ይህን ርዕሰ ጉዳይ በኢቢሲ ይሁን በፋና ባየሁና በሰማው ጊዜ ስለጉዳዩ አስተያየቴን ላካፍል ምክንያት ሆነኝ።
ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ክብነት ያላቸው ናቸው። በሌላ አገላለጽ ክብነት ሕይወት ላላቸው ነገሮች መገለጫ ነው። ጠርዝነት፣ ጫፍነት፣ ሹልነት ወይም ጽንፍነት ያላቸው ነገሮች ሕይወት አልባ ናቸው። እንደውም እነዚህ ሕይወት ከሚኖርባቸው በተቃርኖ ሕይወት የሚያልፍባቸው ናቸው። ሕይወትንም አይፈጥሩም። ስለክብነት፣ ጎባባነት ወይም ቅንፍነት ቅርጽ በጥሩ አብነት የሚሆነን የሰው ልጅ ነው።
ለምሳሌ ያህል የራስ ፀጉሩ ቅንጣት፣ ጭንቅላቱ፣ አንገቱ፣ ደረቱ፣ ሆዱ፣ እጁ ፣ እግሩ፣ ከውስጥ አካሎቹ እስከ ደምስሮቹ ድረስ ያሉት የሰውነት ክፍሎቹ ፍጹም ክቦች፣ ለክብነት የቀረቡ ወይም ቢያንስ የተቀነፉና ጎበብ ያሉ እንጂ የትኛውም አካሉ ጠርዝነት፣ እጥፋት፣ ሹልነት፣ ጫፍነት…. ያለው አይደለም። ከዚህም ጋር የሚዛመዱ ሕይወት ያላቸው እንስሳት፣ አራዊት፣ አዕዋፋት፣ እንደሰው ልጅ ውጪአዊም ውስጣዊም የአካል ክፍሎቻቸው ክብነት፣ ጎባባነት ያላቸው ናቸው። እንዲሁም ከደቂቅ የሳር ዘር እስከ ግዙፉ ዛፍ ድረስ ከስር እስከ ጫፋቸው ክብነት፣ ጎባባነት ያላቸው እንጂ ጠርዝ ወይም ጫፍ የላቸውም።
በሌላ አተያይ ብንመረምር የሕይወት ምሳሌና ሕይወትን የሚሰጡን ነገሮች እንኳን ክቦች ናቸው። ለምሳሌ ስርና ፍሬ የዕፅዋት ዐይነቶችን የሚሰጡን፤ ዘርና እንቁላል ሰውንና እንስሳትን የሚያስገኙልን ክብነት ያላቸው ናቸው። የሕይወት ምሳሌ የሆነው ውሃም በጣት አልያም በጠጠር ቢነኩት ክብነትን ይሰራል ወይም ያሳያል። የፈጣሪም እስትንፋስ ክበብ አለው። ቃልም ሕያው የሆነው በእስትንፋስ ውስጥ በክበብ ስለሚወጣ ነው። በዚህም የፈጣሪም የሰውም ቃል መዋቲ አይደሉም። ሕያዋን ናቸው። የፈጣሪ እስትንፋስ አዳም ላይ እፍፍፍ… ባለበት ጊዜ ነፍስ መዝራቱ የሕያውነት ሕያው ምስክር ነው። በሰው ዘንድም ቃሉን ከአንደበቱ ባወጣ ጊዜ አይሞትም። ቃል በክበብ እስትንፋስ እንደሚወጣ በቀዝቃዛ የአየር ንብረት ውስጥ ከሰው አፍ የሚወጣውን ትንፋሽ ማየቱ በቂ ነው።
ክብነት ዘላለማዊነትም ነው። ፍጹምነትም ነው። ቋሚነትም ነው። ለምሳሌ የሰው ልጅ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ይሁን ዘላለማዊነትን ያምናል። ዘላለማዊ አምላክ አማኝ ስለሆነ ለዘላለማዊነቱ ይተጋል። ክብነት መነሻና መድረሻ የለውም። ጫፍና ጠርዝ የለውም። በክብ ውስጥ ላለ ጽንፍ የለውም። ክብነት የፍጽምና ያህል የእኩልነትም ልክ ነው። ከመሐል ተነስቶ ለሁሉም እኩል ይሆናል። አምላክ ለሰው ልጆች እንደሆነው። ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ለየትኛውም ዘር፣ ሃማኖት፣ ጎሳ፣ ብሔር፣ ጎጥ፣ ቀለም፣ ቡድን… ሳያደላ የምድር እምብርት በሆነች በቀራንዮ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል ራሱን ሰጠ። በክብ ዓለም በምድር መሓል ለሰው ሁሉ ሳያደላ ፍጹም በሆነ እኩልነት ራሱን ሰጥቶ ዓለምን አዳነ።
