“ያልታደልሽ እንዴት ከረምሽ”
ከመንግሥታዊ ሥርዓት መሸጋገሪያ “ጥቋቁር” ታሪኮቻችን መካከል ሁለቱ መገለጫዎች በእጅጉ የጎሉና ተደጋጋሚነት የሚታይባቸው ናቸው ። አንደኛው መገለጫ አሮጌውን ሥርዓት በነፍጥም ሆነ በብልጠት አስወግዶ መንበረ ሥልጣኑን የሚቆጣጠረው አዲሱ መንግሥት “ተሸናፊውን መንበር የሚገለብጠው” እጁን በደም ታጥቦ ሲሆን፤ ሁለተኛው መገለጫ ደግሞ አዲሱና መጤው መንግሥት የቀዳሚውን ሥርዓት የታሪክ ውርስና ቅርስ ተሽቀዳድሞ የሚያጠፋውና የሚያወድመው በጭካኔና በበቀል መሆኑ ነው ።
በሁለቱ መገለጫዎች ማሳያነት ብቻ ከትናንት እስከ ዛሬ ኢትዮጵያን የመሩ መንግሥታትን ታሪክ ብንመረምር እውነታው በሚገባ ፍንትው ብሎ ሊታየን ይችላል። ትናንትን ከዛሬ ያቆራኙትን ሥርዓተ መንግሥታት ችግርና ስህተት ብቻ እየነቀስን ከማዋረድና ታሪካቸውን ከማጠልሸት ይልቅ በጎነታቸውንና ትሩፋታቸውንም ጎን ለጎን አጉልተን ላለማሳየት ማንና መቼ አዚም አድርጎ እንደቀረጸን ለጊዜው ምክንያቱ ይህ ነው የሚባል የጥናት ውጤት ስላላገኘን “ይህንን ድፍን ዕንቁላል” ይሉት ዓይነት ሀገራዊ እንቆቅልሻችንን የምንዘለው እንደተለመደው “በሆድ ይፍጀው” ትዝብት ይሆናል ። ጽናቱን ይስጥሽ ኢትዮጵያዬ!
“አባባ ጃንሆይ”
ለዛሬው ጽሐፍ መቆስቆሻ የሆነን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ዜና መዋዕል በፎቶግራፍ አካቶ የታተመውና በደማቅ ሥነ ሥርዓት ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል የተመረቀው “አባባ ጃንሆይ” የሚለው ሥዕላዊ መጽሐፍ ነው ። የመጽሐፉ አሰናጅና አርታኢ ወዳጄ ጌታቸው ተድላ አበበ (ዶ/ር) ብርቱ ደራሲና ለሀገር በጎነት የሚተጉ መሆናቸውን ብቻ በመጠቆም ወደ ግለ ወግ ትረካዬ አመራለሁ ።
የንጉሠ ነገሥቱ 130ኛ ዓመት የሚከበረው በዚሁ ሳምንት ሐምሌ 16 ቀን 2014 ዓ.ም መሆኑን በማስታወስ ይህ ጸሐፊ የልጅነቱን ወራት ገጠመኝ ማስታወስ ብቻም ሳይሆን “አባባ ጃንሆይን መልካም ልደት!” በማለትም መልካም ምኞቱን ይገልጣል ። የንጉሡን ታሪክና በጎ አሻራዎች ከትውልድ ትውልድ ሳይደበዝዙ እንዲተላለፉ ለማድረግ “የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፋውንዴሽን” እያደረገ ስላለው መልካም ተግባርም ማመስገኑ ተገቢ ይሆናል ። “ከታሪክ መሰዊያ ላይ አመዱን ሳይሆን እሳቱን ጫሩ” የሚለውን አባባል ደጋግመን ብናስብበት ለበርካታ ሀገራዊ በሽታዎቻችን ስክነት በጥቂቱም ቢሆን ሊያግዘን ይችላል ።
