የሁለት ሙያዎች ወግ፤
በተቀራራቢ ዲሲፕሊንና ሥነ ሥርዓት ራሳቸውንና አባላቱን ሳይንገራገጩ በመምራት አክብሮት ከተጎናጸፉ የዓለማችን ዕድሜ ጠገብ ተቋማት መካከል ሁለቱ የሚሊቴሪና የፍትሕ ኢንስቲትዩሽን በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ::ሁለቱ ነባር ተቋማት የሰው ልጅ ራሱን በቡድን አደራጅቶ መኖር ከጀመረበት ጥንተ ዘመን ጀምሮ የነበሩና ያሉ ናቸው::ዛሬም ድረስ ሳይናወጡ እንደጸኑና እንደተከበሩ በሙሉ ሞገሳቸው የመሰንበታቸው ምሥጢርም በእጅጉ መደጋገፍ በመቻላቸው ነው፡፡
እነዚህ ሁለት ተቋማት የሚወደሱት የረጅም ዘመናት የዕድሜያቸው የሽበት ፀጋ ግድ ስለሚል ብቻ ሳይሆን እጅጉን በመቆራኘት ስለሚኖሩ ጭምር ነው::ይደጋገፋሉ ከማለት ይልቅ መሠረታዊ ባህርይ ይወራረሳሉ ማለቱ የተሻለ ገላጭ ነው::ከየትኞቹም የዓለማችን የሙያ ዘርፎች መካከል ከተቋም እስከ ግለሰብ በጥብቅ ሕግጋት፣ ሥነ ሥርዓትና ዲሲፕሊን የሚመራው የወታደርነት ሙያ ነው::
«ምንም አይደል» ይሉት አባባል በወታደራዊ ተቋም ውስጥ ቦታም ሆነ ከበሬታ የለውም::«አድርግ» ወይንም «አታድርግ» የአንድ ወታደር ክልኤቱ ትእዛዛት ናቸው::«ባላደርግስ?» ዓይነት መልስ ከወታደር አንደበት የራቀ ነው::ስለዚህም ነው ወታደራዊና የሕግ መርሆዎች ቁርኝታቸው ከመደጋገፍም ከፍ ብሎ የዝምድና ያህል ተጣምረዋል የሚባለው::
«ላብ ደምን ያድናል» የተለመደ የወታደራዊ ብሂል ብቻ ሳይሆን እንደ ሕግ የሚቆጠር የፀና መርህ ጭምር ነው::ወታደራዊ ሕግና ደንብ ሲመች የሚፈጽሙት ሳይመች የሚያመቻምቹት ሳይሆን ትዕዛዙ የእዝ ሰንሰለቱን ጠብቆ የሚተገበረው እንደወረደ ሳይሸራረፍ ነው::የአንድ ወታደር የጊዜ ሰሌዳ በሕግና በሥርዓት የሚተረጎም እንጂ ለይምሰል ወይንም ስለተባለ የሚነደፍ አይደለም::
እልህ አስጨራሹን ወታደራዊ ሥልጠናና ዲስፕሊን ለመግለጽ ሲፈለግም «ላብ ደምን ያድናል» መርህ በጥብቅ ሕግ በተግባር ይተረጎማል::እያላበውም ሆነ እያነባ በሥልጠናና በዲስፕሊን የሚመራ ወታደር በግዳጅ ቀጣናው ድልን መጎናጸፉ አይቀሬ ነው::ከግዳጅ በፊት ሥልጠናና ላብ በአግባቡ ተጣምረው ከተተገበሩ የሕይወትና የአካል መስዋዕትነትን የማስቀረት ወይንም የመቀነስ ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡
ወታደር «ዋትቶ አደር»፤
ይህ የተዘወተረ አባባል አንድ ወታደር የአገሩ ሉዓላዊ ክብር እንዳይደፈርና ሕዝቡ በሰላም እንዲኖር የሚከፍለው አታካችና አድካሚ መዋተት የተገለጸበት ብሂል ነው::የወታደር ዋነኛው ትኩረቱና የግዳጁ ተልዕኮ አገሩን፣ ሕዝቡንና የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማውን ክብር ማስጠበቅ ነው::የተቀረው የዕለት ኑሮው ሩጫ ሁለተኛ ወይንም ሦስተኛ ግዴታው ነው – ቤተሰቡ እንኳን ሳይቀር::ስለዚህም ነው የአገሩን ሉዓላዊነትና ክብር ከሁሉም ነገር ስለሚያስቀድም የወታደርነት ሙያ የተከበረና የተመሰገነ ነው የሚባለው::ታሪክም ሆነ ተሞክሯችን የሚመሰክረው ይህንን እውነታ ነው፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ዓላማ የተከበረውን የወታደርነት ሙያና ግዳጅ ከ እስከ ከ ለመተንተነት ተፈልጎ ሳይሆን ለዛሬው ትኩረታችን እንደ ማሳያና መንደርደሪያነት ይጠቅም ስለመሰለን ነው::የአገሬ ዜጎች በሙሉ ወታደር መሆን ባንችልም እንኳን የወታደር ሞራሉና መንፈሱ ቢኖረን ኖሮ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ መልክ እንዲህ በማዲያት ባልወየበ ነበር የሚል ቁጭትን ለመግለጽ ጭምር ነው፡፡
