የጉዳያችን ማዋዣ፡- “በልሃ ልበልሃ!”
የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ የፍትሕ አካሄድ ሥርዓት እንደዛሬው እንዳልነበረ “ጥንታዊነቱ” ራሱ ለራሱ መልስ ይሰጣል። እርግጥ ነው፤ ዛሬን ከትናንት ጋር ማነጻጸሩ አግባብ ያለመሆኑ ባይጠፋንም አንዳንዴ ግን “አምሳያ ገጠመኞችን” ስናስተውልና ያለፉትን ዓመታት በአርምሞ ስንቃኝ ትናንት ትዝ እያለን ብንቀዝዝ “የነበር ምርኮኞች” አሰኝቶ ሊያስነቅፈን አይገባም። ደግሞስ የትናንትን የጉዞ አሻራ (ፈለግ) በማስታወስ የዛሬውን እርምጃችንን ብንመረምርና “የእድገታችንን” ቁመት ብንፈትሽበት ምን ክፋት ይኖረዋል?
የጥንታዊው የበልሃ ልበልሃ የሙግት አካሄድና ሥርዓት እንደ ዛሬው ዳኝነት በተደራጀ አዳራሽ ውስጥ ዋናዎቹ ፈራጆች ከፍ ባለ ሞገሳማ መንበር ላይ ተሰይመውና ጥቁር ካባ ደርበው፣ ዐቃቤ ሕጉና ጠበቃውም ግራና ቀኝ ቆመው፣ ከሳሽና ተከሳሽ አንገታቸውን ዘልሰውና እጃቸውን አጣምረው፣ የጸጥታ ሠራተኞችም አጥር ሆነው ማስረጃ እየተጎለጎለና ምስክሮች እየተነተኑ የሚፋለሙበት ዓይነት የሙግት አካሄድ አልነበረም።
ለሙግቱ መፋለሚያ የሚመረጠው ቦታ የዛፍ ጥላ ወይንም አውላላ ሜዳ ሆኖ ተመልካች ዙሪያውን ከቦ የሚያዳምቅበት ትዕይንት ነበር። ተሟጋቾቹም ሆኑ ተመልካቹ እንደ ዛሬው የፍርድ ቤት ሥነ ሥርዓት “ኮፍያህን አውልቅ፣ ያጣመርከውን እግር ዘርጋ፣ የተዝናኖት አቀማመጥሽን አስተካክይ፣ ከሹክሹክታ ታቀቡ ወዘተ.” ከሚሉ የማስፈራሪያ ትብታቦች በእጅጉ የጸዳ ነበር።
ይልቅስ፤ “ተውኔታዊ ባሕርይ የነበረው የከሳሽና የተከሳሽ አለባበስ፣ አቋቋም፣ ዘንግ አያያዝ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ፣ የነገር አቀራረብ ሞቅና ደመቅ ያለ ጥምር የአሞጋገት ስልት የነበረው ማራኪ ጥበባዊ ሙግት ነበር። ተሟግቶ ለመርታት፣ ረትቶም እርካታን ለማግኘት፣ ዝናና ክብርን ለመቀዳጀት በቅድሚያ የተሟጋቹን ንቃት፣ ብልህነትና ብርታት ይጠይቅ ነበር።
ከሰውነት እንቅስቃሴው በተጨማሪ የመሟገቻው ቋንቋ በተዋቡ ቃላት፣ በምሳሌያዊ አነጋገር፣ በተረት፣ በአፈ ታሪክ፣ በእንቆቅልሽና በመሳሰሉት ዘዴዎች የበለጸገ ለዛማ መሆኑ ግድ ይሏል። የእነዚህ ሁሉ ውህድ የችሎቶቹ ነፃ ትርዒት ነበር። በዚህም ምክንያት ወጭ ወራጁና አላፊ አግዳሚው ሁሉ በችሎቱ ይማረክና ይማልል ነበር።” (ስለሺ ለማ፤ ተጠየቅ፤ ገጽ 15)።
