በ18ኛው የኦሪገን የአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና 4 የወርቅ፣4 የብርና 2 የነሐስ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ከአለም ሁለተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ ሆኖ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልኡካን ቡድን አስደሳች የአገር ቤት ጉዞውን ዛሬ ይጀምራል።
ቡድኑ ዛሬ ማክሰኞ ሀምሌ 19/2014 ከፖርትላንድ ኦሪገን ተነስቶ ወደ ኒውዮርክ ይጓዛል። ኒውዮርክ ላይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አመራሮች በተገኙበት አቀባበል ተደርጎለትም ወደ አገር ቤት የክብር ሽኝት ይጠብቀዋል።
ከኒውዮርክ ቆይታው በኋላም በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ የሚበር ሲሆን ነገ ረቡዕ ሀምሌ 20/2014 ምሽት 3 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ልዑካን ቡድኑ በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ይደረግለታል። በስካይላይት ሆቴል አርፎ ሌሊቱን ካሳለፈ በኋላም ሀሙስ ሀምሌ 21/2014 ጠዋት በክፍት አውቶቢስ ከስካይላይት ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ ይጓዛል።
ከረፋድ ጀምሮም በመስቀል አደባባይ የጀግና አቀባበል ይደረግለታል። ከመስቀል አደባባይ ስነስርዓት በኋላም ለቡድኑ የምሳ ፕሮግራም በአንድነት ፓርክ ተከናውኖ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበሉ እንደሚጠናቀቅ ታውቋል።
ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው በነበራት ተሳትፎ ታምራት ቶላና ጎተይቶም ገብረስላሴ ማራቶን፣ ለተሰንበት ግደይ 10ሺ፣ ጉዳፍ ጸጋይ 5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ሲያስመዘግቡ፣ የብር ሜዳሊያዎቹን ለሜቻ ግርማ 3ሺ ሜትር መሰናክል፣ ሞስነት ገረመው በማራቶን፣ ወርቅውሃ ጌታቸው 3ሺ ሜትር መሰናክልና ጉዳፍ ጸጋይ 1500 ሜትር አስመዝግበዋል። ሁለቱን የነሐስ ሜዳሊያዎች ደግሞ ዳዊት ስዩም 5ሺ ሜትርና መቅደስ አበበ 3ሺ ሜትር መሰናክል ማስመዝገባቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2014