በዓለም አቀፍ ደረጃ በብልፅግና የሚታወቁ አገራት ለከፍታቸው ምክንያት የሆኑ አበይት ምክንያቶችን እንደሚጠቅሱ ሁሉ፣ ከድህነት መላቀቅ የተሳናቸውም ለዝቅታቸው በርካታ ሰበቦችን ይደረድራሉ። መልከአ ምድራዊ አቀማመጣቸው ምቹ አለመሆኑና በተፈጥሮ ሀብት አለመታደላቸው ደግሞ ከሰበቦቻቸው መካከል ጎልቶ ይሰማል።
እንደ ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ምልከታ ግን እነዚህ አገራት በዕድገት ወደ ኋላ ለመቅረታቸውና ለድህነታቸው በምክንያትነት የሚያቀርቧቸው ምክንያቶች ሚዛን የሚደፉ ሆነው አይገኙም። በእርግጥ ለግብርና ምቹ በሆነና በበቂ ሁኔታ የተፈጥሮ ሀብት ባለበት አካባቢ የሚኖር ሕዝብ ከሌላው የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ይኖረዋል። ይህ ማለት ግን የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ብቻውን ኢኮኖሚን ያሳድጋል ማለት አይደለም።
‹‹በተፈጥሮ ሀብት መበልፀግ ብቻውን የእድገት ምንጭ ቢሆን ኖሮ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን የመሳሰሉ አገራት ድሃ ሆነው፣ ምንም ዓይነት የተፈጥሮ ሀብት የሌላቸው እንደ እስራኤል ዓይነት አገሮች ደግሞ በኢኮኖሚ የላቁ አይሆኑም ነበር›› የሚሉት ምሁራኑ፣ ከሁሉ በላይ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት የተለያዩ ተቋማት የሚፈጥሩት ሁለንተናዊ አቅም ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ።
በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ስመጥር የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ማርጋሬታ ጂኒክ ሃኑዝ፣ ‹‹የአንድን አገር ብልፅግና ለመገመት ተቋማትን ብቻ መመልከት በቂ ነው፣ ‹‹If you want to predict the prosperity of a country, just look at its institutions.›› ማለታቸው ለዚሁ ነው።
እንደ እርሳቸው ሁሉ ሌሎች ምሁራን ‹‹በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚ የላቁ አገራት የከፍታቸው አብይት ምክንያቶች ውጤታማና ተጠያቂነት የሰፈነበት ተቋም በመገንባታቸው ነው፣ በተለይ ለማደግ የሚታትሩ አገራት ይህን በአግባቡ በመገንዘብ ለተቋማት ፈጠራ ብሎም አቅም ለማጎልበት ትኩረት መስጠት ቢችሉ በቀላሉ ትሩፋቱን መቋደስ አይቸገሩም›› ይላሉ።
የኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ፕሮፌሰር ቢሩ ፓካሽ ፖል፣‹‹Why Institutions Are so Important for Growth›› በሚል ጽሑፋቸው፣ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት በተለይ የተቋማት አቅም ወሳኝ መሆኑን ያሰምሩበታል። ለዚህ እሳቤአቸውም እኤአ እስከ 1970ዎቹ ማብቂያ ተመሳሳይ የኢኮኖሚ አቅም ላይ የነበሩት አይቮሪኮስትና ሜክሲኮን በዋቢነት ያቀርባሉ።
ጸሐፊው ሁለቱ አገራት የትናንትና ገጽታቸው ታሪክ ሆኖ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የዕድገት ደረጃና ገፅታ ላይ የመገኘታቸው ዋነኛው ምክንያት አፍሪካዊቷ አገር የተቋማት አቅምና ሚና በአግባቡ መረዳት ባለመቻሏ መሆኑን ያመላክታሉ።