በወታደራዊ ጥበብ ሳይንስ ውስጥም ሆነ በእያንዳንዱ የዕለት ተዕለት ወታደራዊ ግዳጅ ውስጥ አንዲት ደቂቃ በከንቱ አትባክንም::ከማለዳ ጀምሮ እስከ ተልዕኮ ማጠናቀቂያ ሰዓት ድረስ አንድ ወታደር የሚከውናቸው ተግባራት የታወቁ ናቸው::ከእንቅልፉ የሚነሳበት ሰዓት፣ መኝታ ክፍሉን የሚያሳምርበት፣ አለባበሱ፣ የማለዳ ስፖርቱና ቆጠራው (ፎሌው)፣ የምግብ ሰዓት፣ የግቢው ጽዳት፣ እንቅስቃሴውና የግዳጅ ተልዕኮ አፈጻጸሙ በሙሉ አንድም በኅብረት አለያም በግል ከሥርዓትና ከሕግ ውጪ ዝንፍ አይልም፡፡
በብሔራዊ የውትድርና ግዳጅ ውስጥ መሳተፍ ባህል በሆነባቸው አገራት ዜጎቻቸው በአብዛኛው የጤንነታቸው አቋም የተሻለ፣ አኗኗራቸውና ለሥራ የሚሰጡት ክብርና ትጋትም እንዲሁ የሚያስመሰግን እንደሆነ በበርካታ ጥናቶች ተረጋግጧል::አገሬ ይህን መሰሉን የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ዜጎቿ እንዲያልፉበትና ሥርዓት እንዲሆን አጥብቃ ብትሠራ ከፍ ያለ ትሩፋት ይኖረዋል የሚል እምነት አለን፡፡
ሌባ ባይሰርቅ፤ ዳኛም ባይገድ፤
«ላብ ደምን ያድናል» መርህ በተግባር ሊተረጎም የሚገባው ለወታደራዊ ግዳጅ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ አገራዊ ጉዳዮቻችንም ጭምር ሊሆን ይገባል::ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች፣ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ባለሙያዎችና በኃላፊነት ወንበር ላይ የተመቀመጡትም ሳይቀሩ በሌብነት ተግባር ተሰማርተው የሚልከሰከሱት ላባቸውን ጠብ አድርገው፣ የተሰጣቸውን የኃላፊነት ወንበር አክብረውና ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው አገራቸውንና ሕዝባቸውን ከማገልገል ይልቅ «ለነፍሳቸው ሳስተው» በአቋራጭ ለመክበርና ሕይወታቸውን ለመለወጥ በመጎምዠታቸው ነው::
ለላባቸው ሳስተው ለሌብነት ጀግነው እጃቸውን አርዝመው በጥፋታቸው ሲጋለጡም «የሚያነቡት የደም እንባ» ለአነሳነው ዋና ጉዳይ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል::ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ውስጥ ሕዝቡን በሥራ ሰዓት የጊዜ ዝርፊያና በጉቦ ሲያሰቃዩ የተጋለጡት የመንግሥት ሹመኞች ከእስራቱ ባሻገር የቱንም ያህል «የደም ዋጋ» ቢከፍሉ የጎደፈውን ስማቸውን እንደማያነጹት የተረዱት አይመስልም::