ምሳሌ ምሉዕ አይሆንም የሚባለው እውነት ቢሆንም ከላይ የጠቀስነው አብነት ለሀገራችን ኤሊት፣ ሊዕቃን፣ አክቲቪስትና ምሁራንም ይሆናል። በቀደመ ተምሳሌት የሚሆኑን ያስፈልጉናል ባለኩት ጽሑፌ ኤሊአም ያልኳቸው ናቸው። በዚህ ውስጥ የሃማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሊቃውንቱ፣ ገዢውና አማራጭ መንግሥታትንም ጭምር እሳቤ እንደሆነ አንባቢ ታሳቢ ያደርግልኛል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ ኤሊአም ባልኩት የተጠቀሳችሁ ሁሉ ሀገር ለማዳን ከዳር ላይ ከመቆም፣ ጫፍ ላይ ከመገኘት፣ በጽንፍ ከመሆን መሐል ላይ መገኘት ሀገሩን ሁሉ ለመታደግ በትልቁ ኃላፊነትን መወጣት ነው።
ሀገርም የሐሳብ መሐል፣ የእኩልነት መሐል፣ የሁሉነት መሐል አላትና ኤሊአም ቦታችሁ ከጽንፎች መካከል ወርቃማው አማካይ ያለበት የሁሉ እኩል በሆነው መሐል ላይ ነው። ‹‹ከጽንፎች መካከል ወርቃማውን አማካይ ፍለጋ›› ማለት እኔ በገባኝ ከሀገር ችግር አምብርት/ መሐል/ ላይ ቆሞ ያለአድሎ ለሀገሩ ሁሉ ማሰብ መቻል ነው። ዛሬ ሀገራችን ባለችበት አሁናዊ ችግር ከጠርዘኝነት፣ ከጽንፈንነት ወይም ከሕዝብ ሕልውና ጫፍ ቆሞ የራስን ዓለም የሚፈጥሩትን አርቃቸሁ ወደሀገር ሐሳብ፣ ወደጋራ ማንነት ለማምጣት መታገል ፍሬአማ ያደርጋችኋል።
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ማንም ግለሰብ ሆነ ቡድን ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ሊኖረው ይችላል። አስካልጸነፈ ድረስ ጤናማ ነው። ጤናማ ሐሳብን ለማጋራት ደግሞ መሐል ወደሆነው ወደሁሉ ልብ መጥቶ መመካከር ብዙ ነገር ያቀናል። መሐል መጥቶ ማሰብ እንደቀራንዮ በጉ ቆምንለት ለምንለው ሕዝብና ሌላውንም መታደግ ያስችላል። ዳር፣ ጫፍ፣ ጠርዝ፣ ጽንፍ…መቆም ለመታደግ ሳይሆን ለመግደል ነው የሚመቸው። መሐል ማስታረቂያና መታደጊያ ነው። ዳር ሆኖ የቃል ሰይፍ ከመምዘዝና ነፍጥ ከማንሳት የሀገር መሐል ላይ ከመገኘት በላይ ምን ወርቅ አለ? ከዚህ የሰው ልክነት በላይ ምን አለ? መሐከለኛ ሆኖ በሰው ዓለም ውስጥ መኖር፣ መሐል ሆኖ ሕዝብን ማገልገል፣ ለሀገር መሐል ሆኖ ወርቃማ ሐሳብ ማዋጣት… በራሱ ፀጋ ነው፤ መታደል ነው።
ሕዝብ የጋራ መጠሪያ ነው። ጫፍ፣ ጠርዝ፣ ጥግና ጽንፍ ላይ ያለ ግለሰብም ሆነ ቡድን የራሱ እንጂ የሕዝብ መጠሪያ አይሆንም። የሕዝብ ጫፍ፣ ጠርዝ፣ ጥግና ጽንፍ የለውም። ሕዝብ የሀገር ማዕከል ነው። የሕዝብ መንግሥትም የሀገር ማእከል ነው። ለዚህም ነው ማዕከላዊ መንገሥት የሚባለው። በአንድ ሀገር የሚገለል ወይም ዳር የሚተፋ ሕዝብ የለም። ሕዝብን የሚመራ መንግሥትም እንደማዕከላዊነቱ ‹‹ከጽንፎች መካከል ወርቃማውን አማካይ ፈለጋ ›› ላይ መትጋት አለበት። አማራጭ መንግሥታትም እንዲሁ።
