መቼም አሸባሪው ሕወሓት ነፍሱ አይማርም ባለፉት አራት ዓመታት ጊዜዬን ፣ አእምሮዬንና ጉልበቴን እሱ ላይ እንዳፈስ አስገድዶኛል ። ነገሬን ሁሉ ከእጄ አስጥሎ ስለ እርሱ ብቻ እንድጽፍ አስገድዶኛል ። አሁንም እግዜሩ ይይለትና ነፍሱም አይማርና በዚህ የተነሳ ኦፊሴላዊ ባይሆንም አንጋፋው “አዲስ ዘመን”/የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ “የሕወሓት ጉዳዮች ቋሚና ልዩ ዘጋቢ !?”አድርጎኝ አርፏል ። በዚህ አጋጣሚ እነ በዓሉ ግርማ ፣ ብርሀኑ ዘሪሁን ሙሉጌታ ሉሌና ሌሎች ጉምቱ ጋዜጠኞችና ጸሐፍት በተሰናዘሩበት “አዲስ ዘመን” ለመጻፍ እድሉን በማግኘቴ ከፍ ያለ ክብር ይሰማኛል ።
አብዝቼ ስለ አሸባሪው ሕወሓት መጻፌ ደግሞ ያናድደኛል። ያስቆጨኛል ። ሆኖም ለሀገሬና ለሕዝቤ እንዲሁም ለውጡ ከእነ ውስንነቶቹና ድክመቶቹም ቢሆንም ዳር እንዲደርስ የከፈልሁት ዋጋ ስለሆነ እጽናናለሁ ። ወደ ተነሳሁበት ሀሳብ ስመለስ ስለ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ፣ ስለ ስነ ጽሑፍ ፣ ኪነ ጥበብ ፣ ኪነ ሕንጻ ፣ ስዕል፣ ሙዚቃ ፣ ስፖርት ፣ ወቅታዊ ዓለማቀፍ ጉዳይ ፣ ወዘተረፈ ግድ እንደማይሰጠኝ በተለይ አሸባሪው ሕወሓት ላይ ማተኮሬ ሌላ ጉዳይ ላይ እንዳላንሰላስልና እንዳልጽፍ ጠምዶ ይዞኝ ነበር ።
ዛሬ በስንት ትግል ጥማዱን ፈትቼ ለ2ኛ ጊዜ ስለወቅታዊ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ለዛውም ስለ አሸባሪው ሕወሓት ምንም ሳላነሳ ይቺን መጣጥፍ ጫጭሬያለሁ ። ለራሴ እንኳን ለዚህ አበቃህ ብል መቼም አይበዛብኝም ። በባሕሪዬ ጨለምተኛም ሟርተኛም አይደለሁም ። ሰብዕናዬንና ስሜቴን አውልቄ ወደ ጋዜጠኝነት ስመለስ ግን እንደ ሰው ልጅ ለማሰብ እሞክራለሁ። ተስፋውንም ስጋቱንም እጋራለሁ ።
ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ዳግማዊ ቀዝቃዛ ጦርነት ምን አልባት በኒውክሌርና በሳይበር ለታገዘ 3ኛው የዓለም ጦርነት ይዳርገን ይሆን በሚል ስጋቴን በዚሁ ጋዜጣ አጋርቼ ነበር ። ዛሬ ደግሞ “ፉትቦል “ ስለተሰኘው የአሜሪካ የኒውክሌር ጦር ማዘዣ ቦርሳ፤መረጃ አቀብላለሁ ። እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ደግሞ ስለ ሩሲያው የኒውክሌር ጦር ማዘዣ “ቼጌት”አስከትዬ እጽፋለሁ።
የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ከቀደሟቸውም ከተከተሏቸውም ለየት ያለ ልምድ ነበራቸው። ሰርክ ጥዋት ቢሮ ሲገቡ መጀመሪያ የሚያደርጉት በጠረጴዛቸው የተቀመጠውን የዓለም ሉል/Globe/ ያሽከረክሩና ሶቭየት ኅብረት ላይ ሲደርስ ያቆሙትና የጥሞና ጊዜ ይወስዱና ። የኒውክሌር ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ይጸልያሉ።
በአንጻሩ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ደግሞ የሶቪየት ኅብረት የኒውክሌር ሚሳየል ኩባን ከአሜሪካ ጥቃት ለመከላከል ተጠምዶ ስለነበር ያለ ሞስኮ እውቅና ጥቃት ሊፈጸምብን ስለሚችል ፈጣን የአጸፋ ምላሽ? የምንሰጥበት አሠራር ያስፈልጋል በሚል የዛሬው የፉት ቦል አጠቃቀም ተግባራዊ ሊደረግ ችሏል ። ለመሆኑ ይህ ከአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች አጠገብ የማይለየው የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ማዘዣ ቦርሳ”ፉትቦል” እንዴት ያለ ነው !?