እነርሱና የእነርሱ የሆኑ ቤተሰቦችም ሳይቀሩ «የዚያ የምንትሱ ሚስት/ባል፣ አባት/እናት» እየተባሉ የማኅበረሰቡ መጠቋቆሚያ እንደሚሆኑም ይጠፋቸዋል ተብሎ አይገመትም::ይህ መጠቋቆም የዕድሜ ልክ ውርስ ሆኖ እንደሚከተላቸውም የዘነጉት ይመስላል::ሕዝብን ለማገልገል ለተሾሙበት ኃላፊነት ላባቸውን ከመክፈል ይልቅ የሕዝቡን «ደም ለመምጠጥ» መትጋታቸው ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል እያደር ያዩታል፤ እኛም መጨረሻቸውን እንከታተላለን፡፡
አገር መርጣና ሕዝብ አክብሮ በሰጣቸው ሹመት «ላባቸውን ጠብ እያደረጉ» ለብዙኃን ጥቅም፣ እርካታና ውጤት ከመትጋት ይልቅ ቅዠታቸውና ህልማቸው ዘርፎና ገፎ ለመክበር ከሆነ በአንድ አጋጣሚ መጋለጣቸው እንደማይቀር ብዙዎች የዘነጉት ይመስላል::በገሃድ ተጋልጠው ሀፍረት መከናነባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ፈጣሪ አምላክም የሚከፍላቸው መራራ ብድራት መኖሩንም ሊያስታውሱት ይገባል::
የሰረቁትን ሀብትም ሆነ ጊዜ ተደላድለውና እፎይ ብለው እንዳይበሉ ጤናቸው ሲያውካቸው፣ እንዳሻቸው እንዳይሆኑም ሕሊናቸው ሲያሳድዳቸው የሚኖሩ በርካታ ዜጎችን ቤታቸው ይቁጠረው ብሎ ማለፉ ይቀላል::«ላብና ንጽህና» ከጸጸት እንደሚጠብቅ፣ ከመሳቀቅም እንደሚታደግ፣ «ከደም እምባም እንደሚከልል» ደግሞ ደጋግሞ ለማሰብ ህሊናቸውን ስለደፈኑ ሊሰርቁ እጃቸውን ሲዘረጉ ይህ እውነታ አይታያቸውም::የሚያጭዱት ውጤት የከፋና የከረፋ እንደሚሆን ውስጣቸውን ቢያደምጡ ኖሮ ለስርቆሽ የተዘረጋውን እጃቸውን ወደ ፍም እሳት ለመክተት ባልተጣደፉ ነበር፡፡
ትዕግስት ያደርሳል ከክብረት፤
ምልከታችንን ሰፋ አድርገን «ላብ ደምን ያድናል» የሚለውን መርህ ለሌላ ታላቅ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ እንዋሰው::የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋናውን ተልዕኮውን ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁ እየተገለጸልን ነው::ይህ ታላቅ ሕዝባዊ ተስፋ የተጣለበት ተልዕኮ ብዙ ተግዳሮትና የበረታ ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል ይገመታል::
በጠብመንጃ ካልተዋጣልን፣ በሻምላ ካልተሞሻለቅን፣ በሰይፍ ካልተዋጣልን የሚል መርህ ያነገቡ የጥፋት ቡድኖች ሕዝብ ውስጥ መሽገውና ጫካ ውስጥ አድፍጠው ባገነገኑበት በዚህ ወቅት በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበን እንመካከር ሲባል በእነርሱ ብሶ ሰበብ አስባብና መሰናክል እየፈጠሩ ነገሮችን ለማወሳሰብ እንደሚጥሩ መጠርጠሩ ቀቢጸ ተስፈኛ አያሰኝም፡፡
ቢሆንም ግን «ላብ ደምን ያድናል» ብለናልና ብዙ የሚያበሳጩ፣ አልፎም ተርፎ ልብ የሚሰብሩ ክስተቶች ቢስተዋሉም ሕዝቡ፣ የምክክር ኮሚሽኑ አባላትም ሆኑ «ትልቁ» መንግሥት በልብ ስፋትና በትእግስት ላብ እንደ ውሃ እየተንዠቀዠቀም ቢሆን ለቆሰለችው የአገራችን የሰላም ርግብ ሲባል «የደመኞችን» ዓላማ አክሽፎ መከራችንን ለማስቆም መጨከን የግድ ይላል::
ደም ከሚፈስ ላብ እንደ ውሃ ቢንቆረቆር ይበጃልና::ሕዝቡም ሆነ ባለድርሻ ነን የሚሉ አካላት ለዚህ ተስፋ ለተጣለበት የምክክር ኮሚሽን የተልዕኮ ፍሬያማነት የራሳቸውን ሚና ሊወጡ፤ በጎ አሻራቸውንም ለማተም ሊተጉ ይገባል፡፡
