ክፍል ሁለት
በክፍል አንድ ጽሁፌ የኑሮ ውድነት ከዳግማዊ ዐፄ ሚኒሊክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ እስከ ዘመነ ኢህአዴግ የነበረውን ለማየት ሞክሬያለሁ ። በዚሕ ጽሁፍ በዘመነ ብልጽግና ያለውን የኑሮ ውድነትና በመፍትሄው ዙሪያ አንድ ነገር ለማለት ሞክሪያለሁ ።
የኑሮ ውድነት በዘመነ ብልጽግና
የኢፌዲሪ ጠ/ሚ ክቡር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ስለኢትዮጵያ ከተናገሩት ጥቂቶቹ ላይ የሐሳብ ስንዘራ ኢትዮጵያ የሁላችን አገር፤ የሁላችን ቤት ናት። ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የአገሩን ጸጋና በረከት መጠቀም አለበት። ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን። ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለመኖር በሕይወት መቆየት ያስፈልጋል። ነፍስ ያለስጋ አትቆምምና።
የኢትዮጵያ ማኅፀን ለምለም ናት። እንኳን ዘር ተዘርቶ አይደለም ከወፍ አፍ የወደቀ ጥሬ በሚጸድቅበት አገር ላይ አርሶ መብላት ተስኖን በኑሮ ውድነት መሰቃየት የለብንም።
ፍትሕ ለንጹሃን ተገቢ እንደሆነ እናምናለን። ለአንድ አገር ብልጽግና አይነተኛ መሳሪያው ፍትሕ ነው። ፍትሕ ማጣት ፍቅርን ያነጥባል። ሰላምን ያደፈርሳል። መተባበርን ይፈታል። መደመርን አስትቶ ያነጣጥላል። እኛ ሳይሆን እኔ ያስብላል። ብዙዎች ለፍትሕ የተጋደሉት እኛነትን አስበው ነው። ዛሬ ለአገራችን የሚያስፈልገው እውነተኛ ፍትሕ ብቻ ነው።
የኑሮ ጣጣውም የነቃው ከፍትሕ መዛባት እንጂ በሌላ ተጽሕኖ ብቻ አይደለም። የሕዝብ መቸገር የዳንኪራ ያህል የሚያስፈነጥዛቸው፣ የሕብረተሰቡ አለመረጋጋት እንደአእዋፍ ጥዑም ዜማ የሚመስጣቸው ፍትሕን ገልብጠው በሚመሩ ንጹሕ ባልሆኑ የመንግሥት አካላትና ንጹሕ ባልሆኑ ባለሀብቶች ጥምረት ነው።
አንድ መንግስት ሥራ የሚሰራው ከሕዝብ ጋር በማበር ለራሱ ለሕዝቡ ቢሆንም፣ ሕዝብ የመሪውን ሕልም እንዲጋራና ታምኖ እንዲከተል በኑሮ ውድነት የተሳከረውን መንፈሱን ማብረድ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል። አንድ ሕዝብ እንጀራና ወጥን በሙሉ ኃይሉ ለፍቶ ማግኘት ከተሳነው የልማት መስመሩ ተንሸዋሯል ማለት ነው።
ትልልቅ አገራዊ የልማት ስራ የብልጽግና አጀንዳ ሰንቆ ከመንቀሳቀስ ጎን ለጎን ለኑሮ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችን በተጓዳኝ ማሟላት ተገቢ ነው። ዜጋው ኑሮ ቀንበር ሳይቀነስለት አንጀቱ በርሃብ እየተብላላ ልማት ብሎ ኒውኩለር ማብላያን ዐይነት ማሰብ የተሳካና ዘላቂ ውጤት አያመጣም። የኑሮ አለመቅለል ዜጋን ያሰድዳል። ተሰዳጅ ዜጋም ሲበዛ የሰው ሀብት ይናጠባል።