አሟጋቾቹም ገዢዎች፣ መኳንንት፣ ባላባቶች፣ ወንበሮች (ዳኞች) ወዘተ. ናቸው። የሙግቱ አካሄድ የራሱ ሥርዓት ነበረው። አቋቋማቸውም ከሳሽ በቀኝ፣ ተከሳሽ በግራ ሲሆን እማኝ መቁጠርና ዋስ መጥራት የመጀመሪያ ተግባር ነበር። ተሟጋቾቹ ኩታቸውን ወይንም ሸማቸውን ወገባቸው ላይ ሸብ አድርገውና ጫፉን በግራና በቀኝ ትከሻቸው ላይ ጣል በማድረግ የተጠየቁ አካሄድ ሳይፋለስ ጉዳያቸውን በጥበባዊ አካሄድ ማሰማት ይጀምራሉ። ሙግታቸውን የሚጀምሩትም “እግዜር ያሳይዎ፣ መልአክ ያመላክትዎ” ብለው በመንደርደር ነበር። ይህ ተማጽኖ ልክ እንደ ዘመናዊ የወንጀለኛና የፍትሐብሔር አንቀጽ በቋሚነት የሚጠቀስ መሆኑን ልብ ይባል።
ለመነሻ ጉዳያችንና ለመድረሻ መደምደሚያችን እንዲረዳን አባትና ልጅ ተሟግተውበት ነበር የተባለ አንድ ጥንታዊ ምሳሌ በማስታወስ እንደምን ለሙግት መንደርደሪያነትና ለመሃላ ጭምር ያገለግል እንደነበር ተመልክተን ለዋናው ጉዳያችን ማነጻጸሪያ እንዲሆን እንዋሰዋለን።
“በልሃ ልበልሃ!..የአጤ ሥርዓቱን፣
የመሠረቱን፣ የአብርሃም እራቱን፣
አልናገርም ሀሰቱን፣
ሁልጊዜም እውነት እውነቱን።”
እናም ሙግቱ ይከተላል። ሞጋቹ ልጅ አባቱን “ተጠየቅ?” በማለት ክርክሩን ይጀምራል። ተሞጋቹ አባትም፤ “አልጠየቅም” ብሎ ይንደረደርና መከራከሪያ ሃሳቡን እንዲህ በማለት እንደ ወጨፎ ያዘንበዋል። “ሰማይ አይታረስ፣ ውሃም አይታፈስ፣ መሬት አይተኮስ፣ ብረትም በውሃ አይርስ፣ አባትም አይከሰስ…”
ሞጋች ልጅ መቃወሚያውን እንዲህ ሲል ያቀርባል፤ “ሰማይ በመብረቅ ይታረሳል። ውሃም በእንስራ ይታፈሳል። መሬትም በማረሻ ይተኮሳል። አባትም በጥፋቱ ይከሰሳል።” ተሞጋቹ አባት የክሱን አካሄድ ልብ ብሎ በማጤን ማፋረሻውን እንደሚከተለው ያቀርባል። “ሰማይ ያለ ዓመት ነጎድጓድ አያወርድ፣ ፈጣሪ ያለ በደል ገሃንም አያወርድ፣ ያለ እርሻ በመሬት ላይ እሳት አይነድ፣ ሴትም ያለ እንስራ ወንዝ አትወርድ፣ አባትም ያለ ጥፋቱ ልጁን አይክድ…ስለዚህ አትሞግተኝም ዳግመኛ።” በዚህን መሰሉ ክርክር “ሰማይ አይታረስ፣ አባት አይከሰስ” በሚለው የሙግት ማሳረጊያ በአባት ረቺነት ክርክሩ ተቋጨ ይባላል።
የኑሯችን “በልሃ ልበልሃ!”