ቀ/ኃሥ ከአልጋ ወራሽነታቸው ጀምሮ እስከ ንጉሠ ነገሥት ከፍተኛው የሥልጣን እርከን ድረስ ሀገሪቱን ያገለገሉትና የመሩት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ (1909 – 1967 ዓ.ም) ነው ። የአልጋ ወራሽነት ዘመናቸውን ካሰብነውም ከስድስት አሠርታት በላይ ይዘለቃል ። በእነዚህ ረጅም ዓመታት ውስጥ ንጉሡ ህልቆ መሳፍርት በሌላቸው ዘርፎች ሀገሪቱን ወደ ከፍታ ስለማሸጋገራቸው ታሪክ ምስክር ነው ።
ይህ ማለት ግን ንጉሡ ከስህተት ነጻ ናቸው፤ ምንም በደል የሌለባቸው ፍጹም ነበሩ ማለት እንዳልሆነ አንባቢው የሚረዳ ይመስለናል ። የከሳሾቻቸው ጭፍንም ይሁን ምክንያታዊ ፍረጃ እንደተጠበቀ ሆኖ
ያለ ማንም አስገዳጅነት አብዛኛው የወቅቱ ትውልድ (ተቃዋሚዎቻቸውን ጨምሮ) ይጠሯቸው የነበረው “አባባ ጃንሆይ” እያሉ እንደነበር እድሜውን ያደለን ዜጎች ሕያው ምስክር ነን ።
ይህ ጸሐፊ የንጉሠ ነገሥቱን የዘመነ ስልጣን ትሩፋቶች በትምህርት፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ፣ በጦር ኃይል አደረጃጀት፣ በሰብዓዊ ተግባራት ወዘተ. እያለ ከመዘርዘር ተቆጥቦ ከንጉሡ ጋር የተገጣጠመበትን አዝናኙን የታዳጊነቱ ትዝታ በወግ መልክ መተረኩን መርጧል ።
“አባባ ጃንሆይ የእኛ እናት አባት!”
ምክንያቱን በውል ባንረዳውም አባባ ጃንሆይ ኮልፌ የሚገኘውን ፈጥኖ ደራሽ ግቢና ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታልን (ዛሬ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል የሚባለውን) አዘውትረው ይጎበኙ ነበር ። ንጉሡ ወደእነዚህ አካባቢዎች በመጡ ቁጥር ዛሬ በአስራ ስምንት ቁጥር አውቶቡስ ማዞሪያነት በሚታወቀው መስቀልያ መንገድ ላይ ቆመው፣ ወይንም ዝቅ በማለት ቤተሰብ መምሪያ በማይታወቅበትና ምንትስ የሚሉት የዛሬው ዘር ማምከኛ ባልተፈለሰፈበት በዚያ ዘመን ያለ ዕቅድ ለተፈለፈለው እኛን መሰል የኮልፌ ውሪ አንድ አንድ ብር ያድሉ ነበር ።
በእኛ በውሪዎቹ ዘንድም ሆነ በትላልቆቹ ሠፈርተኞች ዘንድ የአባባ ጃንሆይ መምጣት የሚታወቀው በጋሽ በቀለ ደምሴ (በቀለ ጢሞ) የዶቅዶቄ ድምጽ ነበር ። ብዙ ሰው ሻምበል በቀለ ጢሞን ይጠራ የነበረው “ጋሼ” የሚል ቅጽል በስሙ ላይ እያከለ እንጂ በሻምበልነቱ ማዕረግ አልነበረም። ሞላ ያለ ሰውነት የነበረው ጋሽ በቄ የግራና የቀኝ ፂሙን አሹሎና ኮስታራ ፊቱን አጨፍግጎ ሲመለከቱት አንዳች የፍርሃት ድባብ ያሰፍናል ። ሁሉም ሰው ጋሽ በቄ ጢሞን አንተ ይለው ስነለነበር እኔም አፌን ሞልቼ የተዳፈርኩት ከጀማው አጠራር ላለማፈንገጥ ነው።