ለአንድ አገር የሰው ልጅን የመሰለ ቀዳሚ የተፈጥሮ ሀብት እንደሌለ የታመነ ነው። ዜጎች ዳቦ ተርበው ውሃ ተጠምተው ታርዘውና መጠለያ እርቆአቸው አገር ማልማት፣ ለአገር አርቆ ማሰብ፣ ባለዕራይ መሆን፣ ተምሮ የላቀ ውጤት ማምጣት፣ በጉልበት አገርን ማገልግል፣ በአገሪቷ ላይ ለነገ ሕይወት ዛሬን በተስፋ መኖር የማይቻል ነገር ነው የሚሆነው።
በኑሮ ውድነት ሕዝብ ተስፋ እየቆረጠ ልማትና ብልጽግናን፣ የአገር ፍቅርና ሰላምን ማምጣት ያስቸግራል። ዛሬም የአገራችን የንግድ ሥርዓት እንደክፉ ሱስ እየጨመረ ሄዷል እንጂ እራሱን አርቆና አስተካክሎ አልታየም። በአገር ውስጥ ተመርተው የሚቀርቡ ነገሮች እንኳን የዋጋቸው ማሻቀብ ለአመክንዮ የማይመች ነው።
ምርትም ኖሮ ምርትም ሳይኖር ሁሌም ኑሮና የኑሮ ጉዳዮች የነፍስ ያህል ውድ ይሆናሉ። ለምሳሌ ስኳር ጠፍቶ ዋጋ የጨመረ ሻይ ስኳር ሲገኝ እንኳን ከውድነት ክብሩ አይወርድም። በዚህ ስልት የተለያዩ ቁሶች፣ እህሉ፣ የቤት ኪራዩና ግዢው፣ የመኪና ሽያጭና የትራንስፖርት ዋጋው፣ አልባሳቱ፣ የትምህርት ቤት ክፍያው፣ የሕክምና ክፍያው፣ የሆቴልና የካፌ ዋጋ….. ሁሉም በዚህ አገር ላይ ለራሳቸው ክብር ፈጥረዋል።
በኑሮ ውድነት ጉዳይ ላይ የተነሱት ሐሳቦች በጊዜ እልባት ሊያገኙ ይገባል። በተለይ ስር ሰዶ ደሃው ሕዝብ ሊቆጣጠረውና ሊገበያየው ያልቻለው ከዕለት ፍጆታ እስከወር ቀለብ፣ ከተራ ቁስ እስከዐመት ልብስ …. በተመጣጣኝ ዋጋ ባለመሸመቱ ኑሮው የከፋ አድርጎታል። ሕዝቡ ተረጋግቶ በመኖር ምርትና ልማትን አፋጥኖ፣ ለነገው አትርፎ የሚኖርበት፣ ሥራ አጥ የሚቀነስበት፣ የጎዳናው ተዳዳሪ የሚጠፋበት፣ ለልመና የተሰማሩ ሕጻናት፣ ወጣቶችና አረጋውያን ወደ ኑሮ ሥርዐት የሚገቡበት …. እንዲሆን የሕዝቡ ኑሮ ይሻሻል ዘንድ ግድ ይላል። መንግሥትም የብዙኀኑ ሕዝብ ተግዳሮት የሆነው በሕይወት የመኖር የሕልውናን ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቁን ቁጥር የሚይዘው አርሶ አደር ሕዝብ ለዘመናት ከችግር አለመላቀቁ ጉዳይ እንደ አንድ ዐብይ ምስክር አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ምክንያቱም ገበሬው 80 ከመቶው የአገሪቷ ሕዝብ ሆኖ ሳለ አርሶ የሚያገኘው ምርት የዕለት ጉርሱንና የዓመት ልብሱን የማይሸፍን ከሆነ በወል አገራችን ችግር ውስጥ ናት ማለት ይችላል። ዛሬ ገበሬውና የገበሬው ልጅ ከማጀቱ ወጥቶ በየከተሞቹ በቤት ውስጥ አገልግሎት፣ በጉልበት ስራና ከዚያም ሲያልፍ በልመና ተሰማርቶ የሚገኘው የገጠር ኑሮው ተግዳሮት ቢሆንበት ነው። ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሆነው የግብርና ሥርዓታችን ለማጠናከርና ፍትሕን በማስፈን ነው።