እንደ ጥንቱ የሙግት አካሄድ ሥርዓት የዛሬይቱን ጀንበር እየሞቀች ባለችው ኢትዮጵያ “በልሃ ልበልሃ” እየተባባልን በደጅና በቤት፣ በሜዳና በመንገድ፣ በሚዲያና በሹክሹክታ የምንሟገትባቸውና የምንሞገትባቸው ጉዳዮቻችንና አገራዊ አጀንዳዎቻችን ብዙዎች ናቸው። ማን በሰጣችሁ ሥልጣንና ስለምን መሟገትን መረጣችሁ ተብለን በተቆጭዎቻችን እንዳንጠየቅ ድፍረት የሚሆነን ቀደም ሲል ያስታወስነው የነባሩ ትውፊታችን ውርስና ቀጥለን የምንጠቅሰው የኢዮብ እና የፈጣሪ የሙግት ታሪክ ነው።
ፈጣሪን ተሽቀዳድሞ የከሰሰው ኢዮብ የመከራዎቹና የእንቆቅልሾቹ ምክንያቶች ምን እንደሆኑ ከፈጣሪው ጋር ለተሟገተበት ጥያቄ ከፈጣሪ ከራሱ የተሰጠው መልስ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ይነበባል፤ “ኢዮብ ሆይ! እንግዲህ እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ አንተም መልስልኝ” (ኢዮብ 38፡3)። ለክርክራችን መደላድል የመረጥነው እነዚህን ሁለት የማሳያ ታሪኮች ነው።
ፖለቲከኞች በየመድረኮቻቸው፣ ፍትሕ የተጠሙ ዜጎች በየፍርድ ቤቱ፣ አቅሉን ስቶ ጨርቁን በመጣል ያበደው ኢኮኖሚ የዕለት እንጀራቸውን የቀማቸው ዜጎች በየመገበያያው ስፍራ፣ ተማሪው በየትምህርት ቤቱ፣ ወላጆች በየቤታቸው፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ፣ መንግሥትም በሕዝብ ላይ፣ ምእመናን በየሃይማኖቶቻቸው መሪዎች ላይ፣ ንፁሐን ዜጎች በደም ጥማተኞች ላይ፣ ተጠርጣሪ የፍርድ ተማጻኞች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ወዘተ. ያልተከፈተ አገራዊ የመካሰሻ ዶሴ፣ የማይደመጥ የብሶት ድምጽ፣ የማይፈስ እምባ እንዲያው በጥቅሉ “በልሃ ልበልሃ” እየተባባልን በመጯጯህም ሆነ በለሆሳስ በነጋ በጠባ የምንሟገትባቸው የአበሳዎቻችንና የተግዳሮቶቻችን ብዛት እንደ ሰማይ ከዋክብት የማይቆጠሩ፣ እንደ ባህር አሸዋ የማይሰፈሩ ለመሆናቸው መስካሪ አያሻውም።
ብዙ ዜጎች “ሰማይ አይታረስ!?” በማለት ተስፋ ቆርጠው የቆዘሙባቸው አገራዊ ጉዳዮቻችንም ተቆጥረው የሚዘለቁ አይደሉም። “ሰማይ እንዴት እንደሚታረስ” የጨለመባቸውና ተምሳሌታዊ ትርጉሙ ባልገባቸው ግፈኞች ደማቸው ደመ ከልብ የሆነ፣ በእብሪተኞች ሴራና በደል በኑሯቸው ላይ መከራ እንደ ወስከንባይ የተደፋበቸው ዜጎች ብዙ ናቸው ከማለት ይልቅ ቤቱ ይቁጠራቸው ማለቱ ይቀላል። ሰማዩ የሚታረስበት መብረቅ እያስደነገጣቸውም ከቋጥኝ ጋር እንደ መላተም በመቁጠር ለአገር የሚተርፉ በርካታ ምሁራንና ቅን ዜጎች አጉራህ ጠናኝ በማለት “በየጎሬያቸው” መሽገው አህህ እያሉ መቆዘማቸው ሌላው የተቃርኖ እውነታችን ነው።