ጋሽ በቀለ ጢሞ የሚይዘው የሞተር ቢስክሌት የታርጋ ቁጥር 80 እንደነበር አስታውሳለሁ ። ጋሽ በቄ ጢሞ ንጉሡን ለምን እንደሚያዋክባቸው ባናውቅም እንደ ክረምት አሸን አካባቢውን ያጥለቀለቀው ውሪ የአንድ ብር ዳረጎቱን ተቀብሎ ሳይጠናቀቅ ሞተር ብስኪሌቱን እያስጓራ አባባ ጃንሆይን አክለፍልፎ ይወስድብን ነበር ።
አንድ ዕለት በሠፈራችን ኳስ ሜዳ እየተራገጥን ሳለ እንደ ቤተሰቦቻችን ንብረት የተለማመድናት የጋሽ በቀለ ጢሞ ዶቅዶቄ ከሩቅ እያንባረቀች ስትመጣ ሳይረኗ ጆሯችን ውስጥ ጥልቅ ይላል ። ያ አመዳም የኮልፌ ውሪ ሁላ የቡሆ ዕቃ የመሰለ አፍንጫውን እያበሰ በነፋስ ፍጥነት መክነፍ ይጀምራል ።
ይሄን ግዜ ቅንድበ ግጥሙ አብሮ አደጋችን ክንፍዬ (ንጉሡ የሚታሙበትን ያልተረጋገጠ አሉባልታ ሰምቶ ኖሮ) ከእኛ ከጓደኞቹ ወደ ኋላ ቀረት ብሎ የተጋጠመውን የቅንድቡን ፀጉር ለማስወገድ መላ ብሎ በዘየደው ብልሃት በአካባቢው ባገኘው ስለታም የባልጩት ድንጋይ ቅንድቡን ሲፈገፍግ ክፉኛ ስለቆረጠው ደሙ እየተንዠቀዠቀ ከኋላችን ከች አለ ። ግማሽ ልባችን ክንፍዬ ዘንድ፣ ግማሽ ልባችን አባባ ጃንሆይ ዘንድ እንደተከፈለ ፤
አባባ ጃንሆይ፣ አባባ ጃንሆይ፤ የእኛ እናት አባት፣
አሳድገውናል፣ አሳድገውናል፤ በማር በወተት ።
እያልን በመዘመር፣ ክንፈም ደሙን እያበሰ ከእኛ ጋር ተቀላቅሎ የአንድ ብር ግባችንን ልንመታ ችለናል ። ዕድሜና የሥርዓተ መንግሥታት መለዋወጥ ያላደበዘዘው የክንፈ ጠባሳ ግን ዛሬም ድረስ በቅንድቡ አካባቢ አሻራው ሳይጠፋ ምልክቱ ሆኖ ቀርቷል ። በወቅቱ “ቅንድበ ግጥም ሕፃናትን” በተመለከተ ያልተረጋገጥ የሀሜት ሹክሹክታ ይወራ ስለነበር እኛም ውሪዎቹ መላምቱን እውነት አድርገን ክንፈን መሰል ቅንድበ ግጥም ጓደኞቻችንን ማብሸቃችን እውነት ነበር ። ይህንን አፈ ታሪክ ያስታወስኩት በይባላል መሆኑ ልብ ይባልልኝ ። እንኳን እኔ ከቁምጣ ያልዘለልኩ ውሪ ቀርቶ ማንም ሰው በወቅቱ ስለ ሃሜቱ እርግጠኛ ስላልነበረ ተረት ነው ብሎ ማለፉ ይቀል ይመስለኛል ።
የንጉሡ ብር “የበረከት ምሥጢርና” ድንክዬዋ ውሻ፤
ከንጉሥ እጅ አዘውትሮ ብርና የማበረታቻ ቃል መቀበል እንዴት ደስ እንደሚል ከእኔና ከዕድሜ አቻዎቼ የተሻለ የሚመሰክር ያለ አይመስለኝም ። የአባባ ጃንሆይን አንድ ብር ለበረከቱ ሲል በብር ከሃምሳ ሣንቲም የሚመነዝርልንን የባለሱቁን አብደላንና የወላጆቻችንን ልማድ ሳላስታውስ ማለፉ ተገቢ አይመስለኝም ።
ከንጉሡ እጅ የምንቀበለው አንድ ብር ትርፍ ሣንቲሞችን እየጨመሩ የሚመነዘሩልን የንጉሥ እጅ የነካው ብር ልዩ በረከት አለው እየተባለ ስለሚታመን ነበር ። አንዱን ብር በትርፍነት ከለወጡ በኋላም ከሌሎች ብሮች ጋር ደባልቀው የሚያስቀምጡት ለብዙ ግዜያት ነበር ። እናቴም በትርፍነት የገዛችኝን የአባባ ጃንሆይን ብር ከሌላ ገንዘብ ጋር ደባልቃ ሙዳዩዋ ውስጥ ስታስቀምጥ በተደጋጋሚ አስተውያለሁ ።