የኒውክሌር ጦር መሣሪያን ለማዘዝ የሚያስችል መሣሪያን አልያም ቁልፍን ለመያዝ ተብሎ በልዩ ሁኔታ የተሠራ ሳምሶናይት ወይም ቦርሳ የኒውክሌር ሳምሶናይት ወይም ቦርሳ ይሰኛል ። መሪዎች ከሀገር ሲወጡ ፤ እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራት ደግሞ ከአንዱ ግዛት ወደ ሌላው ሲንቀሳቀሱ ከኋላ ወታደራዊ መለዮ በለበሰ የጸጥታ ሰው ተይዞ ሲከተል የሚታየው የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ማዘዣን የያዘ ቦርሳ ነው። ሆኖም የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የታጠቁ ሀገራት ሁሉ እንደ አሜሪካና ራሽያ የኒውክሌር ማዘዣቸውን በሳምሶናይት ወይም በቦርሳ ይዘው ይዞራሉ ማለት አይደለም።
ፈረንሳይ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ከታጠቁ ሀገራት አንዷ ብትሆንም ኦፊሴላዊ የኒውክሌር ማዘዣ ቦርሳ የላትም። ይሁንና ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት አጠገብ የማይለይ ሳምሶናይት አለ ። ዳሩ ግን የኒውክሌር ማዘዣ መሣሪያ ስለመያዙ እርግጠኛ የሆነ የለም ። ሕንድ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ብትታጠቅም ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሯ አጠገብ የማይለይና አብሮ ዓለምን የሚዞር የኒውክሌር ቦርሳ ወይም ሳምሶናይት የለም ።
እንዲያውም የሕንድ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንደ ሌሎች ሀገራት በሀገሪቱ መሪ ሳይሆን የሚታዘዘው ለዚሁ የተለየ ተልዕኮ በተቋቋመው የ”ኒውክሌር ማዘዣ ባለስልጣን፤”አማካኝነት ነው ። ባላንጣዋና ጎረቤቷ ፓኪስታን ግን ከመሪዋ አጠገብ የማይለይ የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ማዘዣ የያዘ ሳምሶናይት አላት ። በሕንድ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ማዘዣው በመሪው ብቻ ሳይሆን ለዚሁ በተቋቋመ ባለስልጣን መመራቱ ከግብታዊና ስሜታዊ ውሳኔዎች ይታደጋል ።
የአሜሪካው የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ማዘዣን የሚይዘው ቦርሳ “አቶሚክ ፉትቦል” ወይም “ፉትቦል” በመባል ቢታወቅም ፤ “የአደጋ ጊዜ ቦርሳ” ፣ “ቁልፉ” እና “ጥቁሩ ሳጥን” የሚሉ ቅጽሎች አሉት ። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በዋሽንግተን በኋይታወስ ከሆኑ የከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻዎች በሚመሩበት “ሲቹየሽን ሩም” በመባል በሚታወቀው ክፍል ከካቢኔያቸውና ከአማካሪዎቻቸው ጋር ሆነው ነው ። ከነጩ ቤተ መንግሥት ውጭ ከሆኑ ግን በየትኛውም ቦታና ምንጊዜም ከአጠገባቸው የማይጠፋውን “ፉትቦል”ን ተጠቅመው የኒውክሌር ጥቃትን ያዛሉ ።