እውነት እውነቱን እንመስክር ከተባለ የሕዝባችን የበልሃ ልበልሃ የመሟገቻ አካሄድ ቅጥ አምባሩ የጠፋ እስኪመስል ድረስ አገርና ዜጎች በአንድነት ግራ ተጋብተናል፣ ተደነጋግረናል ማለቱ ይቀላል። ለምሳሌ፤ “ብሔራችን ከሰውነታችን” ገዝፎብን አናንቆናል። መታወቂያችን ዜግነታችን ሳይሆን የየት መጣችን የዘር ትምክህት ሆኖብን “ማን ማንን ቢወልድ” ወደሚል የጎጠኝነት አዘቅጥ ውስጥ ከተዘፈቅን ሰነባብተናል።
አገርን ለማገልገል ወንበር የሚያዘው በአወቁና በበቁ መስፈርት ሳይሆን በተዋወቁና በተዛመዱ መሳሳብ ከሆነም ውሎ አድሯል። በአእምሮው ውስጥ ምን እውቀት አለ ሳይሆን “ከበስተጀርባው ማን ደጀን አለው?” የጊዜያችን ፋሽን ሆኗል። የፖለቲካ አሸናፊነት “የጠቅልሎ መግዛት” ላይሰንስ ከሆነም ዓመታት ተቆጥረዋል። ስለዚህም የአገራችን አየር የታጠነው በዜጎች “የበልሃ ልበልህ” ሙግት ነው ቢባል ከእውነት አያርቀንም። ሰማያችንም እንዳይታረስ ጭንጫ የሆነው በዚህን መሰል አገራዊ የልክፍት ደዌ ስለተጠቃን ይመስላል።
“ኑ እንዋቀስ!?”
ልክ እንደ ዛሬው እንደ እኛ ዘመን መንግሥትና ሕዝብ፣ ሕዝብና ሕዝብ፣ የሃይማኖት መሪዎችና ምእመናኖቻቸው፣ አገልጋዮችና ተገልጋዮች፣ ፖለቲካውና ፖለቲከኞች ግራ እንደተጋቡበት ያለ ሁኔታ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥም መሰል ታሪክ ተመዝግቦ እናነባለን። በዚህ ወቅት ግራ ከተጋበው ሕዝብ ጋር ለመወቃቀስና ለመሟገት ቀድሞ ዝግጁነቱን ያረጋገጠው ልክ ከኢዮብ ጋር እንዳደረገው ፈጣሪ ራሱ ነበር።
እንዲህ በማለት፡- “ኑ እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል። እንደ ደም ቢቀላም እንደ ባዘቶ ይነጣል። እሺ ብትሉ ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ። እምቢ ብላችሁ ብታምጹ ግን ሰይፍ ይበላችኋል። እግዚአብሔር ይህንን ተናግሯል።” (ትንቢተ ኢሳይያስ 1፡18 – 20)።
መቼም ፈጣሪ በሰው ደረጃ ልክ ራሱን ዝቅ አድርጎ“ኑ እንዋቀስ” ብሎ “ከወደረኞቹ” ጋር ፈቃደኛነቱን ከገለጸ ዕድሜው የተመጠነው ሟቹ የሰው ልጅማ እንዴት ራሱን አዋርዶ ማጎንበስ ይሳነዋል? እርግጥ ነው መንግሥታችን ሊተገብረው በዝግጅት ላይ ያለው ሁሉን አካታች የብሔራዊ ምክክር መድረክ “ለመነጋገሩና ለመወቃቀሱ” ጥሩ ጅማሮ እንደሆነና ሊበረታታ እንደሚገባ እናምናለን።
