ታላቁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በአንድ ወቅት ይህን ብሎ ነበር፤ ‹‹ዓለም እንዲያውቀው የምፈልገው ሃገሬ ኢትዮጵያ በቆራጥነትና በጀግንነት እንደምታሸንፍ ነው››። ይህ አባባል ደግሞ በግብር የታየ በታሪክም የተመዘገበ ሆኖ ዘመናትን ዘልቋል። ቆራጥና ጀግና አትሌቶቿ በጸሃይ ሃሩር በጋለ ጎዳና ባዶ እግራቸውን ደማቸውን እያፈሰሱ ለስሟ ከመሮጥ አልቦዘኑም።
ተደራራቢ ውድድሮች፣ ጉዳትና ድካምም አልበገራቸውም። ህመም፣ ሃዘንና ከወሊድ መልስ ባልጠና አካል ከመሮጥም ወደኋላ አላሉም።ዛሬም ድረስ ራሳቸውን ሳይሆን ሃገራቸውን አስቀድመው ለድሏ፤ ሃገራትን ሁሉ በልጦ ለሚውለበለበው ባንዲራዋና ዓለም ለሚሰማው ብሄራዊ መዝሙሯ ከውድድር አውድ ተሰይመው ለአሸናፊነት ይፋለማሉ።
ሌላኛው ታላቅ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ‹‹አሸናፊ ለመሆን ሶስት ነገሮች ያስፈልጋሉ፤ ራስን መግዛት፣ ጠንክሮ መስራት እና ቆራጥነት›› እንዳለው፤ እነዚህን ያጣመሩ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከዘመን ዘመን ሃገራቸውን እያኮሩ ይገኛሉ። በኦሊምፒክ፣ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንዲሁም በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም እግር በእግር እየተተካኩ በመሮጥ ላይ ናቸው። በድላቸውም ለኢትዮጵያ ክብርን ከመደረብ አልፈው ለህዝባቸውም ደስታን ብቻም ሳይሆን፣ የሃገር ፍቅርን፣ መስዋዕትነትን፣ የዓላማ ጽናትንና አሸናፊነትን ሲያስተምሩ ኖረዋል።
ከሰሞኑ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፤ የዓለም ህዝብ ዓይን፣ ጆሮና ቀልብን በአንድነት በያዘው ውድድር የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል አድራጊነት እየታየ ነው።ኢትዮጵያ የዓለም መገናኛ ብዙሃንም የዕለት ዜናቸው ማሟሻ፤ የጋዜጦችና መጽሄቶቻቸው አርዕስት ሆናለች። በአሜሪካ ምድር በዩጂን ግዛት ኦሪጎን ከተማ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የሜዳሊያ ብዛት ኢትዮጵያ ልዕለ ኃያሊቱን ሃገር አሜሪካንን ተከትላ በሁለተኛነት መቀመጧ ከክብርም በላይ ኩራት የሚሆን ነው።
የድል ዜናው በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የስፖርታዊ ፉክክር ውጤት ከመሆን በዘለለ ትርጉም ያለው ነው።ይኸውም ከወቅታዊው የሃገር ውስጥና እና የውጪ ጫና ጋር በተያያዘ በህዝቡ ስነልቦና ላይ ለደረሰው ህመምም ማስታገሻ በመሆን ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለስፖርት ካለው ልዩ ፍቅር እንዲሁም ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ ከተለመደው ስኬት አንጻርም ሳቁን የመለሰ ድል ሆኗል። በተለይ በታላላቆቹ የውድድር አውዶች ኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮናዎች ላይ ይመዘገብ የነበረው የበርካታ ሜዳሊያዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ ማሽቆልቆል እያሳየ መምጣቱ አያጠያይቅም።
በዚህም ምክንያት የስፖርት ቤተሰቡ ቅያሜና ጥርጣሬ አድሮበት ሰንብቷል። ስለ ስፖርት ሲል የትኛውንም መስዋዕትነት ለሚከፍለው ህዝብም ይህን የልብ ስብራት ሊጠገን የሚችለው ዳግም ወደ ድል በመመለስ ነውና ኦሪጎን ላይ የተመዘገበው ውጤት ተስፋ ሰጪ ሆኗል።