“ፉትቦል”ተንቀሳቃሽ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ማዘዣ ማዕከል ነው ። የቀድሞው የኋይታወስ ወታደራዊ ቢሮ ዳይሬክተር ቢል ጉሌ ፤” በፉትቦል”ውስጥ አራት ሁነኛ ነገሮች ይገኛሉ ይለናል ። የመጀመሪያው ጥቁሩ መጽሐፍ የሚባል ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ በጥብቅ ሚስጥር የሚጠበቁ ቦታዎችን የሰነደ መጽሐፍ ፤ ሶስተኛው “የማኒላ ማህደር” ሲሆን የአደጋ ጊዜ መልዕክት ማሰራጫውን አጠቃቀም የሚያብራራ ነው ። አራተኛው ደግሞ የማረጋገጫ ምስጢር የያዘ ካርድ ነው ። ጥቁሩ መጽሐፍ በጥቁርና በቀይ የተተየቡ 75 ገጾችን ሲይዝ ፤ በጥብቅ ሚስጥር የሚጠበቁ ቦታዎችን የሰነደው መጽሐፍም እንደ ጥቁሩ መጽሐፍ ተቀራራቢ ገጽ ያለውና ጥቁር ሲሆን እንደ ነውክሌር ጥቃት ባለ አደጋ ጊዜ ፕሬዚዳንቱ በሀገሪቱ የት የት ሊጠለሉ እንደሚችሉ የሚያመለክት እጅግ ጥብቅ መረጃ ነው ።
በ2005 ዓም በዋሽንግተን ፖስት ለንባብ በበቃ መጣጥፍ ፤”ፉትቦል”የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ማስተኮሻ ምስጢራዊ ቁልፍ የያዘ መሆኑን ያትታል። ክብደቱ 20 ኪ.ግ ሲመዝን ፣ የኮሙኒኬሽን አንቴናም አለው። ይህ “ፉትቦል” የኮሙኒኬሽን መሣሪያም እንደያዘ ያመለክታል። ፕሬዚዳንቱ በተንቀሳቀሱበት ሁሉ ፉትቦሉን ይዞ የሚከተለው ወታደራዊ የደንብ ልብስ ከላይ እስከታች የገደገደው የጸጥታ ሰው ፎቶ ሳይቀር በዚሁ የኒውክሌር መልዕክተኛ ቦርሳ ይገኛል ሲል ዋሽንግተን ፖስት በአግራሞት ይገልጻል ።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ፕሬዚዳንቱ የኒውክሌር የጦር መሣሪያን ለመጠቀም ከወሰኑ “ፉትቦሉን” ይዞ እንደ ጥላ የሚከተለው ወታደር ፕሬዚዳንቱን ወደ ዘዋራ ቦታ ይወስድና ይከፍትላቸዋል ። ወዲያው ወደ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦሩ ሹም ማዘዣ የማስጠንቀቂያ ምልክት ይተላለፋል ። በማስከተል ፕሬዚዳንቱ ከኤታማዦር ሹሙና ከመከላከያ ሚኒስትሩ ጋር የጥቃት ኢላማዎችን ይለያሉ። ከዚያ እንደ አስገዳጅ ሁኔታው አንድ ወይም በርካታ አህጉር አቋራጭ የባሊስቲክ ሚሳየል ሊተኮስ ይችላል።ይህ ውሳኔ የቀድሞው አንድ ወጥ የተቀናጀ የዘመቻ ዕቅድ ወይም የአሁኑ ኦፕላን 8010 ወይም OPLAN/OPerational pLAN/ አካል ነው ።ሚሳየሉ ከመተኮሱ በፊት ፕሬዚዳንቱ “ብስኩት” በመባል የሚታወቀውን የፕላስቲክ ካርድ እንደ ይለፍ በመጠቀም ያረጋግጣሉ ። የመከላከያ ሚኒስትሩም ትዕዛዙ በእርግጥ በፕሬዚዳንቱ የተላለፈ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ በተዋረድ የመጨረሻ ማረጋገጫ ለምድብተኛ ተኳሽ ትዕዛዝ ይሰጣሉ ። ሆኖም እያንዳንዱ ውሳኔ በጥልቅ ይመረመራል። ይረጋገጣል ። ይህ ማለት የፕሬዚዳንቱ ስልጣን ገደብ የለሽ ነው ማለት አይደለም።
የአሜሪካ ሕግ ጥቃቱ ሕጋዊ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል። ፕሬዚዳንቱ የጦርነትን ሕግ ተላልፎ ትዕዛዝ የሚሰጥ ከሆነ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙም ሆነ በተዋረድ ያሉ ባለ አራት ኮከብ ጄነራሎች ወይም አድሚራሎች ውሳኔውን ያለመቀበል መብት አላቸው። ጄነራል ጆን ሀይተንን ጨምሮ በርካታ ወታደራዊ አዛዦች ሕገ ወጥ የኒውክሌር ጥቃት ትዕዛዝን እንደማይቀበሉ በኮንግረሱ ፊት ሳይቀር ቀርበው መተማመኛ ሰጥተዋል። ጥቃቱ ከመፈጸሙ የሕግ ባለሙያዎችም ማረጋገጫ እንዲሰጡ ይደረጋል ።
