ኢትዮጵያ የበርካታ ከዋክብት አትሌቶች ምድር ናት። በዚያ ልክ ግን አንድም የአለም ኮከብ የሆነ አትሌት የሌላቸው አገራት በብዛትም በጥራትም የሚያካሂዱት የጎዳና ላይ ውድድር በስፋት የላትም። በኢትዮጵያ ወጥ የሆነና በጥራት ደረጃም ትልቅ የሚባለው የጎዳና ላይ ውድድር ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ነው። ሌሎች የጎዳና ላይ ውድድሮች በተለያዩ አካባቢዎች ሲካሄዱ ቢስተዋልም ወጥ ሆነው ሲቀጥሉ አይታዩም። የጥራት ደረጃቸውም ጥያቄ ይነሳበታል።
በቅርብ አመት ውስጥ ተመስርቶ በጣት በሚቆጠሩ ውድድሮች ብቻ የተሻለ የጥራት ደረጃን ይዞ ብቅ ያለው “ኬር ኦድ” የጎዳና ላይ ውድድር ግን ለኢትዮጵያ የጎዳና ላይ ውድድር አንዱ እሴት የመሆን ትልቅ ተስፋ እንዳለው አሳይቷል።
ኬር ኦድ የጎዳና ላይ ሩጫ በአለም ላይ ታዋቂ በሆኑ የጉራጌና አካባቢው ኢትዮጵያውያን ተወላጅ አትሌቶች እንዲሁም ታዋቂ በሆኑ የአካባቢው ተወላጅ ሰዎች በጋራ ሆነው የመሰረቱት ውድድር ነው። ከአንድ አመት በፊት በወልቂጤ የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር በማድረግ የጀመረው ኬር ኦድ የጎዳና ላይ ሩጫ ከወር በፊትም በተመሳሳይ ወልቂጤ ላይ ሁለተኛውን ውድድር በማድረግ ለበርካታ አትሌቶች የውድድር እድል መፍጠር ችሏል። ባለፈው እሁድ ደግሞ በቡታጅራ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ የ10 ኪሎ ሜትር የተሳካ ውድድር ማድረግ ችሏል። በዚህም ባለፉት ሁለት ውድድሮች የነበሩ ክፍተቶችን በማረም የጥራት ደረጃውንና የሽልማት መጠኑን በማሳደግ ወደ ፊት ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ሆኗል።
ኬር ኦድ የሚለው ቃል ከጉራግኛ ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም ሰላምን ማብሰር ማለት ነው። ይህን መሪ ቃል መሰረት አድርጎ በቡታጅራ በተካሄደው ውድድርም ከተለያዩ ክለቦች፤ የአትሌት ማኔጅመንቶች፤ እና በግል የሚሮጡ ከአንድ ሺ በላይ ስመ ጥርና ታዋቂ አትሌቶች ተሳትፈውበታል። ከሃያ ሺ በላይ የአካባቢው ሕዝብም ታሪካዊቷ ኦሊምፒያን አትሌት ጌጤ ዋሚ በክብር እንግድነት በተገኘችበት ውድድር ላይ ተሳታፊ ሆኗል። በድምቀትና በስኬት ለተጠናቀቀው ውድድርም የኬር ኦድ ፕሬዚዳንት አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ለቡታጅራ ህዝብ ምስጋናውን አቅርቧል።
በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 6ኛ የወጡ አትሌቶች ከሰላሳ እስከ ስድስት ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የ10 ኪሎ ሜትር ውድድሩን በወንዶች ሀለፎም ተስፋዬ ቀዳሚ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ጀምቤሳ ደበሌ፣ ተሰማ መኮንን፣ ምትኩ አያሌው፣ አብራራው ምስጋናውና ሀብታሙ ብርሌው ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል። በሴቶች መካከል የተካሄደውን ተመሳሳይ ፉክክር ደግሞ የኔነሽ ሽመክት ቀዳሚ በመሆን አጠናቃለች። እቴነሽ አላምረው፣ ዘውዲቱ አደራው፣ ጥሩዬ መስፍን፣ ሰናይት ጌታቸውና አለምገነት ሞላ ተከታትለው በመግባት የገንዘብ ሽልማቱን እንደየደረጃቸው ተቀብለዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2014