ጠርዘኝነትና ጽንፈኛ ሐሳብ እንዲፈጠር የሚያደርጉት ወርቃማው አማካይ ሐሳብ ሌላቸው የፖለቲካው ሊዕቃንና የተለያዩ የሕዝብ መሪዎች አካላት ናቸው። ሕዝብ በአንድ ልብ አይጸንፍም። መንግሥት ሁሉን ሕዝብ በፍትሐዊነት በክበቡ ውስጥ ወርቃማውን አማካይ እስከያዘ ድረስ መንጋውን ከእረኛው የሚነጥቀው አስኮብላይ አይኖርም። መቼም ቢሆን ለጽንፈኝነት የሚያደርስ አስተሳሰብ የሚመጣው በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከሕዝብ ሳይሆን ከገዢውና ከአማራጭ መንግሥታት ነው። በሕዝብ መካከል ተጸናንፎ የሚኖር ከሆነ የጋራ ገበያ፣ የጋራ ቋንቋ / ለመግባቢያ የምንጋራው…./ በጋራ ማምለክ፣ በጋራ መማር፣ በጋራ መስራት፣ ተጋብቶ መዋለድ… አይኖርም ነበር። በሀገራችን ጥንትም፣ ዛሬና ነገም ይህ የሕወት መንገድ ይቀጥላል። ጸንፎ የሚቀር ሕዝብ የለም፤ አይኖርምም።
ሕዝብ በባሕሪው ማዕከላዊ አስተሳሰብ ያለው ነው ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም መራጭ ነውና። መራጭ ደግሞ ከዚህ ይህ ይሻላል እያለ እያወዳደረ ለጋራ የሚሆነውን የሚመርጥ ነው። ሕዝብ ‹ከጽንፎች መካከል ያለ ወርቃማውን› ሐሳብ የያዘውን ተወዳዳሪ መንግሥትን እንጂ ጫፍ የቆመ ሐሳብ ያለውን የሚመርጥ አይደለም። ዛሬ ላይ እንደሀገር የሚያስፈልጉን ሕዝብን መካከል ሆነው የሚያሳምኑ ወርቃማ ሐሳብ ያላቸው ናቸው።
ሀገሪቷን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመሩ ባለድርሻ አካላት በዚህ ከታመኑና በተግባር ካሳዩ ሰላምንና ልማትን በቀላሉ ማምጣት ይችላሉ። ከጽንፎች መካከል ያለው ወርቃማው ቁልፍ ጉዳይ ደግሞ ፍትሕ ነው። ፍትሕ ሲሰፍን አድሎ የለም። እኩልነት ይረጋገጣል። ሌባ ሙሰኛ አይኖርም፤ በወዝ ማደር ይመጣል። አንደኛ ሁለተኛ ሕዝብ አይኖርም፤ ሁሉም በሁሉም ዘንድ እኩል ይሆናል። ውንብድናና ሽብር አይኖርም፤ በሁሉም ዘንድ ሰላም ይሰፍናል። ነቀፋና ጥላቻ አይኖርም፤ ፍቅር ይነግሳል።
በሀገር ላይ እኛ ፣እኛ፤ ይኼ፣ ይኼ የሚያስብለው የፍትሕ መዛባት ነው። የሰው ልጅ ፍትሕ አማኝና ለማኝ ነው። በየትኛውም እምነት ያለው ኢትዮጵያዊ ፈጣሪው ሲቀጣው እንኳን አያጉረመርምም ምክንያቱም ፈጣሪው ፍትሐዊ ነው ብሎ ስለሚያምን። ምሕረቱንም ቅጣቱንም በፀጋ ይቀበላል። እንዳውም እንዳልተተወና በፈጣሪው እንደተጎበኘ ያስባል። ዘረ አዳም ይህን የተማረው ከሰው ልጆች አባት ከአዳም ጀምሮ ሕግ ሲተገበር ፍትሕ ሲከወን በልቦናው አኑሮ ተምሯል። ጽንፈኛ ደግሞ የሚፈጠረው የፈጣሪን ሕግ ከልቦናው ባስወጣው ነው።
