በአገራችን የዘመናዊ ትምህርት መጀመር ኢትዮጵያ ከሌላው አለም ጋር እንድትተዋወቅ ብሎም ከተኛችበት ጥልቅ እንቅልፍ ነቃ ብላ ሌላው አለም የደረሰበትን እንድትረዳ ትልቁን በር ከፍቷል። ዛሬም ቢሆን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ከተተበተብንበት የኋላቀርነት ውስብስብ ቋጠሮ ሊያወጣን የሚችለው አማራጭ መንገድ ትምህርት ነው።
በአግባቡ ከተጠቀምንበት ለማለት ያስደፈረኝ በአገራችን ዛሬ እግር ከወርች አስሮ አላንቀሳቅስ ያለንንና በየቀኑ የሰቀቀን ዜናዎችን እንድንሰማ ያደረገን ችግር ምንጮቹ ምሁራን የሚባሉት /ስለ አገር ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው/የአገር ልጆች በራስ ፈቃድም ሆነ የሌሎችን አላማ ለማሳካት እየሄዱበት ያለው ጠማማ መንገድ በመሆኑ ነው።
ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ ስልጣኔ፤ የራሷ አስተምህሮና የትምህርት ስርአት ያላት አገር ናት። አሁን ያለውን የስልጣኔ በጥራዝ ነጠቅነት እንድትቀላቀል ያስቻላት ከአውሮፓ የመጣው ዘመናዊ ትምህርት ነው። የአውሮፓው አስተምህሮ ደግሞ ወደአገራችን የገባው እዛው ሄደው በተማሩ የኛው ልጆችና በግብዣና በፈቃዳቸው ወደ አገራችን በገቡ የአውሮፓ ዜጎች ነው።
በተለይ ከ1960ዎቹ በኋላ የመጡ ምሁራን ከየተላኩበት አለም የቃረሙትን ርዕዮተ አለም አቅሟ በተዳከመው አገራችን ላይ ነባራዊውን ሁኔታ ከግምት ሳያስገቡ ሊተገብሩ ሲጣጣሩ አገራችንን መሽቶ በነጋ በቁልቁለት መንገድ ሲያምዘገዝጓት ቆይተዋል። እነዚህ የተለያዩ የአውሮፓ አገራትን ረግጠው የመጡ “ምሁራን” እንደ ሰለጠነ ሰው መደማመጥ ተስኗቸው፤ ብእራቸውን ወርውረው ነፍጥ በማንገባቸው የተነሳ የሀሳባቸውን መነሻም መድረሻም ያልተረዳ በርካታ የደሃ አርሶ አደር ልጅ ጭዳ ሆኖ ቀርቷል።
የእነሱ በሃሳብ መከፋፈል ሳያንስ በስራ፣ በማህበራዊ ህይወትና በተለይ በመምህርነት በአገር ውስጥ ሲያገለግሉ ይህንኑ አሻፈረኝ ባይነት በአገሪቱ እንዲስፋፋ አድርገውታል። ይህ «እኔ ብቻ አውቃለሁ» «እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን» እሳቤ ዛሬም ከስልሳ አመት በኋላ የአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ከአርባ በላይ በደረሰበት ወቅትም በኢትዮጵያ የተማረ ሰው መለያ ሆኖ ቀርቷል።
እያንዳንዱ “ምሁር” አንድ ቃል በተናገረ አልያም አንድ ቃል በጻፈ ቁጥር የኢትዮጵያ ህዝብ የአብሮነት ገመድ እየላላ መምጣት ጀመረ ብል ማጋነን አይሆንም። ይኸው እኔ ብቻ አሸናፊ ልሁን ትንቅንቅን ስር እየሰደደ መጥቶ ዛሬ ዛሬ በበርካታ ወጣት አእምሮ ውስጥ እየተሰነቀረ እየረበሸን ይገኛል። እንዲህ አይነት የተጣመሙ እሳቤዎችን የነ አገር ተረካቢ በሆኑ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም መመልከት አዲስ አይደለም።
አገር ወዳድ ትውልድ በመፍጠሩ ሂደት ምሁራንና ንቁ የምንላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የችግር መነሻ ከመሆናቸው ባሻገር ለሚያምኑት ህዝብ ጀባ የሚሉትም የመፍትሄ ሀሳብ አዳማጭ ስለጠፋ ብቻ ሳይሆን ብዙ ግዜ ከውጪው አለም የተኮረጀ በመሆኑ ውሃ የሚቋጥር መፍትሄ ሲያስገኝልን አልታየም። በመሰረቱ የትምህርት አላማ ነገሮችን ሁሉ የሰው ልጅ ለራሱና ለወገኑ ወደ በጎ ነገር መለወጥ ማስቻል እንጂ ከሰውነት ተራ አውርዶ ባለ ቋንቋ እንስሳ ማድረግ አይደለም።
እውነት ለመናገር ዛሬ ዛሬ ትምህርት ቤቶች በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን በስነ ምግባር አርቆ የማውጣቱ ጉዳይ የተሳካላቸው አይመስልም። ለነገሩ በየትምህርት መስኩ ተመርቀው የሚወጡ ልጆች ስለተማሩበትም ዘርፍ ምን ያህል መሰረታዊ እውቀት ይዘው እንደሚወጡ የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው። ስለዚህ ትምህርት ተቋማት ይህንን የአገርን ህልውና ለማቆም የሚያስችል ኃላፊነትን ለመወጣት በቂ አቅም አላቸው ብዩ ለመናገር አልደፍርም። ነገር ግን አሁንም ቢሆን እያንዳንዱ ወጣት ለቤተሰቡ፤ ለአካባቢው ማህበረሰብና ለየሀይማኖት አባቶች የሚሰጠው ክብር የተሸረሸረ አይመስለኝም።
