18ኛው የአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከአስራ አንድ ቀናት በኋላ ትናንት በኦሪገን ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ በ4ወርቅ፣4ብርና 2 ነሐስ ሜዳሊያዎች አሜሪካን ተከትላ ከአለም ሁለተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ ሆና አጠናቃለች። አንጸባራቂ ድል በውድድሩ ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ በውድድሩ ታሪክ ትልቁን ስኬት ተጎናጽፋለች። ባልተጠበቁ ርቀቶች ጭምር የተለያዩ ስኬቶችን ማግኘት የቻለችው ኢትዮጵያ ድል በተለመደባቸው የወንዶች 10 እና 5ሺ ሜትር አንድም ሜዳሊያ ማስመዝገብ አልቻለችም። በነዚህ ርቀቶች የተለመዱ ድሎች መመዝገብ አለመቻላቸው የበለጠ አንጸባራቂ ድል እንዳይመዘገብ ማድረጉም የስፖርት ቤተሰቡ መነጋገሪያ ሆኗል።
ኢትዮጵያ በተለይም በቻምፒዮናው ሁለተኛ ቀን ውሎ በ10ሺ ሜትር የርቀቱ ኮከብ አትሌቶቿ ሜዳሊያ ውስጥ መግባት አለመቻላቸው የሚያስቆጭ ቢሆንም ትናንት በውድድሩ ፍጻሜ እለት በተካሄደው የ5ሺ ሜትር ውድድር ይካካሳል የሚል ተስፋ ነበር። ያም ሆኖ ኢትዮጵያውያኑን የርቀቱ ኮከብ አትሌቶችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ አትሌቶች ደካማ አቋም አሳይተዋል። ይህም ባለፉት ሁለት ቻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ በወርቅ የደመቀችበት የርቀቱ ክብር ዳግም ፊቱን እንዲያዞር አድርጎታል።
ኢትዮጵያ በ5ሺ ሜትር ሴቶች ውድድር በአለም ቻምፒዮና መድረክ ያላትን የአለም ቀዳሚ ስኬት በወንዶች የላትም። በሴቶች ያላትን የስኬት የበላይነት ከትናንት በስቲያም በኦሪገን መድገሟ ይታወቃል። እ.ኤ.አ በ1991 ቶኪዮ የአለም ቻምፒዮና ላይ በፊጣ ባይሳ የብር ሜዳሊያ የተጀመረው የኢትዮጵያ የርቀቱ ስኬት ወደ ወርቅ ለመሸጋገር ብዙ ጊዜ ፈጅቷል። ራሱ ፊጣ ባይሳን ጨምሮ እንደ ጀግናው አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ፣ ስለሺ ስህን፣ ሚሊዮን ወልዴና ሌሎችም ታሪካዊ አትሌቶች በሩጫው አለም የተለያዩ ርቀቶች መንገስ ቢችሉም ኢትዮጵያን በ5ሺ ሜትር ወደ ወርቅ ሜዳሊያ ማሸጋገር አልቻሉም። እ.ኤ.አ 2003 ሴንት ዴኒስ ላይ በነሐስ ሜዳሊያ የርቀቱን ክብር ያሟሸው የምንጊዜም የረጅም ርቀት ምርጥ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እ.ኤ.አ 2009 በርሊን ቻምፒዮና ላይ የርቀቱን የወርቅ ሜዳሊያ ታሪክ አንድ ብሎ ጀምሯል።
ከዚያ በኋላ ግን አልደገመም። ኢትዮጵያም በርቀቱ ዳግም ወደ ወርቅ ሜዳሊያ ክብር ለመመለስ እ.ኤ.አ የ2017ቱን የለንደን ቻምፒዮና መጠበቅ ነበረባት። ከዚያ በፊት በነበሩ ቻምፒዮናዎች በዘመናቸው የርቀቱ ፈርጥ የሆኑ እንደ ሃጎስ ገብረህይወት አይነት አትሌቶችም ከብርና ከነሐስ የዘለለ ሜዳሊያ ማስመዝገብ አልቻሉም። ለንደን ላይ በወቅቱ ቁጥር አንድ የነበረውን ፋራህን በአገሩና በደጋፊው ፊት በማሸነፍ ወርቅ ያጠለቀው ድንቅ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሙክታር ኢድሪስ ግን በቀጣዩም ቻምፒዮና 2019 ዶሃ ላይ ዳግም በወርቅ የደመቀበትን ታሪክ አኑሯል። ዛሬ ግን ይህ ታሪክ ሳይቀጥል ቀርቷል።
የርቀቱ ከዋክብት የሆኑ የአለምና የኦሊምፒክ ቻምፒዮኖች ጭምር እጅግ ደካማ አቋም ባሳዩበት ውድድር አዲስ ቻምፒዮን ብቅ ብሏል። ታላላቆቹም አትሌቶች ለትንሿ አገር ኖርዌይ ወጣት አትሌት ጃኮብ ኢንግብሪግስተን ክብሩን አሳልፈው ሰጥተዋል። ኬንያዊው ጃኮብ ክሮፕና ዩጋንዳዊው ኦስካር ቼሊሞ ታላላቆቹ የርቀቱ ፈርጦች በሙቀት በተፈተኑበት ውድድር ብርና ነሐስ አምጥተዋል። የርቀቱም የአፍሪካውያን ዙፋን ተገርስሶ ከሁለት ቻምፒዮናዎች በኋላ ዳግም ወደ አውሮፓ አምርቷል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በርቀቱ 3ወርቅ፣ 6 ብርና 4 ነሐስ አስመዝግባለች። ትውልደ ሶማሊያዊው የእንግሊዝ አትሌት ሞሐመድ ፋራህ እ.ኤ.አ ከ2011 እስከ 2015 ድረስ በተከታታይ ቻምፒዮናዎች ወርቅ ያጠለቀ አትሌት ብቻ ሳይሆን በርቀቱ ሦስት ጊዜ በማሸነፍም የሚስተካከለው የለም። ፋራህ በርቀቱ አንድ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀበት ታሪክም አለው። እሱን ተከትሎ ኬንያዊው አትሌት ኢስማኤል ኪሩይ ሁለት ወርቆችን በማሸነፍ የሚጠቀስ ሲሆን ኢትዮጵያዊው ሙክታር ኢድሪስ ባለፉት ሁለት ቻምፒዮናዎች ይህን ታሪክ የሚጋራበትን ድል ማስመዝገቡ ይታወቃል።
ኬንያ በርቀቱ በወርቅ ሜዳሊያ ብቻ ሰባት ጊዜ በማሸነፍ የአለም እጅግ ስኬታማዋ አገር ነች። የቻምፒዮናው ክብረወሰንም በኬንያዊው ድንቅ አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ እ.ኤ.አ 2003 ሴንት ዴኒስ ላይ 14:26:72 የተያዘ ሲሆን እስካሁንም የሚደፍረው አልተገኘም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2014