ጥቂት ስለመሬት ሀብታችን
መንግሥት በድሃ ሆድ ውስጥ ለማደር የእርሻውንና የመሬት ሥርዐቱን በአጽንኦት ማየት አለበት። የኢትዮጵያ ቆዳ ስፋት ከአፍሪካ ከትልልቆቹ አንዷና ከዓለም ወደ 20ኛ አካባቢ ትሆናለች። በምሁራኑ የቁጥር ስሌት ደረጃ የአገሪቷ የመሬት ስፋት 111 ሚሊዮን ካሬ ያላት ሲሆን ከዚህ ውስጥ መታረስ የሚችለው ደግሞ 84 ሚሊዮን ካሬ ነው። ከግማሽ ክ/ዘ በፊት የታረሰው 13 ሚሊዮን ካሬ ነው። በዛ ዘመን የሕዝቡ ብዛት 30 ሚሊዮን ነበር።
ዛሬ ላይ ደግሞ እየታረሰ ያለው 16 ሚሊዮን ካሬ ሲሆን ልዩነቱ 3 ሚሊዮን ካሬ ነው። በዚሁ የእርሻ ውጤት ደግሞ በልቶ ለማደር የተፈጠረው የሕዝብ ብዛት ከ115 ሚሊዮን በላይ ነው። ለዛውም ለውጭ ገበያ ተልኮ የተረፈውን ነው ሕዝቡ የሚጠቀመው። ለእርሻ የተካለለው የመሬት ስፋት በ50 ዓመታት ውስጥ ያለለውጥ የተቀመጠ ነው። ዛሬ ላይ ያለው ሕዝብ እንጀራና ዳቦ በልቶ ለማደር መታረስ የነበረበት እስከ 50 ሚሊዮን ሔክታር የእርሻ መሬት ይመስለኛል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በገበሬው የኑሮ ዘይቤ ውስጥ የሚስተዋለው የመሬት ሥርዓት ደግሞ ወላጆች ልጆቻቸው ለጋብቻ ሲደርሱ ከማይጨመር የመሬት ሀብት ላይ ከጥማድ በሬ ጋር ለልጆቹ እየሸነሸነ ይሰጣል። ይህ አካኤድ ሁሌም የሚቀጥል አልሆነም። ለምሳሌ ዛሬ ላይ አርሶ መብላት፣ ጎጆ ቀልሶ መኖር የሚችለው የገበሬው የልጅ ልጅ ቁጥር መጠን ከአገሪቷ ሕዝብ ከግማሽ በላይ ሆኖ ሳለ ከወላጆቹ የመሬት ውርስ በማጣቱና ከመንግሥት የመሬት ምሪት ካለማግኘት የተነሳ በተለያዩ የክልል ከተሞችና በአገሪቱ መዲና ተሰዳጅ ሆኖ ሕይወቱን ይገፋል። ይባስ ብሎም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የተለያዩ የውስጥ የርስበርስ ጦርነቶችና የጎረቤት አገሮች ትንኮሳና ጣልቃ ገብ ግጭትና ጦርነቶች ተዳምረው ውጤቱን የጓሮ አድርገውታል።