አገራዊ ጉዳያችንን ሰፋ እናድርገው::ድህነት ሕዝባችንንና አገራችንን እግር ተወርች ጠፍሮ ያሰረው በተፈጥሮ ሀብት ስላልተባረክን ሳይሆን ለሥራና ለጊዜ ፊት ነስተን ባይተዋር ስላደረግናቸው ነው::እንደ ወንዞቻችን በከንቱ ሲፈስ የኖረው የጊዜ ሀብታችን የሚታደስ ወይንም ተመልሶ ሊመጣ የማይችል መሆኑን እየዘነጋንና ላባችንን ጠብ ለማድረግ እየሰሰትን ድህነት ሞቆን ደርበነው መኖራችን ምስክሩ ሌላ ሳይሆን ኑሯችን ነው::
ለስንዴ ልመና አኩፋዳችንን ተሸክመን ለምጽዋት ስንዞር የኖርነው፣ በድርቅ በትር ክፉኛ ስንደበደብ ወደንና ፈቅደን ጀርባችንን ለግርፋቱ የሰጠነው ላባችንን ለማፍሰስ፣ ጊዜን አክብረን በአግባቡ ለመጠቀምና ሕይወታችንን መርህ አልባ በማድረግ ተጎሳቁለን መኖርን ተቀዳሚ ምርጫችን ስላደረግን ብቻ ነው፡፡
ከተፈጥሮ ጋር እርቅ ለመፍጠርና አረንጓዴ አሻራውን ለማሳረፍ ሕዝቡ ከአገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ ተንቀሳቅሶ ታሪክ ለመሥራት መጨከኑ «ላብ እንደምን ከመከራ እንደሚታደግ» ጥሩ ማሳያ ነው:: ልክ እንደ አረንጓዴ አሻራ ዘመቻችን ሁሉ የሥራ ባህላችንን ለመለወጥም ብሔራዊ ስትራቴጂ ተነድፎ ትንሽ ትልቁ «የላብ መዋጮውን» ለማበርከትና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ሊሠራበት ግድ ይሏል፡፡
ሳይሰሩ ለመብላትና ሳይደክሙ ለመክበር የሚቃዡ ዜጎችም ባንነው ከእንቅልፍ ሊቀሰቀሱ ጊዜው ግድ ይላል::በተለይም ለዘመን አመጣሹ የማኅበራዊ ሚዲያ ምርኮኛና እስረኛ የሆነው አብዛኛው ወጣት ከተሽመደመደበት የቅዠት ዓለም ነፃ እንዲወጣና አርነቱን እንዲያውጅ «ላብ ደምን ያድናል» የሚለው የትድግና ጥሪ በይፋ ሊቀርብለት ይገባል፡፡
«ልጅን ማሳደግ እንደ ዘመኑ ነው» ለሚል ፍልስፍና ተገዢ የሆኑ ወላጆችም ጊዜ እንዴት እንደሚዋጅና ላብ ደምን እንደምን እንደሚያድን በግልጽ ቋንቋ ለልጆቻቸው ሊነግሯቸውና በወላጅነት ሥልጣን በአግባቡ ሊያርቋቸው ይገባል::የትምህርት ሥርዓታችንም ቢሆን ለትውልዱ የከንቱነት መሹለኪያ ቀዳዳ ከፍቶ በምኞት ከሚያማልል ይልቅ ቢመርም ቢጎመዝዝም ከወታደራዊ መርሆዎች መካከል ጥቂቱን ተውሶ በመተግበር አደራውን ሊወጣ ጊዜው ዛሬ ነው፡፡
ላብ ከደም የሚታደገው በጦር ሜዳ ውሎ ብቻ አይደለም::በዕለት ተዕለት አኗኗራችን ውስጥም ሊተረጎም የግድ ነው::ጦርነት የአንድ ወቅት ክስተት ነው::ድህነት ተጣብቶ ያስገበረን ግን የቤታችን ማደጎ ሆኖ በጠላትነት ስለሰለጠነብን ነው::ድህነት የሚሸነፈው በክላሽንኮፍና በአዳፍኔ አይደለም::
ድህነትን ወልደን ያሳደግነው እኛው ስለሆንን አምክነን የምናስወግደው የላባችንን ጠብታ አስተባብረን «እምብየው!» በማለት በሥራና በፈጠራ ትጋት ስንዘምትበት ብቻ ነው::የተጠቃቀሱት የችግሮቻችን ዓይነቶች በርከት ይበሉ እንጂ መፍትሔው አንድ ነው፤ «ለላባችን የቅድሚያውን ክብር እንስጥ!» – ኑሯችንን የምንለውጠውና የምንለወጠው በሥራ ነው::የምናሸንፈውም ለትእግስትና ለመርህ እጅ በመስጠት ብቻ ነው::ሰላም ይሁን!
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2015