በአጠቃላይ ሶስት የኒውክሌር “ፉትቦል”ሲኖር ፤ ሁለቱ በፕሬዚዳንቱና በምክትል ፕሬዚዳንቱ እጅ ሲገኙ ፤ ሶስተኛው ደግሞ በቋሚነት በኋይታወስ ቤተ መንግሥት ይቀመጣል ። ፕሬዚዳንቱ በተለያዩ ምክንያቶች ኃላፊነታቸውን መወጣት የማይችሉ ከሆነ ምክትሉ በእግራቸው ይተካሉ ። ይህ አሠራር የተጀመረው በጂሚ ካርተር አስተዳደር ነው ። ምን ጊዜም ቢሆን የ”ፉትቦል”ሚስጥራዊ ካርድ ከአንዱ ፕሬዚዳንት ወደ ተተኪው የሚተላለፈው በቂ ገለጻና ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ ነው ።
ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ተተኪውን በቤተ መንግሥት ከተቀበሉ በኋላ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው በመመኘት “ፉትቦል”ንም ያስረክቡታል። አዲሱ ፕሬዚዳንትም በዓለ ሲመቱን ካከናወኑና ቃለ መሐላ ከፈጸሙ በኋላ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ማዘዣን ሚስጥራዊ ቁልፍ ይረከባሉ ። በዘመነ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሆነው ግን እንግዳና ያልተጠበቀ ነበር ። በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ ብዙ ባልተለመደ ሁኔታ አፈንጋጩና አወዛጋቢው ተሰናባች ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን የምርጫ ውጤቱን አልቀበልም በማለት ፤ ተመራጩን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን በኋይታወስ ካለመቀበላቸው ባሻገር በበዓለ ሲመቱም አልተገኙም ።
ፉትቦሉንም ሳያስረክቡ ወደ ፍሎሪዳ በመሔዳቸው ወዲያው እንዳይሠራ ከመደረጉ ባሻገር ከፕሬዚዳንቱ ጋር የነበረው አቃቤ ፉትቦል ወደ ኋይታወስ በአስቸኳይ ይዞ እንዲመለስ ታዟል ። የኒውክሌር “ፉትቦል”ዘፍጥረት ከፕሬዚዳንት አይዘንሀወር የሚነሳ ሲሆን ፤ ከፍ ብሎ የተመለከተውን አሠራር መከተል የተጀመረው ግን ከኩባው የሚሳይል ቀውስ በኋላ በጆን ኤፍ ኬኔዲ የስልጣን ዘመን ነው።
“ፉትቦል”የሚለው መጠሪያ ስረወ-ቃል የመጣው “ኳስ መለጋት/Dropkick”ከሚለው ልዩ መጠሪያው ሲሆን፤ በተወዳጁ የአሜሪካ ፉትቦል ደግሞ ኳስን መለጋት የጨዋታው አካል ስለሆነ”ፉትቦል”ሊባል ችሏል ይለናል የአሜሪካው የዜና አገልግሎት አሶሼትድ ፕሬስ/ኤፒ/ ። ከሰው መርጦ ለሹመት ፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት ፤ እንዲሉ በፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተርና ሮናልድ ሬገን የአስተዳደር ዘመን “ፉትቦሉን” በኃላፊነት ይዞ ይከተላቸው የነበረው ኮሎኔል ጆን ክሊኔ ነበር ።
በነገራችን ይህ ኃላፊነት በዙር ለምድር ፣ ለባሕርና ለአየር ኃይሉና ለሌሎች የመከላከያና የጸጥታ መሥሪያ ቤቶች ሲሰጥ፤ እያንዳንዱ ወታደራዊ ክፍል ተራው ሲደርስ እጩውን በጥንቃቄ ይለይና ለአሜሪካ የስለላ ድርጅት/ሲአይኤ/ያቀርባል። የቀደመም የአሁንም ማንነቱ በደንብ ተብጠርጥሮ ተፈትሾ መስፈርቱን ሲያሟላ ፉት ቦሉን ለመያዝ ብቁ ይሆናል።
እዚህ ላይ አንድ አስገራሚ ገጠመኝ ላንሳ ፤ የፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ የሚረጋገጥበት “ብስኩት” በመባል የሚታወቀው የፕላስቲክ ካርድ መቼም ቢሆን ከፕሬዚዳንቱ እጅ ወይም ኪስ አይጠፋም ። በ1981 ዓ.ም በፕሬዚዳንት ሮናልድ ላይ የግድያ ሙከራ ተደርጎ ፤ የድንገተኛ ክፍል ሐኪሞች ሕይወታቸውን ለመታደግ እንዲያፈጥናቸው ልብሳቸውን በመቀስ ቀደው እርዳታ ያደርጉላቸዋል ።