የዛሬ ወገብ የሚያጎብጥ የኑሮ ውድነት ለነገ መልስ የሌለው የሚበስል ጥያቄ ይዘን እንድንኖር የሚያደርገን የእርሻው የመሬት አስተዳደርና የግብርና መር የምጣኔ ሀብት ሥርዓታችን መዛባት ይመስላል። አገራችን ባላት የተለያዩ የአየር ንብረት አካባቢዎች መሬቶቹ የየራሳቸውን ዘር መስጠት የሚችሉ ናችው። በዚህም ከ80 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መታረስ የሚችል መሬት ይዘን መሬቱንም ሕዝቡንም ጦም እያሳደርን ከድሃ ልክ ወርደን የድሃ ድሃ የኑሮ ደረጃ ሕዝብ አፈራን። የአገራችን የመሬት ሀብት ሌላውን አገራት መመገብ የሚያስችል ሆኖ ሳለ ቀድሞ ከነበሩ የንጉሣዊ ሥርዓት ጨምሮ የመሬት ሀብት የሕዝብ ሳይሆን የመሪዎች የሀብት ምንጭ የመደረጉ ውጤት በምግብ ራሳችንን እንዳንችል አድርጎናል።
መሬት በፊውዳል ሥርዓቶች ውስጥ የገበሬው ሳይሆን የነገሥታቱና የርዝራዦቻቸው ነበር ማለት ይቻላል። በዚህም ገበሬው ጭሰኛ ነበር። ወታደራዊ መንግሥትም መሬት ላራሹ ቢያሳውጅም የከተማውና የገጠሩ የመሬት ድርሻ ለስራና ለኑሮ እምብዛም ምቹ አልነበሩም ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም በመንግስት ቁጥጥሩ ስር ነበሩና። የኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥትም የመሬት ፖሊሲው የበለጠ ወደራሱ በማድረግ የገጠሩም ሆነ የከተማው የመሬት ሀብት ትልቁ የመንግሥት ካዝና መሙያ ምንጭ አደረገው።
በዘመኑም ከአውሮፓ አገራት በላይ የመሬት ዋጋ በኢትዮጵያ ውድ ሆነ ተብሎ እስኪተች አደረሰው። በዘመነ ብልጽግናም የመሬት ፖሊሲ ላይ የተሻለ ብርሃን አልታየም። ይባስ ብሎም ገበሬው ከመቼውም በላይ ብዙ ነገሮች ተዳምረው የማዳበሪያ ዋጋ መቋቋም አቅቶት ባለችው ውስን መሬት እንኳን አርሶ መብላት ተግዳሮት ሆነው። ከተማውም በጥቂት የናጠጡ ሀብታሞች ቤተ መንግሥት ያህል መኖሪያ እየገነቡ ሲኖሩ ብዙኀኑ ድሃው ጎኑና ቁመቱ ፤ ዐይነትና ደረጃው በማይሻሻል የቀበሌ ቤት ጥገና ሆኖ ይኖራል።
ቢያንስ አያትና ቅድማያቶቹ የኖሩበት ቤት ውስጥ የሚኖር የከተማው ነዋሪ የራሱ ቤት አድርጎ ግብር ከፍሎ እንዲኖር አልተደረገም። ነዋሪው ቀበሌ ቤትን የራሱ ሆኖለት በጥሩ መልኩ አሻሽሎ መኖሮ ቢፈቀድለት በራሱ መንግሥትን በሰፊ ያግዘው ነበር። ይህም የፍትሕ አንዱ ጥያቄ ነው።
ኢትዮጵያ ሰፊ አገር ናት። ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም የምትበቃ አገር ናት። የቆዳ ስፋቷ በምጣኔ ሀብት ኃያላንና በኑሮ ምቹ ከሆኑ ሦስት የአውሮፓ አገሮች ማለትም እንግሊዝ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ ተደምረው የማይተናነስ የቆዳ ስፋት ያላት አገር ሆና ሳለ ገበሬው የሚያርሰው ከተሜው የሚኖርበት መጠለያ ማጣት ተገቢ አይደለም። ለዚህም የአገሪቱ መሬት ፖሊሲ ሊታሰብበት ይገባል።