ብሶተኞቹ፣ እብሪተኞቹና በደም ውርርድና በባሩድ ጭስ ካልታጠን እያሉ የሚፎገሉት የዚህች አገር ልበ ደንዳ የጫካ ጦረኞችም ለጥሪው በጎ ምላሽ ሰጥተው ወደ ሰላማዊ “የመዋቀሻና የመነጋገሪያ” መድረክ እንደሚመጡ ተስፋ ይደረጋል። ያለበዘለዚያ ግን በግፋ በለው የትእቢት ቀረርቶና በይዋጣልን የጅል ፉከራ አሸንፎ የተጨበጨበለት፣ ድል ቀንቶትም የተመሰገነ ስለሌለ የሚመለከታቸው ሁሉ ልብ ተቀልብ ሆነው ቢያስቡበት ይበጃቸዋል።
አገሬ እንደ ሰማይ የራቁና እንደ ደመና የከበዱ በርካታ መከራዎችን እየተሻገረች ስለመጣች በየወቅቱ ለሚገጥሟት ተግዳሮቶች ሁሉ እንዴት ማለፍ እንደምትችል ዘዴውንም ሆነ ጸሎቱን ታውቅበታለች። በአድዋ የፍልሚያ ሜዳ አያቶቻችን የተጎናጸፉት የድል ታሪክ “ሰማይን ከማረስ” በምን ይተናነሳል። አዎን “የጥንቱ አድዋ ሰማይ በነፃነት ፍቅር መብረቅ ታርሷል፣ ተከታታይ የጦርነቶች የባሩድ ጭስም በጀግኖች አባቶቻችን ደምና ላብ ተዳፍኗል።
ከአባይ ወንዛችን ውሃም የብርሃን ጸዳል ፈልቋል። ጦም ማደር የለመደው መሬታችንም በኩታ ገጠም እርሻ ስንዴ ተመርቶበት ከራሳችን ተርፎ ሌሎችንም ሊመግብ ጫፍ ላይ መድረሱ እየተነገረን ነው። ማንም ይሁን ማን ሕዝብን በክፋቱ የሚለክፍ ከሆነ የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በጥፋቱ ይከሰሳል፤ እጁም በሰንሰለት ካቴና ይጠፈራል።
የሚበጀውና የሚያዋጣው “በልሃ ልበልሃ” እየተባባልን በየአደባባዩ፣ በየጓዳችን፣ በየሚዲያዎቻችንና በየመሸሸጊያ ዋሻችን ውስጥ በማድፈጥ የምንካሰስባቸው መከራዎቻችን መፍትሔ በሚያገኙበት ጉዳዮች ላይ መመካከሩ ብቻ ነው። “ሰማይ እንደማይታረስ ሁሉ የሚመጣውን እናያለን!” እየተባለ በመንግሥት ሹመኞችም ዘንድ ሆነ በአንዳንድ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚፎከረው ቀረርቶ “የታሪካችንን ጠባሶች” በማስታወስ ቢለዝብ ለሁላችንም ይበጃል።
“ሰማይ በመብረቅ መታረሱን” ትናንት በሚገባ አስተምሮናል። ይህ መብረቅ የሚወክለው በተፈጥሮ ዳመና ውስጥ የሚከሰተውን ኤሌክትሪካዊ ብርቅርቅታ ብቻ ሳይሆን የግፉዓን ሕዝብን የተባበረ ድምጽ ጭምር ነው። ድምጹ እንኳን የምድሩን ግፍ ቀርቶ ጸባኦትን የማናወጥና የመነቅነቅ አቅሙና ብርታቱ እጅግ ከፍ ያለ ነው። ቀኑ ሳይዳምን ዛሬውኑ በምናለቅስባቸውና በተራብንበት ዘርፈ ብዙ አገራዊ ጉዳዮቻችን ዙሪያ በሆደ ሰፊነት መወያየት ልንጀምር ግድ ይላል። መብረቁ ቀድሞ አንጎዳጉዶ ዶፉን መልቀቅ ከጀመረ ማጣፊያው የሚያጥረው እከሌ ከእከሌ ሳይባል ለሁለም ዜጋ ነው። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2014