ለአገራት ሁለንተናዊ እድገት የተቋማት ሚና ወሳኝ መሆኑን ከመስማማት ባሻገር ከተቋማት መካከልም በይበልጥ ወሳኝ የሆኑ መኖራቸውንና እነርሱን በመለየት ትኩረት አድርጎ መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም የሚያስገነዝቡ ምሁራን ቁጥርም ቀላል አይደለም። የእሳቤው አራማጆች በአንድ አገር ውስጥ ሁለንተናዊ እድገትና ብልፅግናን ለማስተዋወቅ በተለይ የፋይናንስ፣ የትምህርት፣ የፍትህ ብሎም የሕዝብ አስተዳደር ተቋማት ከሌሎች በተሻለ የላቀ ሚና እንዳላቸው ይጠቁማሉ።
በሊዝበን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ኢኮኖሚስት የሆኑት ሊያም ብራንትን የመሳሰሉ ምሁራን በአንፃሩ ‹‹፣Which institutions matter for economic growth? በሚል ጥናታቸው፣ ይህን እሳቤ ውድቅ ያደርጉታል። አቋማቸው ደግሞ ‹የፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚያዊም ሆነ የማህበራዊ ተቋማት ሁለንተናዊ አቅም የአንድን አገር እድገት ቢወስንም ከሁሉ ገዝፎ አቅም መፍጠር የሚችለውና ዋነኛው አስፈላጊ ተቋም የትኛው ነው የሚለውን በቀላሉ መግለፅ ይቸግራል›› የሚል ነው።
አገራቱ ኢኮኖሚያቸውን በላቀ መልኩ ለማሻሻል አፈፃፀማቸውን ለማጎልበት ይረዳል የሚሉትን ተቋማት በፈለጉት መልኩ የማዋቀር ነፃ ፈቃድ ያላቸው መሆኑን የሚነግሩን ምሁሩ፣ ፋይዳቸው የላቁ ተቋማትን መለየትና ትኩረት ለመስጠት ከተቸገሩም ብቸኛ አማራጫቸው የሌሎችን በተለይ በኢኮኖሚ እድገት ማማ ላይ የተሰቀሉ አገራትን የተቋማት ልየታና አወቃቀር መቃኘት እንደሚችሉም ያመላክታሉ።
ምልከታቸው ይለያይ እንጂ ሁሉም ምሁራን የተቋማት አቅም የአንድ አገር እድገት መሠረት ስለመሆኑ ያሰምሩበታል። ኢትዮጵያ በአንፃሩ የተቋማት የእድገት ቁልፍነት መረዳት ሳትችል አመታትን አስቆጥራለች። የኢትዮጵያ የተቋም ስሪት በድርጊትና ባላቸው ውቅር በርካታ ችግሮች ሲታይበት ቆይቷል።
የተቋማት አቅም ግንባታ በዘመቻ መልክ ያዝ ለቀቅ በሚል መልኩ ካልሆነ በስተቀር መድረሻውን በመወሰን በተጠና እና ወጥ በሆነ መልኩ ሲካሄድም አይስተዋልም። ተቋማቱ ሌላው ቀርቶ እርስ በእርስ አይነጋገሩም። አይደጋገፉም። አንደኛው የሚሠራው ፕሮጀክት ሌላኛው ማወቅ መወያየትና ብሎም ተቀራርቦ መሥራት ሲገባው ይህ ሲሆን ግን አይስተዋልም። ጠንካራ ተቋማት ባለመኖራቸውም ምክንያት ኢትዮጵያ ከአመት አመት ግዙፍ የሚባሉ ኪሳራዎችን ስታስተናግድ ቆይታለች።
ይሁንና መሰል ችግርን ፈጥኖ ማስተካከል ካልቻለ አገር በምትፈልገው ፍጥነት መራመድ አትችልም። ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ከተፈለገ ተቋማት በመገንባት ሂደት ውጤታማ የሚሆኑበትን መንገድ መፈለግ አቅምና አደረጃጀታቸው ምን ያህል አዋጭ ብሎም አመቺ ነው? የሚለው በየጊዜው መከታተል የግድ ነው።