ለፍትሕ የለዘበ ሕዝብ ባለበት ሀገር ላይ ያሉ መሪዎች ሁሉ በተለይ የፖለቲካው ሊዕቃን ከጽንፎች መካከል ያለውን ወርቃማውን ሕግ ማስተግበር ይችላሉ። ለሕዝብ መካከለኛ ሆኖ ማገልገል መታደል ነው። መሐከለኝነት በራሱ ሰፊ ፍካሬ አለው። ለምሳሌ ያህል መሐከለኝነት ጥልቀት ነው፤ ግልብነት አይደለም። እኩልነት ነው፤ ኢፍትሐዊ በሆነ መልኩ መበላለጥን አያመጣም። ማኅፀንነት ነው መውለድ መወለድ አለው፤ ቢወለዱ ለሁሉም ነው የሚያገለግሉት ልክ ከሀገር ማኅፀን እንደወጡ ነው አይመክኑበትም። ሚዛንነት ነው ሁሉን ይጠብቁበታል፤ መርጠው አያደሉበትም።
ልብነት ነው ማስተዋልና ብስለት አለው፤ በኃይለ ስሜትና በደመነፍስ አይመሩበትም። እነዚህ በመካከል ወርቃማው ላይ ያሉ ናቸው። በተቃርኖ ያሉት በሐሳብና በሕይወት ዳር፣ ጫፍ፣ ጠርዝና ጽንፍ…. መቆም ግን መጨረሻነት ነው፤ አላዋቂነት ነው፤ ማርጀት ነው፤ ቀንድና ጭራ መሆንን ያመጣል። የሀገር ወገንተኝነት፣ ኅብረ ብሔራዊት ሀገር፣ አብሮነትና ለሌላው ማሰብ የሌለበት ሐሳብ ከጠርዘኝነት ወይም ከጽንፈኝነት ወደ አክራሪነት ከመሸጋገር የዘለለ ትርፍ የለውም።
ለሰው ሁሉና የሰው ሁሉ ሆኖ ዘላለማዊ ወርቃማነት ተጎናጽፎ መገኘት ማትረፍና የሰውነት ልክነት ማሟላት ጭምር ነው። ወርቅ ውድ ገንዘብ ነው፤ ወርቃማ ሐሳብ እንደወርቅ ውድ ነው የወርቅን ባሕሪ ገንዘብ ያስደርጋል። ወርቅ ንጹሕ ማዕድን ነው፤ ወርቃማ አማካይ ሐሳብም ንጹሕ አስተሳሰብ ነው። ወርቅ የከበረ ጌጥም ነው። ወርቃማ ሐሳብም ያን ያህል ያደምቃል። ወርቅ በቀላሉ አይገኝም አይረክስምም፤ ወርቃማ ሐሳብም እንዲሁ ልዩ፣ ውብና ውድ ነው።
የ ‹‹ከጽንፎች መካከል ወርቃማውን አማካይ ፍለጋ›› ፋይዳዎች።
- የከረሩ አመለካከቶችን ያረግባል።
- ከሁለት ዋልታ ሐሳቦች ወደማዕከላዊ ሐሳብ ያመጣል።
- ድርድራዊ ጽንሰ ሐሳብና ውይይታዊ ስሜትን ያበለጽጋል።
- ለሀገራዊ የጋራ ጥቅም በተለያዩ ወገኖች መካከል በራሱ አሸናፊ የሆነ መሸናነፍን ያመጣል።
- የሦስተኛው ዐይን/ የአማራጭ መንገድ/ ያሰፋል።
- ሚዛናዊ አስተሳሰብን ያጎናጽፋል።
- ወርቃማ አማካይ ውስጥ ያለው የሐሳብ ባለቤትነት የጓነ የሕዝብ ፍቅርን ያጎናጽፋል።
- በጥሩ መንገድ ሰውነትን ይፈጥራል። እንደየብርሃን መልአክ ቅዱስና እንደጨለማው መልአክ እርኩስ ተባብለን እንዳንሳሳል ይረዳል። ሰውነት ደግሞ በራሱ ከጽንፎች መላእክቱ መካከል ያለ ነው። ሰው መሆን በራሱ ወርቃማ አማካይም ነው።
በአጭሩ ከጽንፎች መካከል ወርቃማውን አማካይ ሐሳብን ለመጠቀም ነባር የአብሮነት እሴቶቻችን ገንዘብ ማድረግ አለብን። ይህ ለሀገር ሰላም፣ ዕድገት፣ ልማትና ሥልጣኔ ወደር ሌለው አማራጭ ነው። ለዚህም የሀገሪቷ ኤሊት፣ ሊዕቃን፣ አክቲቪስታና ምሁራን /ኤሊአም/ ከጽንፎች መካከል ወርቃማውን አማካይ ሐሳብ አንጥራችሁና አጥርታችሁ በማውጣት ሀገር አቅኑ።
መኩሪያ አለማየሁ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2014