የፕሬዚዳንቱ ጉዳት ለክፉ እንደማይሰጥ ሲረጋገጥና ሁኔታዎች ሲረጋጉ ፤ የደህንነት ሰዎችም ወደ ቀልባቸው ሲመለሱ “ብስኩቱ” ሲፈለግ ይጠፋል ። ወዲያው ሁሉም ይደናገጥና በየፊናው ፍለጋ ይገባል ። ከብዙ ድካም በኋላ ባልተገመተ ቦታ ላይ ማለትም በፕሬዚዳንቱ ጫማ ውስጥ ተወሽቆ ይገኛል ። እንዴት በፕሬዚዳንቱ ጫማ ውስጥ ሊገባ እንደቻለ ዛሬም መልስ አልተገኘለትም ።
አብጠልጣይ የሆነው ሚዲያው በኋላ ላይ ፕሬዚዳንት ሬጋን ሚስጥራዊ ቁልፉን ለካ በካልሲያቸው ውስጥ ነበር የሚይዙት በማለት ተሳለቀ ። ፉትቦሉና ፕሬዚዳንቶች በተደጋጋሚ እየተለያዩ ጭንቅ ጥብ የተሆነባቸው ሰዓታትም ነበሩ ይለናል ኤፒ ። በፕሬዚዳንት ሬጋን ላይ የግድያ ሙከራ የተደረገ ጊዜ ፤ ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን በ1973 ዓም የሶቪየት ኅብረቱን መሪ ሊዎኒድ ብሬዥኔቭ በተቀበሉ ዕለት፤ ፕሬዚዳንት ጌራልድ ፎርድ ፣ ጂሚ ካርተር ፣ ጆርጅ ኤች ደብሊው ቡሽና ቢል ክሊንተንም በተለያዩ አጋጣሚዎች ከፉትቦል ተለይተው ያውቃሉ ።
የኒውክሌር ፉትቦሉን ሁል ጊዜ ከፕሬዚዳንቱ በቅርብ እርቀት መሆን ስላለበት ፤ የያዙት መኮንኖች ምስል በጋዜጠኞች ካሜራ አደባባይ መዋሉ የተለመደ ነው ። አወዛጋቢው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያደረጉት ግን ከዚህ ወጣ ያለ ነበር ። ፉትቦሉን ከያዘው መኮንን ጋር ቆሞ ፎቶ ይነሳና ስሙን ተገልጦ በፌስቡክ ይለጠፋል ።
ይህ የሆነው የወቅቱ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ አሜሪካንን እየጎበኙ ፤ ሰሜን ኮሪያ የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳየል ሙከራ ካደረገችበት ሰዓት ጋር ሁኔታዎች ስለተገጣጠሙ እና አንድምታውም ከጸረ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፉክክር መርህ ጋር ስለሚጻረር፤ የአሜሪካ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ያልተለመደውን ሁኔታ በማውገዝ ድርጊቱም ሕገ ወጥ መሆኑን ፤ ፉትቦሉን የያዘው መኮንን ፎቶ መነሳቱ ስህተት እንደነበር ገልጸዋል ። ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሕዳር 2017 ዓ.ም ቻይና ለኦፊሴላዊ ጉብኝት ባቀኑበት ወቅት ከሀገሪቱ መሪ ዢ ዢንፒግ ጋር ለመነጋገር ወደ ተዘጋጀ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየገቡ ሳለ
የፕሬዚዳንት ትራምፕ አጃቢዎችና ፉትቦሉን የያዘው መኮንን በአንድ በኩል ፤ የፕሬዚዳንት ዥንፒንግ አጃቢዎች በሌላ በኩል እኔ ልቅደም እኔ እያሉ ግብግብ ሲገጥሙ ፉትቦሉ አደጋ ላይ ወድቆ እንደነበር በወቅቱ በስፍራው የነበረው የፖለቲካዊ ጉዳዮች ዘጋቢ ጆናታን ስዋን እማኝነቱን ሰጥቷል ። ሆኖም ለተፈጠረው እንግዳ ነገርና ስህተት የቻይና የጸጥታ ኃላፊዎች ይቅርታ ጠይቀዋል ።