በመሆኑም ቤተሰብ ልጆቹን በመምከርና በመገሰጽ ለማረም ተመራጩ ወቅት አብረውት ብዙ ግዜ የሚያሳልፉበት ይሄ ክረምት ነው የሚል ትልቅ እምነት አለኝ። ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡም በተለይ የአገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ክረምትን ቤታቸው የሚያሳልፉ ተማሪዎችን የሚያርቁበት የሚቀርጹበት ሊሆን እንደሚገባም ይሰማኛል። በነገራችን ላይ ብዙዎቹ አገራዊ የሰላም እጦት ችግሮች መነሻቸው በትምህርትና በኃይማኖት ተቋማት ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ናቸው ብዬ ስለማምን እንጂ ተግባሪዎቹ በየመንደሩ ስራ ፈትተው የሚውሉ «የራስ ሀሳብ አልባ» ወጣቶች መሆናቸውን አልዘነጋሁትም።
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ከምታስተናግዳቸው ብዝሃነቶች መካከል እንደ ምግብ እንደ አለባበስ በየአካባቢው ያሉ የግጭት አፈታት ስርአቶቻችንም ተጠቃሾች ናቸው። በኢትዮጵያ በቋንቋ ከተመዘገቡት ብሄረሰቦች ቁጥር በላይ የግጭት አፈታት ስርአቶች እንዳሉን ይታወቃል። እነዚህ የግጭት አፈታት መንገዶች የየራሳቸው የአከዋወን ስርአት ያላቸው ቢሆኑም ሁሉንም ከመነሻ አላማቸውና ከሚሰጡት ማህበረሰባዊ ፋይዳ አንጻር እንደሚከተለው ልናስቀምጣቸው እንችላለን።
በኃይማኖት ረገድም ልጆችን ልናርቅበት የሚያስችለን በቂ አስተምህሮዎች እንዳሉን ይታወቃል። ለዚህም የኃይማኖት አባቶችም ከእርስ በእርስ ፉክክር ወጥተው የነፍስ ልጆቻቸው ሰውን በሰውነቱ እንዲቀበሉ ፍቅርንና አብሮነትን እንዲያስቀድሙ ማስተማሪያው ግዜ አሁን ነው ብዬ አምናለሁ። በክረምቱ በየእምነት ተቋማቱ የኃይማኖት ትምህርት ለመስጠት የሚወጡት ማስታወቂያዎች ከላይ የጠቀስኩትንም ቢያካትቱ የተሻለ ነው።
ማህበራዊ ችግሮቻችንን ለመቅረፍ ማህበራዊ ተቋማቶቻችን መጠቀማችን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው። እነዚህ ባህላዊና ኃይማኖታዊ ስርአቶቻችን በአንደኛ ደረጃ ከማህበረሰቡ የፈለቁ በመሆናቸው ማህበረሰቡ በፈቃደኝነት አምኖ የሚተገብራቸውና የሚገዛላቸው መሆናቸው ሲሆን፤ በሁለተኛ ደግሞ በተለይ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርአቶች እንደ ፍርድ ቤት ለግጭቱ አካላት ለሆኑት ግለሰቦችም ይሁን ቡድኖች ጥፋተኛውን በመለየት ተገቢውን ቅጣት በመስጠት ለተበዳይ ፍትህ ከመስጠት ባሻገር የበዳይና የተበዳይ ቀጣይ ግንኙነት በቂምና በቁርሾ የታጀበ እንዳይሆን ግጭቶችን ከስር መሰረታቸው የመቅረፍ አቅም ያላቸው ናቸው።
በአንጻሩ በዘመናዊ መንግድ በህግ አግባብ ችግሮቻችን እንቅረፍ ብንል ከተደራሽነትና ከተነሳችሽነት ጀምሮ ያለንን አቅም ባለፉት ጥቂት ወራት በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶች ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩን ይመስለኛል። ለነገሩ የህግ አስከባሪ አካላት ያላቸውን አቅም አሟጠው ይጠቀሙ እንኳን ብንል ከአገራችን የቆዳ ስፋት፤ ከህዝብ ብዛት፤ ከአሰፋፈር ሁኔታችንና ካላቸው የቁሳቁስ ግብአት አቅም አንጻር የትም መድረስ አይቻልም።
እናም ወላጆች የኃይማኖት አባቶችና በመንግስት መዋቅር ስር የሚገኙ የወጣት ማእከላትና የተለየዩ አደረጃጀቶች ሰው ሰው የሚሸቱ፤ ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚቀበሉና በምክንያት የሚኖሩ ልጆችን በመስከረም ወደትምህርት ገበታ እንዲልኩላት ኢትዮጵያ አበክራ ትጠይቃለች። ስለዚህ ሁላችንም በያለንበት የፍቅር፣ የመተሳሰብና የአንድነት ስንቅ አስይዘን ልጆቻችንን፤ ወንድምና እህቶቻችንን አሰንቀን አዲሱን አመት ለማስጀመር ዛሬ እንነሳ እልሀለሁ። ቸር እንሰንብት።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2014