ወሳኝ የሚባሉ ተቋማትን በአግባቡ ማደራጀትና ተደራራቢ ተግባር የሚፈፅሙትን መለየት ብሎም ወደ አንድ ማጠፍ ከተቻለም አለአግባብ ይባክን የነበረ ከፍተኛ መጠን ያለው የሕዝብና የአገር ሀብትን ከኪሳር መታደግ ያስፈልጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም ኢትዮጵያ የፈለገችውን ለማሳካት እና ያሰበችበት ቦታ ለመድረስ ተቋማዊ ግንባታ ላይ በጣም መሥራት እንዳለባት ጠንቅቆ የገባቸው ይመስላል። ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የኢትዮጵያን ለማበልፀግ በሚያግዝ መልኩ ተቋማዊ አቅምን ለማጎልበት የተለያዩ ጥረቶችን አድርገዋል። እያደረጉም ይገኛል። በዚህም መሻሻሎች እየታዩ ለውጦችንም መመልከት እየተቻለ መጥቷል።
በተለይ ከዚህ ቀደም በሙስና ተተብትበው የነበሩ በአግባቡ ቢሠራባቸው የአገር ካስማ የሆኑ ተቋማትን ከተዝረከረከ አሠራር ማላቀቅ ብሎም ፈር ማስያዝ ተችሏል። ለዚህም በተለይ የገቢዎችና ጉምሩክ ተቋማት አፈፃፀም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሆኖ ይጠቀሳል።
ሌላኛው ማሳያ በቀድሞ ስሙ «ሜቴክ» ተብሎ ይጠራ የነበረውና ከለውጡ ወዲህ ስሙን የኢትዮ -ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ወደሚል ስያሜ የቀየረው ተቋም፣ ቀድሞ የግዥ የነበረ ሲሆን ከለውጡ ወዲህ ግን አምራች ተቋም እየሆነ ይገኛል። የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አምባሳደር ምስጋናው አረጋ፣ ‹‹ግዥ ባህሪ ብቻ ይዞ የነበረውን -የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ተቋም ከለውጡ ወዲህ የማምረቻ ተቋም አድርገነዋል ማለታቸውም ይታወሳል።
ከለውጡ በፊት የሙስና ገነት የነበረውና ከለውጡ በኋላ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 398/2009 የተቋቋመው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንም እንዲሁም ልማት ባንክ በተቋማት ሪፎርም ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ካስመለከቱት ተርታ የሚጠቀስ ነው።
ከለውጡ ወዲህም ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ የደህንነት ጥበቃ ተቋማትን እንደ አዲስ በሚባል መልኩ ማደራጀት ተችሏል። በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እንዲሁም ለታላቅ አገር ታላቅ ተቋም በሚል የተደራጀው ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንም በዚህ ረገድ አብይ ማሳያ ሆነው ይጠቀሳሉ።
ይህ ማለት ግን ተቋማዊ አቅምን በመገንባት ረገድ በተከናወኑ ተግባራት የሚፈለገው ተክለ ቁመና ላይ መድረስ ተችሏል ማለት አይደለም። የተሠራው አድናቆት የሚነፈገው ባይሆንም የሚቀረው ብዙ ትግል የሚጠይቅ ነው። በቀጣይም ተቋማት እየለዩ የሚሻሻለውን ማሻሻል፣ አንዳንዶቹንም እንደ አዲስ ማደራጀትና አፍርሶ መገንባት ይጠይቃል።
ኢትዮጵያን በጽኑ መሠረት ላይ የሚያቆሙ ጠንካራ ተቋማት የመፍጠሩ ትግልም ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል። ከዚህ ባሻገርም የአንዳንድ ተቋማት ግንባታ ውጤት በአንድ ጀንበር የሚመጣና የሚመዘን እንዳልሆነም ጠንቅቆ መገንዘብ ያስፈልጋል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም