ከአስር ዓመቱ ሀገራዊ የልማት እቅድ ስትራቴጂካዊ ምሰሶዎች (Strategic Pillars) መካከል አንዱ የቴክኖሎጂ አቅም እና ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት ነው። ይህን ለማሳካት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ውጤታማነት ማሳደግ ወሳኝ ግብዓት እንደሆነ ይታወቃል።
የዘርፉን ውጤታማነት ለማጎልበት ከሚተገበሩ አቅጣጫዎች መካከል ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ሃሳባቸውን ወደ ቢዝነስ ተግባራት የሚያሸጋግሩባቸው የኢንኩቤሽን ማዕከላት ይጠቀሳሉ። የቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን ማዕከላት፣ የተለያዩ ድጋፎች ተደርገውላቸው የፈጠራ ሃሳቦችን ወደ ቢዝነስ ማሳደግ የሚያስችል ከባቢ የሚፈጥሩና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዱስትሪዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ወጣቶች ልምድ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ማዕከላት ናቸው።
እነዚህ ማዕከላት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተቋቋሙ ሲሆን፣ በየክልሎቹ ከሚገነቡ የቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን ማዕከላት በተጨማሪ በትምህርት ተቋማት፣ በሲቪል ማህበራት እና በመንግስት ድርጅቶች ውስጥ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ባህልን በተጨባጭ ለማሳደግ የሚረዱ አዳዲስ አሰራሮችን ለመዘርጋት እና የኢኖቬሽን ስነ-ምህዳሩን ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽን ልማትና ምርምር ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ፣ የቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን ማዕከላት ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽንን መሰረት ያደረጉ ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች (Startup Businesses) ሃሳባቸውን ወደ ቢዝነስ እና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ወደ አላቸው ተግባራት የሚያሸጋግሩባቸው ማዕከላት ወይም ተቋማት እንደሆኑ ያስረዳሉ።
የቴክኖሎጂ ጀማሪ ቢዝነሶች (Technology Startup Businesses) ሲባሉ በመሰረታዊነት አዲስ ወይም የነበሩ ኢንተርፕራይዞች ሆነው፤ ሳይንስ (ምርምር)፣ ቴክኖሎጂ ወይም ቢዝነስ ላይ የተመሰረተ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ያላቸው፤ በአንድ ሰው ወይም ከዛ በላይ በሆኑ ሰዎች ስብስብ የሚፈጠሩ የቢዝነስ ዓይነቶች ሲሆኑ፤ እምቅ የማደግ አቅም እና ይህንንም የማሳካት ቁርጠኙነቱና ብቃቱ ያላቸው፤ ወሳኝ የመወዳደር አቅማቸው ፈጠራ የሆነና ቴክኖሎጂን በቢዝነስ ሞዴላቸው ውስጥ የሚጠቀሙ ናቸው።
ይሁን እንጂ እነዚህ የቢዝነስ ስራዎች በአብዛኛው በቀላሉ ሊጠፉ የሚችሉ (Volatile) እና በከፍተኛ እርግጠኛነት በሌለው (Uncertain) ሁኔታ የተከበቡ ናቸው። ስለሆነም በተለየ ሁኔታ በመንግስትም ሆነ በግል የሚፈጠሩ የሳይንስ (ምርምር)፣ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን ማዕከላት ዋናው ስራቸው እንዲህ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን መሰረት ያደረጉ ጀማሪ ቢዝነሶች እንዳይጠፉ ማድረግ እና መሰናክሎችን በማሻገር ቀጣይነት አደ አለውና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ ወደሆኑ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ የግል የቢዝነስ ተቋማት ማሸጋገር ነው። ከግል ዘርፉ ባሻገር በመንግሥት የሚሰሩ መሰል ተቋማትም ለታዳጊ አገራት እድገት ቁልፍ ሚና እንደሚኖራቸው በዘላቂ የልማት ግቦች (Sustainable Development Goals) ላይ በግልጽ ተመላክቷል።
ማዕከላቱ ከሚያከናውኗቸው ተግባራት መካከል ሃሳብ የሚመነጭበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤ ሃሳቦች የሚሞከሩባቸው የመስሪያ ቦታዎች፣ ላቦራቶሪዎች፣ መሰረተ ልማቶችና የቁሳቁስ አገልግሎት ማቅረብ፤ የፈጠራ ውድድሮችንና ሽልማቶችን ማከናወን እንዲሁም ከተለያዩ የኢኖቬሽን ስነ ምህዳር አካላት፣ ማለትም ከምርምር ተቋማት፣ ከባለሀብቶች፣ ከፋይናንስ ተቋማትና ከማኅበራት ጋር ግንኙነት የሚደርግበት ማዕከል ሆኖ ማገልገል የሚሉት ይጠቀሳሉ።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከ15 በላይ የቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን ማዕከላት እንደሚገኙ አቶ ሰላምይሁን ይገልፃሉ። ከእነዚህም መካከል በኦሮሚያ ክልል (በአዳማና ጅማ)፣ በአማራ ክልል (በባህር ዳርና ጎንደር)፣ በሶማሌ ክልል፣ በአዲስ አበባ ከተማና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ማዕከላት ተጠቃሽ ናቸው። ማዕከላቱ በዋናነት የቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽንና ሳይንስ ባህል እንዲጎለብት ማድረግን ብቻ ታሳቢ ተደርገው የተሰሩ ናቸው። በቀጣይ ጊዜያት አካታች የሆኑ የቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን ማዕከላትን ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት የሚከናወኑ ይሆናል።
በሌላ በኩል ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተቋቋሙ የቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን ማዕከላትም አሉ። ለአብነት ያህል በኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ (Information Communication Technology Park) ውስጥ በሁለት ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እየተገነባ የሚገኘው ‹‹ Kinobiz Center›› እና ኦሬንጅ ዲጅታል ማዕከል (Orange Digital Center) ይጠቀሳሉ።
በመንግሥት ከተቋቋሙ የኢንኩቤሽን ማዕከላት በተጨማሪ የግል ኢንኩቤሽን ማዕከላትን ማስፋፋትም ትኩረት የሚሰጠው ተግባር እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሰላምይሁን፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ ለግል የኢንኩቤሽን ማዕከላት መስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ይናገራሉ። በግል ዘርፉ ከሚጠቀሱ የቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን ማዕከላት መካከል ‹‹አይስ አዲስ›› (Ice Addis)፣ ‹‹ብሉ ሙን›› (Blue Moon) እና ‹‹1888EC›› የሚባሉት ይገኙበታል። ከእነዚህ የግል ኢንኩቤሽን ማዕከላት ጋር በተደረገ ትብብር ብዙ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶችንና ታዳጊዎችን ማገዝ ተችሏል።
የኢንኩቤሽን ማዕከላቱ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ስራዎቻቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩና ከስራዎቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን በመጥቀስ፣ የማዕከላቱ መቋቋም አበረታች ውጤቶችን ማስገኘቱንም አቶ ሰላምይሁን ያስረዳሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የማዕከላቱ መቋቋም ጀማሪ ቢዝነሶች በሃገሪቱ እየተበራከቱ እንዲመጡ በር ከፍቷል። በተለያዩ መንገዶች በእነዚህ ማዕከላት ተደግፈው ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ማሸነፍ የቻሉ ጀማሪ ቢዝነሶች መፈጠር ጀምረዋል። ከ500 በላይ እምቅ አቅም ያላቸው ስታርትአፕ ቢዝነሶችንና እስከ 38 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ሀብት መፍጠር ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪም የማዕከላቱ መቋቋም የኢኖቬሽን ባህል ግንዛቤና አስፈላጊነት እንዲያድግ እድል ፈጥሯል።
በኢኖቬሽን ስነ-ምህዳር ውስጥ ቁልፍ ሚና ካላቸው አካላት ውስጥ የሚጠቀሱት እነዚህ የኢንኩቤሽን ማዕከላት፣ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ምርትና አገልግሎት በማምጣት ረገድ በጎ አስተዋፅኦዎችን የሚያበረክቱ መሆናቸውን በመግለጽ፣ መንግሥት ለማዕከላቱ ልዩ ልዩ ድጋፎችንና ክትትሎችን ያደርጋል ይላሉ።
በዚህ ረገድ ለማዕከላቱ ስለሚደረገው ድጋፍና ክትትል አቶ ሰላምይሁን ሲያብራሩ ‹‹መንግሥት ከማዕከላቱ ዲዛይን ጀምሮ በማቴሪያል እስከማደራጀት የዘለቀ ድጋፍና የቴክኒክ እገዛ ያደርጋል። በመዋቅር፣ በህግና በፖሊሲ እንዲደገፉ የማድረግ፤ የተለያዩ ስልጠናዎችና ተያያዥ ድጋፎችን የማቅረብ፤ ለችግሮቻቸው መፍቻ የሚሆኑ ዳሰሳዎችን የመስራት እንዲሁም የኢኖቬሽንና ስታርት አፕ ስትራቴጂዎችን የመቅረጽ ተግባርን ያከናውናል። እነዚህ ድጋፎችም ማዕከላቱ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ባህልን በማጎልበት ረገድ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ሰዎች ለማሳደግና ወደ ገበያ ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት በተሻለ ብቃት ለመፈፀም ያግዟቸዋል ሲሉ ያብራራሉ።
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የምርምርና ልማት ዘርፍ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚገኙ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም የሚያስችል የዕውቀትና የክህሎት አቅም እንዲሁም የአመለካከት ውስንነት በስፋት የሚስተዋል በመሆኑ የቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን ማዕከላቱ ብዙ ተግዳሮቶች ያጋጥሟቸዋል ሲሉም ይጠቁማሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ቀደም ሲል በሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ግልጽ ግብ ያለውና ወጥ የሆነ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማስፈን አኳያ የአሠራር ሥርዓት ክፍተቶች ነበሩ። በግዥም ሆነ በምርምር የሚገኝ የቴክኖሎጂ ዕውቀትን ለማሰባሰብ፣ ለማከማቸት እና ለማሰራጨት የሚያስችል ሥርዓት አለመኖሩ ሀገሪቱ ቴክኖሎጂና ዕውቀትን ለማከማቸትም ሆነ ከተከማቸው ዕውቀት የሚገባትን ጥቅም ማግኘት አልቻለችም። በተጨማሪም የቴክኖሎጂ ሽግግር ስልቶችን ከመለየት ጀምሮ እስከ አጠቃቀም ድረስ በርካታ ክፍተቶች ነበሩ። ይህ ደግሞ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ፈጠራን በመጨመርና ቀጣይ ቴክኖሎጂዎችን በማበልፀግ የተሻለ እሴት ለመፍጠር የሚያስችል ሁኔታ እንዳይኖር አድርጓል።
የአንድ ሀገር ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ሊያድግ የሚችለው ምርታማ የሆነ ኢኮኖሚ መገንባትና በርካታ ተወዳዳሪ ኢንተርፕራይዞችን መፍጠር ሲቻል ነው። ይሁን እንጂ ኢንተርፕራይዞችን ለመፍጠርም ሆነ በተለዋዋጭ የቢዝነስ ከባቢ ውስጥ ተላምደው መጓዝ እንዲችሉ የሚያግዝ የኢኖቬሽን ሥነ-ምህዳር ስላልተገነባ በሀገርም ሆነ በዓለምአቀፍ ደረጃ ብቁ እና ተወዳዳሪ መሆን የቻሉ ኢንተርፕራይዞችን በበቂ መጠን መፍጠር አልተቻለም። ይህ የዘርፉ ክፍተት ደግሞ በቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን ማዕከላት ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ጫና ፈጥሮ ቆይቷል።
አዲሱ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ የኢንኩቤሽን ማዕከላት እንዲጠናከሩ ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገልጿል። ፖሊሲው ጀማሪ ተቋማት እና የኢኖቬሽን ሥርዓተ-ምህዳር ገንቢዎች (STI Incubation Centers) የፋይናንስ፣ የቴክኒክ፣ የመስሪያ ቦታ እና መሰል ድጋፎችን የሚያገኙበት፤ ለጀማሪ ተቋማት (Technology Startups) የገበያ ዋጋ ትመና እና የኢንቨስትመንት እድል የሚፈጠርበት፤ ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት ባላቸው የቴክኖሎጂ መስኮች የግልና የመንግስት አጋርነት የሚኖርበት፤ በጥናት ላይ የተመሠረተ የእሴት ሰንሰለት እና የኢኖቬሽን ክላስተሪንግ ስርዓት የሚስፋፋበት እንዲሁም ውጤታማነታቸው የተረጋገጠና ወደ ምርትና አገልግሎት የተቀየሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚያበረታታ የግዥ ሥርዓት የሚዘረጋበት የአሰራር ስርዓት እንዲኖር ያደርጋል።
በፖሊሲው ላይ እንደተመለከተው፣ ከመሰረታዊ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የተቃኘ መሰረታዊ የሰው ሀብት ልማት እንዲገነባ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ መጪውን ጊዜ ማዕከል ያደረገ የሰው ኃይል እንዲገነባ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራ ይደረጋል። በዚህም የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እንቅስቃሴን በብቃት መምራት የሚችል የሰው ኃይል ይገነባል። ከዚህ በተጨማሪም ከመደበኛው የትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራሞች በተጓዳኝ ለዜጎች የተለያዩ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ባህል ግንባታ ሊፈጥሩ የሚችሉ የማህበረሰብ ልማት ተግባራት ይከናወናሉ።
ከዚህ በተጨማሪም የቴክኖሎጂ አቅም ክምችትንና የዕውቀት ሽግግሩን ለማሳለጥ የቴክኖሎጂ ልማት ላይ ትኩረት የሚያደርጉ የምርምር እና ስርፀት ዩኒቶች (Technological Research Units) በማምረቻና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲቋቋሙ ድጋፍ እንደሚደረግ፤ ሀገርን ምርታማና ተወዳዳሪ ለሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ እንዲሁም ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀምና ለማሳደግ የሚያስችል ስርዓት እንደሚዘረጋ በፖሊሲው ላይ ተመላክቷል። የኢኖቬሽን ሥነ-ምህዳር በመፍጠርና የሃገሪቱን የኢኖቬሽን አቅም በማዳበር ኢኖቬሽንን በሰፊው ለልማትና ሰፊ የሥራ ዕድሎችንና ሀብቶችን ሊፈጥር በሚችል መልኩ፣ በሀገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ በርካታ ኢንተርፕራይዞችን ለመፍጠር ይሰራል።
ፖሊሲው የግል ኢንኩቤሽን ማዕከላት የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ እና በራሳቸው የሚንቀሳቀሱበትን አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገልጿል። በዚህ ረገድ ጀማሪ ተቋማት እና የኢኖቬሽን ሥርዓተ-ምህዳር ገንቢዎች የፋይናንስ፣ የቴክኒክ፣ የመስሪያ ቦታ እና መሰል ድጋፎች የሚያገኙበት የአሰራር ሥርዓት እንደሚዘረጋ፤ ኢንተርፕራይዞች ቴክኖሎጂን መሰረት አድርገው ምርታማነትን እንዲያሳድጉ የሚደግፉ ልዩ ተቋማት እንደሚመሰረቱ እንዲሁም አምርተው ወደ ዉጪ ለሚልኩ፣ የገቢ ምርትን ለሚተኩ እንዲሁም ወደ ሌሎች ሃገራት ለሚስፋፉ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዞች ድጋፎችና ማበረታቻዎች እንደሚደረጉ ፖሊሲው ያሳያል።
በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሥራዎች የግሉ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ መሆን እንዳለበትና የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ልማትና ተሳትፎ እያደገ እንዲሄድ የግሉ ዘርፍ በቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር፣ በኢኖቬሽን ልማት እንዲሁም በምርምር ሥራዎች ላይ የመሪነት ድርሻ እንዲኖረው እንደሚጠበቅ የሚጠቅሰው ፖሊሲው፤ ዘርፉ በመሠረተ-ልማት ሥራዎች፣ በሀብት ምደባ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ስለሚኖረው በመንግስት ይተገበሩ በነበሩ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የልማት ሥራዎች ላይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እያደገ እንዲሄድ እንደሚደረግ ያመላክታል።
በፖሊሲው ላይ እንደተመለከተው፤ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ ‹‹ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ልማት ተደራሽ፣ አካታችና ቀልጣፋ የፋይናንስ አቅርቦት አማራጮች ይዘረጋሉ፤ ለሳይንሳዊ ምርምር፣ ለቴክኖሎጂ ልማትና፣ ለኢኖቬሽን እንዲሁም ለቴክኖሎጂ ግብይት የሚውሉ ፋውንዴሽኖችና ፈንዶች ይቋቋማሉ፤ኢኖቬተሮችንና ኢንተርፕረነሮችን ለማበረታታት የሚያስችል እንዲሁም ለኢኖቬሽን ልማት ሥራዎች የግሉ ዘርፍ ከመንግስት በቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኝበት አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል፤የተመራማሪዎች ማበረታቻ ስርዓትም ይተገበራል። በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ለተሰማሩ ኢንቨስተሮች ልዩ ልዩ የታሪፍ፣ የታክስ እና ተዛማጅ የፋይናንስና የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች እንዲሰጡ እንዲሁም ለዘርፉ ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ተዋናዮች እንዲበረታቱ ይደረጋል›› የሚለው በፖሊሲው ላይ ተገልጿል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2014