የዛሬው ዐይነት የኑሮ ውድነትም የመጣው ከብዙ ምክንያቶች በላይ በእርሻው ላይ አጠንክረን ባለመስራታችን ነው። ዛሬ ላለው ችግር ማለፊያ ተደርጎ የተወሰደው የጓሮ አትክልት ከድሃው ጎጆ እስከ ቤተ መንግሥት ጓሮ ድረስ የሚያስተክል ርብርብ የመጣው ሌላውን ዓለም መመገብ የሚችል የመሬት፣ የውሃ ሀብት፣ የተፈጥሮ ምቹ የአየር ንብረትና 80 ከመቶ ያላነሰ ትጉ ገበሬ ባለባት አገር ግብርናውን ዞር ብለን ልናየው ይገባል።
የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል ከመንግስት ቀጥሎ ዋና ባለድርሻ አካላት የአንድ አገር የኑሮ ዘይቤ የተሳካ እንዲሆን የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው መንግስት ቢሆንም የሕዝቡና የባለሀብቱ ሚና ቀላል የሚባል አይደለም
ባለሀብት
ባለሀብቶች ችግርን ሁሉ በገንዘብ ይለፍልኝ ብላችሁ የምታስቡ መሆን የለባችሁም። እናንተ ተግዳሮቱን መቋቋም በመቻላችሁ በቀላሉ የምትተውት የተዛባ የገበያ ሥርዓት በአገሪቱ ድሃ ኅብረተሰብ ላይ አሉታዊ ተጽሕኖ ያሳድራል። ምንም እንኳን ገንዘባችሁ የችግር በሮችን የምትፈቱበት መሳሪያ ቢሆንም በገንዘባችሁ አገሪቷንና የድሃውን ማኅበረሰብ የግብይት ሥርዐት ማዛባት ግን ተገቢ አይደለም።
ገበያ ወይም ንግድ ሥርዓት ነው። ሥርዓት ላይ ደግሞ ያፈነገጠውን በመደገፍ የሚደረግ አስተዋጾ የብዙኀንን ኅብረተሰብ የኑሮ እሴት ያበላሻል። ሁሌም ቢሆን ነገሮች መታሰብ ያለበት በተጠራቀመው ጥሪት ልክ ሳይሆን ነገሩ በጊዜው በያዘው እውነታ መሆን አለበት – በዋጋው።
የተሻለ ዋጋ መከፈል ያለበት ለቀላሉና ለተራው ነገር ሳይሆን እሴት ለተጨመረበት ነገር ነው። ልዩነታችሁን ከድሃው ማኅበረሰብ ጋር ማነጻጸርም ሆነ ማወዳደር የለባችሁም። ጉዳዩ በያዘው ልክ እንጂ። መቻል ዋጋ አውጥቶ መግዛት ብቻ ሳይሆን ዋጋው ነው ወይ? ብሎ ለዜጋው አስቦ፣ ለትውልድ ተገቢ ሥርዓት ዘርግቶ መገበያየት መቻል ከአንድ ዜጋ የሚጠበቅ ነው።
ብዙኀን ሕዝብ
በአንድ አገር መንግስት አገርን በሥርዓት ለመምራት የሚያወጣው ሕግና ደንብ ወሳኝ እንደሆነ ሁሉ በመንግስት የሚተዳደረው ሕዝብም ለመንግስት ሥርዓት፣ ሕግና ደንብም ተገዢ ሊሆን እንደሚገባ ይታመናል። አንዳንዴ ደግሞ መንግስት ፈር ማስያዝ የከበደውን ነገር ከምንም በላይ ሕዝብ ሥርዐት ሊያሲዘውም ይችላል።
ትናንት በተመጣጣኝ ዋጋ የገዛነውን ቁስና የዕለት ፍጆታ ያለምንም እሴት ጭማሪና በነገሮቹ ላይ ምንም ዓይነት ዋጋ የሚያስቀጥል ምክንያት ሳይኖርበት ንጹሕ ያልሆነው ነጋዴ ባቀረበለት ዋጋ የሚሸምት ከሆነ ከምንም በላይ ኑሮው እንዲወደድ ትልቁን ድርሻ እየተጫወተ ያለው ራሱ ተጎጂው ማኅበረሰብ ነው።