አባባ ጃንሆይ ለእያንዳንዱ ልጅ ብር የሚያድሉት “በመሬት አንቀጥቅጥ” የንጉሥነት ክብራቸው ተኮሳትረው አልነበረም ። ተራችን ደርሶ ጫማ ስመን ብድግ በማለት እጃችንን ብር ለመቀበል ስንዘረጋ ብዙውን ግዜ ትኩር ብለው በርህራሄ እያስተዋሉን “አንተ ንፍጣም፣ አንተ ረባሽ” በማለት ከቀለዱብን በኋላ “ስታድግ በምን ሙያ መሰማራት ትፈልጋለህ? ስንተኛ ክፍል ነህ? በትምህርትህስ ጎበዝ ነህ?” በማለት ይጠይቁንና “በል ይህንን ብር አልባሌ ቦታ እንዳታጠፋው” ብለው በመምከር ያሰናብቱናል ።
ከአባባ ጃንሆይ እጅ የመጨረሻውን ድፍን ሽልንግ (ሃምሳ ሣንቲም) የተቀበልነው ካልተሳሳትኩ በስተቀር በ1960ዎቹ መጀመሪያ ገደማ ሳይሆን አይቀርም ። የተቀበልንበትን ቦታና ሁኔታ አልዘነጋሁትም እዚያው ዛሬ አስራ ስምንት ቁጥር አውቶቡስ ማዞሪያ እየተበላ በሚጠራው መስቀልያ መንገድ ላይ ቆመው ነበር ።
ንጉሡ ዝርዝር ሣንቲም ሰጥተው ስለማያውቁ በዚያን ዕለት የሰጡን ስጦታ ለአዋቂዎቹም ሆነ ለእኔ ብጤ ዘመነ አቻዎች ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕስ መሆኑን አስታውሳለሁ ። አንዳንድ አዋቂ ሰዎችም ባልተጠበቀ ሁኔታ ለመጀመሪያ ግዜ ንጉሡ ሣንቲም መስጠታቸውን እንደ መልካም ምልኪ አልቆጠሩትም ነበር ።
በዚያን ዕለት የማስታውሰው ሌላው ክስተት እንዴትና በምን ሁኔታ እንደሆነ በማናውቀው ምክንያት የንጉሡ ድንክዬ ውሻ ከእግራቸው ሥር ሹልክ ብላ በመውጣት በቅርብ ርቀት ይገኝ በነበረ ጫካ ውስጥ መገኘቷ ጉድ አሰኝቶ ነበር ። አቤት በውሻዋ መጥፋት የደረሰው ትርምስ? ትዕይንቱ ዛሬም ድረስ ከዓይነ ህሊናዬ አልጠፋም ። የክብር ዘበኛ ወታደሮችና የፈጥኖ ደራሽ ፖሊሶች በአካባቢው ፈሰው ሰውን መቆሚያ መቀመጫ አሳጥተው ማንም ሰው ካለበት ቦታ አንዳይንቀሳቀስ በማዘዝ ያደረጉት ፍተሻና አሰሳ አጀብ የሚያሰኝ ነበር ።
ደግነቱ ያቺ ተንኮለኛ ውሻ ጊዜያዊ ትርምስ ብትፈጥርም እጅግም ሳትርቅ ወደ ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል መታጠፊያ ጫካ ውስጥ ስትልከሰከስ ስለተገኘች አሰሳውና ውጠራው በቀላሉ ሊጠናቀቅ ችሏል። ከውሻዋ መጥፋት ጋር ተያይዞ ይሰጥ ስለነበረው መላ ምትና ትርጉም ግን ለአንባቢ ግምት መተውን መርጫለሁ ። “በቤተ መንግሥት ውስጥ ተንደላቆ መኖር አስመርሯት የእኛን ኑሮ ለመኖር ተመኝታ ያደረገቸው ነው” በማለት የኮልፌ ልኳንዳ ተራ ተልከስካሽ ውሾች ቀለዱባት እየተባለ ሲፌዝ እንደነበርም ትዝ ይለኛል ።