ጥር 6 ቀን ፣ 2021 ዓ.ም የትራምፕ ደጋፊዎች የምርጫውን የኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጽ ውጤት ለማጽደቅ በወቅቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ሰብሳቢነት ሴኔቱ በካፒቶል ሒል ተሰብስቦ እያለ ደርምሰው በገቡበት ወቅት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ፣ ቤተሰቦቻቸውና ሴናተሮች ለደህንነታቸው ወደ ማያሰጋ ምስጢራዊ ቦታ በመውሰድ ከጥቃት ማትረፍ ቢቻልም ፤ ፉት ቦል ግን በሁከተኞች እጅ ከመውደቅ ለትንሽ መትረፉ ሌላው መነጋገሪያ ነበር ።
ከፍተኛ ሚስጥራዊ መረጃዎች በተለይ የኒውክሌር ጥቃት ሊሰነዘርባቸው የሚችሉ ኢላማ ዝርዝሮች ፤ በአሜሪካ ጥቃቱ ቢሰነዘር ፕሬዚዳንቱ የሚጠለሉባቸው ምስጢራዊ ቦታዎች፤ ባልተገቡ አካላት እጅ ወድቀው የሀገሪቱን ደህንነትና ጸጥታ አደጋ ላይ ጥለውት ነበር በሚል ድንጋጤ ፈጥሮ አልፏል ። የትራምፕ ደጋፊዎች የአሜሪካ ልሒቃን እንደ ዴሞክራሲ ቤተ መቅደስ የሚያዩትን ካፒቶል ሒልን በሀይል ሰብረው ገብተው በነበረበት ወቅት ምክትል ፕሬዚዳንቱና ፉትቦሉ ተጠልለው በነበሩበት ክፍል በ30 ሜትር እርቀት ተቃርበው ስለነበር መሠል ተጋላጭነት እንዳይኖር የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና ተቆጣጣሪ ምርመራ ጀምሯል ።
ኋይታወስና ፔንታጎን እንደዚህ ያለ መሰል ቀውስ ቢያጋጥም ፤ ፉት ቦሉ እንዳይሰረቅና እንዳይጠፋ ደህንነቱን ማረጋገጥ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት አለመዘርጋታቸውን እያጣራ ነው ። የምርመራውና የማጣራቱ ግኝት በያዝነው የሐምሌ ወር ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ። የኮንግረስ አባላቱ ስቴፈን ሊንችና ጂም ኮፐር ፤ ፉትቦሉን አስመልክቶ ዋና ተቆጣጣሪው ምርመራና ግምገማ መጀመሩ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ገልጸው በካፒቶል ሒል ላይ የተፈጸመው ጥቃት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ላይ የተፈጸመ ጥቃት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሀገራችንን ደህንነት ለአደጋ ያጋለጠ እኩይ ተግባር ነው ብለዋል ።
በጥቃቱ ዕለት ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክና ፉትቦሉን የያዘው ረዳታቸው የተደበቁበት ቦታ ከአመጸኞች በቅርብ ርቀት ላይ ስለነበሩ ፉትቦሉ በአመጸኞች እጅ ሊወድቅ ሰከንዶች ቀርተውት እንደነበር ፔንታጎን እራሱ መረጃው እንዳልነበረው የኮንግረስ አባላቱ ከሲኤንኤን ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ አስታውቀዋል ።
ሆኖም ፉት ቦሉ ላይ አደጋ ቢደቀን እንዴት መከላከል እንደሚቻል በግልጽ የተቀመጠ ቅደም ተከተልና የራሱ የአፈጻጸም ሒደት እንዳለው ብናውቅም ደህንነቱን የሚያረጋግጡ አሠራሮችን በየጊዜው መፈተሽና ማሻሻል ግን ግድ ይላል ብለዋል።
ሲኤንኤን ያነጋገራቸው ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ግን ፉት ቦሉን የያዘው መኮንን እንዴት ከአደጋ መከላከል እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል ካለ በኋላ በማስከተል የከፋ ነገር ቢከሰት ደግሞ ወዲያው እንዳይሠራ በማድረግ መቆጣጠር ይቻላል በማለት ስጋቱን ያቃልሉታል ።ፈጣሪ ዓለማችንን ከኒውክሌር ጦርነት ይጠብቅ ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2014