አንድ ዳቦ ላይ ከነበረው ግራምና እሴት ሳይጨምር፣ በአገሪቷ ላይም የስንዴ ዋጋ ባልጨመረበት ሁኔታ ላይም እንኳን ዳቦው ከቀደመው ግራም ቀንሶ፣ ዋጋ ጨምሮ ለገበያ ሲቀርብ መሸመት ተገቢ አይደለም። በቀን ልዩነት ያለምንም ምክንያት እንደዱብ ዕዳ ዋጋ ጨምሮ ሲያድር ለምን? የማይል ሕዝብ ሊኖር አይገባም።
የኑሮ ውድነት አቀጣጣይና ተዋንያን ሆነን ስንተውን አንዳንዴ ድህነትን የምንወድ፣ መከራን የምንወድ፣ ችግር ሲከበን የማንደነግጥ፣ በሰራነው ሥራ ለነገው ትውልድ ሊገጥመው የሚችለውን ተጽሕኖ ቆም ብለን የማናስብ ዓይነት እንመስላለን። ዛሬ ዛሬማ በውድ ተመን ለሽያጭ የቀረቡ ቁሶችን ሆይ ሆይታ እየፈጠሩ ሰልፍ እያስረዘሙ፣ ነጋሪት እያስጎሰሙ፣ መለከት እያስነፉ፣ አዋጅ እያሳወጁ መገበያየት ዓይነት የሕዝብ የዕለት ተዕለት የዝና ስራ አይደለም።
አንዳንዶቻችን ኑሮን አቅልሎ ከመኖር ይልቅ አማራጭ ያለውም የሌለውም አስቸጋሪ በሆነም ባልሆነም ጊዜ ሆቴልና ሬስቶራንት እንጀራ ካልቆረስን፣ በየካፌው ሻይ ቡና ካልጠጣን፣ የቡቲኩን ፋሽን ካልለበስን፣ በየማጌጫው ቤት ቁሶች ካልደመቅን፣ ውድ ስልኮችን ካልያዝን፣ በኮንትራት ታክሲ ካልሄድን… ሰው የሆንን አይመስለንም። ኑሮና ሕይወትን ንጹሕና ቀላል በሆነ መንገድ መኖር መቻል ከሰው በታች የሆንን ይመስለናል።
የምንጫማቸው ጫማና የምንለብሳቸው አልባሳት፣ የምንገለገልባቸውና የምናጌጥባቸው ቁሶችን የዋጋ ውድነት ብቻ መተረክ የሰብዕናችን መለኪያዎች አይሆኑንም። በዝቅተኛና በተመጣጣኝ ዋጋ መገበያየት የበታችነት መለኪያም አይደለም። የኑሮ ልከኝነት እንጂ። ቲማቲም በስጋ ዋጋ የዘንድሮ ቲማቲም ደም አለው ወይ? አለች አንዷ የስራ ባልደረባዬ፣ ሽንኩርት በዶሮ ዋጋ፣ ኪሎ ስጋ በበግ ዋጋ፣ ዳቦ በእንጀራ ዋጋ መሸመት ኑሮን ማሸነፍ አይደለም። በኑሮ መሸነፍ እንጂ።
በዕለት ተዕለት የግብይትና አገልግሎት አጠቃቀም ሥርዓታችንና በሌሎችም ተዛማጅ ነገሮች ላይ በሥርዐት ልንኖር ይገባል። ቢያንስ በታወቁ መንግስት በተመነላቸው ታሪፎች በመገበያየት የኑሮውን ውድነት ልንታገለው እንችላለን። እንዲህ አይነት የኑሮ ዘይቤ ሁሌም በመንግስት አዋጅ፣ በጋዜጣዊ መግለጫ፣ በምክር ቤት ውሳኔ የሚስተካከል አይደለም። ሥርዓትን በማክበር የሚመጣ ነው። ሁሌም ውድ ነገር የትልቅነት መለኪያም አይደለም። ተገቢውን የገበያ ሥርዐት ማሰብና መፍጠር አሪፍነትና ዘመናዊነት ነው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2014