ስፖርት ለሃገራትና ለዜጎቻቸው የአካላዊና አእምሯዊ ጤና መጠበቂያ ስልት፣ የመዝናኛ አማራጭና የገቢ ማግኛ ዘርፍ ከመሆኑም በላይ ማንነትና መለያ ስለመሆኑ እሙን ነው። የዓለም እግር ኳስን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ያሉት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እአአ በ2018 ናይጄሪያን ከጎበኙ በኃላ፤ ‹‹በናይጄሪያ የእግር ኳስ ስፖርት ፍላጎት ነው ብትሉ ውሸት ነው፤ ምክንያቱም እግር ኳስ ከዚያም በላይ ነው። ፍቅር ወይም እምነት ነው ብትሉም ውሸት ነው፤ ምክንያቱም እግር ኳስ በናይጄሪያ ህይወትም ነው›› ማለታቸው ብዙዎችን አነጋግሮ ነበር።
በእርግጥም የፕሬዚዳንቱ ምልከታ ስፖርት ማንነት ስለመሆኑ በግልጽ ያመላከተ ነው። በአፍሪካ ትልቋና የእልፍ ወጣቶች ሃገር ለሆነችው ናይጄሪያ እግር ኳስ አንድ የስፖርት ዓይነት አሊያም የመዝናኛ ዘርፍ ብቻም አይደለም። ይልቁንም ሚሊዮኖች በፍቅር ነገን እያለሙ የሚጫወቱት፣ ለበርካቶች የስራ እድልን የከፈተ፣ ሃገሪቷን በአህጉርና ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ በኩራት እንድትቆም ያስቻለ እንዲሁም የገቢ ምንጭ የሆነም ዘርፍ ነው። እናም ለናይጄሪያዎች እግር ኳስ ህይወት መሆኑ የማያከራክር ነው።
ይህ እውነታ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሲመጣ ደግሞ በአትሌቲክስ ስፖርት የሚገለጥ ነው። ከቀጣናው ሃገራት መካከል አንዷ ለሆነችው ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከስፖርትም በላይ ትርጉም አለው። እንደሃገርም ሆነ እንደህዝብ የማንነት መገለጫና የኩራት ምንጭ ሆኗል። ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ነገር ግን እጅግ በርካታ የሆኑ ወጣቶች ነገን አሻግረው እየተመለከቱ ይሮጣሉ። ተስፋቸው በአትሌቲክስ ላይ የተመሰረተ ነው፤ የትኛውንም መስዋዕትነት ከመክፈል ወደኋላ አይሉም። ሲሳካላቸው ደግሞ በገንዘባቸው ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ከማገልገል ወደኋላ አይመለሱም።
ኦሪጎን ላይ የታየው የአትሌቶቻችን ጀግንነትና ብርታትም ምንጩ ይኸው የሃገርና የህዝባቸው ፍቅር ነው።ከዚህ ቀደም የደረሰባቸው መጉላላት፣ ዕድልና ትኩረት ማጣት፣ ከቤተሰብና ከወዳጅ መራቅ፣… ቅንጣት ታህል ቅሬታ ሳያሳድርባቸው ሃገራቸውን ወደማገልገል መመለሳቸው በእርግጥም ለሃገራቸው ያላቸውን ጽኑ ፍቅር የሚያሳይ ነው። ከዓመት በፊት በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተከሰተውና የስፖርት ቤተሰቡንም አንገት ያስደፋው አሳፋሪ ችግር በዚህ ውድድር ተሽሯል።
ይህ ለስፖርት ቤተሰቡ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ከመሆኑ ባለፈ እየተገኙ ያሉ ውጤቶችም በአዳዲስ ርቀቶች የተስፋ ጭላንጭል ያስመለከተ ሆኗል። እንደ 3ሺ መሰናክል ባሉ ርቀቶች ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባትና ከጠንካራ ተፎካካሪዎች ተርታ መሰለፍ ሌሎች የስኬት መንገዶችን አመላካችና የአብዮት ጅማሬ ማሳያም ሆነዋል።
አስደሳች ከሆነው ድል በተቃራኒ ቀድሞ በምንታወቅባቸው የመም ላይ ረጅም ርቀት ውድድሮች የታየው ሁኔታ በአትሌቲክስ ቤተሰቡ ላይ ጥርጣሬን የጫረ መሆኑም መታለፍ የለበትም። ከማርሽ ለዋጩ ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር የኦሊምፒክ ድል አንስቶ እስከ 2020(እአአ) ቶኪዮ ኦሊምፒክ ድረስ የዘለቀው የ10ሺ ሜትር የወንዶች ድል፤ ኦሪጎን ላይ መነጠቁ ያስቆጫል።
በርቀቱ የተካፈሉ አትሌቶች ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጋቸው እሙን ቢሆንም ከዓመት ዓመት ተወዳዳሪን ሳይለዩ በተመሳሳይ የአሯሯጥ ስልት መገኘት ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርምና ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2014