ንጉሡ በጸሐፊው ቤተሰብ ላይ ያሳደሩት የማይታለፍ ተፅእኖ እነሆ ከዓመታት በኋላም ቢሆን ዛሬም ድረስ ሲወርድ ሲወራረድ በኑሮው ውስጥ መንፀባራቁ አልቀረም ። ታሪኩ እንዲህ ነው ። ነፍሱን በገነት ያኑረውና የጸሐፊው ታላቅ ወንድም ግርማ በለጠ ልጅ እያለ ከአባባ ጃንሆይ እጅ አንድ ብር ሲቀበል ንጉሡ ራሱን እየዳበሱት “አንተ ንፍጣም ይህንን ብር ምን ታደርግበታለህ?” ብለው ይጠይቁታል ። ግርምሽም ትምህርትና ተማሪን ይወዳሉ ማለትን ይሰማ ስለነበር ፈጠን ብሎ አፉ ላይ እንደመጣለት “እስኪሪቢቶና እርሳስ እገዛበታለሁ” ብሎ ይመልስላቸዋል። እርሳቸውም “ቡና ግዢበት ብለህ ለእናትህ ስጣት” ብለው እንደ ዋዛ ይነገሩታል ።
ጠባዬ ሸጋውና ልዩ የመወደድ ፀጋ የተጎናፀፈው ግርማ አንድ ብሩን ከንጉሡ እጅ እንደተቀበለ ሲሮጥ ሄዶ ለእናታችን “አባባ ጃንሆይ ቡና ግዥበት ብለውሻል” በማለት በታማኝነት የንጉሡን ስጦታ ያስረክባታል ። ከዚያን ዕለት ጀምሮ ነው የቡና ሥነ ስርዓት በቤተሰባችን ውስጥ የተከበረና ደማቅ ባህል ለመሆን የበቃው ። እህቶቼም ቢሆኑ ቡና ሲያፈሉ በጥንቃቄና በአክብሮት እንዲሆን ከእናታችን ዘንድ ጥብቅ መመሪያ ስለተሰጣቸው ይህንን ትዕዛዝ ሲተገብሩ ኖረዋል ። የንጉሥ ትዕዛዝ ነዋ! እኔም ከልጅነት እስከ ጉልምስና ዕድሜዬ ለቡና ግብዣ ያለኝ አክብሮት ከፍ ያለ ነው ።
ወርሃዊ የቡና ወጭዬም ቢሆን ዛሬም ድረስ ትንሽ ሳይጋነን የሚቀር አይመስለኝም ። “አመል ይወጣ ከቤት ይከተል ከጎረቤት” እንዲሉ መሃል አራት ኪሎ በሚገኘው ቢሯችን ውስጥ በወር ሁለትና ሦስት ቀናት ባህሉን በጠበቀ ሁኔታ ድፎው እየተዘጋጀ በምሳ ሰዓት ሞቅ ደመቅ ብሎ ቡና ይፈላልን ነበር ። በቤቴ ውስጥም ቢሆን ባለቤቴ የማለዳ ሥራዋን የምትጀምረው የልማዴን ቡና በማፍላት ነው ። ይህ ልማዷ ዛሬም ድረስ አንድም ቀን ተቋርጦ አያውቅም ። ምን ይደረግ እናቴ በውርስ ያስተላለፈችልኝን የንጉሥ ትዕዛዝ መከበር ስላለበት ነዋ!
ይህ ጸሐፊ አራት ኪሉ በሚገኘው የቀድሞ ወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ) የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ወቅትም ንጉሡ እየመጡ ሕጻናት ናቸው ብለው ሳይንቁ እኛን ተማሪዎችን “የነገ ተስፋ ናችሁ” እያሉ ያበረታቱን እንደነበር ማስታወሱ ግድ ይላል ። አባባ ጃንሆይ የእኛ እናት አባት እያልን ስንዘምር የኖርነውም ንጉሡ ይህንን መሰሉን በጎ ተጽእኖ በሕይወታችንና በአብዛኛው የዚያ ትውልድ ሕይወት ውስጥ ስላተሙ ነው ። እውነት እውነት እንመስክርና ሕዝቡ ‹ከእርሳቸው በፊት እምዬ› እርሳቸውን “አባባ!” እያለ የተገዛለት ሌላ መሪ በታሪካችን ውስጥ ኖሮ ያውቅ ይሆን? በግሌ እኔ እንጃ! ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2014