ አሸናፊነት የማይታሰብ ነው፡፡
ስለሆነም ጀግኖች አትሌቶች በአገር ፍቅር፣ በትብብርና በጽናት አስደናቂ ድል እንዳስመዘገቡ ሁሉ፤ ኢትዮጵያ ከገጠሟት ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንድትላቀቅ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ጥቅም በማስቀደም፣ በጋራ መስራትና በጽናት መሰለፍ ይጠበቅባቸዋል!
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2014